የግርዛት አስከፊ ገጽታ

‹‹ዓይኖቼ ተሸፍነው ነበር የተገረዝኩት። ካደኩ በኋላ በመሆኑ በመንፈራገጥ እንዳላስቸግራቸው ሁለት እጄን ወደ ኋላ ጠምዝዘው አስረውኝ ነበር። ሁለት ሴቶች ሁለት እግሮቼን ከፍተው ግራ እና ቀኝ በመወጠር ይዘውኛል። ህመሙ መፈጠሬን እንድጠላ አድርጎኛል፤ ምነው ሴት ሆኜ ባልተወልድኩም በማለት ፈጣሪን እንዳማርር አስገድዶኛል። ›› ሲሉ ከ30 ዓመት በፊት የነበረውን ስቃያቸውን ወደኋላ ተጉዘው ያስታውሳሉ ወይዘሮ መሠረት ዳኜ።

በዓለማችን በርካታ ሴቶች በንጽህና፤ ድንግልናን ለመጠበቅ፤ የትዳር አጋር ለማግኘት በሚፈጸምባቸው ግርዛት ምክንያት ተመሳሳይ ስቃይ እንደሚያስተናግዱ መረጃዎች ያመለክታሉ። ግርዛትን አስመልክቶ ከተባበሩት መንግሥታት ባሳለፍነው 2024 የወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ በዓለማችን ግርዛት በ24 ሀገራት ውስጥ በስፋት ይፈፀማል። ይሄውም በአፍሪካ፤ በመካከለኛው ምሥራቅ፤ በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በአውስትራሊያ ከሚፈፀምባቸው ውስጥ ይጠቀሳሉ።

“የሴት ልጅ ግርዛት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ኦርካይድ ፕሮጀክት ይፋ ባደረገው ጥናት እንደተመላከተው፤ ከ2016 ጀምሮ በኢትዮጵያ እስካሁን 33 ሚሊዮን ልጃገረዶች እና ሴቶች ለአደጋ ተጋላጭ ሆነዋል። ይህም በምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ውስጥ ትልቁ የልጃገረዶች እና ሴቶች ቁጥር ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከኢንዶኔዥያ እና ግብፅ ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የሴት ልጅ ግርዛት በኢትዮጵያም በስፋት ይፈፀማል። በዚህ ቁጥራቸው በሚሊዮን የሚገመት ሴቶች መሪር ስቃይ ሲያሳልፉ ቆይተዋል። አሁንም እያሳለፉ ይገኛሉ። ወይዘሮ መሠረት አንዷ የግርዛት አስከፊ ገጽታ ማሳያ መሆናቸውን ይናገራሉ። ከተማ ተወልደው በማደጋቸው እስከ ዘጠኝ ዓመት ሳይገረዙ ቆይተዋል። እናታቸው ከባለቤታቸው ተፋትተው ገጠር ወደሚኖሩት አያታቸው ቤት በሄዱበት አጋጣሚ ነው የመገረዝ እዳ የወደቀባቸው። አያታቸው እስከዚያ ዕድሜ አለመገረዛቸውን ሲሰሙ ጎረቤት እንዲሰማባቸው አልፈለጉም። እናታቸውን መሳቂያ እንዳታደርጊኝ አሏቸው።

አያታቸው “ያልተገረዘች ሴት ዕቃ ትሰብራለች፤ ትባልጋለች፤ የትዳር አጋር አታገኝም፤ ግርዛት ንጹህ የሚያደርግ፤ የሁሉም ሴት ልጅ ግዴታና ባሕልም ነው” በማለት እናታቸውን ገፋፍተው ግርዛቱ መፈጸሙን ይናገራሉ።

ወይዘሮዋ መሠረት በግርዛቱ የብልታቸው የውስጠኛው ከንፈር ሙሉ በሙሉ ስለመወገዱም ያነሳሉ። በዚህ ምክንያት በወቅቱ ሰውነታቸው በከፍተኛ ደረጃ ለኢንፌክሽን መጋለጡንም ይጠቅሳሉ። ለኢንፌክሽን በመጋላጣቸው እንደ ልብ ለመፀዳዳት፣ ቁጭ ለማለት እና ለመቆም ካለመቻላቸው ባሻገር ሆስፒታል የሚመላለሱት ታዝለው እንደነበርም ይገልፃሉ። “የወር አበባ ማየት ከጀመርኩ በኋላ እቸገር ነበር “ይላሉ።

ሌላዋ የግርዛትን ስቃይ ያስተናገደችው ደግሞ በአፋር ክልል ፈንታሌ ወረዳ ሳቡሬ ቀበሌ ነዋሪ የሆነችው አፍራን መህዲን ናት። በእርሷ ላይ የተፈፀመው ግርዛት ለየት ያለና ብርቱ ስቃይ የበዛበት እንደነበር ታስታውሳለች። በግርዛቱ የብልቷ ክንፈሮች ሙሉ በሙሉ ተቆርጠዋል። ተገጥሞም ተሰፍቷል።

አሁን ላይ አግብታ በትዳር ውስጥ ብትሆንም ስቃዩ ዛሬ ድረስ አልተዋትም። የግብረ ሥጋ ግንኙነት በምትፈጽምበት ወቅት ስለሚያማት ግንኙነቱን እንድትፈራው አድርጓታል። በዚህም ምክንያት በትዳሯም ደስተኛ አለመሆኗን ትናገራለች።

እ.አ.አ በ2008 በተደረገው የክትትል ዳሰሳ ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ ከ140 በላይ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አሉ። በሴቶች እና ሕፃናት ላይ ከፍተኛ ስቃይ የሚያደርሰው ግርዛት ከእነዚህ አንዱ መሆኑን በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች መብት ጥበቃና ምላሽ መስጠት መሪ ሥራ አስፈፃሚ የሴቶች መብት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ጌትነት አበብል ይጠቅሳሉ።

የሴት ልጅ ግርዛት የአንዲትን ሴት ልጅ የወሲብ ስሜት ሰጪ አካሏን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ መቁረጥ ነው። ይህንን የሚያከናውኑት ሰዎች የሕክምና ክህሎት የሌላቸውና በዘልማድ በድርጊቱ የተሠማሩ ናቸው። የሴት ልጅ ግርዛት አሁን ያለበት ደረጃ አስመልክተውም የሥነ-ሕዝብና የጤና ዳሰሳ ጥናት ዋቢ አድርገው ይናገራሉ። ከ15 እስከ 49 ዓመት ከሆናቸውና የሴት ልጅ ግርዛት እንደ ተፈጸመባቸው ሪፖርት ከተደረጉት ኢትዮጵያውያን ሴቶች መካከል 73በመቶ የሚሆኑት አካላቸው ተቆርጦ ተወግዷል። ሁለት ነጥብ ስድስት በመቶ ያህሉ፤ የተቆረጡ ሲሆን፣ ነገር ግን ሥጋቸው አልተወገደም። ስድስት ነጥብ አምስት በመቶው ተሰፍተዋል። 17 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ምን ዓይነት የሴት ልጅ ግርዛት እንደተፈፀመባቸው አያውቁም።

በሶማሌ ክልል 75 ነጥብ 6 የተሰፉ ሴቶች እና ልጃገረዶች፤ ከአፋር 71 በመቶ የተወሰኑ ቢሆኑም ከተለያዩ ብሔረሰቦች የተውጣጡ የተሰፉበት መኖሩን መረጃው ማመላከቱን ያነሳሉ ከፍተኛ ባለሙያው። እነዚህ ሴቶች ከ15 እስከ 49 ዓመት እድሜ ያላቸው መሆናቸውንም ያክላሉ።

ሙስሊም ሴቶች ከሌላ እምነት ተከታዮች በበለጠ የመገረዝ እድላቸው ሰፊ ስለመሆኑም አልሸሸጉም ከፍተኛ ባለሙያው።

እንደሳቸው በኢትዮጵያ በ2000 ዓ.ም ግርዛት ምጣኔው 79 ነጥብ 9 በመቶ ነበር። በ2005 ደግሞ 74 ነጥብ 3 ሲሆን ባሳለፍነው 2016 ዓ.ም 65 በመቶ ነበር። ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች ሆኖ የተገረዙ ሴቶች ቁጥር 14 ነጥብ 9 በመቶ ሲሆን እስከ 15 ዓመት ድረስ በዚሁ ዓመት የተገረዙት 58 በመቶ ናቸው። የነበረ መሆኑን መረጃው ያመለክታል።

በኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው የግርዛት ሂደት የሚከናወነው አምስት ዓመት ሳይሞላቸው ነው፤ ነገር ግን አንድ አምስተኛ የሚሆነው ከአምስት እስከ ዘጠኝ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፤ ይሁን እንጂ ይህ እንደ የሃይማኖቶች የመኖሪያ አካባቢዎች እና ጎሳዎች ይለያያል ይላሉ።

እንደሚሉት በትግራይ፣ አፋር እና አማራ ያሉ ሴት ልጆች ከተወለዱ ብዙም ሳይቆዩ ነው ለዚህ የግርዛት አደጋ ተጋላጭ የሚሆኑት። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ልጃገረዶች እስከ አንድ ዓመት ድረስ ለግርዛት አደጋ የተጋለጡ ናቸው።

በተለይ በዚህ በኩል ለውጥ ለማምጣት በነፍሰ ጡር ሴቶች እና ገና እርጉዝ ባልሆኑ ወጣቶች ላይ ያነጣጠረ ሥራ እየተሠራ ስለመሆኑም ያነሳሉ።

በኦሮሚያ ያሉ ልጃገረዶች ከተወለዱ ጀምሮ እስከ 11ኛ ዓመት ዕድሜያቸው ድረስ ለግርዛት አደጋ የተጋለጡ ስለመሆናቸውም ያስረዳሉ። በድሬዳዋ በተመሳሳይ ሴት ልጆች ከተወለዱ ጀምሮ እስከ አሥር ዓመት ዕድሜያቸው ድረስ ለግርዛት ለአደጋ የተጋለጡ እንደሆኑም ይጠቅሳሉ።

በጋምቤላ ልጃገረዶች ለግርዛት አደጋ የተጋለጡት ገና አምስት ዓመት ሳይሞላቸው ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ደግሞ አራት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ስለመሆኑም ያብራራሉ ከፍተኛ ባለሙያው። በሶማሌ ክልል ልጃገረዶች ከስምንት እስከ አሥር ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ እና በሐረሪ ከሰባት እስከ አሥር ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ለግርዛት በጣም የተጋለጡ ስለመሆናቸውም ይናገራሉ።

ከፍተኛ ባለሙያው አቶ ጌትነት የዚህን አስከፊ ጥቃት ፈፃሚዎች ሁኔታ አስመልክተውም እንደሚናገሩት እድሜያቸው ከ0 እስከ 14 የሆኑ ኢትዮጵያውያን ልጃገረዶች ለአብነትም የሴት ልጅ ግርዛት ከተፈጸመባቸው 95 ነጥብ 3 በመቶው የተገረዙት በባሕላዊ ገራዦች ነው። ነገር ግን አልፎ አልፎ በልምድ አዋላጆች ለምሳሌ 2ነጥብ 2በመቶ፤ በሕክምና ባለሙያዎች ደግሞ 1ነጥብ 9በመቶ ነው ግርዛት ተፈጽሟል።

በሕክምና ተቋማት ይደረግ የነበረው የሴት ልጅ ግርዛት በኢትዮጵያ መንግሥት በ1999 ዓ.ም መታገዱንም ያስታውሳሉ። ግርዛትን የሚፈጽሙ የሕክምና ባለሙያዎች ህጋዊ ርምጃ እንዲወሰድባቸው የተደረገበት ሁኔታ ስለመኖሩም ያነሳሉ። ነገር ግን በደቡብ ክልል ግርዛት ከተፈጸመ ባቸው ሴቶች መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት የሴት ልጅ ግርዛት የተከናወነው በጤና ባለሙያዎች ነው የሚሉት ባለሙያው ይህም ከሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ልዩነት ያለው ስለመሆኑ አልሸሸጉም።

የሴት ልጅ ግርዛት አስከፊነትን አስመልክቶ መረጃው ይፋ ያደረገው የዳሰሳ ጥናት መካተቱንም ያብራራሉ። እንደሳቸው ማብራሪያ የሴትን ልጅ ግርዛት አስከፊነት የሰሙ 17 ነጥብ 5 በመቶ ሴቶች እና 11ነጥብ 1 በመቶ ከ15 እስከ 49 ዓመት እድሜ ያላቸው ወንዶች ናቸው። ወንዶች ድርጊቱ መቀጠል እንዳለበት የሚያምኑ መሆናቸውን ስለመጥቀሱም ይገልፃሉ። 79 ነጥብ 3 በመቶው ሴቶች እና 86 ነጥብ 7 በመቶ ወንዶች ደግሞ መቀጠል እንደሌለበት ያምናሉ ይላሉ። ከ15 እስከ 49 ዓመት የሆናቸው 23 ነጥብ 6 በመቶ ሴቶች እና 16 ነጥብ 8 በመቶ ወንዶች ግርዛት የሃይማኖታቸው መስፈርት እንደሆነ አድርገው ያምናሉ። ይህ እምነት በሙስሊም ወንዶችና ሴቶች ዘንድ በብዛት እንደሚታይ ይገልጻሉ።

የሴት ልጅ ግርዛት እንዲፈጸም ጠንካራ ድጋፍ የሚያደርጉት የአፋር፣ የሶማሌ እና የሲዳማ ሴቶች እና የአፋር፣ የሶማሌ እና የአማራ ወንዶች መሆናቸውን ሳያክሉ አላለፉም።

በተደረጉ አነስተኛ ጥናቶች ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በቀጥታ ሲጠየቁ ለግርዛት የሚሰጡት ድጋፍ ዝቅተኛ መሆኑን ይናገራሉ። በተዘዋዋሪ ሲጠየቁ ግን የድጋፉ መጠን በላቀ ደረጃ ከፍ ያለ መሆኑን እንደሚያሳይም ያስረዳሉ።

እንደዚህ ያለው ጥንቃቄ የሚፈልግ፣ ሚስጥራዊነትን የተላበሰ እና በማኅበረሰቡ ዘንድ በግልጽ ለማውራት ያልተፈቀዱ ጉዳዮች በሚመረምሩበት ጊዜ የተሻሻሉ የዳሰሳ ጥናት ዘዴዎች አስፈላጊ ይሆናል።

በሀገሪቱ ውስጥ ባሉ ግርዛት በሚካሄድባቸው ቦታዎች ተግባራዊ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው። በአብዛኛዎቹ ጉዳዮች ላይ የድርጊቱ ጠንከር ያሉ አራማጆች ባሕላዊ ልምምዶች ናቸውና ተቀናጅቶ በመሥራት ጭምር ትኩረት መደረግ አለበት። ሃይማኖታዊ ሥርዓት በሚካሄድባቸው ቦታዎች ላይ ለማስተማር እና አመለካከትን ለመቀየር የሃይማኖት አባቶችን ማሳተፍ ወሳኝነት አለው።

የሴት ልጅ ግርዛት ለማስወገድ የአምስት ዓመት የድርጊት መርሐ ግብር ፍኖተ ካርታ ወጥቷል። ፍኖተ ካርታውን ለማስፈፀም በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራ (National alliance to end FGM and CM ) ተቋቁሞ እየተሠራ ይገኛል።

ፍኖተ ካርታው ባለፉት ስድስት ወራት ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤና ንቅናቄ ሥራዎች እንዲሠሩ አግዟል። እንደ ተባበሩት መንግሥታት ተቋማት ተቀናጅቶ ለመሥራት ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብር እንዲኖር አስችሏል። የሀብት፣ የጊዜና የጉልበት ብክነትን ቀንሷል።

“በቅርቡ የፍኖተ ካርታ አፈፃፀሙን ለመገምገም ዕቅድ ይዘናል” ያሉት ባለሙያው ኮቪድ 19ን ጨምሮ ስር የሰደደ እና ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው የሚመሰል የአመለካከት ችግር፤ የግንዛቤ እጥረት፤ በቂ የሰው ኃይልና፤ የበጀት እጥረት በፍኖተ ካርታው አፈፃፀም የገጠሙ ብርቱ ተግዳሮቶች ስለመሆናቸውም ሳያነሱ አላለፉም።

በኢትዮጵያ ግርዛትን ለማስወገድ የሚደረግ የትኛውም እንቅስቃሴ በሕግ የተደገፈ ነው። የሴት ልጅ ግርዛት እና ተያያዥ ድርጊቶች በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ፣ አንቀጽ 565 እና አንቀጽ 566 መሠረት የሚያስቀጡ ናቸው። በኢትዮጵያ በሕገ መንግሥት እና ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አሉ። ሆኖም እነዚህን ሕጎች የሚተላለፉ የግርዛት ተግባራት በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈፀሙ ይገኛሉ። አሁን ባለው ሁኔታ ከኢትዮጵያ ግርዛትን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት ባይቻልም እየቀነሰ እንዲመጣ ማድረግ ተችሏል።

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You