በሴቶች ክንድ የበረታው ኢንቨስትመንት

‹‹እንጀራዬ›› ብላ የያዘችው ሥራ ጅማሬና የእሷ የቦታው ላይ ቆይታ በእኩል ድምር ይዛመዳል። የዛኔ ከዓመታት በፊት አሁን የምትሠራበት ኩባንያ ዕውን ሲሆን የኔነሽ ወዳጄነህ ከመጀመሪያዎቹ ተቀጣሪ ሴቶች መሀል አንዷ ልትሆን ዕድሉን አገኘች። ይህ የሆነው የዛሬ ሃያ ዓመት ግድም በዝዋይ ሮዝስ የአበባ ማምረቻ ኩባንያ ውስጥ ነበር።

ወይዘሮዋ በወቅቱ የበሏን እጅ የምትጠብቅ የቤት እመቤት ነበረች። አምስት ልጆቿን ጨምሮ የመላው ቤተሰብ ተስፋ ወር ጠብቆ የሚደርሰው የአባወራው ደመወዝ እንደነበር ታስታውሳለች። በጊዜው ኑሮ ጥሩ የሚባል አይነት ቢሆንም የባለቤቷ ደመወዝ ግን በቂ አልነበረም። አንድ መቶ ሰማንያ ሰባት ብርን እንደምንም አብቃቅታ ወር ታደርሳት እንደነበር አትዘነጋም።

ይህ እውነት የኔነሽን ሲያስቆጭ፣ ሲያሳስባት ኖሯል። መሥራት እየቻለች ዕድሉን ማጣቷ፣ ወር ሙሉ ተቀምጣ የባሏን እጅ ማየቷ አንገቷን አስደፍቷታል፣ አንዳንዴ የኔነሽ ለምን ብላ ራሷን ትጠይቃለች። ‹‹ለምን ለእኔ የሚሆን እንጀራ ጠፋ? ስለምን ሴቶችን ከቤት የሚያወጣ ዕድል ታጣ?›› ሃሳቡን ደግማ ደጋግማ በውስጧ ታመላልሳለች።

አንድ ቀን ግን የየኔነሽ ጥያቄ መልስ የሚያገኝበት ጊዜው ሆነ። በምትኖርበት የባቱ ከተማ አቅራቢያ ‹‹አዝሩምስ›› የተባለ የአበባ አርሻ ልማት ሥራ ሊጀምር መሆኑን ሰማች። ይህን ባወቀች ጊዜ ዓይኗን አላሸችም። ፈጥና ከድርጅቱ ተቀጣሪዎች አንዷ ልትሆን ተመዘገበች። ከቀናት በኋላ እሷን ጨምሮ ሌሎች አስር ሴቶች የመጀመሪያዎቹ ሠራተኞች ሆነው ሥራ ጀመሩ።

እነ የኔነሽ በወቅቱ ወደ እርሻ ልማቱ ሲገቡ በተገኘው የጉልበት ሥራ ለመሳተፍ ነበር። በጊዜው የግንባታ መሠረት መጀመሩ ነበር። ጥቂት ቆይቶ በእርሻ ቦታው የአበባ ተከላ ሂደቱ ቀጠለ። ሙያውን በባለቤትነት ሌሎች ቢይዙትም የኔነሽና ባልንጀሮቿ ለእነሱ የተባለውን መተዳደሪያ አላጡም። ቅጥራቸው በቋሚነት ጸንቶ ሥራውን ማቀላጠፉን ተያያዙት።

የአስሩ ሴቶች ብርታትና ጥንካሬ ጎልቶ ታየ። ሥራቸውን ያለአንዳች ልግመት መሥራታቸውን ምርታማነታቸው አስመሰከረ። ሁሉም ሴቶች ከጓዳ ሕይወት ተላቀው ራሳቸውን የሚመሩ፣ ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ተምሳሌቶች መሆናቸው ተረጋገጠ።

በአበባ እርሻ ልማቱ ዓመታት በሥራና ብርታት ተዋዝተው ቀጠሉ። የነ የኔነሽ አጋርነትም ሳይፋዘዝ ጊዜያትን ጨመረ። ውሎ አድሮ ኩባንያው ‹‹አዝሩም›› ከሚለው ወደ ‹‹ዝዋይ ሮዝስ›› ስያሜ ሲለወጥ ብርቱዎቹ ሴቶች ከጎኑ አልራቁም።

‹‹ዝዋይ ሮዝስ›› በጠንካራዎቹ ሴቶች ክንድ ምርታማነቱ ዕውን መሆን ያዘ። ሁሉም የተሰጣቸውን ሥራ በሃላፊነትና በልዩ ትኩረት መከወናቸው የሚታየውን ዕድገት የጋራ አደርጎት ቀጠለ። የኔነሽ በተቀጠረችበት የሥራ ጅማሬ ላይ አልዘለቀችም። ጥንካሬዋ አግዟት ወደተሻለ ክፍል የመዛወር ዕድሉን አገኘች።

ይህ አጋጣሚ ከሥራው መለወጥ ጋር መልካም የሚባል የደሞዝ ለውጥ አስገኘላት። ይህኔ የጓዳዋ ጎዶሎ ፣ የልቧ መሻት መሙላት ያዘ። ልጆቿን እያስተማረች፣ ባለቤቷን ማገዝ ጀመረች። ትናትናን በአባወራው ትከሻ ብቻ የቆመው ጎጆ የወይዘሮዋ አዲስ አቅም ታክሎበት ምሰሶው በረታ። ሁለቱም ለቤታቸው በእኩል መልፋት፣ መትጋት ያዙ። ልጆቻቸው እንደየፍላጎታቸው በርትተው ለመማር ዕድሉ ተቸራቸው። የኔነሽ በቤት ፣ በቤተሰቧ ላይ ስለሆነላት መልካምነት ፈጣሪዋን ደጋግማ አመሰገነች።

ጥቂት ቆይቶ በየኔነሽ ሕይወት ክፉ ይሉት አጋጣሚ ደረሰ። በድንገት ወይዘሮዋ ጤናዋ ታውኮ ካልጋ ላይ ዋለች። ይህ እውነት በጥንካሬዋ ለምትታወቀው ሴት ከባድ ጊዜ ነበር። የሥራ ባልደረቦቿን ጨምሮ መላው ቤተሰቧ ግን ዳግም በጤናዋ ቆማ ወደሥራዋ እንድትመለስ ተረባረቡላት።

የየኔነሽ ህመም በቀላሉ ታክሞ ለፈውስ የሚበቃ አልሆነም። ከልጅነቷ ጀምሮ ሲፈትናት የቆየው የጡት ህመም ጊዜ ቆጥሮ አገረሸ። በድርጅቱ በቂ እገዛ አላጣችም። ተገቢውን ህክምና አግኝታ የሚገባትን ምርመራ አካሄደች። ቆይቶ የተገኘው ውጤት አስደንጋጭ ነበር። በጡቷ ላይ የካንሰር ህመም መኖሩ ተረጋገጠ።

በወቅቱ የቤቷ ምሰሶ፣ የመስሪያ ቤቷ ኮከብ ለሆነችው ብርቱ ይህ አጋጣሚ ከባድ የሚባል ነበር። የዝዋይ ሮዝስ ኩባንያና መላው ሠራተኞች ግን ከጎኗ አልራቁም። አራት ዓመታትን በጸበልና በህክምና ታግዛ ወደሥራዋ ስትመለስ ‹‹አለንልሽ›› ብለው ተቀበሏት።

ከህመም ቆይታ በኋላ የየኔነሽ ጥንካሬ አልተለወጠም። ዳግም በቦታዋ ተመልሳ የትናንቱን ብርታቷን በሥራዋ አስመሰከረች። ወይዘሮዋ ከህመሟ ጋር ተያይዞ የአንዳንድ ሰዎችን ጥያቄ ስታስተናግድ ቆይታለች ። የህመሟ መነሻ የሥራ ባህርይዋ ስለመሆኑ እርግጠኞች የሆኑ በርካቶች ሥጋታቸውን ነግረዋታል።

እሷ ግን ለጠየቋት ሁሉ አሳምራ የምታውቀውን እውነት ከመናገር ወደ ኋላ አትልም። የኔነሽ በልጅነቷ በብዙ ፈተናዎች መሃል ተራምዳለች። እንደ እኩዮቿ በእናት እጅ አላደገችምና የምትኖርበትን ቤተሰብ ለማገዝ፣ አረቄ እያወጣች ፣ በእንጨት እንጀራ እየጋገረች ሕይወቷን ስትገፋ ኖራለች።

በወቅቱ ልብሶቿ ሻማ መሆናቸውና ዓመታትን ከእሳት ያለመራቋ ከህመም አድርሷት እንደነበር አትዘነጋም። ይህ አጋጣሚ መነሻ ሆኖም ለጤናዋ እክል ስለመፍጠሩ እርግጠኛ ነች። ችግሩ ዓመታትን ቆጥሮ በመመለሱ ብትደነግጥም ተገቢውን ህክምና ማግኘቷ በሕይወት እንድትቀጥል አግዟታል። ለዚህም በየቀኑ ኩባንያውን ከልብ ታመሰግናለች።

ዝዋይ ሮዝስ ለእሷ የኋላ ታሪኳን ማስረሻ ፣የአሁን ማንነቷን ማደሻ ነው። የኔነሽ በኩባንያው የሃያ ዓመታት ቆይታዋ አምስት ልጆቿን አስተምራ ለቁምነገር አድርሳለች። በኩባንያው የደመወዝ መነሻም የራሷን ጥሩ መኖሪያ ቤት ለመገንባት ችላለች።

ወይዘሮዋ ከአምስት ልጆቿ የመጀመሪያዋን ድራና ኩላ ለትዳር ማብቃቷ ያስደስታታል። ሁለት ልጆቿ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሆነውላታል። አንደኛዋ በትምህርት ላይ ስትሆን ሌላው ደግሞ በኩባንያው የመቀጠር ዕድል አግኝቶ በሥራ ላይ ይገኛል።

የኔነሽ በሃያ ዓመታት የኩባንያ ልምዷ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ መቆየቷ በቂ ልምድ አትርፎላታል። ከትንሽ መነሻ የጀመረው ክፍያዋም ዛሬ የሃያ ሁለት ሺህ ብር ደሞዝተኛ አድርጓታል። አሁን በሥሯ አንድ መቶ ሃያአምስት ሠራተኞችን በሃላፊነት ይዛ እየመራች ነው። እሷና ጓደኞቿ በትምህርት ልቀው ከፍ ያለ ደረጃ ባይደርሱም በደሞዝ ክፍያቸው ከብዙሃን የተሻሉ ናቸውና ደስተኞች ሆነዋል። ወይዘሮዋ የሴት ልጅን ብርታትና ጥንካሬ በራሷ ገምታ ለክታዋለችና በሴቶች ላይ ያሳደረችውን አመኔታ የምትገልጸው በተለየ መተማን ሆኗል።

በሼር ኢትዮጵያ ዝዋይ ለአስራ ስድስት ዓመታት የዘለቀችው ሌላዋ ብርቱ ወይዘሮ የውብዳር ፋንታዬ ትባላለች። የውብዳር የሕይወት አጋጣሚ ወደ ዝዋይ ባቱ ካደረሳት ወዲህ ኑሮዋን ለመምራት አማራጮችን ስትፈልግ ቆይታለች።

የአንዲት ሴት ልጅ እናት ሆነችው የውብዳር ስለልጇ ሃላፊነትን የያዘችው ለብቻዋ ሆኗል። ከልጇ አባት ጋር በፍቺ የተለያየችው ገና በጠዋቱ ነውና እሷን ለማሳደግ ብዙ መልፋት፣ መጣር ግዴታዋ ሆኖ ቆይቷል። ከዓመታት በፊት በዝዋይ ሮዝስ ኩባንያ በቋሚነት የመቀጠርን ዕድል አገኘች።

ይህ እውነት በብዙ ስትፈተን ለቆየችው ወይዘሮ መልካም አጋጣሚ ሆነላት። አንድ ልጇን ትምህርት ቤት አስገብታ ማስተማርና በወጉ ማሳደግ ያዘች። በአቅሟ ቤት ተከራይታም ኑሮዋን ቀጠለች። የውብዳር በዝዋይ ሮዝስ የአበባ እርሻ ልማት ሠራተኛ መሆኗ የሥራ ክቡርነትን አስተምሯታል። በዚህ ሥፍራ ያሉ ሴቶች ዘወትር በሥራ መትጋት መልፋታቸው ሕይወታቸውን በመልካም እንዲቀይሩ፣ የሀገር ኢኮኖሚንም እንዲያሳድጉ ምክንያት ሆኗል።

በአካባቢው ሰፊ የሥራ ዕድል መፈጠሩ እሷን መሰል ለሆኑ ሴቶች ያበረከተው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም። ወይዘሮዋ እንደምትለው ኩባንያው ከምንም በላይ ለሠራተኞቹ ጤና ቅድሚያ ይሰጣል። ሠራተኞች በአግባቡ በሚታከሙበት፣ ደረጃውን የጠበቀ የሼር ኢትየጵያ ሆስፒታል ሁሉም የመገልገል መብት ተሰጥቶታል።

በከአዲስ አበባ ሆስፒታሎችና ከዚህ አለፍ ሲልም እስከከውጭ ሀገራት የደረሰው የሕክምና ሂደት ለሠራተኞቹ የጤና መድህን በመሆን አጋርነቱን እያሳየ ነው። የውብዳር ኩባንያው ለትምህርት የሚሰጠውን ሰፊ ዕድልም አትዘነጋም። ሁሌም የእሷን ልጅ ጨምሮ የሌሎች ሠራተኞች ልጆች ዕውቀት ለመገብየት ተቸግረው አያወቁም።

ሁሉም ወላጆች በሼር ኢትዮጵያ ትምህር ቤቶች ከአጸደ ህጻናት እስከ አስራሁለተኛ ክፍል ልጆቻቸውን በነጻ ያስተምራሉ። በትምህርታቸው መልካም ውጤት አምጥተው ነጥብ ያስመዘገቡ ተማሪዎች በሚኖሩ ጊዜም ኩባንያው በቅርበት በመከታተል አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል።

የውብዳር በሮዝ ኢትዮጵያ የሚታየው የሥራ ባህል ከሴቶች ብርታትና የተለየ ትኩረት ጋር ተያይዞ የመጣ ስለመሆኑ የምትናገረው በእርግጠኝነት ነው። በዚህ ሥፍራ ሁሉም የተሰጠውን የሥራ ድርሻ በሃላፊነት ለመወጣት ወደ ኋላ አይልም። ይህ እውነትም በየቀኑ ከልፋትና ድካም ጀርባ መልካም ውጤት እንዲመዘገብ ምክንያት ሆኗል። ፡

በእርሻ ልማቱ የሴቶችን የኑሮ ጫና ለማቃለል ጥረት የማድረግ ልማድ አለ። ወይዘሮዋም ይህን ተሞክሮ የምታየው በመልካምነት ነው። ሁሌም የኑሮ ጫናውን ባገናዘበ መልኩ በኩባንያው ከወቅታዊ የገበያ ዋጋ የቀነሰ የአስቤዛ አቅርቦት ማድረግ ተለምዷል። እንዲህ መሆኑ ጎንን ደግፎ ፣ ጓዳን በመደጎም አስተዋጽኦው የላቀ ነው።

የውብዳር ከአራት ዓመት ዕድሜዋ ጀምሮ ትምህርትቤት የገባችው ልጇ ዛሬ አስራሁለተኛ ክፍል ደርሳላታለች። ይህ የሆነው በእሷ ጥረት ብቻ ሳይሆን በኩባንያው ድጋፍና እገዛ ነው።

በዝዋይ ሮዝስ ኩባንያ የሚታየው የሴቶች ጥንካሬና ብርታት ዛሬ ላይ የአውሮፓን ገበያ ለተቆጣጠረው የአበባ ምርት ምክንያትና መነሻ ነው የምትለው ወይዘሮ የውብዳር በኩባንያው በበኩሏ ስለ ሀገር ኢኮኖሚ የምታበረክተው ድርሻም ኩራቷ መሆኑን የምትናገረው ከልቧ ነው።

በሼር ኢትዮጵያ ዝዋይ የሮዝስ ኩባንያ ዋና ስራ አስኪያጅ ኤርሚያስ ሰለሞንም ኩባንያው ሃያ ሺህ ሠራተኞችን በቋሚነት ቀጥሮ እንደሚንቀሳቀስ ይናገራሉ። ከነዚህ ሠራተኞች መሃልም ሰማንያ በመቶውን ድርሻ የሚሸፍኑት ሴቶች ናቸው።

በአቶ ኤርሚያስ አገላለጽ በአበባ እርሻ ሥራው ሰፊ ድርሻ ሴቶች እንዲሆኑ የተመረጠበት ምክንያት ሴት ልጅ በባህርይዋ ለነገሮች የተለየ ትኩረትና ጥንቃቄ እንደምታደርግ ስለሚታወቅ ነው። በኩባንያው የሴት ሠራተኞች ቁጥር ማየል በአሁኑ ወቅት ለሚታየው የሥራ ስኬታማነት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ሥራ አስኪያጁ ይገልጻሉ።

ሰማንያ በመቶ ያህሉን ድርሻ በሴት ሠራተኞቹ የሸፈነው ዝዋይ ሮዝስ ሁሌም በጠንካሮቹ እንስቶች ብርታትና ጥንካሬ ይተማመናል። ሃላፊነትን ለእነሱ አሳልፎ ሲሰጥም ግዴታቸውን በብቃት እንደሚወጡ በመተማመን ነው። በአበባ እርሻ ልማቱ ከሥራ በዘለለ መልካም የሚባል ማህበራዊ ሕይወት ይንጸባረቃል። ተከባብሮና ተደጋግፎ መኖርም በሠራተኞች መሃል እንደ ባህል ሆኖ ተለምዷል።

የኩባንያው ሠራተኛ ሴቶች ለማህበራዊ ሕይወታቸው ጠቀሜታ ሲሉ ተደራጅተዋል። ከመሃላቸው አንዳቸው ኀዘንና ደስታ ቢገጥማቸው በተቀማጭ ካኖሩት የገንዘብ ቁጠባ በመቀነስ ላሰቡት ዓላማ ያውሉታል። ይህ አይነቱ መልካም ግንኙነት ሥራውን በውጤት፣ ሕይወትን በፍቅርና ሰላም ለመምራት ምክንያት ሆኖ ዓመታትን ዘልቋል።

ሴቶች በዚህ ሥፍራ መቀመጣቸው የአበቦቹን ውበትና ሕይወት ለማስቀጠል እንደ እስትንፋስ ነው። አበቦቹ በጠንቃቆቹ ሴቶች መዳፍ ውስጥ ሲያርፉ ምቾታቸው ዕውን ይሆናል።

ሴቶች ከወንዶች ይልቅ በተፈጥሮ የተሰጣቸው ትዕግስትና አትኩሮት በዚህ ቦታ ለውጤት አብቅቷቸዋል። ይህ እውነትም ለአበባ እርሻ ልማቱ ተመራጭ አድርጎ ተፈላጊነታቸውን ጨምሯል።

ዛሬ ሀገራችን በኢኮኖሚው ዘርፍ ይዛው ለዘለቀችው የአበባ ግዙፍ ኢንቨስትመንት የሴቶች ጥንካሬ አይነተኛ ድርሻ ያለው በኩባንያው የሚስተዋለው የበርካታ ሴቶች ጥንካሬና ብርታትም ለሀገር ኢኮኖሚው መላቅ ጥብቅ መሠረት ሆኖ ተመዝግቧል።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You