
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያን ጨምሮ በ47 አፍሪካ ሀገራት በበግና በፍየል ላይ የተከሰተውን “የፔስቴ ዴስ ፔቲትስ ሩሚናንት” በሽታን በዘላቂነት ከአህጉሪቱ ለማጥፋት እየተሠራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ የፔስቴ ዴስ ፔቲትስ ሩሚናንት እና ሌሎች ቅድሚያ የሚሰጣቸው ትንንሽ አደገኛ የእንስሳት በሽታዎች ከ55 የህብረቱ አባል ሀገራት በ47ቱ ተከስቷል። ይህን በሽታ ለመቆጣጠር እና ለማጥፋት አፋጣኝ ርምጃ ያስፈልጋል። የበሽታውን ክትባት ተደራሽ ለማድረግ ከአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ሚኒስትሮች ውይይት አድርገዋል። የፔስቴ ዴስ ፔቲትስ ሩሚናንት እና ሌሎች ቅድሚያ የሚሰጣቸው ትንንሽ አደገኛ በሽታዎችን ለማጥፋት በአፍሪካ ደረጃ ያሉ ሀገራት ተሳትፎና የተጠናከረ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸውም ተመክሯል።
በሽታው በጎች እና ፍየሎች ዕርባታ ላይ ጥገኛ በሆኑ ማህበረሰቦች ላይ ከባድ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንደሚያደርስ ገልጸው፤ በአፍሪካ ህብረት ዓለም አቀፍ የእንስሳት ሀብት ቢሮ የፓን አፍሪካ መርሃ-ግብር ማስጀመሪያም ይህንን ተላላፊ በሽታ ለማጥፋት፤ ክትባትን ማዳረስና ስጋትን ማስወገድ ላይ ያለመ ውይይት ስለመደረጉ አስረድተዋል።
የፕሮግራሙ ዋነኛ ዓላማም ውጤታማ የክትባት እና የቁጥጥር ስልቶችን ተግባራዊ ማድረግ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተጀመረው መርሃ-ግብር በአፍሪካ የከብት ርባታን ለመታደግ ብቻ ሳይሆን የማህበረሰቦችን በተለይም የሴቶች እና የወጣቶችን ሕይወት ለማሻሻል እንዲሁም የምግብ ዋስትናን እና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋትን ለመፍጠር፤ ብሎም ለዘላቂ የግብርና ልማት መንገድ ጠራጊ መሆኑን አመልክተዋል።
በሽታውን በማጥፋቱ ሂደትም እንደ የምግብ እና የግብርና ድርጅት እንዲሁም የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት ድጋፍ የሚያደርጉ መሆናቸው ተመላክቷል። ይህን ገዳይ በሽታ እ.አ.አ በ2030 ከአፍሪካ ለማጥፋት እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአፍሪካ ቤተሰቦችን ኑሮ ለመቀየር እንደታቀደ ሚኒስትር ዴኤታው ገልፀዋል።
የፔስቴ ዴስ ፔቲትስ ሩሚናንት ትንንሽ እንስሳትን እስከመግደል የሚደርስ በሽታ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህን ተላላፊ በሽታ በፍጥነት በማጥፋት የእንስሳትን ሕይወት መታደግ እንደሚያስፈልግ እና የብዙ አርብቶ አደሮችን ሕይወት መቀየር እንደሚገባ ተናግረዋል።
አፍሪካ ወደ አንድ ቢሊዮን የሚጠጉ በጎች እና ፍየሎች መኖሪያ ስትሆን ከዓለም አቀፉ አነስተኛ የከብት ርባታ 24 በመቶ በጎች እና 31 በመቶ ፍየሎችን ትይዛለች። በሽታውን ለመከላከል የሚያስችል ክትባት ለማሰራጨት አጠቃላይ የገንዘብ መጠን 526 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ሲሆን የአውሮፓ ህብረት በዝግጅት ደረጃ ለሚከናወኑ ሥራዎች 8 ሚሊዮን ዩሮ መመደቡንም ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰዋል።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 12 ቀን 2017 ዓ.ም