ጸጉርዎን ለምን ያህል ጊዜ ሳይቆረጡ ወይም ሳይስተካከሉ እንዲሁም ሳይታጠቡ ቆይተው ይሆን? ተብለው ቢጠየቁ መልሱ ምን አልባት እንደየሰው ባህሪና የአኗኗር ዘዬ ሊለያይ ይችላል፡ ፡ ከእምነት ጋር በተያያዘም የተለየ መልስ ሊሰጥበት ይችላል፡፡
ሴቶች ከሆኑ በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ ውበት ሳሎን በመሄድ ጸጉራቸውን ሊታጠቡና በሚፈልጉት ዓይነት ሊሰሩ (ሹሩባ አልያም ካውያ ) ይችላሉ ብሎ መገመት ቀላል ነው፡፡
በተመሳሳይ በየቀኑ ጸጉራቸውን የሚታጠቡ ወንዶች ያሉ ሲሆን እንደ ጸጉራቸው የማደግ ባህሪም በሁለት አል ያም በሶስት ሳምንት ጸጉር አስተካካይ ቤት ጎራ የሚሉት ብዙ ናቸው። በጤናማው ሁኔታ ጸጉርን ሳይስተካከሉና ሳይታጠቡ ቢቆዩ ሰዎች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ደግሞ መገመቱ ብዙ ከባድ አይደለም፡፡
በህንድ ማንዳዳ መንደር የሚኖረው የ63 ዓመቱ ህንዳዊ ሳካል ዴቭ ቱዱ ግን ከዚህ ሁሉ የተለየ ነው፡፡ ጭንቅላቱ ላይ የተጠመጠመው ነገር ጸጉር ነው ብሎ ለማመን ያስቸግራል፡፡
ይህ ሰው ላለፉት 40 ዓመታት በጸጉሩ ላይ መቀስም ውሃም ዞሮ አያውቅም፤ 6 ጫማ የሚረዝመውን ይህን ጸጉሩን ጠቅልሎ በአናቱ ላይ ማኖሩም ጸጉር ብሎ ለመቀበል እንዲከብድ አድርጎታል፡፡
ሳካል በዚህ ሁኔታ የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ጸጉሩን መቆረጥም ሆነ መታጠብ ያቆመው ገና የ22 ዓመት ወጣት ሆኖ ነው፤ ከምክንያቶቹ አንዱ ደግሞ አንድ ጠዋት ከመኝታው ሲነሳ ጸጉሩ ተወሳስቦ ያየዋል፤አድጎ የተወሳሰበውን ጸጉሩን በመመልከትም በህንዶች አማልክት “ሺቫ” በመባርኬ ያተርፍኩት ነው ማለትም ይጀምራል። ከዚያ ቀን ወዲህም ነው በጸጉሩ ላይ አስገራሚ ውሳኔ ያሳለፈው፡፡
በአሁኑ ወቅት ይህ አስገራሚው የሳካል ድሬድ ወይም በእነሱ ቋንቋ “ጃታ” የጸጉር አያያዝ ስድስት ጫማ ያህል የረዘመ ሲሆን፣ባይታጠበውና ባይቆረጠውም የበኩሉን እንክብካቤ ያደርግለታል። ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በሚንቀሳቀስበት ወቅት የተለያዩ ቆሻሻዎች በጸጉሩ ላይ እንዳያርፉ ነጭ ሻሽ በማልበስ ይጠብቀዋል።
ሳካል በአሁኑ ወቅት በተለይም በማንዳዳ
መንደር ላይ የተለየ ክብር ያለው ሰው ከመሆኑም ባሻገር፣ የእኛ “ማሀተመ ጂ” ‘Mahatma Ji’ ነው በማለት ሰዎች የተለየ ክብር ይሰጡታል። ከመላው ህንድም ሰዎች ሳካል የተለየ ሀይል አለው ብለው በማሰብ ወደቤቱ ይመጣሉ።
ሳካል በህንድ በዚህ መልኩ ጸጉሩን አሳድጎ በመሄድ የመጀመሪያው ሰው አይደለም፤ ከዛሬ 3 ዓመት በፊትም በተመሳሳይ 19 ሜትር ርዝመት ያለውና ታጥቦ የማያውቅ ጸጉር ያለው ህንዳዊ ብቅ ብሎም ነበር ይላል የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2011
እፀገነት አክሊሉ