
በሼር ኢትዮጵያ ዝዋይ ሮዝስ ኩባንያ ውስጥ በቁጥር በርካታ የሆኑ ሠራተኞች ሥራቸውን ማልደው ጀምረዋል፡፡ በዚህ ሥፍራ ዓመቱን ሙሉ በብርታት ከሚተጉት መሐል ሰማንያ በመቶውን የሚሸፍኑት ሴቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሴቶች ሁሌም የቆሙበትን የሥራ ኃላፊነት ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ እያንዳንዷ ቀን ከነሱ ሕይወት አልፋ የሀገር ኢኮኖሚን እንደምትገነባ አይጠፋቸውም፡፡ ይህ እውነት ዘወትር ከጥንካሬና ፅናታቸው ጋር አውሎ ያሳድራቸዋል፡፡
የኔነሽ ወዳጄነህ በዝዋይ ሮዝስ የአበባ እርሻ ልማት ውስጥ ለዓመታት ስትሠራ ቆይታለች፡፡ እሷን ጨምሮ መላው ቤተሰቧን የምታስተዳድረው ከድርጅቱ በሚከፈላት ወርሐዊ ደመወዝ ነው፡፡ የአምስት ልጆች እናት የሆነችው የኔነሽ በኩባንያው የሃያ ዓመታት ቆይታዋ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ ስትሳተፍ መቆየቷን ትናገራለች፡፡ ለዓመታት ያለአንዳች ሥራ የቤት እመቤት እንደነበረች የምታስታውሰው ወይዘሮ፤ በባለቤቷ የአንድ መቶ ሰማንያ ሰባት ብር ደመወዝ ኑሮዋን ትመራ እንደነበር ትገልጻለች፡፡
በአካባቢዋ ኩባንያው ከተመሠረተ ጀምሮ ግን ራሷን በሚያስችል ሥራ ተሠማርታ ሃያ ዓመታት አብራ መዝለቋ ደስተኛ አድርጓታል፡፡ የኔነሽ በእርሻ ልማቱ በጥንካሬ ከሚወሱ ሴቶች መሐል አንዷ ነች፡፡ እሷን ጨምሮ ሌሎች ባልደረቦቿ በተለየ ፍላጎትና ጥረት መሥራታቸው ሁሌም እንደሚያኮራት ትገልጻለች። ቅድሚያውን ለሴቶች በሚሰጠው ኩባንያ ከአስር ጓደኞቿ ጋር ከሃያ ዓመታት በፊት ስትቀጠር በአነስተኛ የጉልበት ሥራና በጥቂት ደመወዝ መነሻ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ እሷን ጨምሮ አስሩም ሴቶች በተሻለ የሥራ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ዛሬ የኔነሽ የሃያ ሁለት ሺህ ብር ደመወዝተኛ ናት፡፡ ቤት ሠርታ፣ ልጆቿን አስተምራና አስመርቃ ለቁምነገር አድርሳለች፡፡ በወይዘሮዋ ዕምነት ሁሉም ለዚህ ዕድገት የመብቃታቸው ምስጢር ሥራውን ወደውና አክብረው በጥንካሬ መዝለቃቸው ነው፡፡
በሥሯ የምትመራቸው 125 ሠራተኞች መኖራቸውን የምትገልጸው የኔነሽ ሁሉም በተመደቡበት የሥራ መስክ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የበረቱ መሆናቸውን ትናገራለች፡፡ ለበርካቶች ኑሮ መሠረት በሆነው የአበባ ልማትና የኬሚካል አጠቃቀም ጋር በብዙዎች ዘንድ የተለመደው አባባል እውነት ያለመሆኑን ታረጋግጣለች፡፡
እሷ በሃያ ዓመታት ቆይታዋ በሚባለው ሥጋት ውስጥ አላለፈችም፡፡ ሌሎች የሥራ ባልደረቦቿም ይህ ዓይነቱ ችግር እንዳልገጠማቸው ትናገራለች፡፡ በእርሻ ልማቱ የተቀጠሩ ሴት ሠራተኞች የባለቤቶቻቸውን እጆች ከማየት ያለፉ ብርቱዎች ናቸው የምትለው ወይዘሮ፤ ሌሎችም ከእሷና ከባልደረቦቿ የሥራ ባሕል ተሞክሮን ቀስመው ልምድን ሊጋሩ ይገባል ትላለች፡፡
በዝዋይ ሮዝስ የአበባ እርሻ ልማት ለአስራ ስድስት ዓመታት የቆየችው ወይዘሮ የውብዳር ፋንታዬ፤ ሕይወቷን የምትመራው ከኩባንያው በሚከፈላት ደመወዝ መሆኑን ትገልጻለች፡፡ የውብዳር ራሷን ለመቻል ብዙ ስትለፋ መቆየቷን ትናገራለች፡፡
ከዓመታት በፊት በኩባንያው የመቀጠር ዕድል ካገኘች ወዲህ ግን ሀሳቧ ተሰብስቧል፡፡ አንዲት ልጇን በወጉ አሳድጋ አስተምራለች፡፡
የውብዳር በእርሻ ልማቱ በተለያዩ የሥራ መስኮች ማሳለፏን ታስታውሳለች ፡፡ በርካታ ሴቶች በሚሳተፉበት በዚህ ኩባንያ ሁሉም በብርታት ሲተጋ መዋሉ ተለምዷል፡፡ የውብዳር እንደምትለው ኩባንያው ለአካባቢው የሥራ ዕድልን በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡ በጤና አጠባበቅም ለሠራተኞቹ ሕክምናን ከአዲስ አበባ ሆስፒታሎች እስከ ውጭ ሀገራት ልኮ የማሳከም ዕድል ይሰጣል፡
እንደ ወይዘሮዋ ኩባንያው ትምህርትን ለሁሉም ለማዳረስ በሚያደርገው ጥረት ወላጆች ልጆቻቸውን በሼር ኢትዮጵያ ትምህርት ቤት ከመዋዕለ ሕጻናት አስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል በነፃ ያስተምራሉ፡፡ ኩባንያው ውጤታቸው ለዩኒቨርሲቲ የሚያበቃቸውን ተማሪዎች በቅርበት በመከታተልም ተገቢውን እገዛ ያደርጋል፡፡
የኑሮ ጓዳችንን ለመደጎም የአበባ ልማቱ ሁሌም ከጎናችን ነው የምትለው የውብዳር፤ ከገበያ በቀነሰ ዋጋ ለቀለብና ለዕለት ፍጆታ ድጎማ ማድረጉ የኑሮ ውድነትን ለመቋቋምና ሕይወታችንን በወጉ ለመምራት አግዞናል ትላለች፡፡ በዝዋይ ሮዝስ ኩባንያ የሚታየው የሥራ ባሕል ለበርካቶች የሚጋራ ጠንካራ ልምድ ነው ብላ የምትገልጸው ወይዘሮ የውብዳር፤ የልማቱ ተቀጣሪ ሴቶች የየዕለት ብርታትም የሀገርን ኢኮኖሚ ለመገንባት ድርሻው ከፍ ያለ መሆኑን ትናገራለች፡፡
አቶ ኤርሚያስ ሰለሞን በሼር ኢትዮጵያ ዝዋይ የሮዝስ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ኢንቨስትመንቱ በሀገራችን የሃያ ዓመታትን ዕድሜ ማስቆጠሩን ይናገራሉ፡፡ ኩባንያው መገኛውን ዝዋይ ባቱ ላይ በማድረግም ሃያ ሺህ ቋሚ ሠራተኞችን ቀጥሮ ይንቀሳቀሳል፡፡
በኢትዮጵያ የሥራ ዕድልን በመፍጠር በኩልም ከ200 ሺህ በላይ ሠራተኞችን ማሳተፍ ተችሏል። በኩባንያው የልማቱ ሞተር የሆኑት ሴቶች ሰማንያ በመቶ ድርሻ ይሸፍናሉ፡፡ አቶ ኤርሚያስ የሴቶቹ ቁጥር ማየል ለሥራው ስኬታማነት አስተዋፅዖ ማበርከቱን ይናገራሉ፡፡
ሴቶች በባሕርያቸው ለሥራ ትኩረት የሚሰጡና ጠንቃቆች ናቸው የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ይህ እውነታ በኩባንያው ልማት ላይ በጎ ውጤት ማስመዘገቡን ይናገራሉ፡፡
እንደ አቶ ኤርሚያስ አገላለጽ፤ የሴቶች ቁጥር አብላጫ መሆን የአበባ ምርት በአውሮፓ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲዘልቅ አስችሏል፡፡ ኩባንያው በዋንኛነት የሚያመርተው ‹‹ሮዝ›› የተባለው አበባ በአሁኑ ጊዜ ተፈላጊነቱ ጨምሯል፡፡ ‹‹የሮዝ ምድር›› ተብላ የምትጠራው ሀገራችንም በዚህ ምርት በዓለም የሦስተኝነት ደረጃን ይዛለች፡፡
ኢትዮጵያ ከኮሎምቢያና ኢኳዶር ቀጥሎ አበባውን በማምረት እውቅናን አግኝታለች የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፤ የዝዋይ ባቱም ለዚህ ውጤት መገኘት ላቅ ያለውን ድርሻ እንደሚይዝ ይናገራሉ፡፡
በኔዘርላንድ፣ ሕንድ፣ ኢኳዶርና እሥራኤል ባለሀብቶች የሚመራው የኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬዎች አምራችና ላኪዎች ማኅበር 130 አባላት ያሉት ግዙፍ ኩባንያ ነው፡፡ ማኅበሩ ምርታማነቱን በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በቅንጥብ አበቦችና ዕፀ ጣዕሞች ላይ በማድረግ በዓለም ገበያ ላይ ተሳትፎውን ቀጥሏል፡፡
መገኛቸውን ዝዋይ ባቱ ላይ ያደረጉ አምስት የአበባ አምራች ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ለአውሮፓ ገበያ በማቅረብ ተወዳዳሪነትን አስፍተዋል፡፡ ለሀገር የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት በዓለም ሦስተኝነት ላይ የምትገኘው ሀገራችን በአሁኑ ጊዜ በአበቦቿ ምርት ተፈላጊነትን አትርፋለች፡፡
እንደ አቶ ኤርሚያስ አገላለጽ፤ ይህ ኢንቨስትመንት ከዛሬ ሃያ ዓመታት በፊት በሀገራችን ጅማሬውን ሲዘረጋ አብዛኞች በዘርፉ ላይ በቂ ዕውቀት አልነበራቸውም፡፡
በአሁኑ ጊዜ ግን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓመቱን ሙሉ 365 ቀናትን በማመላለስ የአውሮፓ ገበያን የሚቆጣጠር የኢኮኖሚ መሠረት ለመገንባት መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም