
ጀግንነት ዓይነቱ ብዙ ነው። በተለይም በአሁኑ በዘመናዊው ዓለም ጀግንነት ገዳይነት ሳይሆን ታጋሽነት፣ ሰላም ፈላጊነት፣ ታታሪ ሠራተኛነት ማለት ነው። በነገራችን ላይ በወታደራዊ ትርጓሜም ጀግነት ገዳይነት አይደለም። ወታደራዊ ልምድ ያላቸው ሰዎች ሲያወሩ እንደምንሰማው፤ የአንድ ጄኔራል ተቀዳሚ ተግባር ጦርነት ሳይሆን ጦርነት የማይነሳበትን መንገድ ማመቻቸት ነው። እንኳን ለሲቪል ዜጋ ይቅርና የጦር መሪና ለጄኔራል ሳይቀር ጦርነት የመጨረሻ አማራጭ ነው። ስለዚህ ጀግንነት የግድ ገዳይነት አይደለም!
ያም ሆኖ ግን የኢትዮጵያ ባሕል ሁሉንም ያውቅበታል። ሁሉም አይነት ጀግንነት ከባሕሉ ጋር የተዋሓደ ነው። ኢትዮጵያ ጀግና ናት! ኢትዮጵያ ጀግና ናት የምንለው የጀግንነትን መስፈርት ስላሟላች ነው። ጀግና ሳይነኩት አይነካም፤ የነኩትን ግን ልካቸውን ያሳያል። ኢትዮጵያ ደግሞ በታሪኳ ማንንም ነክታ አታውቅም፤ ኢትዮጵያን የነኩ ግን ልካቸውን አይተው ተመልሰዋል።
ይህ የኢትዮጵያ ጀግንነት ከየት የመጣ ነው? ከተባለ፤ የኢትዮጵያን ባሕል ልብ ብሎ ማስተዋል ነው። ሰሞንኛውን የዓድዋ ድል በዓል ምክንያት በማድረግ እስኪ የኢትዮጵያን ሕዝብ ባሕል ልብ እንበል።
ጀግንነት ለኢትዮጵያውያን ዘረመላዊ ተፈጥሮ ይመስላል። ባሕላችን ራሱ በተዋጊነት፣ በአይሸነፌነት ላይ የተመሠረተ ነው። የሀገር ቤት የባሕል ዘፈን ውስጥ ‹‹አያ በለው በለው!›› የሚለው አዝማች የብዙ ዘፈኖች ማስጀመሪያ ነው።
ለልጅ ስም ሲወጣም እንደዚሁ ነው፤ በለው፣ ደምመላሽ፣ አሸንፍ፣ አስጨንቅ፣ ቅጣው፣ አሳምነው….. ብቻ የሆነ የአሸናፊነት መልዕክት ያለው ስም ነው።
የልጆች ጨዋታ ራሱ እንደዚሁ ነው። ግንባር ፈጥሮ መጋጠም፤ አሸናፊው ቡድን ይጨፍራል ተሸናፊውም ይቆጫል። የሚገርመው እኮ ደግሞ ተሸናፊው ራሱ ተሸናፊ አይደለም፤ መልሶ መጋጠም ያምረዋል። ልጆች ገና እረኛ እያሉ ትግል ይገጥማሉ፤ በትግሉ የወደቀ ተነስቶ እንደገና ይይዛል። እንኳን ልጆቹ ራሳቸው የሚጠብቋቸውን ከብቶች ራሱ ማጋጠም የተለመደ ነው። በሬው ያሸነፈለት እረኛ ከጦር ሜዳ ድል ያደረገ ያህል ኩራት ይሰማዋል።
የገና ጨዋታው፣ የኳስ ጨዋታው፣ የድብብቆሽ ጨዋታው፣ የዒላማ ጨዋታው ሁሉ ከአሸናፊነትና ተሸናፊነት ጋር የተያያዘ ነው።
በዓድዋ ጦርነት ጊዜ ምንሽር ከያዘው ወታደር እኩል ማሲንቆ የያዘ አዝማሪ ይሰለፍ ነበር አሉ። እንዲያውም የወታደሩ ወኔ አዝማሪው ነው። ይሄ ታሪክ ተጽፎ የምናነበው ታሪክ ነው።
እኔ ደግሞ በዓይኔ ያየሁትን በጆሮዬ የሰማሁትን ልናገር። ገጠር ውስጥ እንደ ሠርግ የመሳሰሉ ድግስ የሚደገስባቸው ጉዳዮች ሲኖሩ ተሰባስቦ መጫወት የተለመደ ነው። ጨዋታ ማለት ታዲያ ቀረርቶና ፉከራው ነው። በዚህ ቀረርቶና ፉከራ ውስጥ ነው እንግዲህ ተዓምር የሚታየው። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ አባቶች ቀረርቶና ፉከራውን ያስቆሙታል። በአካባቢው የተጣላ ሰው ካለ በአቅራሪነት የሚታወቁ ሰዎችን ቀደም ተብሎ ይነገራቸዋል። እገሌና እገሌ ተቀያይመዋልና የዚያን ዕለት አዳራችሁን ምንም ዓይነት ቀረርቶ እንዳትጀምሩ ይሏቸዋል። ቀረርቶው ከተጀመረ ፉከራ አለ፤ ፉከራ ካለ እንግዲህ መሣሪያውን አቀባብሎ አለበለዚያም ዱላውን ይዞ ወደተጣላው ሰው መሮጥ ነው።
እዚህ ላይ አንድ ነገር ይገመት ይሆናል። እንዲህ አይነት ጉዳይ ላይ መጠጥ ስላለ በስካር ተገፋፍተው ነው የሚል ግምት ማለት ነው። ከገመታችሁ ትክክል ናችሁ፤ ስካርም አለ። ዳሩ ግን ከስካሩ በላይ ቀስቃሹ ቀረርቶና ፉከራው ነው። ይሄን ነገር ብዙ ሰው ልብ የሚለው አይመስለኝም። የገጠር ነዋሪዎች በስካር ከሚነሳሱት ይልቅ በእንዲህ አይነት ነገር የሚነሳሱት ነው የሚበልጠው። በነገራችን ላይ የገጠር ነዋሪ ሁሉ የሚጠጣ አይደለም፤ መጠጥ በሄደበት የማይሄዱ አሉ፤ እነዚህ ሰዎች ግን ቀረርቶና ፉከራ ሲነሳ ሳግ እየተናነቃቸው ይፎክራሉ። እንዲያውም ተቃራኒውን ልንገራችሁ። እንዲህ ዓይነት ጉዳይ ላይ ጥንብዝ ብሎ የሰከረ ሰው ሊያቅራራም ሊፎክርም፣ ሊጣላም አይችልም። ዝም ብሎ ይዘባርቃል እንጂ ወኔ ቀስቃሽ ግጥም ሊናገር አይችልም።
እንዲህ አይነት አጋጣሚ ለገጠሩ ነዋሪ እንደነፃ ፕሬስ ያገለግላል። የልባቸውን የሚናገሩት፣ በነገር የሚወጋጉበት ነው። ለዚያውም በቅኔ ነዋ! ዓድዋን ምክንያት አድርገን እስኪ አንዳንዶቹን እንያቸው!
የተጣላን ሰው ማስታረቅ የተለመደ ነው። ታዲያ በእርቁ ያልተስማማ ወይም እርቁን ማፍረስ የፈለገ ብሶተኛ ለተቀናቃኙ እንዲህ ይላል።
ውሽልሽል ነው አልጠበቀም እርቁ
ዓውድማው ይለቅለቅ በሮችም አይራቁ
ይላል። ሁለቱም ተቀናቃኞች ነገረኛ ከሆኑና ጠቡ የማይቀር መሆኑን ለመግለጽ ይመስላል ሌላ (ሦስተኛ ወገን) ደግሞ ለሽማግሎች መልዕክት ይሆን ዘንድ እንዲህ ይላል።
አንድ መልክ በሮች ከዳገት ጠምዳችሁ
ኋላ መመለሻው እንዳይቸግራችሁ!
በእንዲህ ዓይነት ጉዳይ ላይ የተከፋን ሰው ከሚናገረው ግጥሞች መረዳት ይችላሉ። ገና አዲስ ጠብ ለመጀመር ያሰበ ራሱ ያስታውቃል። ከሰው ተጣልቶ ቤቴን፣ ልጆቼንና ንብረቴን ያለ ሰው ደግሞ እንዲህ ሊል ይችላል።
ጓዜን ጠቅለል ጠቅለል፤ ከብቴን ነዳ ነዳ
ምናልባት ሰው ሆኜ ጠላቴን ብጎዳ
ብዙ ጊዜ በጠብአጫሪነት የሚታወቁት ደግሞ ብዙም ሀብትና ንብረት የሌላቸው ናቸው። ታዲያ እነዚህ ሰዎች ጓዝና ሀብት ባላቸው ደግሞ እንደ ጀግና ሳይሆን እንደ ቦዘኔም ይታያሉ። ‹‹ማረስና ሀብት ማፍራት ሲያቅተው›› እያሉ በነገር ጎሸም ያደርጉታል። እሱም ደግሞ ይሄን ቦዘኔነቱን እንደጀብዱ ነው የሚቆጥረው። ከአንድ ሀብታም ጋር ቢጣላ እንዲህ ሊል ይችላል።
አትንኳት ጎጆዬን በአንድ እግሯ ቆማለች
ትልቁን አዳራሽ ይዘው ትጓዛለች!
የውስጡ ወኔ አላስቀምጥ አላስተኛው ይለውና ዳሩ ግን የልጆቹ፣ የቤቱና የቤተሰቡ መጉላላትን ሲያስበው ደግሞ ግራ ይጋባል። ጓዝና ቤት ያለው እንዲህ ዓይነቱ ሰው ደግሞ እንዲህ ይላል።
ላሚት እሳት ወልዳ
እንዳትልሰው ፈጃት
እንዳተወው ቆጫት
የማይረባ ኑሮ ያደርጋል እመጫት!
እንግዲህ የሚረባ ኑሮ ማለት ለእርሱ ክላሽ ይዞ ሰውን ማስፈራራት ነው ማለት ነው።
ሰሞንኛው ዓድዋ ስለሆነ እነዚህን ጥቂት ስነ ቃሎች እንደ ማሳያ ተጠቀምን እንጂ ብዙ ናቸው። አንድ ነገር ያሳየናል። ጀግንነት የኢትዮጵያውያን የደም ዓይነት ሆኗል። እነዚህን ሥነ ቃሎች ያስፈጠራቸው የውስጥ ወኔያቸው ነው። እነዚህ ገበሬዎች የዓድዋን ታሪክ ላያውቁት ሁሉ ይችላሉ። ጀግና ያደረጋቸው የምንም ነገር ተፅዕኖ አይደለም፤ ሲወርድ ሲወራረድ የተዋረሰ ነው። ጀግንነትን በየዘርፉ ያውቁበታል። ጠብ አጫሪነት ጀግንነት እንዳልሆነ በሥነ ቃሎቻቸው ይመሰክራሉ። ክብርና ሞገስ በአጥንትና ደማቸው ሀገራቸውን ላስከበሩ ጀግኖች እያልን በዚች የሕዝብ ሥነ ቃል እንሰናበት።
ቆራጥ ጎበዝ እና ነብር አንድ ናቸው
ሰው ደርሰው አይነኩም ካልደረሱባቸው!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም