* አፈፃፀሙ 43 በመቶ ብቻ ነው፤
* ግንባታውን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 30 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል፤
* የፕሮጀክቱ እቃዎች በጸሐይና ዝናብ ከጥቅም ውጪ እየሆኑ ነው፤
የተራራው ግማሽ ጎን ተሰንጥቋል። በተሰነጠቀው ተራራ ስር ሰፊ ደልዳላ ሜዳ ተሰርቷል። በተሰራው ሜዳ ላይ
እዚህም እዚያም ጅምር የፋብሪካ መትከያ ህንፃዎች፣ መጋዘኖች፣ ቢሮዎች፣ ቤተ ሙከራዎች፣ ጅምር የኤሌክትሪክ ማመንጫ ፋብሪካዎችና ሌሎች ህንፃዎች ጉች ጉች ብለው የአካባቢውን ተፈጥሮ በዙሪያቸው እየተመለከቱ ቆዝመዋል። ወደ ቤቶቹ ውስጥ ሲገባ በእርጥበት ወይበዋል። ፍየሎች ከዝናብ ስለሚጠለሉበት ከእነርሱ ጠረን ጋር ተዳምሮ ሰፋፊዎቹ ህንፃዎች ውስጣቸው በመጥፎ ጠረን ታውዷል። በአጠቃላይ የዋሻ ዘመንን ኑሮ ያስታውሳል።
ከአንደኛው ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ ለመድረስ የሚያታክተው ሰፊ ግቢ በአረምና በሳር ተወርሯል። ግቢው ከጫፍ እስከ ጫፍ በቁርጥራጭ ፣ ትላልቅና ወፋፍራም ብረቶች፣ በትናንሽና ትላልቅ ማሽኖች፣ ኮንቴይነሮች፣ ተሽከርካሪዎችና ሌሎች ተዘርዝረው በማያልቁ ቁሶች ተሞልቷል። ዝናብ፣ ቁሩና ጸሐይ የተፈራረቀባቸው ቁሶች በዝገት መልካቸው ጠፍቷል። ይህ የሀገር ሀብት ብክነትና ብልሽት ሲታይ ህሊናን በኀዘን ይሸነቁጣል።
የያዮ ማዳበሪያ ፋብሪካ በዓመት 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል አውጥቶ በመጠቀም 90 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ፣ በዓመት 300ሺ ቶን ዩሪያ ማዳበሪያ፣ 60ሺ ቶን ሜታኖል፣ 5ሺ ቶን አሞኒያ፣ 4ሺ500 ቶን ሰልፈር እንዲሁም ኦክስጂን፣ ካርቦንዳዮክሳይድ፣ ናይትሮጂንና አርገን የሚባሉ ጋዞችን እንዲያመርት የታለመለት ግዙፍ ፕሮጀክት ነበር።
መንግሥት 80 በመቶ ለሆነው አርሶ አደርና ሌሎች ግብዓቶችን ለማምረት ለያዘው እቅድ 10 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ አፍስሶበታል። ይህ ፕሮጀክት በ2006 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ላይ 43 በመቶ አፈፃፀም ላይ ቆሞ ጸሐይና ዝናብ የሚፈራረቅበት ሆኗል። ይህ ፕሮጀክት ትልቁ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ማሳኪያ ከተባሉት ፕሮጀክት አንዱ ነው። ነገር ግን ዛሬ ላይ የአገሪቱን ቢሊዮን ገንዘብን እየበላ አጣብቂኝ ውስጥ አስገብቶ የቆመ ፕሮጀክት ሆኗል።
የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽንን በመወከል ፕሮጀክቱን ለመረከብ በቦታው ያገኘናቸው መሃንዲስ ደረጀ ቡርቃ፤ በፕሮጀክቱ ሁኔታ እጅግ ውስጣቸው መነካቱን በኀዘን ይናገራሉ።
እሳቸው እንደሚሉት ለሁሉም ፋብሪካዎች መነሻ ግብዓት የሚሆነው የድንጋይ ከሰል ፋብሪካ ማውጫ ግንባታ አልተጀመረም። ለፋብሪካው ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ የሚያስፈልግ ቢሆንም እንኳ፤ የግድብ ሥራው አልተጀመረም። እነዚህ ሥራዎች በመጀመሪያ ወይም ከሌሎቹ ሥራዎች ጋር እኩል መሰራት ያለባቸው ነበሩ። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ሌሎቹ ፋብሪካዎች ቢያልቁም እንኳ የፋብሪካዎቹ ግብዓት የድንጋይ ከሰልና ውሃ ሳይኖር ፋብሪካው በመቆም ብዛት ከመበላሸት ውጭ ጥቅም የሚሰጥ አይሆንም።
ለኤሌክትሪክ ማመንጫው ከተደረገው የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራው ውጪ የማሽን ገጠማ እንዳልተካሄደለት የሚናገሩት ተወካዩ፤ ለፋብሪካ ተከላው ቦታው የደረሱ ማሽኖች፣ የተለያዩ ብረቶችና ቁሶች እንደአልባሌ ነገር ሜዳ ላይ ተጥለው ለብልሽት መዳረጋቸውን፣ ለማንሳትም አስቸጋሪ እንደሆነ፣ እንዲገዙ የታዘዙ ማሽኖችም በቦታው ያለመኖራቸውን፣ በሜዳ ላይ የተጣሉት ማሽኖችና ቁሶች “ይሰራሉ አይሰሩም” የሚለው በባለሙያ ሳይረጋገጥ ሊገጣጠሙ እንደማይችሉ ያስረዳሉ።
የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር መሃንዲስ ተባበል ውድነህ፤ በርካታ እቃዎች ተበትነው የተበላሹ በመሆናቸው ርክክብ ሳይደረግ ለማስተካከል አለመቻላቸውንና የፋብሪካው ግንባታ በድምሩ 43 በመቶ ደርሷል ቢባልም የድንጋይ ከሰል ማውጫ ፋብሪካውና የውሃ ግድቡ ሥራ እንዳልተጀመረ ገልፀዋል።
የኤሌክትሪክ ማመንጫው በፋይናንስ ደረጃ 98 በመቶ ቢጠናቀቅም ተግባራዊ ሥራው ግን ከ57 በመቶ አይበልጥም። ለኤሌክትሪክ ማመንጫው ማቀዝቀዣ የሚሆነው ‹‹ኩሊንግ ታወር›› በመሰንጠቁ መፍትሔ ለመስጠት ሁለት ዓመት ቢወስድም አሁንም ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ባለመቀረፉ እንደገና የዲዛይን ማስተካከያ ያስፈልጋል። የኩሊንግ ፋርሞች ሥራ አልተሰራም፤ በአገር ውስጥ ይመረታሉ የተባሉ እቃዎችም አመራረታቸው ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ፍቃድ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑና ደረጃቸው ስላልተረጋገጠ መገጠም እንደማይችሉ መሃንዲሱ ያስረዳሉ።
የማዳበሪያ ፋብሪካው ሜታኖል፣ ዩሪያና የካርቦንዳይኦክሳይድ ማምረቻ ኮምፕረሰርና ሌሎቹ ፋብሪካዎቹ ከሲቪል ሥራቸው ውጭ የኤሌክትሮ መካኒኩ ሥራቸው አልተጀመረም። የቢሮ፣ የመጋዘንና ሌሎች የሲቪል ሥራዎችም የማጠናቀቂያ ሥራ እንደሚቀራቸው መሃንዲሱ ጠቁመዋል።
እንደ መሃንዲሱ ገለፃ ፕሮጀክቱ በጥራት፣ ጊዜና በተያዘለት በጀት መጠናቀቅ ነበረበት። ሆኖም ተቋራጩ አጠናቅቃለሁ ብሎ ከገባው የሁለት ዓመት ውል ተጨማሪ በአራት ዓመት እንኳ ማጠናቀቅ አልቻለም። ፕሮጀክቱን በ9 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር እጨርሳለሁ ብሎ ውል ቢገባም ተጨማሪ ሥራ አከናውኛለሁ በሚል ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ጠይቋል። በአማካሪው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተደረገው ጥናት ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ 30 ቢሊዮን ብር እንደሚያስወጣ አመላክቷል። ይህም በአዋጭነት ጥናቱ ከአስር ዓመት በኋላ ወጪውን ሸፍኖ ወደ ትርፍ ይገባል የተባለውን እቅድም ያዛባ ሆኗል።
መሃንዲስ ተባባል ‹‹ ለተቋራጩ ብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የወጪውን 60 በመቶ 5 ቢሊዮን 938 ሚሊዮን 532ሺ 286 ብር በጥቅሉ ተከፍሎታል። የገንዘቡ ምንጭ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በብድር የተገኘ ሲሆን፤ ድርጅቱ በሶስት ጊዜ 10 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ተበድሯል›› ይላሉ።
መሃንዲስ ተባባል ብድሩ ከተወሰደ ጊዜ ጀምሮ ለባንክ ወለድ በየወሩ 95 ሚሊዮን ብር እንደሚከፈል፣ እስካሁንም ለብድሩ ወለድ ብቻ 3 ነጥብ 872 ቢሊዮን ብር መከፈሉን፣ባለፈው ሰኔ ከዋናው ብድር የሶስት ወሩ 400 ሚሊዮን ብር መክፈል መጀመር እንደነበረበትና መክፈል ስለማይቻል ግን ለሶስት ዓመት መራዘሙን አስታውቀዋል። እስካሁን በጥቅሉ 10 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን፣ በዚህ ሁኔታ ፕሮጀክቱ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን መንግሥት በመረዳቱ ፕሮጀክቱን አቋርጦ ፍላጎት ካላቸው ድርጅቶች ጋር በሽርክና ይገንባ በማለት ከተቋራጩ ጋር ያለውን ውል ካለፈው መስከረም ጀምሮ ማቋረጡን ተናግረዋል።
ውሉ ከተቋረጠ በኋላም ከብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር ርክክብ ለማድረግ ሙከራ ሲደረግ ከሙስና ጋር በተያያዙ በርካታ ሰነዶች በመያዛቸው፣ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች በሙስና ተጠርጥረው በመያዛቸውና ሥራ በመልቀቃቸው ለመረከብ አዳጋች ሆኖ አንድ ዓመት ሊሞላው ነው። ይሁንና አሁን የሚረከቡ ባለሙያዎች ወደ ቦታው በመላካቸው በአስር ቀናት ውስጥ ርክክቡ ይፈፀማል የሚል እምነት እንዳላቸው መሃንዲስ ተባባል አስረድተዋል።
እንደ መሃንዲስ ተባባል ማብራሪያ መንግሥት በሽርክና ሊሰሩ የሚችሉ ድርጅቶችን ፈልጉ የሚል የቤት ሥራ ከሰጠ በኋላ በጋራ ሊሰሩ የሚችሉ ድርጅቶችን ለማግኘት ጥሪ ተደርጓል። በመጀመሪያው ጥሪ በቂ ባለሃብት አላገኘንም። በሁለተኛው አምስት ድርጅቶች ቢመጡም እስካሁን ባለው ውይይት የሚፈለገው ሃምሳ በመቶ ወይም ከዚያ በላይ የመግባባት ፍላጎት ያላቸው አለመሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል።
‹‹ ይህን ሁሉ ገንዘብ አፍስሶ ፕሮጀክቱን ማቆም የማይታሰብና ለመጪው ትውልድ የውድቀት ምሳሌ በመሆኑ በጎ ትምህርት አይደለም ፤ ከተቻለ በሽርክና ካልሆነ ደረጃ በደረጃ እየከፋፈለ ለመስራት መንግሥት ውሳኔ ማሳለፍ አለበት። ቶሎ ውሳኔ አሳልፎ ወደ ምርት አለመግባት ለፕሮጀክቱ የተወሰደው ብድር በየቀኑ እየጨመረ በመንግሥት ላይ የከፋ ጫና ያደርሳል፤ የተተከሉና የተገዙ መሳሪዎች ከጥቅም ውጭ ይሆናሉ። በመሆኑም መንግሥት አስቸኳይ እርምጃ ይውሰድ›› ሲሉም መሃንዲስ ተባባል ጥሪ ያቀርባሉ።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 17/2011
አጎናፍር ገዛኸኝ