ሜታ አህጉራትን የሚያዳርስ የኢንተርኔት ገመድ ሊዘረጋ ነው

አዲስ አበባ፡ሜታ ሃምሳ ሺህ ኪሎ ሜትር የሚረዝምና ዓለምን ማዳረስ የሚችል የኢንተርኔት ገመድ ከውቅያኖስ በታች ሊዘረጋ መሆኑን አስታወቀ።ሜታ ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ፕሮጀክት ዋተርዎርዝ ሲል የጠራው የኢንተርኔት ገመድ ዝርጋታ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ህንድ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ብራዚልን እንዲሁም ሌሎች ሀገራትን የሚያገናኝ እንደሆነ ገልጿል፡፡

የሚዘረጋው ገመድ ሃያ አራት ፋይበር ፔይር የተባለ ሲሆን ለፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ጥቅም የሚሰጥ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡ በውቅያኖስ ግርጌ የሚዘረጉት እነዚህ የኢንተርኔት ገመዶች ዳታ በክፍለ ዓለማት መካከል በፍጥነት እንዲንቀሳቀስ ከፍተኛ ጥቅም ያላቸው መሆናቸውም ታውቋል፡፡

ዝርጋታው ሲጠናቀቅ በዓለማችን ረጅሙ የኢንተርኔት ገመድ እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን ጉዳዩን በባለቤትነት የሚመራው የፌስ ቡክ፣ የኢንስታግራም እና የዋትስአፕ ባለቤት የሆነው ሜታ በቴክኖሎጂው ዓለም ያለውን ተጽዕኖ ፈጣሪነት በማህበራዊ ሚዲያው ላይም እንዲታይ መፈለጉ ታውቋል፡፡

ድርጅቱ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (Artificial in­telligence ) ዘርፈ ብዙ አበርክቶው ግንባር ቀደም ሚናን ለመጫወት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ ኩባንያው እንዳለው አዲሱ የኢንተርኔት ገመድ ዝርጋታ አምስት አህጉራትን የሚያገናኝ እና የኤአይ መሠረተ ልማትን የሚደግፍ መሆኑ ታውቋል፡፡

ኩባንያው በመግለጫው ‹የተጀመረው የዝርጋታ ፕሮጀክት ታላቅ የምጣኔ ሀብት ትስስርን በመፍጠር፣ የዲጅታል አካታችነትን በማፋጠን፣ እንደዚሁም ዝርጋታው ተግባራዊ በሚሆንባቸው አህጉራት የቴክኖሎጂ እድገት እንዲፋጠን ምክንያት በመሆን የገዘፈ አንድምታ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ዘጠና አምስት በመቶ የሚሆነው የዓለማችን የኢንተርኔት ዝውውር እየተከናወነ ያለው ከውቅያኖስ ስር በሚገኙ ገመዶች አማካኝነት እንደሆነ የገለጸ ሲሆን ቴሌጂኦግራፊ የተባለው የቴሌኮሚኒኬሽን ጥናት ተቋም እንደሚያስረዳው ከሆነ ደግሞ በአሁኑ ሰዓት ስድስት መቶ የሚሆኑ የኢንተርኔት መተላለፊያ ገመዶች ከዛው ከውቅያኖስ ስር ይገኛሉ ብሏል፡፡

ከነዚህ ስድስት መቶ ገመዶች መካከል በሜታ የሚደገፈው እና ኦሬንጅ፣ ቮዳፎን እና ቻይና ሞባይል የተባሉትን የኔትወርክ አቅራቢዎች የሚያገናኘው አርባ አምስት ሺህ ኪሎ ሜትር የሚረዝመው 2 አፍሪካ የተባለው ገመድ ይገኝበታል። ጎግል ባሳለፍነው በአውሮፓውያኑ 2024 ባወጣው መግለጫ አፍሪካ እና አዎስትራሊያን የሚያገናኝ እና አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ገመድ በፓስፊክ ውቅያኖስ ስር እንደሚዘረጋ ማስታወቁ የሚታወስ ሲሆን በሜታ ሊዘረጋ የታቀደው የኢንተርኔት ዝርጋታም የዚህ አንዱ አካል ነው፡፡

ውቅያኖስን መሠረት አድርገው የሚዘረጉ የኢንተርኔት ገመዶች ከጥቃት ነጻ የመሆናቸው ነገር ተአማኒነት ባይኖረውም እንደጥቃት ያለ መሰል አደጋዎችን ሊያስተናግዱ እንደሚችሉ ስጋት አለ፡፡ ሆኖም ግን ለተያዘው ክፍለ ዓለማትን በኢንተርኔት ትስስር የማገናኘት ዓላማ የተሻለ ምርጫ ሆነው ቀርበዋል፡፡

ሜታ በመግለጫው ጥቃት እና አደጋዎችን ከማስቀረት አኳያ ገመዱን የሚቀብረው ሰባት ሺህ ሜትር ጥቅል በሆነ ሥፍራ መሆኑን አስታውቆ ይህን የሚያደርግበት ዋና ዓላማ በገመዱ ላይ የሚደርስን የጥቃት ስጋትን ለመቅረፍ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ የዓለም አሁናዊ ትስስር በቴክኖሎጂና በመሰል የኢንተርኔት ስርጭት ስር የወደቀ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን በሜታ ግዙፍ የእቅድ እንቅስቃሴ ስር ያለው የኢንተርኔት ዝርጋታም ዓለምን የበለጠ እንደሚቀይር ታምኖበታል።

በየቀኑ የምንሰማቸው የቴክኖሎጂ ሽግግሮች የነበረውን ሽረው ለአዲስ አስተሳሰብ እያሰናዱን ያሉ ስለመሆናቸው ብዙዎቻችን ምስክርነት መስጠት እንችላለን፡፡ ኢንተርኔት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በየጊዜው በሚታዩት ለውጦችና መሻሻሎች ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ የሚመጣው ካለፈው የተሻለ እንደሚሆን ደግሞ ይታመናል፡፡

ዘላለም ተሾመ

አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You