በሃገራችን በተለያዩ ምክንያቶች ሰው ሲጠፋ ዘመዶቹ የአፋልጉኝ ማስታወቂያ በስልክ እንጨት፣በአጥር እና በመሳሰሉት ላይ ይለጥፋሉ፤ አልያም በሬዲዮ ያስነግራሉ። የአፋላጉኝ ማስታወቂያው ሲወጣ ታዲያ አብሮ የሚተላለፍ መልዕክት አለ፡፡ ይህም ‹‹የጠፋውን ሰው ላገኘ ወይም ለጠቆመ ወሮታ የምንከፍል መሆኑን እንገልፃለን›› የሚል ነው፡፡
በአብዛኛው የጠፋውን ግለሰብ ያገኘው ወይም የጠቆመው ሰው ለስራው ወሮታ ወይም ክፍያ ተቀበለ ሲባል ተሰምቶ አይታወቅም። ይሁንና አሁን አሁን ግን የጊዜው ሁኔታና የኑሮ ወድነት ተከትሎ ነው መሰል ወሮታ የሚቀበለው ሰው እየመጣ ይመስላል፡፡ ያም ሆኖ ግን ወሮታው ሊከፈል የሚችለው በአብዛኛው በገንዘብ ይሆናል ተብሎ የሚገመት ሲሆን፣ ከዚህ በተለየ መልኩ ወሮታ ሲከፈል ግን ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡
ኑሮውን በአሜሪካ አሪዞና ግዛት ያደረገው ኤዲ ኮሊን የተሰኘው ግለሰብ ግን ለወሮታ ክፍያ በከፍተኛ ገንዘብ የሚገመት ንብረት
ለመስጠት ውሳኔ ላይ ደርሷል፡፡ ግለሰቡ ይህን ያህል መጠን ያለው የወሮታ ወጪ ለመክፈል ያነሳሳው ምክንያት ግን በእጅጉ አስገርሟል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ከሰሞኑ ጽፏል፡፡
ኤዲ ኮሊንስ የተሰኘው ይኸው አሜሪካዊ የሚወዳትና አብዝቶ የሚንከባከባት ጄኒ የተሰኘች ውሻ ነበረችው፡፡ ልክ እንደ ቤተሰቡ አባል የሚያያት ውሻ ግን ከወራቶች በፊት ከቤት እንደወጣች ሳትመለስ ትቀራለች፡፡ ኤዲ ከዛሬ ነገ የውሻዋን መምጣት በጉጉት ቢጠባበቅም አሁንም የውሃ ሽታ ሆና ትቀራለች፡፡ እርሱ ግን ውሻዋ ትገኝበታለች ብሎ በሚያስብባቸው አካባቢዎች ሁሉ በየቀኑ አሰሳሰውን ቢቀጥልም ሊያገኛት አልቻለም፡፡
የውሻዋን የመገኘት እድል ምን አልባት ሊያሰፋው ይችላል በሚልም የውሻዋን ምስል በወረቀት ላይ በማተም የአፋልጉኝ ማስታወቂያ ይለጥፋል፡፡ ይሁንና አሁንም ውሻዋን የበላት ጅብ አልጮህ ይላል፡፡
በውሻዋ መጥፋት ተስፋ የቆረጠው ኤዲ ብዙ ካወጣና ካወረደ በኋላ የመጨረሻ ያለውን አማራጭ ይወስናል፡፡ ይሄውም ውሻዋን አግኝቶ ለሚያመጣለት ሰው በሚኖርበት አፓርትመንት ውስጥ የሚገኘውን አንድ ክፍል መኖሪያ ቤት፣ የመስሪያ ቦታውንና መጠነኛ መሬት እንደሚሰጥ የገለጸበት ነበር፡፡
‹‹ውሻዬን ብዙ ቦታ ፈለኳት፤ የውሻ ማቆያ ቤትም ሄድኩ፤ ነገር ግን ላገኛት አልቻልኩም›› ሲል ኤዲ ኒውስ ፎር ለተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግሯል፡፡ ‹‹ውሻዬ እንድትገኝ ያለኝ ብቸኛ አማራጭ በአፓርትመንቴ ውስጥ ያለውን አንድ ክፍል መኝታ ቤት፣መስሪያ እና መጠነኛ ቦታ ላገኘልኝ ሰው ለመስጠት ወስኛለሁ›› ሲልም ጨምሮ ይገልጻል፡፡ የውሻዋን ምስልና መልዕክት የያዘ ፖስተር ይዞም ታይቷል፡፡
‹‹እንደ ባለቤቱና እና እንደሰውየው አሳቢነት ቢለያይም ሰውም ይሁን ውሻ ከምንም በላይ ህይወት ይበልጣል፤ ለኔ ጄኒ እንደ እቃ አይደለችም ይልቁንም በጣም የምወዳት የቤተሰቤ አባል ናት›› ሲልም ኤዲ ተደምጧል፡፡
ኤዲ ውሻው እንድትገኝ በራሱ ቢፈልግ፣ ፖስተር ቢለጥፍ፣ ቤትና መሬት ቢያቀርብም እስካሁን ድረስ ግን ውሻዋን አገኘሁ ብሎ የመጣ አንድም ሰው እንደሌለ ፅሁፉ ገልጿል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2011
አስናቀ ፀጋዬ