ውሾቹም ይጮሃሉ፤ግመሎቹም ይጓዛሉ!

ወቅቱ እኤአ አቆጣጠር 1869 የስዊዝ ካናል መከፈቱን ተከትሎ የግብጽ ተሰሚነት ከፍ አለ። አልፎ ተርፎም የቀይባሕር እና አካባቢውን ለመቆጣጠር እና ኢትዮጵያን ከቀጣናው የማራቅ ሴራ በስፋት ተጀመረ፡፡ ከእንግሊዝ የቅኝ ገዢ ኃይል ጋር በመሆን ኢትዮጵያ ለዘመናት ከናኘችበት የቀይባሕር ውሃ የማራቅ እና የማግለል ሴራዎች ተጠናክረው ቀጠሉ።

በዚህ መሃል ግብጾች አንድ ችግር ገጠማቸው ከድርቡሾች ጋር የገጠሙት ጦርነት በሽንፈት ተጠናቀቀ፡፡ ጭራሹኑ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራዊት በድርቡሾች ተከበበ፡፡ ግብጾች መግቢያ መውጫው ጠፋቸው፡፡ ስፍር ቁጥር የሌለው የግብጽ ሠራዊት የደርቡሾች እራት ሊሆን ጥቂት ቀናት ብቻ ቀሩ፡፡

በዚህች አጣብቂኝ ሰዓት ግብጾች የነበራቸው ብቸኛ መውጫ ኢትዮጵያን መማጸን ነው፡፡ ከድርቡሾች መዳፍ የምታላቅቃቸው እና በሞት አፋፍ ስር የሚገኙት ወታደሮቿ ነጻ ልታወጣቸው የምትችል ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ ስለዚህም ግብጾች አጼ ዮሃንስን ተማጸኑ፤ ከጉድ አውጡን ብለው እጅ ነሱ፡፡

አጼ ዮሃንስም በምትኩ ለኢትዮጵያ የሚገቧትን ጥያቄዎች አነሱ፡፡ በዋነኝነትም በቀይባሕር ላይ ያላት ታሪካዊ ትስስር እንዲከበር እና የኢትዮጵያ የባሕር በር ለዘለቄታው መፈታት እንደሚኖርበት አሳሰቡ። በጭንቅ ውስጥ የሚገኙት ግብጾች የንጉሡን ማንኛውንም ጥያቄ ሳያቅማሙ ተቀበሉ፡፡ ጀግናው የኢትዮጵያ ሠራዊትም ግብጾችን ከድርቡሾች መዳፍ አስወጥቶ ነጻ አደረጋቸው፡፡ ወደሚፈልጉበት ቦታም ሸኛቸው፡፡ ይህን አስመልክቶ ግብጽና ኢትዮጵያ ያደረጉት ስምምነት በታሪክ የሕይወት ስምምነት ውል ተብሎ ይታወቃል፡፡

ከሞት አፋፍ ያመለጠችው ግብጽ ቃሏን ለማጠፍ ቀናት አልወሰዱባትም፡፡ በጭንቅ እና በመከራ ጊዜ የደረሰችላትን ኢትዮጵያን ገሸሽ በማድረግ ወዳጅነቷን ከእንግሊዞች ጋር አጠናከረች። ለኢትዮጵያ ጥያቄዎችም ፊቷን አዞረች፡፡ በተለይም የባሕር በር ጥያቄዋን ላለመቀበል ወሰነች፡፡ የገባችውን ውል አፈረሰች፡፡

ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ የምትፈጽማቸው ደባዎች ከፍጥረታት ጊዜ ጀምሮ ቢሆንም ታሪክ መዝግቧቸው ከሚገኙ ክህደቶች ውስጥ ግን በአንድ ጀንበር ያፈረሰችውን የሕይወት ውል ያክል የከበደ ክህደት የለም፡፡ በክህደት የታጀበው የግብጽ እና የኢትዮጵያ ግንኙኘት መልኩን እየቀያየረ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡

ከበርካታ ክህደቶች እና ሴራዎች ውስጥ አንዱ ሲመዘዝ ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችበትን ሴራ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፡፡ ከቀይ ባሕር በ60 ኪሎ ሜትርና ከህንድ ውቂያኖስ በ2 መቶ ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ቢሆንም እነዚህን አካባቢዎች ተጠቅማ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን እንዳታደርግ የማግለል ሁኔታዎች ፈጥረዋል።

በተለይም ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ የሚባለው ግብጻዊ የተባበሩት መንግሥታትን ለአራት ዓመት በመራበት ወቅት ኤርትራም ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል ትልቅ ሚናን የተወጣ ነው። ግለሰቡ የሴራ ተግባሩን ለመፈጸምም ከጅቡቲ እስከ ሱዳን ድረስ በጀት አሲዞ አዲስ በምትወለደው የአረብ ሊግ ላይ ኤርትራን አባል ማድረግ አለብን በማለት ብዙ ሠርቷል፡፡ በመጨረሻም ኢትዮጵያን ወደብ አልባ አድርጎ ከኃላፊነቱ ለቋል፡፡

በየዘመናቱ የሚመጡ የግብጽ መሪዎች ቀዳሚ አጀንዳቸው ኢትዮጵያ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ሰላሟ እንዳይረጋገጥ፤ ልማቷ እንዳይፋጠን እና በተፈጥሮ ሀብቷ እንዳትጠቀም በርካታ ሴራዎችን ሲሠሩ ኖረዋል፡፡ ተቃዋሚዎችን ማስታጠቅ፤ በአረብ ሊግ አማካኝነት ኢትዮጵያን የሚወነጅሉ ሃሳቦችን ማራመድ እና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ስለኢትዮጵያ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲያዝ ማድረግ ከብዙዎቹ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በሌላም በኩል ተጽዕኖ ፈጣሪ ምሁራን እና ፖለቲከኞች በገንዘብ በመግዛት ጭምር ኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳደር እና አለፍ ሲልም ከዓለም መድረክ እንድትገለል ማድረግ የግብጾች ሌላኛው ስልት ነው። ለዚህ ደግሞ ሰሞኑን የተከሰተውን ክስተት እና በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጭምር የመወያያ አጀንዳ ሆኖ የሰነበተውን ጉዳይ ማንሳቱ አስረጂ ይሆናል፡፡

ሴናተር ቦብ ሚንዴዝ ታዋቂ የአሜሪካ ፖለቲከኛ ናቸው፡፡ በፖለቲካ ውስጥ በርካታ ዓመታትን በመቆየታቸው ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸውም የዚያኑ ያህል የገዘፈ ነው፡፡ ስለዚህ ለኢትዮጵያ ተኝታ የማታድረው ግብጽ እኒህን ጉምቱ ፖለቲከኛ ወጥመዷ ውስጥ ማስገባት ፈለገች፡፡ ከፍተኛ ዶላር በመክፈልም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ኢትዮጵያን እንዲያብጠለጥሉ ትዕዛዝ አስተላለፈች፡፡ ረብጣው ዶላር መንገድ ያሳታቸው ሴናተር ቦብ ሚንዴዝ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስለኢትዮጵያ በሚችሉት ሁሉ ክፉ መልዕክት አስተላለፉ፡፡ ኢትዮጵያን ወረፉ፤አወገዙ፡፡

ሁኔታው ግር ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት እና አንዳንድ የአሜሪካ ፖለቲከኞች የሴናተሩን ጉዳይ በጥብቅ መከታተል ጀመሩ፡፡ ግብጽ በዶላር እንደገዛቻቸውም ደረሱበት፡፡ ሁኔታወም ሳይውል ሳያድር ለፍትህ አካላት ቀረበ፡፡

የሕግ አካላትም በጥብቅ ጉዳዩን ሲመረምሩ ቆይተው ሴናተር ቦብ ሚንዴዝ ከግብጽ ጋር በገንዘብ መወዳጀታቸውን ደረሰባቸው፡፡ ጥፋተኛም ብሎ 15 ዓመታት በመፍረድ ወህኒ ወረወራቸው፡፡ የኢትዮጵያ እውነትም በዓለም መድረክ ከፍ ብሎ ታየ፡፡

ስለኢትዮጵያ ተኝታ የማታድረው ይህቺው ሀገር ሰሞኑን ደግሞ የናይል ተፋሰስ ሀገራት የዓባይን ግድብ እንዳይጎበኙ በደብዳቤ ጭምር ብታስታውቅና ብታስጠነቅቅም አባል ሀገራቱ ለዛቻ እና ማስፈራርያው ጆሮ ሳይሰጡ የዓባይን ግድብ ጎብኝተው ተመልሰዋል፡፡ በአዩትም ነገር መደመማቸውን ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያም የይቻላል መንፈስ ያነገበች አሸናፊነት ተምሳሌት መሆኗንም አወድሰዋል፡፡ ትናንት በዓድዋ ዛሬ በዓባይ ግድብ ጠላቶቿን አሳፍራ የምትመልስ የጀግኖች መፍለቂያ መሆኗን ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት በአንድ ድምጽ መስክረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአኩሪ ታሪኮች የታጀበች ሀገር ነች። በየዘመናቱ የመጡ ሀገር ወራሪዎችን አሳፍራ ከመመለሷም ባሻገር ለተጨቆኑ ሕዝቦች ጭምር የነጻነት ተምሳሌት ተደርጋ ትወሰዳለች፡፡ ከዚሁ ባሻገር ደግሞ የትኛውንም ሀገር በሃይል ወርራ የማታውቅና መልካም ጉርብትናን የምታስቀድም ሀገር ነች፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራትም አልፋ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሲቸገሩ ፈጥና የምትደርስና ከችግሮቻቸው እንዲወጡ እስከሕይወት መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል ከተቸገሩት ጎን የምትቆም መከታ ነች፡፡ ለአብነትም ደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ ጭቆና ስር በነበረችበት ጊዜ የነጻነት ታጋዩን ኔልሰን ማንዴላን ሀገሯ ድረስ ጠርታ በመከለልና በማሰልጠን ደቡብ አፍሪካ ነጻነቷን እንድትጎናጸፍ የበኩሏን ድርሻ ተወጥታለች፡፡ በቅኝ አገዛዝ ስር የነበረችውም ዙምባቤም ነጻነቷን እስክታውጅ ድረስ የኢትዮጵያ ድጋፍ ተለይቷት አያውቅም፡፡

ወደ ጎረቤት ሀገራትም ስንመጣ ይኸው ሚናዋ ጎልቶ ይታያል፡፡ ግጭት ባልቆመባቸው በሱዳን የአብዩ ግዛትና በሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ኃይልን በመላክ ኢትዮጵያ ለአባል ሀገራቱ ጥላና ከለላ መሆን ችላለች፡፡ በቀውስ ውስጥ የምተገኘውን ሱዳንን ወደ ሰላም ለመመለስም በብቸኝነት የበኩሏን ጥረት በማድረግ ላይ የምትገኝ ሀገር ነች፡፡

በተለይም ደግሞ ላለፉት 17 ዓመታት የሰላም አስከባሪ ኃይሏን ጭምር በመላክ መንግሥት አልባ ሆና የቆችውን ሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት እንድትመሰርት እና አንጻራዊ መረጋጋት እንዲኖራት የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል ቀጣናዊ ግዴታዋን ተወጥታለች፡፡

ሆኖም ይኸው ውለታዋ በአንዳንድ ሀገራት ዘንድ በአግባቡ ከግንዛቤ የገባ አይመስልም፡፡ ወይንም ደግሞ ሆን ተብሎ የተዘነጋ ይመስላል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሕዝብና መንግሥት የከፈለችውን ውለታ ቸል በማለት ድንበር አቋርጠው ከመጡ የሀገሪቱ የተፈጥሮ ጠላቶች ጋር በማበር ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት እስከማወጅ ተደርሷል፡፡

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ እየገነባች ያለች ሀገር ነች፡፡ የሕዝብ ቁጥሯም በአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ የያዘ እና በቀጣይም እያደገ የሚሄድ ነው። ስለዚህም የዚህን ሕዝብ ፍላጎት ለማሟላት መጠነ ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ ያስፈልጋታል። ይህንን ለማሳካት ደግሞ በዋነኝነት አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እና የባሕር በር ጥያቄዎቿ ሊመለሱላት ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በኃይል እጥረት የሚሰቃይ ሕዝብ ነው፡፡ 60 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ምንም አይነት የኤሌክትሪክ አገልግሎት አያገኝም፡፡ አብዛኞቹ ፋብሪካዎች በኃይል እጥረት ምክንያት በተገቢው መጠን ለማምረት የሚቸገሩ ናቸው፡፡

ስለዚህም ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት ተጠቅማ የኃይል ፍላጎቷን ማሟላት ለነገ የማትለው ጥያቄ ነው፡፡ ይህን መሠረት በማድረግም ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በዓባይ ወንዝ ላይ ታላቁን የህዳሴ ግድብ በመገንባት ዛሬ ላይ ወደማጠናቀቁ ደርሳለች። እስካሁንም ባለው ሁኔታ አራት ተርባይኖች ወደ ኃይል ማምረት የገቡ ሲሆን ቀሪ ሥራዎችም እስከ 2017 መጨረሻ ድረስ ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይታሰባል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ኃይል ባመነጨበት ቅጽበትም ከሀገር ውስጥ ፍላጎት አልፎ ለጎረቤት ኬንያ እና ሱዳን ጭምር የኃይል አማራጭ መሆን ችሏል፡፡ በጎረቤት ሀገራት ዘንድም የትብብር እና የወዳጅነት ማህተም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

ሆኖም ይህ ግድብ እዚህ ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ በርካታ ፈተናዎችን አልፏል፡፡ በተለይም በውሃው ላይ የቅኝ ግዛት ውሎችን ጭምር በማንሳት የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱ ሀገራት ገንባታውን ለማስተጓጎል ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። በሀገር ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ ቅጥረኞችን ከማሰማራት አንስቶ በጸጥታው ምክር ቤት ጭምር በርካታ ጫናዎች ተደርገውበታል፡፡

ሆኖም የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት የያዙት ፍትሃዊ የመልማት ጥያቄ በመሆኑ ልማቱን ለማስተጓጎል የቻለ አንዳችም ኃይል የለም፡፡

በተመሳሳይም ኢትዮጵያ ኢፍትሃዊ በሆነ መልኩ የባሕር በር ያጣች ሀገር ነች፡፡ በዚህም ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነልቦናዊ ጫና ተዳርጋ ቆይታለች። ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነቷም አሽቆልቁሎ ቆይቷል፡፡

ስለዚህም እያደገ የሚሄደውን የሕዝብ ቁጥሯን ለመመገብ እና የኢኮኖሚ ጥያቄዋን ለመመለስ የአማራጭ ወደቦች ባለቤት መሆን አለባት፡፡ ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ ሰላማዊ አማራጮችን እየተጠቀመች ነው፡፡

ሆኖም የኢትዮጵያ ጥያቄ መልስ እንዳያገኝ የሚመኙ እና በህዳሴው ግድብ የተሸነፉ ሀገራት ጉዳዩን የተለየ መልክ በመስጠት በሰላም አስከባሪ ስም ምስራቅ አፍሪካ ድረስ በመምጣት ቀጣናውን የግጭት ማዕከል ለማድረግ ቢጥሩም ኢትዮጵያ በተከተለችው በሳል ዲፕሎማሲ መንገድ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ሰላም ዳግም ማበብ ጀምሯል፡፡

ስለዚህም የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ያነሱት ጥያቄ ፍትሃዊ ነውና ጥያቄውን በአግባቡ ከመመለስ ውጭ አማራጭ የለም፡፡ ኢትዮጵያውያን ያነሱት ትክክለኛ የመልማት እና የማደግ ጥያቄ በመሆኑ እነዚህን ጥያቄዎች በጭራሽ ማስቆም አይቻልም፡፡ ለዘመናትም በክህደት እና በሴራ ውስጥ መኖር ውጤት እንደማያመጣ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለው የእድገት ግስጋሴ ቋሚ መዘክር ነው፡፡ ውሾቹ ቢጮሁም ግመሎቹን ከመንገዳቸው የሚያስቆማቸው አንዳች ኃይል የለም፡፡

አዲስ ዘመን ሐሙስ የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

አሊሴሮ

አዲስ ዘመን ሐሙስ የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You