‹‹ለባህል ህክምና እውቅና የምንሰጥበት ሕጋዊ ማሕቀፍ የለንም›› አቶ እንጋ እርቀታ

 

አቶ እንጋ እርቀታ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምግብና መድሃኒት ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ

የአዲስ አበባ ከተማ ምግብና መድሃኒት ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 84/2016 የምግብ፣ ጤና እና ጤና ነክ ብቃት ማረጋገጥ፤ የምርት እና አገልግሎት ደህንነት እና ጥራት እንዲረጋገጥ ማድረግ፤ ወቅታዊ የምግብ፣ ጤና እና ጤና ነክ ቁጥጥር ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ፤ የምግብ፣ የጤና እና ጤና ነክ አገልግሎት እና ምርት ተገቢነትን ማስጠበቅ፤ እንዲሁም አግባብነት ማረጋገጥ ከተሰጡት ተግባርና ኃላፊነት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ባለሥልጣኑ ሕገ ወጥ የምግብ፣ ጤና ነክ እና መድኃኒት ዝውውር በመቆጣጠር እና በመከላከል የምርት ጥራት እና ህክምና መሣሪያዎች ደህንነት የማረጋገጥ ተግባሩን በምን መልኩ እየተወጣ ነው? ለባህል ህክምና የሚሰጣቸው እውቅና ወይም ምዝገባ ምን ይመስላል? በሚሉ እና መሰል ጥያቄዎች ዙሪያ የባለሥልጣኑን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ እንጋ እርቀታን አዲስ ዘመን የተጠየቅ እንግዳ አድርጎ አቅርቧቸዋል።

አዲስ ዘመን፡- የባለሥልጣኑ ዋና ዓላማ ምንድን ነው?

አቶ እንጋ፡- በዋናነት የተቋሙ ተግባር በምግብና መድሃኒት ላይ ቁጥጥር ማድረግ ነው። ይህም የብቃት ማረጋገጫ፤ ለጤና ባለሙያዎች ፈቃድ መስጠት ሲሆን፣ በቁጥጥር ዘርፍ የምግብና መጠጥ ተቋማት አሉ። ተቋማት በተሰጣቸው ብቃትና ‹‹ስታንዳርድ›› መሠረት የማረጋገጥና የመቆጣጠር ሥራ ያከናውናል። ስለዚህ በዓመት ቢያንስ ሁለት ጊዜ መደበኛ የቁጥጥር ሥራ ይሠራል። በተመሳሳይ ደግሞ በጤና ተቋማት ላይ ማለትም ከመጀመሪያ ጤና ጣቢያ ጀምሮ እስከ ሆስፒታል ድረስ ያሉ የህምክና ተቋማት እና የመድሃኒት ማከማቻ መጋዝን (ፋርማሲዎች) የቁጥጥር ሥራ ይከናወናል።

የቁጥጥሩ ሥራ የሚከናወነው ተቋማቱ በተቀመጠላቸው የመመዘኛ ደረጃ መሠረት ነው፤ አይሠሩም የሚለውን መስፈርት መሠረት ባደረገ መልኩ ነው። የጤና ባለሙያዎች በተቀመጠላቸው መስፈርት መሥራታቸውን፤ የሚሰጡት ክሊኒካል አገልግሎት ቁጥጥር ይደረጋል። ብቃት የማረጋገጥ ሥራ ማለት የምግብ ማብሰያ ወይም ምግብ ቤት አገልግሎት ለሚሰጡ ተቋማት የፍቃድ ማረጋገጥ ሥራ ነው። በሚያመለክቱት ማመልከቻ መሠረት በመፈተሽ አገልግሎት መስጠት በሚችሉት ደረጃ ላይ መሆናቸውን የቅድመ ፍቃድ ኢንስፔክሽን ተሠርቶ ይሰጣቸዋል።

ተቋማት ዕድሳት ሲያስፈልጋቸው በየዓመቱ ወደ ተቋሙ በመምጣት እንዲያድሱ ይደረጋል። የጤና ባለሙያዎች በአሠራር መሠረት በየሶስት ዓመቱ የአንድ ጤና ባለሙያ ፈቃድ መረጋገጥና መታደስ አለበት። እነዚህን የተሰጡና የተሠሩ ሥራዎችን በቁጥጥር ይፈትሻሉ።

የቁጥጥር ሥራው ሁለት አይነት ሲሆን፣ መደበኛ የቁጥጥር ሥራ እና ችግራቸውን ባነጣጠረ ሁኔታ የሚካሄድ ቁጥጥር ነው። ለምሳሌ አንድ ሺህ ተቋም ቢኖር ወደ ሁሉም ተቋም አይኬድም። ለአብነት አንድ ሺህ ቢኖር ከእነዚህ መካከል ለአደጋ የተጋለጡ የተባሉ ቅድሚያ በመስጠት በተለየ መልክ ክትትል ይደረግባቸዋል። በሁለተኛ ዙር የቁጥጥር ሥራ ማስተካከላቸውን የመፈተሽ ሥራ ይሠራል። ስለዚህ ድንገተኛ እና መደበኛ ቁጥጥር ሥራ ይካሄዳል።

በተቋሙ ጎታች የነበረውን አሠራር ለማስቀረት የሪፎርም ሥራ ሠርተናል። ተቋሙን በአዲስ መልክ ከላይ እስከታች የማደራጀት ሥራ ተሠርቷል። ሥራው በተቻለ መጠን በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ለማድረግ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አሉ። በተጨማሪም ሁሉንም ማስተናገድ የሚያስችል አዲስ ቴክኖሎጂ በአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ቢሮ አማካኝነት እየተጠና ነው። አሁን ላይ የፈቃድ አሰጣጡ በሙከራ ደረጃ ሥራ ጀምሯል። የቢሮ አደረጃጀታችን የተጠያቂነት ሥርዓት እንዲሰፍን ማስቻል ነው። ከተቆጣጠርናቸው ተቋማት 31 ሚሊዮን ብር የሚገመት ምግብና መድሃኒት እንዲወገድ ተደርጓል። ምግብና መድሃኒትን ጨምሮ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድሃኒቶችና ባዕድ ነገሮችን ከምግብ ጋር በማቀላቀል ጥቅም ላይ ለማዋል ሲደረግ የነበረው ተግባር ተገኝቶ ሊወገድ ችሏል።

የተወገደበት ምክንያት በአያያዝ ችግር ምክንያት የተበላሹ፤ በጸሀይ ብርሃን ምክንያት ተጋላጭ ሆነው በሕገ ወጥነት ተይዘው፤ በህብረተሰቡ ጥቆማ እና በተቋሙ የቁጥጥር ሥርዓት ተደርሶባቸው ርምጃ የተወሰደባቸው ናቸው። የርምጃ አወሳሰዱ በሁለት መልክ ሲሆን፣ ችግሩ የሚቀርበው ምግብ ላይ ወይም መድሃኒት ላይ ከሆነ መጀመሪያ በምርቱ ላይ ጥቅም ላይ እንዳይውል የማስወገድ ርምጃ መውሰድ ነው። በተጨማሪም ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ እስከ ማሸግና ስረዛ ድረስ ያደርሳል። በስድስት ወር ውስጥ ማስተካከል ያልቻሉ ሁለት ተቋማት ላይ የሥራ ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ ተደርጓል። በበርካታ ተቋማት ላይ ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ ለሶስት ወር የታሸገባቸው የመድሃኒት ቤቶች አሉ። በማዘዣ ተጠቅመው መድሃኒት ያለመሸጥ ሁኔታ በተደጋጋሚ ያጋጥማል። የትኛውም መድሃኒት ከሀኪም ትዕዛዝ ውጭ መሸጥ የለበትም። ለምሳሌ ከፓራስታሞል ወይም አንቲፔይን በስተቀር ከሀኪም ፊርማ ውጭ መድሃኒት አይሸጡም። አንዳንድ ጊዜ መድሃኒቱ የመጣበት ከትክክለኛ ምንጭ ሳይሆን በሕገ ወጥ መንገድ ሊመጣ ይችላል።

አዲስ ዘመን፡- የምግብና መድሃኒት ጉዳይ ሲነሳ አብሮ የሚነሳው የሰው ልጅ ሕይወት ነው እና የቁጥጥር ሥራው የላላ ነው ይባላል፤ ካለው አደረጃጀት አቅም አንጻር ሥራው በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አቶ እንጋ፡- አደረጃጀቱ ሲነሳ ግልጽ መሆን ያለበት ከማዕከል እስከታችኛው የወረዳ መዋቅር ድረስ በክላስተር በሶስት እርከን በማደራጀት በማዕከል ሰባት የሚደርሱ ዓላማ ፈጻሚ አደረጃጀቶች አሉት። እነዚህ በቀጥታ ሥራውን የሚቆጣጠሩ ናቸው። ለምሳሌ የጤና ተቋማት ባለሙያዎች ቁጥጥር ዳይሬክተር፤ የምግብና ጤና ነክ ተቋማት ቁጥጥር የሚባል አንድ ዳይሬክተር እስከታችኛው የሥራ እርከን ድረስ የተዋቀረ አደረጃጀት ያለ ሲሆን፣ በተጨማሪም የህክምና ስህተትና ተያያዥ ጉዳዮች ዳይሬክተር በሥራ አደረጃጀቱ ውስጥ አለ። በዚህም የህክምና ስህተት ተፈጥሮብኛል የሚል አቤቱታ ሲመጣ አቤቱታውን ተቀብሎ የሚያይ የህክምና ችሎት ስላለ ይታያል።

በሌላ በኩልም የሰርቪላንስ ሥራ የሚሠራ በህቡዕ የተደራጀ የኢንተለጀንስ ቡድን ተዋቅሮ ሥራ ላይ ነው። ይህ የሚሆነው በመደበኛው ቁጥጥር የማይገኝና በተለይም በሕገ ወጥ ምግብና መድሃኒት ዝውውር ላይ ከፍተኛ ወንጀል ስለሚኖር በጥልቀት ክትትል ያደርጋል። መዲናዋ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መውጫ መሆኗን ታሳቢ ያደረገ የሕገ ወጥ ምግብና መድሃኒት ሰርቪላንስ ዳይሬክቶሬት ተደራጅቶ ሥራ እየሠራ ነው። ስለሆነም ተቋሙ የአደረጃጀትና የሰው ኃይል ችግር የለበትም።

በ11ዱም ክፍለ ከተማ የባለሥልጣኑ ቅርንጫፎች ያሉ ሲሆን፣ በተመሳሳይ 36 ክላስተሮች አሉ። ሁሉም በየደረጃው ሥራውን ይሠራል። ትልልቅ ተቋማት በማዕከል ደረጃ ይሰጣሉ። አብዛኛዎቹ ሆስፒታል የሚባሉት ጀነራል ሆስፒታል፣ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እና መሰል ሆስፒታሎች በማዕከል ደረጃ ይሰጣሉ። ፈቃድ የሚሰጠው በማዕከሉ ሲሆን፣ ቁጥጥሩም በራሱ በማዕከሉ ነው። ከዚያ በታች ያሉት ስፔሻሊቲ ክሊኒክ፣ መካከለኛ ክሊኒክ፣ መለስተኛ ክሊኒክ ቅርንጫፍ የሌላቸው መድሃኒት ቤት፤ በቅርንጫፍ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል።

አንዳንድ ፋርማሲዎች ቅርንጫፍ ያላቸው አሉ። በአንድ ፈቃድ ብዙ ቦታ ላይ የሚከፍቱ አሉ። እነዚህን በተገቢው መንገድ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት የእርምት ርምጃ ተወስዷል። አንድ ጥቆማ ከመጣ በጥቆማው መሠረት በቀጥታ ይፈልጋል። ኦፖሬሽን ሠርቶ ለዋና ሥራ አስኪያጅ ያቀርባል። በዚህ መንገድ ርምጃ የተወሰደባቸው አካላት አሉ።

ዘመኑ የቴክኖሎጂ እንደመሆኑ መጠን ሰው የተወሰነ ህመም ሲሰማው በራሱ ይህ በሽታ ነው ያመመኝ ብሎ ፋርማሲዎች ዘንድ በመሄድ መድሃኒት ሽጡልኝ የማለት ዝንባሌ ይስተዋላል። አሁን እንዲህ በሚያደርጉ ተቋማት ላይ በቀጥታ መዝጋት ብቻ ሳይሆን በሁለቱም ቁጥጥሮች የተሸጠ ያልተሸጠ መረጃ ይያዛል። በቁጥጥር ማስተካከያ ማድረጉንና አለማድረጉን የመከታተል ሥራ ይከናወናል። በተለይም ደግሞ ያለሀኪም ትዕዛዝ መሸጥ የማይቻሉ ብዙ መድሃኒቶች አሉ። ስለዚህ በትክክል ተቀምጠዋል አልተቀመጡም የሚለው ክትትል ይደረግባቸዋል። መድሃኒትን ባልተገባ መንገድ ሲሸጥ የተገኘ ፋርማሲ ቤት ወዲያወኑ ርምጃ ይወሰድበታል።

የትኛውም መድሃኒት ቤት ብራንድ የሆኑ መድሃኒቶች ያለሀኪም ትዛዝ ሊሸጡ አይችሉም። ፡ ምክንያቱም ከፍተኛ ቅጣት ይጠብቃቸዋል። ህብረተሰቡ ያለሀኪም ትዕዘዝ መድሃኒት እንዳይገዙ ለማድረግ በሕዝብ የንቅናቄ መድረክ ግንዛቤ ፈጥረናል። በተጨማሪም የቁጥጥር ፎረም በሚል በሁሉም ክፍለ ከተሞች ላይ ተደራጅቶ እንዲሁም 36ቱም ክላስተሮች ላይ ‹‹እኔ ለጤናዬ ባለሥልጣን ነኝ›› በሚል መርህ በ8864 ነጻ የስልክ ጥሪ መቀበያ በርካታ የሕዝብ ጥቆማዎች እየመጡ ነው።

በቀን በርካታ ጥቆማዎች እየደረሱን ነው። ራሳቸው በራሳቸው መከታተልና መቆጣጠር እየቻሉ የመጡ ተቋማት አሉ። ለአብነት ብንጠቅስ ባለኮከብ ሆቴሎች የጥራት ማኔጀር እና የጤና ባለሙያ ቀጥረው በራሳቸው ክትትል የሚያደርጉበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። እንደ ሸራተን እና ስካይላይት ሆቴል ራሳቸው ቀጥረው እየሠሩ ነው። ባለሥልጣኑ በየጊዜው የቁጥጥር ሥራውን ይሠራል። ተቋማት ራሳቸው በራሳቸው ተቆጣጣሪ መሆን አለባቸው። የጤና ሙያ ያለው ማኔጀር እንዲቀጥሩ ምክረ ሃሳብ ቀርቦ ራሳቸው እንዲቆጣጠሩ ይደረጋል። በየጊዜው ስለሚመዘኑና ቁጥጥር ስለሚከናወን ስጋት የሚሆን ነገር የለም።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን የባለሥልጣኑን የምስክር ወረቀት ስለሚፈልጉ በጥንቃቄ ይሠራሉ። ስመ-ጥር የሆኑ ሱፐር ማርከቴት ሱቆች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ከመድረሱ በፊት ሱቃቸው በር ላይ አከማችተው እንዲሸጡ ያደርጋሉ። አንድ ምርት የመጠቀሚያ ጊዜው ሶስት አራት ወር የቀረው ካለ በር ላይ በማምጣት እንዲሸጥ ያደርጋሉ። ይህ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የሥራ ውጤት ነው። ካልተሸጠ የሚወገደው በራሳቸው ሳይሆን ለባለሥልጣኑ በማመልከት ነው። በመሆኑም የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድሃኒቶች ለይተው የሚያስቀምጡበት ማከማቻ ክፍል መኖር አለበት። ለይተው ያስቀመጡትና የሽያጭ ሰነዱ ላይ የተመዘገበው ታይቶ ስለሚረጋገጥ በትክክለኛው ሥርዓት ገብተው እንዲሰሩ የሚያደርግ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ባለሥልጣኑ በአደረጃጀቱ ልክ እየሠራ አይደለም፤ ጥቆማ ስንሰጥ በተገቢው መንገድ የእርምት ርምጃ ሲወሰድ አናይም በማለት ማህበረሰቡ ቅሬታ ሲያነሳ ይደመጣል፤ ርምጃ ከመወሰድ ይልቅ የቁጥጥር ሠራተኞች ድርድር ያደርጉበታል የሚል ቅሬታም አለ፤ በዚህ ላይ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው?

አቶ እንጋ፡- አንድ ገዥ የሚሆነው ነገር የትኛውም አካል ጋር ብልሽት እንደሚያጋጥመው ሁሉ እኛም ጋር ያጋጥማል። አገልግሎቱን ፈልጎ የሚመጣ ሳይሆን ሠራተኞች ወደ ነጋዴው ጋር በመሄድ የሚሠራ ሥራ ነው። ለዚህም የመማር ማስተማር ስትራተጂ አስቀምጠናል። ኦፕሬሽን ሊወስድ የሚችል አደረጃጀት አለ። ለምሳሌ ከበላይ አመራሩ ውጭ ማንም የማያውቀው የክትትልና ቁጥጥር ሥራ የሚሠራ ቡድን ተቋቁሞ እየሠራ ነው። አንዱ ነገር ተቋማት ብዙ ናቸው። የጤና ተቋማት በተለይ ክሊኒክና ፋርማሲ ላይ ቁጥጥር ይደረጋል። ብዙ ጊዜ ሕገ ወጥነት የሚበዛው ምግብ ቤቶች አካባቢ ነው። አንዳንዱ ሕገ ወጥነቱን የሚጀምረው ከንግድ ፈቃድ አለማውጣት ነው።

መደብ ይዞ የማይሠራ መመረቻቸው የማይታወቁ ምርቶችን በየጓዳው የሚሸጥ አካል አለ። ተዘዋዋሪና ኮንትሮባድ የሆነ ተግባር ይስተዋላል። ይህን ለመቆጣጠር በቅንጅት እየተሠራ ነው። መደበኛ ነጋዴው በቁጥጥር ሥርዓት መድረስ ስለሚቻል በቁጥጥር ይደረስበታል። ችግር እያለ አንድ የቁጥጥር ሠራተኛ ተደራድሮ መጣ ማለት ከሕዝብ የተደበቀ ነገር ስለሌለ ይደረስበታል። እስከሚደረስበት ግን ሊበላ ይችል ይሆናል። ነገር ግን ለዚህ ሥራ ሲባል የቁጥጥር ፎረም ተደራጅቷል። እኛ ዘንድ ችግር ካለ ጥቆማ ማድረስ የሚችል ነው። የትኛውም ሕገ ወጥነት ሥራ ከህብረተሰቡ የተሰወረ አይደለም። ከባለሥልጣኑ ባለሙያዎች በላይ ህብረተሰቡ በጎረቤቱ ምን እየተሠራ እንደሆነ ያውቃል። ስለዚህ የሕገ ወጥነትን አስከፊነት ግንዛቤ የምንሰጥበት አደረጃጀት ፎረም ትልቅ ተፅዕኖ አምጥቷል።

ለጸሃይ ተጋላጭ የሆኑ የምግብና መድሃኒት ቦታዎችን የመቶ ቀን እቅድ በማውጣ እየፈተሽን ነው። ህብረተሰቡ በጥቆማ መስጫው የነጻ የስልክ መስመር ላይ በጸሃይ የሚንቃቃ ምርት አለ ብሎ ጥቆማ የሚሰጠው ህብተሰብ እየጨመረ ነው። ለዚህም በቴሌ አማካኝነት ነጻ የስልክ መስመር ስልኩን እንደገና የማስተዋወቅ ሥራ ሠርተናል። በዚህ ደረጃ ብልሹ አሠራሮችን ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር እየተሠራ ነው። ተቋሙ ብር ቢሰጥና ባይሰጥ የትኛው ነው የተሻለ የሚሆነው የሚለውን ለባለሀብቱ ግንዛቤ ፈጥረናል። ሁልጊዜ ጉቦ እየከፈለ ይቀጥላል ወይ የሚለውን መገንዘብ ያስፈልጋል።

የኮሪደር ልማቱ በርካታ መልካም ዕደሎችን ይዞልን መጥቷል። አሁን ላይ በጸሃይ ተጋልጦ ልስራ ቢል ሁሉም የሚታይ ስለሆነ የሚያሠራው አካል የለም። ግልጽ በሆነ ሁኔታ ለክትትልና ለቁጥጥር አመች ሁኔታ ስለፈጠረ የሚደበቅ ነገር አይኖርም። ከዚህ አምልጦ የሚመጣ ሌብነት ካለ ርምጃ ላለመውሰድ የምንደራደርበት ምክንያት አይኖርም። ለምሳሌ ሙያቸውን ያለአግባብ ለሌብነት የተጠቀሙ አራት ባለሙያዎች ከሥራ ገበታቸው ተሰናብተዋል። ርምጃው ሌላውን እንዲሰበሰብ የሚያደርግ ነው። ለዚህም የተጠራጠርነው የሥራ ክፍል ሲኖር በተዘዋዋሪ እንዲታይ ይደረጋል። ተጋላጭነታችንን ተንተርሶ የሚመጣ የሌብነትና የብልሽት ዝንባሌ እንዲቀንስ ለማድረግ በሕዝብ በኩል በሚመጣ ጥቆማና በራስ የቁጥጥር አቅም ርምጃ እየወሰድን የማስተካከል ሥራ እየተሠራ ነው። በተጨማሪም ማህበረሰቡ ብር አውጥቶ በሚገዛው ንብረት ላይ ሙሉ ባለሥልጣን ነው። የሚገዛው ምርት ከየት እንደተመረተ አውቆ ጠይቆ የመግዛት ኃላፊነት አለበት። ይህ ሲሆን ችግሮች እየቀነሱ ይመጣሉ። በዚህ አግባብ ሲሠራ ሕገወጥነቱ አይቀጥልም።

አዲስ ዘመን፡- ማህበረሰቡ ብዙ ጊዜ ጥቆማ ለመስጠት የሚዳዳው ርምጃ ፍራቻ ነው፤ “ጠቋሚ ነህ ቢለኝስ” የሚል ስጋት ስላለ ነውና እንዲህ አይነትና መሰል ስጋቶችን የምትቀንሱት በምን መልኩ ነው?

አቶ እንጋ፡- ጥቆማ የሚሰጡ ሰዎች በምንም መልኩ አይገለጹም። በአካል መምጣት አይጠበቅባቸውም። ይህ ማለት ደህንነቱ የተጠበቀ ነው። የጥቆማ መቀበያው ስልክ የሰውን ማንነት አይገልጽም። አንዳንድ ጥቆማ ሰጪዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ቦታው ድረስ ላደርሳችሁ እችላለሁ ብለው ይናገራሉ። ሕገ ወጦች በቻሉት መጠን በተራቀቀ መንገድ ነው የሚንቀሳቀሱት። ስለሆነም ማን ሊጠቁም ይችላል የሚለውን ሃሳብ ብዙ ጊዜ አይዘጋጁበትም። ይህን በሚያደርጉ አካላት ላይ የተደራጀ ጥናት በማካሄድ ጠበቅ ያለ ርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል።

ርምጃ ለመውሰድ ስምሪት የሚወስዱ ፈጻሚዎች ጥቆማውን ማን እንዳመጣው አያውቁም። የአሠራር ሥርዓቱ የቁጥጥር ሥራ የሚያከናውን የቁጥጥር ክፍል ሲሆን፣ ጥቆማውን የሚቀበል የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ነው። ክፍሉ ጥቆማውን ተቀብሎ ታሊ በማድረግ ለቁጥጥር ክፍል በፊርማ ሲያስረክቡ የጥቆማ ሰጪው አድራሻ አይገለጽም። ለምሳሌ ማታ ማታ ከቤታችን አጠገብ የሚቀጠቀጥ አለ፤ የሚል ጥቆማ ሲሰጡ የኢንተለጀንስ ቡድኑ ወደ ሥፍራው በመሄድ ጥናት አድርጎ ሲያረጋግጥ ርምጃ ይወሰድ ብሎ ሪፖርት ያቀርባል። ርምጃ ሲወሰድ አጥኚው ቡድን ሳይሆን ሥራውን የሚሠራው ሌላ ቡድን ነው። ቁጥጥርና ክትትል የሚያደርጉ ባለሙያዎች ወደ ሥፍራው የሚያቀኑት የት እንደሚሄዱ ጭምር ሳይነገራቸው ሲሆን፣ ከሄዱ በኋላ ቃለጉባዔ ይዘው ወደ ፍተሻ ገብተው የተጠቆመውን ነገር ካላገኙ ርምጃ አይወስዱም።

ማህበረሰቡ ምርት ሲገዛ የአገልግሎት ጊዜውን በተገቢው መንገድ መመልክት አለበት። ጊዜው ያለፈበት ሲያገኝ ለባለሥልጣኑ ጥቆማ በመስጠት ራሱንም ሆነ ማህበረሰቡን ከጤና አደጋ መከላከል አለበት። ከዋጋ ባለፈ ምግብ ነው ብሎ መጠየቅ አለበት። ቁጥጥሩን ለማሳደግ በየጊዜው ህብረተሰቡ ላይ የባለቤትነት ስሜት እንዲፈጠር የግንዛቤ መፍጠር የቅድሚያ ሥራ ሊሆን ይገባል። ይህ ካልሆነ ከአራት ሚሊዮን በላይ በሚገመት ማህበረሰብ ውስጥ አንድ ሺህ ሠራተኛ ተሠማራ አልተሠማራ ትርጉም አይኖረውም።

አዲስ ዘመን፡- ለጤና ባለሙያዎች ፈቃድ አሰጣጡ ምን ያህል የዘመነ ነው?

አቶ እንጋ፡- የሙያ ፈቃድ አሰጣጡ በቴክኖሎጂ የታገዘ ነው። አንድ የጤና ባለሙያ ኦንላይን በመሙላት የሚጠበቅበትን መስፈርት አሟልቶ ይመዘገባል። ትልቁ ችግር በኦንላይን ሞልተው መቅረብ አይፈልጉም። ሁልጊዜም በተለመደው መንገድ መሄድ ያስባሉ። ወቅቱ የድጂታላይዜሽን እንደመሆኑ መጠን መረጃዎች በኦንላይን አርካይቭ መሆን አለባቸው፤ እንዲከዚህ ቀደሙ ዶክመንት የሆነ ቦታ መከማቸት የለበትም። የማደሻ ጊዜው ሲቃረብ ሁሉም እንዳልቀጣ በማለት መጥተው የሚሰለፉበት ጊዜ ሰፊ ነው። ከዚያ ውጭ ግን የሙያ ፈቃድ መስጫ አሠራሩ በጤና ሚኒስቴር የበለጸገ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ሲሆን፣ ፈቃዱ በየሶስት ዓመቱ የሚታደስ ነው። የሚለማው ቴክኖሎጂ በተገቢው ሁኔታ ወደ ሥራ እስከሚገባ በጤና ሚኒስቴር የበለጸገው የኦንላይን ቴክኖሎጂ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል። ይህ አሠራር ሰው በአካል መምጣት ሳያስፈልገው ቤቱ ሆኖ መሙላት የሚችለው ነው። ስለዚህ የቁጥጥር ሥራው በጂፒኤስ ጭምር ክትትል ይደረጋል።

ሬስቶራንት ልከፍት ነው ብሎ ፈቃድ ሊጠይቅ የመጣ ሰው ፍቃድ ከማግኘቱ በፊት ሬስቶራንቱ ለምግብ ቤትነት መሆንና አለመሆኑን እና ተቀጥረው የሚያገለግሉ ሠራተኞች የጤና ምርመራ መኖርና አለመኖሩን እንዲሁም ማዕድ ቤትና ሌሎች አሰፈላጊ ሁኔታዎች በተገቢው ሁኔታ መኖራቸው ይረጋገጣል።

ማንኛውም ሰው የመድሃኒት ቤት መክፈት ይችላል። ነገር ግን ፈቃድ አውጥቶ መሸጥ የሚችለው የጤና ባለሙያ ነው። ባለሀብቱ መድሃኒት የሚገዛበት ገንዘብ ከቻለ እና የጤና ባለሙያ የሥራ ፈቃድ አውጥቶ መሥራት ላይ ስምምነት ከፈጠሩ መሥራት ይችላል። ተጠያቂ የሚሆነው ግን የፈቃድ ኃላፊነቱን የወሰደው አካል ነው።

ምግብ ላይ ተቋሙን ማሸግ እና ግለሰቡን በወንጀል መጠየቅ ይችላል። ነገር ግን በጤናው ዘርፍ የባለሙያውን ፈቃድ እስከመጨረሻው መንጠቅ የሚያደርስ ነው ስለዚህ እያንዳንዱ ፋርማሲ የሚሸጥ ቦታ ላይ ዋና ፋርማሲ ይኖራል። በሁሉም ክፍለ ከተማ ፖሊስ፣ ምግብና መድሃኒት ባለሥልጣን ደንብ ማስከበር ንግድ ቢሮ ተቀናጅተው ሕግን እያስከበሩ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በምግብ ቤቶች ወይም ሬስቶራንቶች ላይ ቁጥጥር የሚደረግ ከሆነ ብዙ ቤቶች መጸዳጃ ቤት ቆልፈው የማያስጠቅሙ፤ ምግብ አቅርበው የቧንቧ ውሃ የለም የሚሉ በርካታ ናቸው። በእነዚህና መሰል አካላት ላይ ምን የማስተካከያ ርምጃ ትወስዳላችሁ?

አቶ እንጋ፡- አንድ ሰው ሻይም ምግብም አይጠቀም፤ መጸዳጃ ቤት መዝጋት የተከለከለ ነው። መጸዳጃ ቤት መጠቀም ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው። ለዚህም ተብሎ ነው ኮሪደር ልማቱን ተከትሎ መጸዳጃ ቤት እየተሠራ ያለው። ሰው መንገድ ላይ አትሽና ከተባለ መጸዳጃ ቤት ይፈልጋል። ስለዚህ መጸዳጃ ቤት የሚቆልፉ አካላት ላይ ርምጃ ለመውሰድ ማህበረሰቡ ጥቆማ መስጠት መለማመድ አለበት። ምግብ ነክ ነገርን ለጸሃይ ተጋላጭ የሚያደርጉ አካላትን ህብረተሰቡ ጥቆማ ከሰጠን ርምጃ እንወስዳለን።

እያንዳንዱ የክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ጥቆማ ከሚሰጠው አካል ጋር እንዲገናኙ በማድረግ ርምጃ እንዲወሰድ እንሠራለን። ምግብ ያዘዘ ተጠቃሚ ውሃ የመጠቀም መብቱ የተጠበቀ ነው። ነገር ግን አሁን ላይ በርካታ ሰው የኃይላንድ ውሃን ማዘዝ እንደ ልምድ እያዳበረ መጥቷል። ውሃ አምጣልን ማለት መብት ነው። እነሱም አላመጣም አይሉም ውሃ የለችም የሚል ምላሽ ይሰጣሉ። አሁን ላይ እንደባህል ሆኖ ለስላሳ ወይስ የኃይላንድ ውሃ ብለው ቀድመው ይጠይቃሉ። ይህ ግን ትክክል አይደለም፤ ሰው በአቅሙ የሚፈልገውን ማግኘት አለበት።

አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ የባህል ህክምና ባለቤቶች ከአዲስ አበባ ምግብና መድሃኒት ባለሥልጣን በተሰጠን ሙሉ እውቅና መሠረት እያሉ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አማራጮች ማስታወቂያ ሲያስነግሩ ይደመጣሉና እውቅናው ትክክለኛ ነው?

አቶ እንጋ፡- በቅርብ ጊዜ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ጠርተን የፓናል ውይይት አድርገናል። የውይይቱ ዋና ዓላማ የማስታወቂያ አነጋገርን በተመለከተ ሲሆን፣ ቅጥ ያጣ ማስታወቂያ መልክ እንዲይዝ ሰፊ ውይይት ተደርጓል። ያልተገባ ማስታወቂያ እየተነገረ ስለሆነ ከተለያየ አቅጣጫ ቅሬታና ጥያቄ እየቀረበ ነው። የባህል ህክምና እንሰጣለን የሚሉ አካላትን የሚፈልገው የሚዲያ ተቋማት እስኪመስል ድረስ ማስታወቂያው መስመር አልፏል። ለባህል ህክምና ለሚሰጡ ተቋማት ምዝገባ እንጂ እውቅና አንሰጥም። በተለይም የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ያለ ባህል ህክምና ማስታወቂያ የደም ስራቸው የማይሠራ እስከሚመስል ድረስ ሲያስተዋውቁ ይስተዋላል።

የባህል ህክምናን ማዘመን፤ ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር ማገናኘት የምግብና መድሃኒት ባለሥልጣን ተግባር አይደለም። ለባህል ህክምና እውቅና የምንሰጥበት ሕጋዊ ማሕቀፍ የለንም። ምክንያቱም እውቅና መስጠት የሚያስችል የባህል ሀኪም ሊኖርና የሕግ ማሕቀፍ ሊኖረው ያስፈልጋል። አንዳንድ የባህል ህክምና ሰጪዎች ባልተገባ መንገድ ለስንፈተ ወሲብ ወዘተ..ብለው ሲያስነግሩ ይደመጣል። መድሃኒት በማስታወቂያ ማስነገር አይቻልም። ለምሳሌ የዚህ ቢሮ ኃላፊ የመድሃኒት ስም ያለበት እስክሪብቶ ቢይዝ ሕገ ወጥነትና ወንጀል ነው።

መድሃኒት ሰው ሲታመምና ሲቸገር የሚገዛው ነው። እኛ መድሃኒትን የተመለከቱና የባህል ህከምና ላይ ያልተገባ ማስታወቂያ የሚያስነግሩ አካላትን እንዲያስቆም ለመገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ደብዳቤ ጽፈናል። በከፍለ ከተሞች የባህል ህከምና ከሚሰጡ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ ከተሰጣቸው ምዝገባ ባሻገር ማስታወቂያ ያስነገረ ይዘጋበታል ተብሎ ውይይት ተደርጓል። ማስታወቂያ ለመገናኛ ብዙሃን ሰጥተው ከመነገሩ በፊት ማን ከማን ምን ይጠይቅ የሚለው የጥናት ቡድን ተዋቅሮ ጥናት እየተደረገ ነው። አንዳንድ የባህል ህክምና ሰጪ አካላት የባህል ህክምና ስሙን እንዲጠፋ እያደረጉት ነው። የባህል ህክምና ሰጪ አካላት የሚሰጡት ህክምና እያንዳንዱ ባሕር መዝገብ ላይ ተመዝግቦ መገኘት አለበት።

አዲስ ዘመን፡- በመዲናይቱ የማሳጅ ቤቶችን በተመለከተ አንዳንዶች ባልተገባ ንግድ እየተጠቀሙበት ነው የሚል ቅሬታ ከማህበረሰቡ ሲነሳ ይደመጣል፤ ስለሆነም ቤቶቹን ከመቆጣጠር አንጻር ምን ተሠርቷል? የተገኙ ለውጦችስ አሉ?

አቶ እንጋ፡- በማሳጅ ቤቶች ላይ ቁጥጥር እናደርጋለን። አስፈላጊ ሲሆን ባልተገመተና በድንገተኛ ሰዓት ጭምር ወደ ቤቶች በማቅናት ቁጥጥር ይደረጋል። የማሳጅና ስፓ ቤቶች ላይ ችግሩ አለ። የሆነ ጉራንጉር ቦታ በመሆን ሞሮኮና መሰል አገልግሎት በመስጠት ላልተገባ ጥቅም የሚሠሩ ይኖራሉ። ነገር ግን በተገኘው ሁሉ ርምጃ እንወስዳለን። ከሺሻ እና መሰል አዋኪ ድርጊቶች ጋር በተያያዘ ከደንብ፣ ከሰላምና ጸጥታ መዋቅሩ ጋር በጋራ በመሆን ቁጥጥር እየተደረገ ነው።

ሁሉም ባለደረጃ ሆቴሎችችን ስፓ፣ ማሳጅና ስቲም (እንፋሎት) ሁሉም አገልግሎት አላቸው። አንዳንዱ ዘንድ ማታ ማታ ነው የሚሠራው ይባላል፤ የቁጥጥር ሥራ ይሠራል። በዚህ ዘርፍ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ለመስጠት ጥናት እየተከናወነ ነው። በመዲናይቱ አዋኪ የሆኑ ተግባራት ለመዲናዋ ስጋት በማይሆኑበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።

በርበሬ ላይ ብቻ ሶስት ክፍለ ከተሞች ላይ ርምጃ ተወስዷል። በአንድ ወር ውስጥ ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ላይ እንዲወገድ ተደርጓል።

አዲስ ዘመን፡- ከእህል ምርቶች ውጪ ለእንጀራ የተፈቀደ ምርት አለ? ካለ ስሙ ምን ይባላል?

አቶ እንጋ፡- አዎ አለ! ስሙ ካዛቫ ይባላል። ከምግብ ምድብ ውስጥ ገብቷል። ካዛቫ የስራስር አይነት ሲሆን፣ በደቡቡ የሀገሪቱ ከፍል ምርቱ ይበዛል። ይህን ተገን በማድረግ ሌላ ባዕድ ነገር የሚቀላቅል ስለማይጠፋ በተቻለ አቅም የቁጥጥር ሥራ ይሠራል። በምግብ ነክ ነገሮች ቅሬታዎች ይበዛሉ። አንዳንድ ሰው ርምጃ መውሰድ የምታቆሙት መቼ ነው ይላል። ለዚህ መልሳችን መብላት እስካቆምን ድረስ ነው የሚል ነው።

በርበሬ ላይ አፍላቶክሲን የሚባል ንጥረ ነገር ያለ ሲሆን፣ በሀገሪቱ የተፈቀደው ስታንዳርድ አለ። ከተፈቀደው በላይ ወደታች ዝቅም ከፍም ማድረግ አይቻልም። ከዚህ ውጭ ከሆነ ርምጃ ይወሰዳል። ይህ ማለት አፍላቶክሲኑ በቀጥታ ከጉበት ጋር ግንኙነት አለው። በዚህ ሁኔታ በሚያጋጠመው ችግር ፍርድ ቤት ክስ ስንሄድ ችሎት ላይ የሞተ ሰው አለ የሚል ጥያቄ ይነሳል። ነገር ግን ሁሉም ሰው በዚህ ተጠቂ ይሆናል። እንደማኅበረሰብ “መጀመሪያ ሆዴን ልሙላ” የሚል አስተሳሰብ አለ። ይህ መቀረፍ አለበት። መጀመሪያ ጤና ሊቀድም ይገባል።

የትኛውም አካል በምግብና መድሃኒት ህክምና ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች ሲኖሩት “በ8864” ነጻ የስልክ መስመር መጠቆም ያስፈልጋል። ህብረተሰቡ ለሚገዛው ምርት ሥልጣን ስላለው በአግባቡ ይጠቀም። የታሸገ ምግብ የሚገዛ የአገልግሎት ጊዜውን ማየት፤ በተለይ እቃው ላይ የተጻፈውን ማየት ያስፈልገዋል፤ ከሚለጠፈው ላስቲክ ላይ ሊቀየር ስለሚችል አስተማማኝ አይደለም። በየመስኩ ታርደው ከሚቀርቡ ስብና ሌሎች ነገሮች ላይ ራስን መጠበቅ ይገባል።

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍላችን ስም አመሰግናለሁ

አቶ እንጋ፡- እኔም ስለሰጣችሁኝ እድል ከልብ አመሰግናለሁ።

ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You