
የስብሰባ ወይም ሥልጠና ዋና ዓላማ ምንድነው? ተብሎ ቢጠየቅ ያን ያህል ውስብስብና ሰፊ ማብራሪያ የሚጠይቅ አይመስለኝም:: የስብሰባ ዋና ዓላማ በአንድ ጉዳይ ላይ በጋራ ለመወያየት የሚደረግ እና ለችግሮች መፍትሔ የሚቀመጥበት ነው:: ሥልጠና ደግሞ በአንድ ጉዳይ ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ወይም የነበረ ሙያን ለማዳበር በባለሙያ የሚሰጥ ተጨማሪ ክህሎት ነው::
ስለዚህ በዚህ ስብሰባ (ሥልጠና) ውስጥ መደማመጥና ሃሳብ መለዋወጥ የግድ ነው:: ተሰብሳቢው ተገልጋዮች የሚስተናገዱበትን ሥራ ዘግቶ ነው የመጣው:: ምክንያቱም በስብሰባው ላይ ተወያይተው ለሆነ ጉዳይ መፍትሔ መምጣት ስላለበት ማለት ነው፤ ወይም በሥልጠናው ላይ ለሥራው የሚያግዝ ዘመኑንና ወቅቱን ያማከለ ተጨማሪ ክህሎት መያዝ ስላለበት ነው::
ታዲያ የስብሰባዎችን(ሥልጠናዎችን) ነገር ካየን በጣም ብዙ ነገር መታዘብ እንችላለን:: ውድ የሆነው ሰዓትና የሰው ኃይል ይባክናል:: በተሰብሳቢዎች ሰዓት ማርፈድ የሚባክነው ጊዜ እና ገባ ወጣ በማለት ሌሎችን መረበሽ የተለመዱ ናቸው::
ከዚህ ሁሉ በላይ ግን አንድ የሚገርመኝ ነገር አለ:: በትልልቅ የስብሰባ አዳራሾች ውስጥ ‹‹ዋይ ፋይ›› ተገጥሟል:: ይሄ ማለት እኮ ‹‹ስብሰባውን ተውትና ፌስቡክ ተጠቀሙ›› ማለት ነው:: ይሄ የሚሆነው በትልልቅ የስብሰባ ቦታዎች ላይ ነው፤ ዓለም አቀፍ ጉዳይ በሚወራባቸው ስብሰባዎች ላይ ጭምር ነው:: አንዳንድ ቦታዎች ላይ ግን (ለምሳሌ ስካይላይት ሆቴል) ስብሰባው እስከሚያልቅ ነው ተብሎ ዋይ ፋይ እንዳይሠራ ተደርጎ አይቻለሁ (ምናልባት እኔ ባየሁበት አጋጣሚ ብቻ ሊሆንም ይችላል)::
በብዙ ቦታዎች ግን ገና ወደ አዳራሹ እንደገባችሁ የቤቱ የዋይ ፋይ የምስጢር ቁጥር ከፊት ለፊት ይለጠፋል:: ይህኔ እንግዲህ ሌላ ቦታ ‹‹ኮኔክሽን›› ሲያስቸግረው የነበረ ሁሉ ጥሙን የሚወጣው እዚያ ነው:: ከኢንተርኔት ማውረድ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ የሚያወርድ የዚያን ዕለት ነው:: በዚያ ላይ ነፃ ስለሆነ በራሱ ‹‹ዳታ›› አለመሆኑ ሌላው ቀልብ ሳቢ ነገር ነው:: እዚህ ስብሰባ ውስጥ ያለ ሰው ጆሮውን ቢቆርጡት አይሰማም፤ ሌላ ዓለም ውስጥ ነው ያለው::
ስብሰባ ውስጥ ‹‹ዋይ ፋይ›› የሚያስፈልግበት አጋጣሚ እንዳለ አምናለሁ፤ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ የግዴታ የሚሆንበት ሁኔታም አለ:: ለምሳሌ ሥልጠናው ‹‹ሳይበር›› ነክ ነገር ከሆነ ሁሉም ኢንተርኔት እየተጠቀሙ ነው ልምምዱ የሚደረገው:: አንድን ጊዜ ደግሞ በሌሎች ሥልጠናዎችና ስብስባዎች ውስጥም ዘመኑ የፈቀደው ነውና ነገሮችን ለማረጋገጥ ወደ ኢንተርኔት ጎራ ማለት የግድ ሊሆን ይችላል::
በሌላ በኩል ደግሞ ስብሰባዎች በተባለላቸው ሰዓት ተካሂደው አያውቁም፤ ቀድሞ የደረሰ ሰው የሚደርስበትን መጉላላት አስቡት! ስለዚህ በነፃ ኢንተርኔት መካስ አለበት ይሄ ሰውዬ:: የባከነውን ሰዓቱን ቢያንስ በማንበብ ሊጠቀምበት ይገባል::
ትዝብቴ ዋይ ፋይ ስብሰባ ቦታ ውስጥ ሙሉ በሙሉ አያስፈልግም ሳይሆን አጠቃቀሙ ግን አልታወቀበትም፤ ወይም የሆነ ሌላ ዘዴ ሊፈጠርለት ይገባል የሚል ነው:: ለምሳሌ፤ ስብሰባው ሲጀመር የዋይ ፋይ አገልግሎት መቋረጥ አለበት፤ ወይም ሌላ የክልከላ ዘዴ መኖር አለበት:: ይህ ካልሆነ ስብሰባው እየተካሄደ ያለው ለመርሐ ግብርና ለሪፖርት ብቻ ነው ማለት ነው:: መድረክ መሪውም ማንም እንደማይሰማው እያወቀ ከሆነ የሚያወራው፤ እሱም የይውጣልኝ ነው እየሠራ ያለው:: እዚያ ላይ እኮ ሀገራዊ ጉዳይ ነው እየተወራ ያለው:: መድረክ ላይ ምን እንደቀረበ ያልሰማ ተሳታፊ ምን ብሎ አስተያየት ሊሰጥ ይችላል?
ያለመደማመጥ ነገር ቀላል ችግር አይደለም:: ሳይሰሙ የሚናገሩት ይኖራሉ:: መድረክ መሪው ‹‹እባካችሁ የተነሳ ሀሳብ አትድገሙ›› እያለ ደጋግሞ ይናገራል፤ እሱን ራሱ ማን ሰምቶት:: መድረክ መሪው ባስ ሲልበት ተናጋሪውን በማቋረጥ ‹‹እሱ ሃሳብ ተነስቷል›› ሲለው ካፈርኩ አይመልሰኝ በሚል ‹‹ቆይ ልጨርስ›› እያለ ሌላ ሰው የተናገረውን ሁሉ ደግሞ ይናገራል:: እንግዲህ አስቡት በጥሞና ያላዳመጠ ሁሉ ሲናገር ሃሳቦች እጥፍ እጥፍ ሊደገሙ ነው ማለት ነው::
በአንድ ትልቅ አዳራሽ ውስጥ የታዘብኩትን ልጥቀስ:: ስብሰባው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ነው:: በየጠረጴዛው ላይ ላፕቶፕ ተቀምጧል:: መጀመሪያ ሳየው ለስብሰባው የግድ አስፈላጊ የሆነ ነገር ነበር የመሰለኝ:: በኋላ ውይይቱ ሲጀመር ሳይ ግን የሚጠቀሙት ነገር ከስብሰባው ጋር ምንም የሚገናኝ አይደለም:: አንዳንዱ ፌስቡክ ይጠቀማል፤ አንዳንዱ ቪዲዮ ያያል፣ አንዳንዱ ሌላ ጽሑፍ ያነባል፤ መድረክ ላይ የሚባለውን ነገር የሚሰማው ከፊቱ ላፕቶፕ የሌለ ሰው ብቻ ነበር:: ላፕቶፕ ከሌላቸው ሰዎች ውስጥም በራሱ ስልክ የሚጠቀመው ቀላል አይደለም::
ሌላው የዋይፋይ ትዝብቴ ደግሞ ጋዜጠኞች ላይ የማየው ነው:: አንድ ጋዜጠኛ ሊዘግብ የሄደበትን ጉዳይ በጥሞና ነው መከታተል ያለበት:: ምናልባት እሱ የፈለገው የራሱ አንግል ይኖረው ይሆናል:: ምንም ይሁን ምን ግን ስብሰባው ላይ የተባለውን ነገር ሳይሰማ የራሱን ጥያቄ እንኳን መጠየቅ አይችልም:: ያ የሚያናግረው ሰው እንኳን ‹‹ውይይቱ ላይ እንደሰማኸው…›› እያለ ነው የሚያወራ:: ይህኔ ጋዜጠኛው የተባለውን አልሰማም:: ለዚህ እኮ ነው ጋዜጠኞች ጥያቄ ሲጠይቁ ‹‹የዛሬው ስብሰባ ስለምንድን ነበር›› ብለው የሚጀምሩት::
የዋይ ፋይ ነገር ቦታ ሊመረጥለት ይገባል:: አንድ ስብሰባ የጋራ መደማመጥ ከሌለበት ለምንድነው ጊዜ የሚባክነው? ምን ጊዜ ብቻ ያ ስብሰባ እኮ ብዙ ብር ወጪ የተደረገበት ነው:: ስለዚህ ለውይይት የሚጠራው ሰው የማይከታተለው ከሆነ ብክነት ብቻ ነው የሚሆነው::
አከራካሪው ነገር ‹‹እንዴት ትልልቅ የስብሰባ ቦታ ላይ ዋይ ፋይ ይጥፋ! ይባላል›› የሚል ነው:: እርግጥ ነው ዋይ ፋዩ በራሱ እኮ ችግር የለበትም:: እሱ የተሠራበትን አገልግሎት እየሰጠ ነው:: እኛ ግን አጠቃቀሙን ካልቻልንበት ያለው አማራጭ አለመኖሩ ሊሆን ነው:: አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ያገልግል እንጂ ለመረባበሻማ መሆን የለበትም::
አንዳንድ ጊዜ አስቂኝ ነገር ሁሉ ይፈጠራል:: የሆነ የድምፅ ብልጫ የሚያስፈልገው ነገር ካለ እጅ እንዲያወጡ ይቀሰቀሳሉ:: የምርጫ ሀሳቡ ሲሰጥ ለየትኛው ሃሳብ ያውጡ? ከደጋፊውና ከተቃዋሚው ይልቅ ድምፀ ተዓቅቦ የሚባለው ይበልጣል ማለት ነው:: ይሄ የሆነው እንግዲህ ምን እንደሆነ ስላልገባው ነው:: በዘፈቀደ ካወጣም የሚፈጠረውን መጭበርበር አስቡት:: እናም ወይ አጠቃቀማችን ይስተካከል ካልሆነ በስብሰባ ቦታ ውስጥ ዋይፋይ ገደብ ይኑረው!
በጣም እየከፋ የመጣው ችግር ደግሞ ስልክ ነው:: ኢትዮጵያ ውስጥ የእጅ ስልክ መጠቀም ከተጀመረ ከ20 ዓመት በላይ ሆኖታል:: በዚህ ዘመን ‹‹የተማረ›› የሚባለው ሰው በትንሹ ከ10 ዓመት በላይ የእጅ ስልክ የያዘ ነው:: ሰው እንዴት ይህን ያህል ዓመታት አሁንም ብርቅ ይሆንበታል? ስልክ አጥፉ ወይም ድምፁን ፀጥታ (ሳይለንት) ላይ አድርጉ እየተባለ የሚሰማ የለም::
በነገራችን ላይ አንዳንድ የሥራና የሙያ አይነቶች ጭራሹንም ስልክ የማይያዝባቸው አሉ፤ እኛ ግን ለሰዓታት እንኳን መለየት እየቸገረን ነው:: ጥሩ ማብራሪያ እየተሰጠ እያለ ድንገት የአንዱ ስልክ ያንባርቃል:: ሊያናግር ወደ ውጭ ይወጣል:: በር ይዘጋል ይከፍታል:: በዚህ ሁሉ ውስጥ ታዳሚው እየተረበሸ ነው::
ከዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ አሁንም ስለእጅ ስልክ አጠቃቀም መተዛዘብ ሌላ ትዝብት ነው!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 15 ቀን 2017 ዓ.ም