
ወዳጄ ጉልላት እንደገደል ዛፍ መወዝወዙ ይብቃህ ስንለው “ስተኩስና ስጸልይ ነበር የምንበረከከው፤ አሁን ግን አረቄ አሸንፎኝ በተመልካች አስገመተኝ ከእንግዲህ አልጠጣም” ብሎ ቃሉን ከሰጠን በኋላ መለኪያ ጋር “አይንህን ላፈር” ተባብለው ተራራቁ። ታዲያ አንድ ቀን የሰርኩን ነፋሻማ አየር እየተቀበልን የንጉሥ ተክለሃይማኖትን አደባባይ ስንቃኝ የደንበጫን አረቄ ጭኖ ወደአዲስ አበባ ከሚኳትን መኪና አንድ ጀሪካን ወድቆ ጉልላት እግር ስር አረፈ፤ ከፍቶ ሲያየው አረቄ ነበርና “እስከዛሬ ድረስ በኔ ስትጫወቺ ኖረሽ አሁን ብቻሽን ወደቅሽ?” አለ አተላ እንደሸተተው በሬ አፍንጫው ቆሞ። ነዋሪው ጉልላትን “የማርቆስ ምልክት ያደባባይ ጌጥ ነው” ይሉታል፤ እናም በጉልላት ትዝታ ማርቆስ ይህን ትመስላለች።
ከጉልላት አንደበት የማይነጥብ አንድ ነገር አለ። “አዲስ አበባ ጠላ፣ ጎጃም ቢራ የጠጣ፣ ከበግና ፍየል ሲባል ነብርን ማን ችሎት” ብሎ የሚመልስ ነው፤ እንዳለውም ማርቆስ ደርሰው ያብማን ጠላ ካልቀመሱ አድባሩ ተጣልቶ ይጎንጣል ይባላል።
“ጢስ” የምትል እማሆይ ኅብስቴ የምትሰኝ ያባ አሰፋ መኪና ነበረች፤ አባ ኮራም ደገሙና ሁለት ሆኑ። ሕዝቡ በሆታ አጅቧቸው ጌቶቹን አመሰገነ። ጋጡ የተጨነቀ ጎተራው የተጠቀጠቀ ከበርቴ ሙክትና ቅቤ ማሩን እጅ ያጠራት ባተሌ ደግሞ ጠርሙስ አረቄ አሸንቅረው “በመኪናው መንገድ በኮረሪማው፣ አንቺን ተከትዬ ይብላኝ አሞራው።”
በማለት እየዘፈኑ እነአባ አሰፋንና አባ ኮራን አደመቋቸው። እረኞችም አስከተሉና ለከንፈር ወዳጃቸው
“በነጠላ ጫማ ባንቺ አረማመድ፣
እንዲህ ቅርብ ነው ወይ የማርቆስ መንገድ።”
ሲሉ አዜሙ። “የማያንኳኳ ይውጣ” ከሚል ጠላ ቤት ደርሰን ካቻማሌ ብርጭቆ ሰይመን አሹቅ፣ በቆልትና ግብጦ አዘን ከጨዋታ ጋር ስናዋዛው ጥያቄ ጣልኩ። ለምን የማያንኳኳ ይውጣ ተባለ?
“አንድ ጊዜ ነው አሉ” ሲል ጉልላት ወጉን ጀመረ። “የቤቱን መድመቅ አይቶ አንድ መጽሐፍ አዟሪ ወደውስጥ ዘልቆ የያዘውን በሞላ ሸጦ ጨረሰ። ሴትዮዋ ተከትለው ወጡና “እዚህ የመጡት ሊጠጡ እንጂ ሊያነቡ መሰለህ? የነሱ ኪስ የኔም ነው፤ ዘርፈህ እንደወሰድክብኝ ነው የምቆጥረው። ዳግመኛ ድርሽ እንዳትል” ሲሉ መጽሐፍ አዟሪውን አስጠነቀቁት። ከዚያም ተመለሱና ማንቆርቆሪያውን አንቀው የሚያንኳኳ ቢያማትሩ ሁሉም ጠጪ ብርጭቆውን ትቶ መጽሐፉ ውስጥ ይዋኛል። ይህን ጊዜ ባልቴቷ ተናደው “የማያንኳኳ ይውጣ” አሉ።
በሌላኛው ቀን ደግሞ አዲንግ ይዋሻል?” ጠላ ቤት ይዞኝ ገባ። “ይሄን ሙሊት አዳሜ ልፎ ሂሳብ ሲጠይቅ ሴትዮዋ ከጠጣው ውጪ 2 እና 3 ጨምረው ይነግሩታል። ከፋዩ ሰውዬ በንዴት ጦፎ የጠጣውን መጠን ሲያስረዳቸው ባልቴቷ ረጋ ብለው “እኔስ ግዴለም ልሳሳት ሰው ነኝ ሌላው ቢቀር አዲንግ ይዋሻል?” ሲሉ “እሱስ አይዋሽም” አለና አዲንግ ማሽኑን አምኖ ከፈለ” አለና የስያሜያቸውን መነሻ አጫወተኝ።
እዚህ ቦታ ባይተዋርነት የለም። አንድ ሰው ያዘዘው መብል ሲመጣለት ሁሉንም እየዞረ ያስቆነጥራል። ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችም ሲንሸራሸሩ “ያውቁኛል አያውቁኝም?” ሳይል ሃሳቡን ይሰነዝራል።
የእጅ ሰዓቴን ተመለከትኩና ሳጨበጭብ “እመት” ብለው ባልቴቷ ሲመጡ ብርጭቆዬን ካስሞላሁ በኋላ ኳስ ጨዋታ መኖሩን ገልጬ ቴሌቪዥን አስከፈትኳቸው። ማንቼስተር ዩናይትድ አርሴናልን 1 ለባዶ መምራት ጀምሮ ስክሪኑ የሊሳንድሮ ማርትኔዝን ጎል በምልሰት እየደጋገመ ሲያሳየን ሴትዮዋ “5 እስቲገባባቸው ድረስ ሞተዋል?” ሲሉ ጉልላት “እመይቴ ይታክቱ ደግሞ ይህን ያህል ዓመት ኖረሽ ሃይላይት አታውቂም?” አለ ሳቅ እየቀደመው። “ላስቃችሁ ብዬ ነው እንጂ ኮረንቲ ጠፍቶኝ ነው?” ሲሉ በተራቸው ካንጀት ሳቅንላቸው። የቤቱ ታዳሚ ጉም ጉም አለና ኳስ ጨዋታው ቀርቶ ወደዘፈን ቻናል ሲቀየር ሃሊማ ስትንጎማለል ደርሼ አንድ ወግ ትዝ አለኝ። የሃሊማ አልበም ሲመረቅ አንድ ጋዜጠኛ ማይኩን ደቅኖ “የሃሊማን አልበም እንዴት አገኘኸው?” በማለት ታደለ ሮባን ጠየቀው፤ ታደለ ሮባም “ካዟሪዎች” ብሎ መለሰለት።
አንድ ጊዜ እንደዚሁ መንገደኛው ከሐይቁ ዳር ቀርቦ መረብ የጣሉ ወጣቶችን ምን እያደረጉ እንደሆነ ሲጠይቃቸው ዓሣ እያጠመዱ እንደሆነ ይነግሩታል፤ ቀጠለና “ለመሆኑ ከየት ነው የምታጠምዱት?” ሲላቸው ተገርመው “ወዲያ ማዶ ያለው ዛፍ ይታይሃል? ከሱ ላይ ነው የምንሸመጥጠው” አሉት። ቅቤ አጥቶ እንደሚጮህ ደረቅ አናት በልማድ የኖረና በንባብ ያልበሰለ ሃሳባችን ይፈጥና አለማወቃችንን ያጎላዋል፤ ስለሆነም ሙያው የሚፈልገውን ብሂል እንድናዳብር ጎበዝ እናንብብ። አይኔን ወደቴሌቪዥኑ ስመልስ
“በላይ ካልተጠራ፣
አይደምቅም የጎጃም ጭፈራ።”
እያለ ይደልቃል። ጉልላት ዘፈኑን ተንተርሶ ጨዋታ መዘዘና የውይይት ሃሳብ ዘረጋ። “የጥበብ ሥራዎቻችን ናቸው ወደመንደርተኛነት የገፉን ወይስ እኛ ነን የሳብናቸው?”
በእድሜ ጠና ያሉ ሰውዬ ጥያቄውን ቀለቡና ንግግር ሲጀምሩ አፍ ሲያላምጥ ጆሮ አያዳምጥምና የማመነዥገውን ግብጦ ትቼ ትኩረቴን ሰበሰብኩና የሚያነሱትን ሃሳብ በጥንቃቄ ከልቦናዬ ጻፍኩት። “ጸሐፊው የነበሩት ፊት አውራሪ ቀለም ወርቅ ማዘንጊያ አሳይተውኛል ማኅተሙ እንኳን አርበኛ በላይ ዘለቀ የኢትዮጵያ ደም መላሽ ነው የሚለው፤ እኛ ግን ዓባይን እንዳይሻገር አጠርነው። ዓለም ያነገሠው እኛ ያኮሰስነው አብዲሳ አጋ ብሔራዊ ጀግናችን ሆኖ ሳለ ከወለጋ እንዳይወጣ አደረግነው። አሉላ አባ ነጋን አንሰን አሳነስነውና ተንቤን ቀበርነው። ዓፄ ቴዎድሮስ ስለኢትዮጵያ ሲያልሙ በቋራ ወሰንናቸው። ከእንዲህ ዓይነቱ የመንደርተኛነት ትብታብ ፈልቅቆ የሚያወጣን የጥበብ ሥራ ስንሻ እነሱ ግን ቅቡልነትን ለማግኘት በሚል በመንደራቸው ተወሸቁ። ትውልዱም ያሉትን ተከትሎ ለጀግኖቹ ድንበር አበጀላቸው” አሉ በቁጭት ጺማቸውን እየላጉ። ታዲያ ምን ይበጀናል? ስል ጥያቄዬን አቀረብኩላቸው መፍትሔውን ቢጠቁሙኝ ብዬ። ብርጭቆውን ከከንፈራቸው አገናኝተው ጉሮሯቸውን አረጠቡና “ሶቅራጠስ እኔ ትንኝ ነኝ እንደትንኟ የተኛውን ፈረስ ጢዝ እልበታለሁ” እንዳለው ጠቦ በሚያጠብ የፖለቲካ ሃሳብ ተከናንቦ አጉል መኝታ ላይ ለወደቀውና ቅዠት የሞላበት እንቅልፍ ለሚያንጎላጀው ትውልድ የጠቢባን ብዕር እንደትንኟ ሊሆን ይገባል።
እንቁራሪቷ ከአዞው ሆድ ውስጥ ወጥታ ካፉ ብትደርስ ሌላ ሰማይ መኖሩን ልብ ትል ነበር፤ ዳሩ ምን ይሆናል አልሞከረችውም። ትውልዱም ከድንበር ይልቅ ስለነፃነት ሰውነትን አስቀድማ ከራሷ አልፋ ለደቡብ ኮሪያ፣ ሩዋንዳ፣ ሱዳን ሶማሊያና ለመሳሰሉት ውድ ልጆቿን የገበረች እንዲሁም የዘመን ጥበቧ የሚያስደንቅ ዓለምን የምታስንቅ ሰፊ ሀገር እንዳለችው ልብ ካላለ “አዞ ሆድ ውስጥ ያለች እንቁራሪት ሌላ ሰማይ ያለ አይመስላትም” እንዲሉ ከመንደርተኛነት ያልወጣ እሳቤ ኢትዮጵያንም ከመዳፍ ያሳንሳታል። ስለዚህ በየጊዜው ለሚፈበረክ ሐሰተኛ ትርክት ጭራዋን ያልቆላች ጥበብ በብዕሯ እየሸነቆጠች እንደትንኟ የተኛውን ትውልድ መቀስቀስ ይኖርባታል” አሉ በሙሉ ዓይናቸው እያዩኝ።
ሀብታሙ ባንታየሁ
አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም