ባለውለታዎቻችን አስራሁለቱ የዓድዋ የጦር ጄኔራሎች

ኢትዮጵያ የጀግኖች መፍለቂያ ናት። በየዘመናቱ የሀገሬን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር አላስደፍርም ያሉ ጀግኖች ልጆቿ እምቢ ለሀገሬ በማለት አጥንታቸውን ከስክሰው፤ ደማቸውን አፍሰውና ሕይወታቸውን መስዋዕት አድርገው የሀገራቸውን ሉዓላዊነት አስጠብቀዋል፤ ለተተኪው ትውልድም አስረክበዋል።

ከኢትዮጵያ የጀግንነት መገለጫዎች ውስጥ አንዱ እና ዋናው ዓድዋ ነው። ዓድዋ ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር እና የጥቁር ሕዝቦች አለኝታ መሆኗን ያሳየ ደማቅ ታሪክ ነው። የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማኅተም፤ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው። የመላው ዓለም ተፈጥሯዊ ግብር እና ሠብዓዊ ክብር የታደሰው፤ በእውነት በፍትህ እና በህልውና ላይ የተቃጣው ጥቃት ድባቅ የተመታው በዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ታላቅ ድል ነው።

የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በግሩም ሥነሥርዓት የተደራጀ ግዙፍ የኢትዮጵያ ሠራዊት የማይታሰበውን ፈጽሟል። ወራሪው የጣሊያን ኃይል ላይ ድባቅ በመምታት ድልን ተቀዳጅቷል።

ሃያ ዘጠኝ ሺህ ፈረሰኞችን ጨምሮ ከመቶ ሺህ እስከ መቶ ሃያ ሺህ የሚገመት አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በባዶ እግሩ የተጓዘ የኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት፤ በወታደራዊ አካዳሚ የሠለጠነውን የአውሮፓ ወራሪ ጦር የካቲት 23 ማለዳ አሥራ አንድ ሰዓት ግድም ገጥሞ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ማሸነፉን ዓለም አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ገበሬ ሠራዊት ፈረሱ ላይ ሆኖ የጋሻውን እምብርት መሬት ላይ እያጣቀሰ ጐራዴውን አየር ውስጥ እየቀዘፈ በተቆጣና በቆረጠ መንፈስ በጀግንነት ተዋግቷል። ጦርነቱ በተጀመረ ከአምስት ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሃምሣ ስድስቱም የኢጣሊያ መድፎች ሙሉ ለሙሉ ተማርከዋል። የቅኝ ገዢውን ወራሪ ሠራዊት ከመሩት ጀኔራሎች ጄኔራል አልቤርቶኒ ሲማረክ የሠራዊቱ ዋና አዛዥ ጄኔራል ባራቴሪ ከጥቂት አጃቢዎቹና በሽንፈት ከተበታተኑ የጣሊያን ወታደሮች ጋር ሸሽቷል።

በዚህ ድብልቅልቅ ያለ ውጊያ ከሃምሣ ስድስቱ የጣሊያን መድፎች በተጨማሪ ብዙ ሺህ ቀላልና ከባድ መትረየሶች እንዲሁም የነፍስ ወከፍ ጠመንጃዎች በአሥር ሺዎችና በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩ መሰል ጥይቶቻቸው ጋር ተማርከዋል። በአጠቃላይ ምርኮው ወደ አዲስ አበባ የተጓጓዘው በአምስት መቶ አጋስሶች ተጭኖ ነው። ታላቁ የጥቁር ሕዝቦች ድል የዓድዋ ድል በመላው ዓለም ፖለቲካ ላይ ከፍተኛና ዋነኛ ለውጦች አምጥቷል።

የእንግሊዝ ጋዜጦች በዓድዋ ድል ማግስት የዓለም ታሪክ ተገለበጠ ታላቅ የትውልድ ኃይል በአፍሪካ ተቀሰቀሰ … ብለው ፃፉ። ዘመናዊት ኢትዮጵያን የፈጠሩ የተባሉት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በሌሉበት እና በአካል ባልተገኙበት የነፃነት ተጋድሎ መሪዎች ጉባዔ የአፍሪካ ብሎም የመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ መሪ ተደርገው ተመርጠዋል።

በዚህ ለነፃነት፣ ለፍትህና ለእኩልነት በተደረገው ተጋድሎ በግንባር ቀደምትነት የሚነሱ 12 የጦር መሪዎች አሉ። በመጀመሪያ የምናገኛቸው ፊት አውራሪ ገበያው ገቦ ጉርሙ ወይም በጀግንነት ስማቸው አባ ጎረው ናቸው። እኚህ ሰው ከዓድዋ ጦርነት አስቀድሞ ከነበረው ከአምባለጌ ጦርነት ጀምሮ ለሀገራቸው ነፃነት ትልቅ ተጋድሎ ያደረጉ አዋጊና ተዋጊ ሰው ናቸው። በመድፍ ተኳሽነታቸው የሚታወቁት ፊት አውራሪ ገበያው ከጠላት ጋር በጀግንነት ሲዋጉ ቆይታው በጦርነቱ የመጨረሻ ቀን በክብር ተሰውተዋል።

ሌላኛው የዓድዋ ጀግና ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ጉዲሳ ናቸው። በጀግንነት ስማቸው ደግሞ አባ ቃኘው። እኚህ ጀግናም ከአምበላጌ ጦርነት ጀምሮ እስከ ዓድዋ ጦረኛ በማዝመት ፈረሰኛና እግረኛ በመምራት ተዋግቶ በማዋጋት ለሀገራቸው ሉዓላዊነት ትልቅ ጀብዱ የፈፀሙ ሰው ናቸው። እኚህ ሰው ከዚህ በተጨማሪ ወራሪው ጣሊያን የውጫሌን ውል አስታኮ ኢትዮጵያን ለመውረር ሲመጣ ጉዳዩን በሰላም እልባት እንዲያገኝ ለማድረግ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ያደረጉ ሰው ናቸው። ጦርነቱ አይቀሬ ሲሆን ግን በጀግንነት ተፋልመው ሀገራቸውን ከወራሪ ታድገዋል።

በሶስተኛነት የምናነሳቸው ደግሞ ንጉሥ ተክለሃይማኖት ተሰማ ጎሹ ናቸው። በጀግንነት ስማቸው ደግሞ አባ ጠና ይሰኛሉ። ንጉሥ ተክለሃይማኖት ከዓድዋ ጦርነት አስቀድሞ በነበሩ በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ተሳትፎ አድርገዋል። በዓድዋ ጦርነት ደግሞ ፈረሰኛን ከእግረኛ አዋህደው በመምራት ጠላትን በጀግንነት ተፋልመው ያርበደበዱ ለሀገራቸው ነፃነት መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግና ናቸው።

ሌላኛው ሰው ደግሞ ንጉሥ ሚካኤል አሊ ሊበን ናቸው። የጀግንነት ስማቸው ደግሞ አባ ሻንቆ ይሰኛል። እኚህም ሰው በተመሳሳይ ከዓድዋ ጦርነት ባሻገር በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ማለትም በመቀሌ፣ በአምባለጌ ጦርነቶች እግረኛና ፈረሰኛ ጦር ድንቅ በሆነ ሁኔታ በመምራት ለሀገራቸው ውድ ዋጋ የከፈሉ ጀግና ኢትዮጵያዊ ናቸው።

በአምስተኛ ደረጃ ላይ የምንመለከታቸው ደግሞ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ሮባ ናቸው። አባ ነፍሶ በተሰኘው የፈረስ ስማቸው የሚታወቁት እኚህ ጀግና የንጉሥ ምኒልክ የግምጃ ቤት በጅሮንድም ነበሩ። እኚህ ጀግና ሰው በተመሳሳይ በመቀሌና በዓድዋ ጦርነቶች እግረኛና ፈረሰኛ ጦር በመምራት ለሀገራቸው በጀግንነት የተፋለሙ ሰው ናቸው። “ገበያው ቢሞት ተተካ ባልቻ መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ” ተብሎ የተገጠመላቸው ደጃዝማች ባልቻ በዓድዋ ጦርነት ሽንፈት ተከናንቦ የተመለሰው የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን ከዓመታት በኋለ ዳግም ሲወራት በወቅቱ ከንጉሥ ኃይለሥላሴ ጋር ስምምነት ባይኖራቸውም ከራሳቸው ጉዳይ ሀገራቸውን በማስቀደም ደግም በጀግንነት ተፋልመው የተሰው ጀግና ናቸው።

ራስ ወሌ ብጡል ሃይለማርያም ደግሞ ሌላኛው ሰው ናቸው። በጀግንነት ወይም በፈረስ ስማቸው አባ ጠጣው የሚሰኙት እኚህ ሰው ጀግና ጦረኛ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል። እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ጀግኖች ሁሉ ጦራቸውን ከአምባላጌ እስከ ዓድዋ ዘምተውና አዘምተው ለሀገራቸውና ሕዝባቸው ሉዓላዊነትና ነፃነት ትልቅ ዋጋ የከፈሉ ጀግና ናቸው። ራስ ወሌ የእቴጌ ጣይቱ ወንድም ሲሆኑ ደጀኑን ጦር ከደብረ ታቦር ተነስተው እየመሩ በቅድሚያ የዘመቱት በአምባላጌ ግንባር ነበር።

በሰባተኛ ላይ የምናነሳቸው ጀግና ደግሞ ፊት አውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ሁንዱል ናቸው። አባ መቻል በተሰኘው የጀግንነት ስማቸው የሚታወቁት እኚህ ሰው በጦር አማካሪነታቸውም ይታወሳሉ። እኚህ ሰው ፊት አውራሪ ገበያው በጦር ሜዳ በጀግንነት ሲሰው የሳቸውን ቦታ ተረክበው ጦር በማዝመት ድል የተቀዳጁ ጀግና ናቸው። በፈረስም በእግርም ተዋግተውና አዋግተው ለሀገር ነፃነት የተዋደቁ ሰው ናቸው።

ፊት አውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ በጦረኝነታቸው ወደር ከሌላቸው ውድ ኢትዮጵያዊ ጀግኖች መካከል አንዱ ናቸው። በዓድዋ የጦርነት ውሎ በርከት ያለ ሠራዊት ይዘው ጉልህ የጀግንነት ተጋድሎ አድርገዋል። እኚህን ሰው በፍርድ አዋቂነታቸው ስማቸውም ሀብቴ አባ መላ ይሉዋቸዋል። አባ መላ አጼ ምኒልክ ካረፉ ቡኋላ የሥልጣን ሽኩቻ እንዳይነሳ በማለት ሀገሪቷ በማረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

ራስ አሉላ እንግዳ ቁቢ ሌላኛው የዚህ ታሪክ አካል ጀግና ናቸው። በጀግንነት ስማቸው አባ ነጋ ይሰኛሉ። በስለላ ታሪካቸው የሚታወቁት እኚህ ሰው በተለይ የጣሊያን ጦር አሰላለፍ ምን ይመስላል የሚለውን በደንብ በመረዳት የኢትዮጵያ ጦር የተሻለ ቦታ ይዞ እንዲጠብቅና በወራሪው የጣሊያን ጦር ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እንዲያደርስ ጉልህ አስተዋጽኦ የነበራቸው ሰው ናቸው። ተዋግተውና አዋግተውም በጦር ሜዳ ጀብዱ የፈፀሙ የጦር መሪ ናቸው።

ሌላኛው ጀግና ደግሞ ራስ መንገሻ ዮሐንስ ምርጫ ናቸው። በጀግንነት ስማቸው አባ ግጠም ይሰኛሉ። እኚህ ሰው ከዓድዋ አስቀድሞ በነበሩ አውደ ውጊያዎች የተሳተፉ ናቸው። በተለይ በሁናትና ሰናፍ ግንባር ትልቅ ታሪክ የሠሩ ሰው ናቸው። በዓድዋ ጦርነትም በመሪነት ተሳትፈው የተዋደቁና ለሀገራቸው ትልቅ ዋጋ የከፈሉ ጀግና ሰው ናቸው።

ታሪክ በደማቅ ቀለም ከትቦ ከስቀመጣቸው የጦር መሪዎች መካከል ዋቅሹም ጓንጉል ብሩ ገብረመድህን አንዱ ናቸው። በጀግንነት ስማቸው አባ መርከብ ይሰኛሉ። እኚህ ጀግና በተለያዩ አውደ ውጊያዎች የተፋለሙ ሰው ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ የወራሪውን የጣሊያን ጦር መሪ ጄኔራል አልቤርቶኒን ጨምሮ ሌሎች የጠላት ጦር አባላትን በመማረክ ለዓድዋ ድል ጉልህ አስተዋጽኦ የነበራቸው የጦር መሪ ናቸው።

ራስ አባተ ቧያለው ንጉሡ ሌላኛው የዓድዋ ጀግና የጦር መሪ ናቸው። በጀግንነት ስማቸው አባ ይትረፍ ይሰኛሉ። የሊቀ መኳንንት ማዕረግ የነበረችው እኚህ ሰው በመድፍ ተኳሽነታቸው የሚታወቀውና በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ትልቅ ተጋድሎ ያደረጉ የኢትዮጵያ ጀግና ናቸው። እዚህ ላይ አንድ ትልቅ ገድል እናነሳለን እሱም ከዓድዋ በፊት የመቀሌውን ስትራቴጅካዊ የውሃ ምንጭ የመያዝ የራስ አባተ ቧ ያለው እና የደጃዝማች ባልቻ አባ ሳፎን ጀብዱ።

አፄ ምኒልክ ጦራቸው መቀሌ ደርሶ ሰፈሩን ተከፋፍሎ ከያዘ በኋላ በጣሊያን ምሽጉ ዙሪያ ራቅ እያለ ሰፈረ። ድንኳን በሚተከልበትና ጭነት በሚራገፍበት ጊዜ አንድ በቅሎ ፈርጥጦ ወደ ጣሊያኖች ምሽግ ሮጠ። አንድ ሰው ሊመልሰው ሲሮጥ ባዩ ጊዜ ጣሊያኖቹ የመድፍ ተኩስ ጀመሩ። ጣሊያኖቹ አብዝተው መተኮሳቸውን ንጉሠ ነገሥቱ በተመለከቱ ጊዜ ሊቀ መኳስ (በኋላ ራስ) አባተ ቧ ያለውን እና በጅሮንድ (በኋላ ደጅአዝማች) ባልቻ አባ ሳፎን ሂዱ እናንተም ተኩሱባቸው ብለው አዘዙ እና የምሽቱ ጊዜ በመድፍ ተኩስ አለፈ። ወደ ማታ ንጉሡ እንደገና ሊቀ መኳስ አባተን እና በጅሮንድ ባልቻን ጠርተው “እነዚህን ጣሊያኖች ከጉድጓዳቸው ሳላስወጣ የትም አልሄድም እናንተም የጠላት መድፍ ጥይት የማይደርስበትን ስፍራ መርጣችሁ ከዚያ ሆናችሁ ምሽጉን በመድፍ ምቱት” ብለው አዘዟቸው።

ሊቀ መኳስ አባተ ጦራቸውን ይዘው በምሽጉ በስተግራ የጣሊያኖችን ቃፊር ጠባቂ አባርረው ምሽግ አበጅተው መድፍና መትረየሳቸውን እንደጠመዱ በጅሮንድ ባልቻም በስተቀኝ በኩል ሌሊቱን ምሽግ ሠርተው መድፍ እና መትረየሳቸውን ጠመዱ። ጣሊያኖችም የእነሱን መጠጋት ባወቁ ጊዜ የመድፍ እና የጠመንጃ ተኩስ አበረከቱ። አነጣጥሮ በመተኮስ የተመሰገኑት ሊቀ መኳስ አባተም በሩቅ በሚያሳየው መነጽራቸው ጣሊያኖች ታቦቱን አስወጥተው መድፍ በመትከል የመሸጉበትን ቤተክርስቲያን ህንፃ በመመልከታቸው አስተካክለው ቢተኩሱ የመድፉ ጥይት በቤተክርስቲያኑ መስኮት ገብቶ የጠላትን መድፍ እግር ሰባበረው። ጣሊያኖችም ከተበላሸው መድፋቸው ጭስ እየጨሰ ባዩ ጊዜ በአፀፋው የመድፍ ጥይት ሊቀመኳስ አባተን እና በጅሮንድ ባልቻ ባሉበት ቦታ ላይ እንደ በረዶ አወረዱባቸው። ነገር ግን አንድም ሰው አልቆሰለም። ይህን ውጊያም አፄ ምኒልክ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት እና ሌሎችም መኳንንቶች ከድንኳናቸው ወደላይ ካለው ከፍተኛ ሥፍራ ላይ ሆነው በመነጽር ይመለከቱ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል።

ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም ቢተርፉ ሌላኛው የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ድል የሆነው ዓድዋ ጦርነት ተሳታፊ የጦር መሪ ናቸው። በጀግንነት ስማቸው አባ ገድብ ይሰኛሉ። በንጉሥ ምኒልክ ይወደዱ የነበሩት እኚህ ሰው የራስ ቢትወደድነት ማዕረግ ያገኙት በጦር ምክራቸው የታወቁ ስለነበር ነው። በዓድዋ ጦርነት እግረኛና ፈረሰኛ አዝምተው ትልቅ ድል የተቀዳጁት እኚህ የጦር ጀግና ከጦርነቱ በኋላም ድሉን ተከትሎ በተካሄደውና አንድ ኢትዮጵያ በፀናችበትና የውጫሌ ውል ደግሞ ውድቅ በሆነበት የአዲስ አበባው ስምምነትና የሰላም ድርድር የተካፈሉ ሰው ናቸው።

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ከጥግ እስከ ጥግ ቀፎው እንደተነካበት ንብ ተምመው በአንድ ጥላ ስር እንዲሰባሰቡ ያደረገ ታሪካዊ ክስተት በመሆኑ የኢትዮጵያውያንን ትብብር እና አንድነት ከማሳየቱም በላይ ለመላው የጥቁር ሕዝብ የነፃነት ምልክት መሆናችንን ማሳያ ነው። ለዚህም ጀግኖች አባቶቻችን የሠሩት ውለታ ዝንተ ዓለም ሲዘከር ይኖራል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You