
አዲስ አበባ፦ አስተዳደሩ ለመምህራን ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሠራ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ። የትምህርት ጥራትን የሚያስጠብቁ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተጠቆመ።
“ትውልድ በመምህራን ይቀረፃል፤ ሀገር በትምህርት ይበለጽጋል” በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ የነበረው የመምህራን ውይይት ትናንት ሲጠናቀቅ፤ ለመምህራኑ ጥያቄዎች መልስ የሰጡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ አስተዳደሩ ለመምህራን ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሠራ አመልክተዋል።
የተነሱ ጥያቄዎችም በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ በዘላቂነት መፍትሔ እንደሚያገኙ የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች፤ መንግሥት የመምህራንን አቅም ለማጎልበትና የትምህርት መሠረተ ልማትን ለመገንባት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል። የመምህራንን ፍላጎት በማሟላት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የመምህራንን ጥቅም ለማስጠበቅ እየሠራ መሆኑን፤ መምህራንና ቤተሰቦቻቸው በነጻ የሚታከሙበት ሆስፒታል ግንባታው በፍጥነት ተጠናቅቆ ወደ ሥራ እንዲገባ የሚደረገው ድጋፍም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ከእዚህ በፊት ለቤት ግንባታ የሚውል መሬትና የብድር አገልግሎት እንዲመቻች መምህራን ጥያቄ ማቅረባቸውን ያስታወሱት ከንቲባዋ፤ ይህን መነሻ በማድረግ ከንግድ ባንክ ጋር ሁለት ዓመት የፈጀ ድርድር ተደርጎ መምህራን 25 በመቶውን ቆጥበው 75 በመቶውን ብድር የሚያገኙበት እድል መመቻቸቱን አስታውቀዋል።
የመምህራንን የቤት አቅርቦት ችግር ለመፍታት በማህበር የማደራጀት ሥራ እየተሠራ ነው፤ እስካሁን ድረስ 350 ማህበራት ተደራጅተዋል። ሌሎችም በማህበር ተደራጅተው እድሉን መጠቀም እንዳለባቸውም ጠቁመዋል። መቆጥብ ለማይችሉትም ሌሎች አማራጮች እንደሚኖሩም አመልክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የመምህራንን የሙያ አቅም ለማጎልበት እየተሠራ ነው፤ ባለፉት ዓመታት ከአምስት ሺህ 500 በላይ መምህራን እንዲሠለጥኑ ተደርጓል፤ በቀጣይነትም የትምህርት ጥራትን የሚያስጠብቁ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
አስተዳደሩ መምህራን የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ አንዳንድ ጥያቄዎች ግን በሀገር አቀፍ ደረጃ የፖሊሲና የስትራቴጂ ማሻሻያ የሚፈልጉ እንደሆኑ አስታውቀዋል።
የውይይት መድረኩ፤ መምህራን ለሀገር ግንባታ ያላቸውን ታላቅ ሚና በመረዳት በሀገራዊ ጉዳዮች የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ፣ ከመምህራን የሚነሱ ጥያቄዎችን እና ሃሳቦችን በማዳመጥ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት የተዘጋጀ መሆኑ ተመላክቷል::
በመድረኩ መምህራንና ቤተሰቦቻቸው በነፃ የሚታከሙበት ሆስፒታል ግንባታንና የጤና መድህን አገልግሎት ፣ የቤት አበል ጭማሪና ጥቅማ ጥቅም፣ የቤት ባለቤትና የኑሮ ውድነትን የተመለከቱ ጥያቄዎችን ያነሱት መምህራኑ፤ በቅርቡ ይፋ የተደረገው የ25/75 የቤት መሥሪያ ፕሮግራምን ተግባራዊ ለማድረግ አቅማቸው እንደማይፈቅድም አንስተዋል።
መንግሥት የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የሚሠራቸው ሥራዎች የሚደነቁ መሆኑን አመልክተው፤ በኮሪዶር ልማት፣ በተማሪዎች ምገባና በሌሎች ዘርፎች ፈጣንና የከተማዋን ገጽታ የቀየሩ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ነው። የመምህራን ሆስፒታልም እንደሌሎች ፕሮጀክቶች በወቅቱ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ከተማ አስተዳደሩ ድጋፍና ክትትሉን እንዲቀጥል ጠይቀዋል። መምህራን ትውልድን የማነፅ፣ ሀገርን የመገንባት ሚናቸውን እንዲወጡ የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
መምህራኑ ከውይይቱ አስቀድሞ በአቃቂ ልህቀት ማዕከል፣ ኢንዱስትሪ ዞን ፣ ገላን ጉራ የመኖሪያ መንደር፣ ቡልቡላ ኢንዱስትሪ ፓርክ ፣ ለነገዋ የሴቶች ተሐድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከልና ብርሀን የዓይነ ስውራን አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ጎብኝተዋል።
በቀጣይነትም በሀገር አቀፍ ደረጃ የመምህራን ውይይት እንደሚካሄድ በእለቱ ተመላክቷል።
በፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 20 ቀን 2017 ዓ.ም