አዲሱ ዳይሬክተር ኤፍቢአይን መልሰው እንደሚገነቡ ገለጹ

የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) በመውቀስ የሚታወቁትና በቅርቡ በዳይሬክተርነት እንዲመሩ በሀገሪቱ ሴኔት ሹመታቸው የፀደቀላቸው ካሽ ፓቴል፤ ሕግ አስከባሪ ተቋሙን “መልሰው ለመገንባት” ቃል ገቡ። የሀገሪቱ የላይኛው ምክር ቤት በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዕጩነት የቀረቡትን አዲሱ ዳይሬክተር ሹመት ያፀደቀው 51 ለ49 በሆነ ጠባብ የድምፀ ብልጫ እንደሆነ ታውቋል።

ሁለት ሪፐብሊካን የምክር ቤቱ አባላት ሹመቱን ተቃውመው ድምፅ ሰጥተዋል። ዲሞክራቶች፤ ዕጩው ተቋሙን ለመምራት የሚሾሙ ከሆነ በትራምፕ ጠላቶች ላይ የበቀል ርምጃ ይወስዳሉ በማለት አስጠንቅቀዋል። ዕጩው በበኩላቸው፤ ፖለቲካዊ በቀሎችን የመውሰድ እቅድ አላቸው መባሉን አስተባብለዋል።

የ44 ዓመቱ ፓቴል ሹመታቸው በፀደቀበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ “ከጀርባ ሆነው መንግሥትን የሚያሾሩ (ዲፕ ስቴት)” ጠላቶች ዝርዝር አላቸው መባሉንም ውድቅ አድርገዋል። ከዚህ ቀደም ትራምፕ ላይ ምርመራ ያደረጉ የሕግ አስከባሪ ባለሥልጣናትን ላይ ተጠቅመው የነበረውን “ወንጀለኛ ወንበዴዎች” የሚል አከራካሪ ገለጻቸውንም አደባብሰዋል።

ፓቴል ሕግ አስከባሪ ተቋሙን ለመምራት የተሾሙት ሴኔቱ አባል የሆኑ ዲሞክራቶች በሙሉ ተቃውመው ነው። ሪፐብሊካን የሆኑት የሜይን ግዛት ተወካይ ሱዛን ኮሊንስ እና የአላክሳ ግዛቷ ሪፐብሊካ ተወካይ ሊሳ ሙርኮውስኪም ተቃውመው ድምፅ ሰጥተዋል።

አዲሱ የኤፍቢአይ ዳይሬክተር፤ ትራምፕ ወደ ሥልጣኑ ከመጡ ወዲህ ሹመታቸው የፀደቀላቸው 18ተኛ የካቢኔ ባለሥልጣን ናቸው። ፓቴል ሹመታቸው ከፀደቀላቸው በኋላ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ “የፌዴራል ምርመራ ቢሮ ዘጠነኛ ዳይሬክተር ሆኜ በመሾሜ ክብር ተሰምቶኛል” ብለዋል።

“እንደ ዳይሬክተር ተልዕኮዬ ግልጽ ነው፤ ፖሊሶች ጥሩና ሙያቸውን የሚያከብሩ እንዲሆኑ እና የኤፍቢአይን እምነት መልሶ መገንባት” ብለዋል።

“የአሜሪካ ሕዝብ ሊኮራበት የሚችልን ኤፍቢአይ መልሰን እንገነባለን” ሲሉም ገልጸዋል።

ፓቴል የተቋሙን ሥልጣን የተቆናጠጡት፤ የሀገሪቱ ፍትሕ ሚኒስቴር የተወሰኑ ከፍተኛ አመራሮቹን ካባረረ እንዲሁም በአውሮፓውያኑ 2021 የትራምፕ ደጋፊዎች ያስነሱትን የካፒቶል ሂል አመፅ የመረመሩ ወኪሎች ስም እንዲሰጠው እየጠየቀ ባለበት ሁኔታ እንደሆነ ተጠቁሟል።

በዋሽንግተን ዲሲ ለዓመታዊው የወግ አጥባቂዎች ‘የኮንዘርቫቲቭ ፖለቲካል አክሽን ኮንፈረንስ’ ተሰብስበው የነበሩት ሪፐብሊካኖች የፓቴልን የሹመት ዜና የተቀበሉት በጭብጨባ ነው። የፍሎሪዳ ተወካይ የሆኑት ሪክ ስኮት በጉባኤ መድረክ ላይ ቆመው “ስለ ካሽ ፓቴል የምናስበው ምንድነው?” በማለት ለታዳሚዎቹ ያቀረቡት ጥያቄ በሞቀ ጭብጨባ ተመልሷል።

ለብዙዎቹ ሪፐብሊካኖች ካሽ ፓቴል ማለት እስካሁን የዘገየውን የሀገሪቱን ከፍተኛ ሕግ አስከባሪ ተቋም ከስሩ የመነቅነቅ ሥራ የሚያከናውን ሰው ነው። ትራምፕ እና ሌሎች ሪፐብሊካኖች፤ ኤፍቢአይ ወግ አጥባቂዎችን ማጥቂያ ሆኗል በማለት ይከስሳሉ።

ዲሞክራቶች በበኩላቸው ፓቴል በሕግ ማስከበር ያለው ልምድ ትንሽ የሆነ ቀኝ አክራሪ የሴራ ተንታኝ ነው ይላሉ። ተቋሙን በነፃነት ለመምራት ከገባው ቃል በላይ ለትራምፕ ያለውን ታማኝነት የሚያስቀድም መሆኑንም ይናገራሉ።

ማርቲን ሃይንሪክ የተባሉት የሴኔቱ አባል በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ “[የፓቴል] ደካማ ማመዛዘን ችሎታ እና የልምድ ማነስ፤ የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ሆኖ የአሜሪካውያንን ደኅንነት ለማስጠበቅ ሙሉ በሙሉ ብቁ እንዳይሆን ያደርገዋል” ብለዋል።

ፓቴል ተቋሙን የመምራት ሹመት ያገኙት እ.አ.አ በ2017 በትራምፕ የተሾሙትን ክርስቶፈር ሬይን በመተካት ነው። ሬይ ባለፈው ወር ከትራምፕ ቃለ መሐላ አስቀድመው ከኃላፊነት የለቀቁት አዲሱ ፕሬዚዳንት እንደሚያባርሯቸው ከጠቆሙ በኋላ መሆኑን የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You