
ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ባለቤት ለመሆን እያደረገች ያለችውን እንቅስቃሴ በተመለከተ በውሃ ምሕንድስና አማካሪነት በሀገር ውስጥ፣ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ28 ዓመታት ካገለገሉት እና ከስድስት ዓመታት ወዲህ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ ከሚገኙት ፕሮፌሰር አድማሱ ገበየሁ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ የባሕር በር የነበራት ሀገር ናት። የወደብ ባለቤትነቷ ታሪካዊ ዳራ ምን ይመስላል ?
ፕሮፌሰር አድማሱ፡– ኢትዮጵያ ከመጀመሪያ ጀምሮ የባሕር በር ነበራት። በተለይም በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል ጅቡቲ፣ አሰብ እና ምፅዋ የኢትዮጵያ ወደቦች ነበሩ። በታሪክ ሂደት ጅቡቲ እንደ ሀገር ሆና ስትፈጥር ከተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ጋር ተያይዞ ወደቡም አብሮ ሄደ እንጂ የጅቡቲ ወደብ የኢትዮጵያ ወደብ ነበር። ጅቡቲ በአጼ ምንሊክ ጊዜ ለ99 ዓመታት በስምምነት የተሰጠ ሀገር ነበር። ፈረንሳይ ለቃ ስትወጣ ሀገር ሆኗል።
ኤርትራ ውስጥ ያሉት ምፅዋና አሰብ ወደቦችም እንዲሁ የኢትዮጵያ ነበሩ። ሁለት ወንድማማቾች ይዞታቸውን ለጣሊያናውያን በመሸጣቸው ቀስበቀስ በመስፋፋት መሠረት መጣል ቻሉ። የቅኝ ግዛት መስፋፋትን ተከትሎ አፍሪካን እና ከአፍሪካ ውጭም ያሉ ሀገራትን አውሮፓውያን በሚቀራመቱበት ወቅት ጣሊያን ይዞታዋን በማስፋፋት ኢትዮጵያ ላይ ወረራ ፈጽማ በተደረገው ፍልሚያ በንጉሥ ምኒሊክ የሚመራው የጀግኖች አባቶቻችን ጦር ዓድዋ ላይ ወራሪውን ፋሽስት ድል በማድረግ ኢትዮጵያን ማስከበር ችሏል።
የዚያን ጊዜ ግን በበሽታ፣ ለረጅም ጊዜ ከተለያየ አቅጣጫ ተሰባስቦ ዘመቻ ላይ የቆየው ጦረኛ በመዳከሙ እና በተለያዩ ምክንያቶች እስከ ትግራይ ያለውን አካባቢ ነፃ ማድረግ ቢቻልም ከዚያ አልፎ ለመግፋት አቅም አልነበረም። ጣሊያንም የኤርትራን ክፍል ቀደም ብሎ ይዞ መሠረቱ በማድረግ ተደራጅቶ ነበር። በዚህም ምክንያት ኤርትራን ተቆጣጥረው መቆየት ቻሉ። በመጨረሻ ደግሞ ጣሊያን እንደሌሎቹ ቅኝ ገዢዎች ኤርትራን ለቆ ሲወጣ መጀመሪያ በፌዴሬሽን በኋላ ደግሞ በውሕደት የኢትዮጵያ አካል ሆነች። በኋላ እነ ኢሳያስ ኤርትራን ከኢትዮጵያ መገንጠል አለብን የሚል ጥያቄ ይዘው ተነሱ። መሣሪያ አንስተው ታገሉ፤ የተለያዩ ወገኖችም አገዟቸው። የኢትዮጵያ መንግሥት ለብዙ ዓመታት በጠመንጃ ኃይል ሀገር እንዳይገነጠል ለማስከበር ቢታገልም አሜሪካን እና እንግሊዝን የመሰሉ ሀገራት በነበራቸው ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ተፅዕኖ ታግዘው በሕወሓት የሚታገዘው ሻዕቢያ አሸንፎ ለውጥ መጣ። ለውጡም ምፅዋ እና አሰብ ወደቦችን አሳጣን። ታሪካዊ ሂደቱ ይህ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ኤርትራ ስትገነጠል ኢትዮጵያ አሰብን ሳትጠይቅ መቅረቷን እንዴት ይመለከቱታል?
ፕሮፌሰር አድማሱ፡– በብዙ ሀገሮች እንዳየነው አንድ ሀገር በታሪክ አጋጣሚ ከአንድ ሀገር ሲገነጠል በዲፕሎማሲ በአንዳንድ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ መደራደር የቻሉበት ሁኔታ ነበር። የአሰብ ጉዳይን ብንመለከት በአስተዳደርም ሆነ በሌሎች ነገሮች ከአብዛኛው የኤርትራ ክፍል ተለይቶ ኢትዮጵያ ጋር የቆየ ነው። የአፋሮች ባለሥልጣናት ሲያስተዳድሩት የነበረ ነው። በአጠቃላይ በክፍለ ሀገርም ብናየው የወሎ ግዛት ሆኖ የቆየ ነው። በዚህ ሁሉ ሲታይ ተዋግተው የመጡት ኃይሎች ሁለት ቦታ ተከፍለው አንደኛው ቡድን የኢትዮጵያ ሌላኛው ደግሞ የኤርትራ ገዢ ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ በኩል የነበረው ሕውሓት ቢያንስ ግልጽ የሆነውን የአሰብን ጉዳይ መደራደር ነበረበት።
ኤርትራ እንዳትገነጠል ማድረግ አልቻሉም፤ ምክንያቱም መጀመሪያም ሲተጋገዙ ይሄን አጀንዳ ይዘው ነበር። ነገር ግን ሕወሓት ኤርትራ ስትገነጠል በአሰብ ጉዳይ መደራደር ይችል ነበር። ምክንያቱም ኤርትራም አጥብቃ የኔ ነው የምትልበት ነገር የላትም፣ ኢትዮጵያም ወደ ኋላ የምታፈገፍግበት ምክንያት አልነበራትም። ይህንን የተለያዩ ኮንፍረንሶችን አዘጋጅቶ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታውን ሚዛን ውስጥ አስገብቶ መከራከር ይቻል ነበር።
እስከ 1997 ዓ.ም. ድረስ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ነበርኩ። በወቅቱ ፓርቲዬ የነበረው ኢዲአፓ መድኅን አንዱ አጀንዳው የነበረው የአሰብ ጉዳይ ነው። እንደዚህ ተሸፋፍኖ ኢትዮጵያ ወደብ እንድታጣ የተደረገበትና በታሪኳ በር ተዘግቶባት እንድትቀር ያደረገ ሁኔታ ስለሆነ የአሰብን ጉዳይ በጉልበት ሳይሆን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በመነጋገርና በመወያየት እልባት ሊገኝለት ይችላል የሚል እምነት ስላደረብን ፖለቲካዊ አጀንዳ አድርገን መስቀል አደባባይ ሁለት ጊዜ ሕዝባዊ ሰልፍ አካሂደናል። ከ150 ሺህ በላይ የተረጋገጠ አድራሻ ያላቸውን ሰዎች ፊርማ አሰባስበን የሰነዱን ቅጂዎች ለአፍሪካ ኅብረት እና ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስረክበናል። ይህ ሁሉ ትክክለኛና አሳማኝ ምክንያቶች መኖራቸው የሞራል ስንቅ ሆኖን ያደረግነው ትግል ነው።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ሰላማዊ እንቅስቃሴ በጥርጣሬ ዓይን የሚመለከቱና ጦርነትን አማራጭ ታደርጋለች ብለው የሚያስቡ ወጎኖች አሉ። የእነዚህ ወገኖች ስጋት ተገቢ ነው ብለው ያምናሉ ?
ፕሮፌሰር አድማሱ፡– አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ባለቤት መሆን የምትችልበት ዕድል አለ። ምንድን ነው የተምታታው አሁን በደረስንበት 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያውያን የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት መንገዳችን ጉልበት ሊሆን አይችልም። የተቀማን ብንሆንም እንኳን ተቀማን ብለን በሕግ እንጠይቃለን እንጂ የጉልበት አማራጭን አንከተልም። ይሄን ጉዳይ መንግሥት የተረዳው ይመስለኛል። አንድም ጊዜ በጉልበት ሲል ሰምቼው አላውቅም። ስለሆነም መንግሥት አሁን ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ድጋፍ አለኝ።
ሌሎች ወገኖች በጉልበት እንወጣዋለን ብለን ያልተናገርነው ለማታለል እንደሆነ በማሰብ በሰላማዊ መንገድ የሚለውን መርሐችንን ሊቀበሉ አልቻሉም። ኢትዮጵያ የባሕር በር አጥታለች፤ አሁን እንዲኖራት ትፈልጋለች ሲባል ለሚነሳው እንዴት የሚል ጥያቄ ቶሎ የሚመጣላቸው ምላሽ ጉልበት ነው። በመንግሥት በኩል ጉልበት አማራጭ ተደርጎ ሲነሳ ሰምቼ አላውቅም። እኔም ደግሞ በአቋሜ ምክንያት አነፍንፌ ጉዳዩን ስከታተል ቆይቻለሁ፤ ምንም ነገር የለም። ስለ ባሕር በር ጉዳይ ከአንዳንዶች ጋር ስንነጋገር መንግሥት የባሕር ኃይል እያደራጀ መሆኑን ምክንያት አድርገው ጉልበት አማራጭ ሊሆን እንደሚችል ሲያነሱ ሰምቻለሁ።
ኢትዮጵያውያን የቁሳቁስ ድሆች ልንሆን እችላለን ነገር ግን በሃይማኖትም ሆነ በሌሎች መንገዶች ያገኘነው ውስጣችን የተገነባ መርሕ አትምጣብኝ የሚል እንጂ ወርቅ ተሸክመህ ብትሄድ ልቀማህ የሚል አይደለም።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያውያን እንደ ባሕር በር ባሉ የሀገርን ዘላቂ ጥቅም በሚወስኑ ብሔራዊ ጥቅሞች ሊያራምዱ የሚገባቸው አቋም ምን መሆን አለበት ?
ፕሮፌሰር አድማሱ፡– ወደብ የሚባል ነገር የሀገር ጉዳይ ነው። የወደብ ጉዳይ የማይነካው ግለሰብ፣ ቡድን እና ድርጅት የለም። ምክንያቱም ሁላችንም ከውጭ በሚመጣ ነገር ተጠቃሚዎች ነን። ሀገራችን ወደ ውጭ የምትልከው ምርት ቢቃና እንጠቀማለን ቢበላሽ እንጎዳለን። ከወደብ ጉዳይ የሚነጠል አካል የለም። ከአንድ መንግሥት ጋር ቅሬታ ቢኖርህ ዕድሜው አጭር ስለሆነ ተከታታይ ትውልዶችን የሚነካ ነገር አይደለም፤ የባሕር በር ጉዳይ ግን ሁሉንም ቤት ያንኳኳል። ስለዚህ የወደብ ጉዳይን መደገፍ ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ሀገራዊ ግዴታ ነው።
የኛ ወገን የሆኑ ግን እያወቁ በተለያየ ምክንያት አሁን ካለው መንግሥት ጋር ቅሬታ አለን በሚል ብቻ መስመር የሚስቱ አሉ። እነሱ ያሳዝኑኛል። የሀገር ጉዳይ ሌላ ነው፤ ሹሞች ሆነው ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ደግሞ ሌላ ናቸው። እንደ ባሕር በር ባለ ጉዳይ የሁላችንም ትብብር ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ሁለት ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ዓመታዊ የወደብ ወጪ አለባት። ይሄ ገንዘብ ሀገሪቱ ከሚያስፈልጋት ዓመታዊ በጀት አንድ ስድስተኛው እንደማለት ነው። ለወደብ ኪራይ የምናወጣው ወጪ ወደ ውጭ የምንልካቸው ነገሮች ገበያ ላይ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ያደርጋል። ከውጭ የምናስገባቸው እቃዎችም ውድ እንዲሆኑ ያደርጋል። ይሄ የጥቂት ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ተደርጎ መቆጠር የለበትም። በባሕር በር ጉዳይ መላው ኢትዮጵያውያን አብረን መቆም አለብን።
መንግሥት በእጁ ያለውን መረጃ ይዞ ነው ውሳኔ የሚወስነው። መረጃ ሳይኖረን ትችት ከመሰንዘር መቆጠብ አለብን። መረጃ ከያዝን ያለውን ጉድለትና በጎ ነገር ለይተን ስለምናውቅ አስተያየት መስጠት እንችላለን። በአጠቃላይ ግን የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሰዎች እስካሁን ከሚሰጡት መረጃ አንጻር ሳየው ጎደለ የምለው የለም።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ የወደብ አማራጯን ለማስፋት ከሁሉም ጎረቤቶቿ ጋር በመሥራቷ የምታገኘው ጥቅም ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር አድማሱ፡– የሶማሌላንድ መሪ ወደ ሀገራችን መጥተው የተፈረመውን ስምምነት
በማንሳት በስምምነቱ ወቅት በተጠቀሰው ጊዜ መሠረት የተከናወነ ነገር የለም በሚል የሚንጫጩ ሰዎች ሰምቻለሁ። ኢትዮጵያ ሰፊ ሀገር ብትሆንም ዙሪያውን በጎረቤቶቻችን የታጠርን ነን። የባሕር በር ለማግኘት በቅርብ ጊዜ የሰማነው ከሶማሌላንድ ጋ ያለው ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም ዙሪያችን ካሉ የቅርብም ሆነ የሩቅ የወደብ ባለቤቶች ጋር በተለያየ ደረጃ ይሁን እንጂ ሙከራዎች እየተደረጉ ነው። ከሁሉም ጎረቤቶቻችን ጋር ወደብን በተመለከተ መነጋገርና ሁኔታዎችን የተሻለ የማድረግ ሂደት ነው መከተል ያለብን። ምክንያቱም ወደ ሲዳሞ ያለው አካባቢ ለኬኒያ፣ ጎንደር ያለው ለሱዳን፣ ምሥራቁ የሀገራችን ክፍል ደግሞ ወደ ጅቡቲ፣ ኤርትራ እና ሶማሌላንድ ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ያስፈለጋት ለምንድን ነው የሚል ጥያቄ ሲነሳ ይሰማል። እርስዎ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጡት ምላሽ ምንድን ነው ?
ፕሮፌሰር አድማሱ፡– ብዙ ጊዜ በተለይ ነጮች ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ለምን ያስፈልጋታል የሚል ጥያቄ ሲያነሱ እሰማለሁ። ያስፈልጋታል፤ ወደብ ላይ የሚንቀሳቀስ ሀብት ንብረት አላት። በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የባሕር ላይ ወንበዴዎች አሉ። ሀብት ንብረቷን በመጠበቅ ራሷን ከነዚህ ኃይሎች ለመከላከል የሠለጠነ ወታደራዊ የባሕር ኃይል ያስፈልጋታል።
ምንጊዜም ቢሆን ጠንካራ ከሆንክ ትከበራለህ። ጥንካሬ በብዙ አቅጣጫ የሚገለጽ ነገር ነው። ዋነኛው ጥንካሬ የአንድ ማኅበረሰብ አንድነት ነው። አንድነት ካለህና እንደ አንድ ቤተሰብ መቆም ከቻልክ ድሃ ሀገር ብትሆንም ማንም አካል አይደፍርህም። ከአንተ ጥቅም ከፈለገ እንኳን በሰላማዊ መንገድ ለመጠቃቀም ነው የሚመጣው። ጥይቱን ትተን ሌሎችን ተፅዕኖ መፍጠሪያ መንገዶች መጠቀም አለብን።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርሕ የወደብ ባለቤት ለመሆን መንቀሳቀሷን እንዴት ይመለከቱታል ?
ፕሮፌሰር አድማሱ፡– ኢትዮጵያ ወደብ ስትጠይቅ በነፃ ስጡኝ አላለችም፤ ሰጥቶ የመቀበል መርሕን ነው የተከተለችው። አሰብ የኢትዮጵያ የነዳጅ ማጣሪያ ማዕከል እና ወደብ ነበረች። ያጣነው ይህን ያህል ሚና ያለውን የባሕር በር ነው። የተለያዩ ሀገራት ከርቀት በመምጣት በቀይ ባሕር የጦር ሰፈር ማቋቋም ደረጃ እየደረሱ ባሉበት ሀኔታ ኢትዮጵያ የተዘጋ በር ከፈት እንዲልላትና ከተቀረው ዓለም ጋር መገናኘት እንድትችል መጠየቋ ትልቅ ጉዳይ የሚሆንበት ምክንያት የለም። ኢትዮጵያ በምንም መልኩ በጉልበቷ ከሌላ ለመንጠቅ የተንቀሳቀሰችበት ታሪክ የላትም። ይሄን መለያዋን ይዛ መቀጠልና ለዓለም ይበልጥ ማስተዋወቅ አለባት። አንዳንድ ሥልጣን የሚፈልጉ ወገኖቻችን ከረጅም ጊዜ አንስቶ ከሚተነኩሱን ጋር አብረው ቆመዋል ሲባል እሰማለሁ። ይሄ ያሳፍራኛል። አንድ ዜጋ የሚፈልገውን ነገር ለማግኘት በቀጥታ ብቻ ሳይሆን በተዘዋዋሪ ውጤቱ ኢትዮጵያን ከሚጎዳ ነገር መጠበቅ አለበት።
አዲስ ዘመን፡– ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር በሚል ግብፅ እና ኤርትራ ከሶማሊያ ጋር ስለፈጠሩት ጥምረት ምን ይላሉ ?
ፕሮፌሰር አድማሱ፡– እነዚህ ሀገራት ለምን ሰጋችሁ መባል የለባቸውም። ነገር ግን የትኛውም ጎረቤት ሀገር ኢትዮጵያን በስጋት እንዲመለከት የሚያደርግ ነገር አለ ብዬ አላምንም። ሶማሌላንድ ነፃ ሀገር ሆና ነው የኖረችው። እንዲያውም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምትከተል ሀገር መሆኗ የሚነገርላት ናት። ከኢትዮጵያ ጋ ካደረገችው ስምምነት በኋላ እንኳን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመንግሥት ለውጥ አድርጋለች። ይሄ ሁሉ ሲሆን የተቃወመና ይመለከተኛል የሚል አካል አላየሁም። መቋዲሾ ያለው መንግሥትም በዚህ ጉዳይ ላይ ትችት ሲያቀርብ ሰምቼ አላውቅም። ለሀገሪቷ እውቅና የመስጠቱን ጉዳይ ማፈር ያዘው እንጂ የተለያዩ ሀገራት ቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ከሶማሊላንድ ጋር ግንኙነት እያደረጉ ብዙ ነገር እየሠሩ ነው። ኢትዮጵያም ያደረገችው ከሀገሪቱ ጋር ጉዳይ የሚፈጽሙ ሌሎች ሀገራት የሚያደርጉትን ነው፤ ከዚህ ያለፈ ነገር የለውም።
ግብፅ ተመሳሳይ ጉዳይን በተለያየ መስፈሪያ የምትለካ ሀገር ናት። የተለያዩ ሀገራት ወደቀጣናው እየመጡ በቀይ ባሕር ላይ የጦር ሰፈር እየገነቡ ባሉበት ወቅት በመቶ ኪሎ ሜትር ባነሰ ርቀት ላይ ያለችው ኢትዮጵያ ላይ ቅሬታ ማሰማት ትርጉም የማይሰጥ ነገር ነው። የግብፅ መንግሥት ባሕሪ እንዲህ ያለ ነው። በየዕለቱ አጀንዳ እየፈጠረ ሕዝቡን ካላታለለ ሕልውናው እንደሚያበቃ የሚያስብ ነው። ግብፅ በእሥራኤል ጉዳይ ከዓረቡ ዓለም የአሜሪካን ቀኝ እጅ ናት። ለዚህ ውለታዋም ከአሜሪካ በጣም ከፍተኛ የሆነ ድጎማ ታገኛለች። አሜሪካ በቀጣናው የምትፈልገውን ነገር ለመፈጸም እንደ መሣሪያ የምትጠቀመው የግብፅን መንግሥት ነው። ዞሮ ዞሮ ግብፅ ብትጮኽ ምንም ትልቅ ጉዳይ አይደለም። ምክንያቱም መንግሥታቸው የራሱን ሕልውና የሚጠብቅበት ስልት ነው።
አዲስ ዘመን፡– በኤርትራ የሚገኙ ወደቦችን የመጠቀም ዕድል አለ ብለው ያምናሉ ?
ፕሮፌሰር አድማሱ፡– አሁን በየቦታው በሚያባክነን የባሕር በር ጉዳይ ኤርትራውያን በአግባቡ ከመጡ ሁለታችንም ተጠቃሚ መሆን የምንችልበት ነው። አሰብንም ሆነ ምፅዋን ወደብን ለመጠቀም የሚፈልግ ሌላ ጎረቤት ሀገር የላቸውም። ወደቡን በመጠቀም እድገታቸውን ለማፋጠን ባለመምረጥ ምክንያታዊ ያልሆነ አቋም መያዛቸው ይገርመኛል። ጠብም ሆነ ቅሬታ ካለ በመሪዎች መካከል መፈታት ያለበት ነው። የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች የሚጠቀሙት ወደቦቹ ለምተው ወደ ሥራ ቢገቡ ነው። ኢትዮጵያ በተለያዩ ትርፋማ የልማት ድርጅቶቿ ውስጥ ድርሻ እንዲኖራቸው በማድረግ ጭምር በሰጥቶ መቀበል መርሕ በጋራ ተጠቃሚ እንሁን የሚል ጥያቄ እያቀረበች ነው ያለችው። የኤርትራ መንግሥት ይህን ዕድል ገፍቶ ከግብፅም ሆነ ከሌሎች ወገኖች ጋር ከወገነ በአንደኛ ደረጃ እየበደለ ያለው የራሱን ሕዝብ ነው። ምክንያቱም እኛ እነሱ እምቢ በማለታቸው በሌሎች ጎረቤት ሀገሮቻችን ወደቦች ለመጠቀም አማራጮችን እያየን ነው፤ እነርሱ ግን አሰብና ምፅዋን መጠቀም የሚፈልግ ሌላ ሀገር አያገኙም።
ከመሪዎች ጋር የተያያዙ ነገሮች ጉዳት ሊያመጡ የሚችሉ ቢሆኑም ጊዜያዊ እና ኃላፊ ናቸው። እኔ የበለጠ የሚያሳስበኝና ሁሉም እንዲያስበው የምፈልገው በሕዝቦች መካከል የሚኖረውን መጠቃቀምና መጎዳዳት ነው። ሌሎቹ ሁሉ ኃላፊ ናቸው። እኔ ዕድሜዬ ስንት እንደሆነ አላውቀውም፣ ምናልባት ዛሬ ሊቋጭ ወይም የተወሰኑ ዓመታት ሊረዝም ይችላል። ሀገር ግን ትኖራለች የትም አትሄድም። ሕዝብም ይተካካል የትም አይሄድም። ኤርትራውያንን ከሐረር፣ ከወለጋ እና ከወሎ ነጥዬ አላያቸውም። ታሪካችንን ከተመለከትን ተለያይተን የኖርነው ትንሽ ጊዜ ነው። አንድ ሀገር ሆነን መቀጠል ባንችልም እንኳን እንደ ጎረቤት ሀገር ከየትኛውም ጎረቤት ሀገር በላይ ለእኛ የሚቀርቡ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡– ሀገራት ለኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባሕር ባለቤት ለመሆን ለምታቀርበው ጥያቄ እውቅና መስጠት መጀመራቸው ምን አንድምታ አለው?
ፕሮፌሰር አድማሱ፡– ዲፕሎማሲ ከላይ እንዳነሳነው የሰጥቶ መቀበል ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ትልቋ ሀገር መሆኗን ብዙዎቹ የዓለም ሀገራት ይቀበላሉ። ከእነዚህ ሀገራት የተረፉ ካሉም አሁን እንኳን ባይሆን ወደፊት ትልቋ ሀገር እንደምትሆን ይቀበላሉ። ኢትዮጵያ ባላት ሀገራዊ ሀብት እንዲሁም በሕዝብ ብዛት አሁን ባለው ወቅታዊ መረጃ 132 ሚሊዮን ዜጎች ያላት በዓለም 10ኛ ደረጃ ላይ የምትቀመጥ ትልቅ ሀገር ናት። በየ25 ዓመቱ የሕዝብ ቁጥሯ በእጥፍ እያደገ ነው። ከ 25 ዓመታት በኋላ ደግሞ ቁጥራችን 260 ሚሊዮን ይሆናል ማለት ነው። ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው የሕዝብ ቁጥር ትልቅ ገበያ ነው። ይህ ሕዝብ አምራች ሆኖ ወደ ውጭ ሀገራት ምርት ይልካል፤ በአንጻሩ ትልቅ ገበያ በመሆን ከውጭ ሀገር የሚገቡ ሸቀጦችን ሸማች ነው። ስለዚህ እንደ ኢትዮጵያ ካለ ትልቅ ሀገር ጋር ጥሩ ግንኙነት መፍጠር የሁሉም ሀገር ፍላጎት ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ ወደብ አግኝታ ይበልጥ ተጠቃሚ ብትሆንም ሌሎች ሀገራትም በተዘዋዋሪ ገበያቸው ይሰፋል። በዚህ ምክንያት በአፍሪካ ቀንድ ካሉ ሀገሮች ኢትዮጵያ ግዙፏ ስለሆነች ዋናው ባሕር ገብተው ከዚያ በኋላ ወደ ኩሬዎቹ መቅዘፍን ይመርጣሉ። ይሄ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ድጋፋቸውን የሚቸሩ ሀገራትን ሁኔታ በገበያ ዓይን ስናየው የምናገኘው ምስል ነው።
በሌላ ዓይን ብናየው ደግሞ ከዚህ ቀደም ዐቢይም (ዶ/ር) ሲናገሩ እንደሰማሁት ይሄ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በችግር ምክንያት ወደ ሥርዓት አልበኝነት የሚገባና በስፋት ለስደት የሚዳረግ ከሆነ የሚሄድባቸው ሀገሮች መቸገራቸው አይቀርም። በአሁን ሰዓት የአውሮፓ ሀገራት ያስጠለሏቸው ስደተኞች ወደመጡበት ሀገር ተመልሰው ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ ብዙ ወጪ ለማውጣት ፈቃደኛ ናቸው። ይህን የሚያደርጉት እንዲሁ ለፅድቅ አይደሉም። ብዙ ችግር እየደረሰባቸው ስለሆነ ስደተኞቹ ከሀገራቸው ሳይነሱ በፊት በዚያው እንዲቀሩ ለማድረግ የተለያዩ መንገዶችን እየተከተሉ ነው።
ስለዚህ ኢትዮጵያንም ሆነ ራሳቸውን ለመጥቀም ሲሉ ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ባለቤት ለመሆን የምታደርገውን ጥረት መደገፋቸው አይቀርም። ተፈጥሯዊ በሆነ ሕሊና ሳስበውና ምክንያቶችን ስመለከት የድጋፋቸው ምንጭ ይሄ ይመስለኛል። በአንጻሩ ኢትዮጵያን እንደፈለጉ ማዘዝ የሚሹ ነገር ግን ለዚህ አልመች ያለቻቸው አንዳንድ ሀገራት ቢተነኩስን ደግሞ ሊገርመን አይገባም። ጤነኛ የሆነ አስተሳሰብ ያላቸውና ከኢትዮጵያ ጋር የጋራ ጥቅም አለን ብለው የሚያስቡ ሀገሮች በርካታ ናቸው። ኢትዮጵያም ከእነዚህ ሀገሮች ጋር የመሥራት አቅም አላት።
አዲስ ዘመን፡– በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለዎት?
ፕሮፌሰር አድማሱ፡– በመጨረሻም አደራ ማለት የምፈልገው ነገር አለኝ። በውስጣችን የፈለገውን ያህል እንጨቃጨቅ። ነገር ግን ሀገራዊ በሆኑ በተለይም ከውጪው ማኅበረሰብ ጋር በሚያያዝ ጉዳይ እኛን የሚለያየን ነገር መኖር የለበትም። የኢትዮጵያን ጥቅም በተመለከተ አብረን መቆም አለብን። በአሁኑ ወቅት የጎደለን ነገር ሁላችንም ለኢትዮጵያ አምባሳደር መሆን ነው። ለአሁኑም ሆነ ለወደፊቱ ተከታታይ ትውልዶች የሚሆን ነገር በሙሉ የጋራ ነገር ስለሆነ ልንጨቃጨቅበት አይገባም፤ ይልቁንም መተጋገዝ ነው ያለብን። ያለው መንግሥት እየመራ ነው። እንዲያስተካከል የምንፈልገው ነገርና ስህትት ሲኖር መወቃቀስ ተገቢ ነው። ነገር ግን የማጠልሸት ሥራ ሀገርን ይጎዳል እንጂ አይጠቅመንም። ለሀገራችን ብለው ደማቸውን ያፈሰሱ፤ አጥንታቸውን የከሰከሱ እና በተለያየ መልኩ ብዙ መስዋዕትነት የከፈሉ አሁን መሬት ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያን በዚህ መልኩ ያቆዩልን ወገኖች በሕይወት ባይኖሩም ቢያንስ በምንረዳው መልክ የሚያፍሩብን አንሁን። የወደፊቱ ትውልድ እና ያለፉት ወገኖቻችን መንፈስ እንዳይወቅሰን በር ዘግተን እንጨቃጨቅ እንጂ ገበናችን ወደ ውጪ አይውጣ። አደራዬ ይሄ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ጊዜ ወስደው ለጥያቄዎቻችን ዝርዝር ምላሽ ስለሰጡን እናመሰግናለን
ፕሮፌሰር አድማሱ፡– እኔም አመሰግናሁ።
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም