«ሕግን ያወጣው የሰው ልጅ ነው፤ እኔ የማጠናው ሰውን ራሱን ነው»  -ጋሽ ፍሬው ከፍያለው የሥነ ልቦና ምሁር

ባለፉት አራት ዓመታት በፓርኮችና መዝናኛ ስፍራዎች አላግባብ የተጣሉ ፕላስቲክ ቆሻሻዎችን በበጎ ፍቃደኝነት ሲያነሳና እንዳይጣሉ ሲያስተምር ብዙዎች ያውቁታል። ከልጆቹ ጋር የጀመረው ይህ በጎ ምግባርፕሎጊንግ ኢትዮጵያበሚል ስያሜ የተሰባሰቡ በሺዎች የሚቆጠሩ አባላቶችን አፍርቷል።

በአሜሪካን ሀገር በሚገኝ ፊውቸር ጀነሬሽን ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ የጥናት ፕሮፌሰር ነው። በአዲስ አበባና በባህርዳር ዩኒቨርሲቲዎች በተጨማሪ ወይም መደበኛ ባልሆነ ቅጥር ልምድና እውቀቱን በበጎ ፍቃድ ያገለግላል።

ስለ ሙያው ሲጠየቅ «የሳይኮሎጂ ተማሪ ነኝ» ቢልም ላለፉት 37 ዓመታት የሙያና የሥራ ልምዶች የሥነ ልቦና ምሁርነቱን ያሳያሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪውን አግኝቷል። በአየር ላንድ የፒኤች ትምህርት በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ኮርክ (UCC) ለአራት ዓመታት ተከታትሏል (ለመመረቅ ጥቂት ሲቀረው በግል ፍላጎት ምክንያት አልጨረሰውም) በኦርጋናይዜሽናል ዴቨሎፕመንት ዓለም አቀፍ አማካሪ ሆኖ ያገለግላል።

ላለፉት በርካታ ዓመታት በተለያየ የሥራ ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ ቆይቷል። 1979 . አንስቶ ከስነ ልቦና አማካሪነት እና መምህርነት እስከ ምግብ ዋስትና፣ ከአደጋ ቅነሳ እስከ ሰላም ግንባታ፣ የሕፃናት መብትና ሌሎች ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸው ሰፋፊ ፕሮግራሞችን በመቅረፅና በመምራት የራሱን አሻራ አሳርፏል። ይህ ሰው የዛሬው የሕይወት ገፅታ እንግዳችን ጋሽ ፍሬው ከፍያለው ነው።

የዝግጅት ክፍላችን (በእንግዳችን ጥያቄ መሠረት) ለጭውውታችን እንዲያመች ጋሽ ፍሬው የሚለውን መጠሪያ ይጠቀማል። መልካም ቆይታ!

ትውልድና እድገት

ጋሽ ፍሬው የተወለደው በ1957 ዓ.ም በጎጃም ሞጣ አውራጃ አንጎት ቀበሌ ነው። በልጅነቱ ነገሮችን የማወቅ ታላቅ ጉጉት ያለውና ብሩህ አዕምሮን ከታደሉ ጥቂት ታዳጊዎች መካከል ነበር። የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን መፈታታት የሚወድ ‹‹ከውስጡ ምን አለ፤ እንዴትስ ነው የሚሠራው?›› በሚል የሚጠይቅና የሚመራመር፣ ለእውቀትና አዲስ ነገር ክፍት አዕምሮ የነበረው እረፍት አልባ ነበር። ይህ ለእውቀት የመጓጓት ፍላጎት ዛሬ ለገነባው የላቀ ስብእናና ለደረሰበት ስኬት እንደ መሠረት ይቆጥረዋል።

‹‹በጊዜው ፈጣን ጭንቅላት ነበረኝ። በቄስ ትምህርት ቤት መልዕክተ ዩሐንስና ወንጌልን እንደጨረስኩ አባቴ የቀለም ትምህርት እንድማር ወደ አዲስ አበባ ይዞኝ መጣ›› የሚለው ጋሽ ፍሬው፤ በጎጃም አንጎት በነበሩበት ወቅት አባቱ በጊዜው የፖለቲካ ትኩሳት ለእስር ተዳርገው እንደነበር ይናገራል። ከትውልድ አካባቢያቸው ለመልቀቃቸው ምክንያት የእርሳቸው ከእስር መፈታት ነበር።

የአባቱን መታሰር ምክንያት ከብዙ ዓመታት በኋላ በአንድ ወዳጁ አማካኝነት አውቆ እናቱን የሻሽወርቅ ብርሀኑን ለምን እንዳልነገሩት ሲጠይቅ ‹‹ቂም ቁምነገር ተብሎ አይነገርም›› በሚል ነበር ምላሽ የሰጡት። በጊዜው ገና በ16 ዓመታቸው አራስ ልጃቸውን ይዘው ብዙ መከራን ቢገፉም ለልጃቸው ግን ቂምን ለማውረስ አልወደዱም ነበር። የእናቱ ብልሀት በልጅነት በአባቱ ላይ የደረሰው ኢ-ፍትሐዊነትን እያብሰለሰለ እንዳያድግ አድርጎታል።

የቤተሰቡ የሥራ ፀባይና የወቅቱ ሁኔታ የልጅነት ጊዜውን በተለያዩ ቦታዎች እንዲያሳልፍ አድርጎታል። ከእነዚህ ውስጥ ምእራብ ሸዋ (አዲስ አለም)ና አቃቂ በሰቃ ይቀኙበታል። አስኳላን አሀዱ ያለው በአዲስ አበባ አጋፋሪ መኮንን ተሰማ ትምህርት ቤት ነበር። መንፈሳዊ ፍላጎቱ እና እውቀቱ ከትምህርት ቤቱ ጀርባ በሚገኘው ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ያጣጥም ነበር።

ጋሽ ፍሬው ለሃይማኖቱ ቀናኢ የሆነና ለማህበረሰብ ባህልና ወግ በጎ ምልከታ ያለው ሰው ነው። ገና በታዳጊነቱ በቄስ ትምህርት ፈጣን አቀባበል ከነበራቸው ጥቂት ልጆች የሚመደብ ነበር። ፈጣን አዋቂነቱ ለማይሸረሸር ስብእናው ግንባታ ረድቶታል። የልጅነት ጊዜውን መለስ ብሎ እያስታወሰ አባቱ አቶ ከፍያለው መኮንን ‹‹ትንሽ ከቆየና ዝም ካልነው የቤተክርስቲያን አገልጋይ ሆኖ መቅረቱ ነው›› ብለው በቀልድ አዋዝተው ወደ መደበኛ ትምህርት ቤት እንደሰደዱት በፈገግታ ተሞልቶ ይናገራል።

በአዲስ አበባ ጣፋጭ የልጅነት ጊዜን አሳልፏል፤ የወቅቱን የከተማዋን ንፁህ አየር እየማገ ለጥቂት ጊዜያትም ቆይቷል። ሆኖም እናቱ የሻሽወርቅ ከትውልድ ቀያቸው ወጥተው መቅረትን ባለመፈለጋቸው ምክንያት ዳግም ወደ ጎጃም፤ ሞጣ አውራጃ ተመለሱ። የጋሽ ፍሬው አብዛኛውን የትምህርትና የልጅነት ጊዜ በዚያ ሊሆን የግድ አለ።

ፈጣኑና ባለ ብሩህ አዕምሮ ባለቤቱ ጋሽ ፍሬው የከተማን ለዛ ከገጠሩ አዋህዶ፣ ከወዳጅ ዘመዶቹ ፍቅርን ተቋድሶ እስከ ስድስተኛ ክፍል ዘለቀ። በገጠሩ ለዛና ወግ፣ ጨዋታ አዋቂነትና ፈሪሀ እግዚአብሔር ስብእናው ታነፀ። ይህ ፍቅር ታዳጊውን በሁለት በኩል የተሳለ ቢላዋ አደረገው። ፈጣን አዕምሮ በርከት ካለ መክሊት ጋር አደለው።

ትምህርትና ንባብ

አቶ ከፍያለውና ባለቤታቸው የ12 ዓመት ታዳጊ ልጃቸውን ይዘው በዝውውር አገው ምድር አውራጃ ዳንግላ ከተማ ከተሙ፤ ጊዜው 1968-69 ዓ.ም አካባቢ ነበር። ጋሽ ፍሬው ገና በልጅነት አዕምሮው የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ንባብ እና ተሳትፎን የጀመረበት ወቅት ነበር ። በጊዜው ዳንግላ ለከተሜ ምቹ ባህሪን ከተላበሱት አካባቢዎች ቀዳሚዋ ነበረች። አጋጣሚው ከእርሱ ንቃትና ፍጥነት ጋር ተዳብሎ ወደ ፖለቲካ ተሳትፎና ንባብ አስገብቶት ነበር።

ለብዙ ነገሮች ተምሳሌት የሆኑት አባቱ ስል አዕምሮ እንዲኖረውና አንባቢ እንዲሆን አድርገውታል። ገና በታዳጊነቱ በጊዜው የብዙዎችን ቀልብ የገዙ የነበሩትን የእነ አቤ ጉበኛው አልወለድም፣ መልክዓ ሰይፈ ነበልባል፣ ሳይኮሎጂ ቱደይ (የእንግሊዘኛ መጽሔት) እንዲሁም የመከራ ጤዛ (በገለታ ገመቹ) የመሳሰሉ መጻሕፍት አንብቧል። በጊዜው ከአባቱ ተደብቆ ያነበበ ይምሰለው እንጂ እርሳቸው ግን እያንዳንዱን እንቅስቃሴውን ይከታተሉ ነበር። ይህንን (ሲከለክሉትና ሲደብቁበት ተደብቆ እንደሚያነብ መረዳታቸው) ዘዴ እንደተጠቀሙ የተረዳው ከብዙ ዓመታት በኋላ አባትና ልጅ በነበራቸው ወግ ነበር። ንባቡ ታዲያ የደረጃ ተማሪ እንዲሆን፣ በሂሳብ ትምህርት እንዲልቅ ትልቅ ድርሻ ነበረው።

የአባቱን በጎ ተፅእኖ አውርቶ የማይጠግበው ጋሽ ፍሬው ‹‹አንደኛ ወጥቼ እሸለማለሁ ብዬ በተገላቢጦሽ ተገርፌያለሁ። አባቴ ኃይለኛና ኮስታራ ነበር። ከክፍል አንደኛ ወጥቼ ሰርተፍኬቴ ላይ 5 ቀን ቀርቷል ተብሎ መጻፉ የመገረፌ ምክንያት ነበር›› በማለት በጊዜው በቀላሉ የማይረኩና በሁሉም ነገር ብቁ እንዲሆን የሚሹ እንደነበሩ ይናገራል። የአባቱ ኮስታራና ቁጡነት ጭርሱኑ እንዳያስደነግጠውና ከመስመር እንዳያወጣው የእናቱ ሩህሩህነት፣ ጊዜ መስጠት፣ ማበረታታት የህይወት ሚዛኑ እንዲጠበቅ መሠረት መሆኑን ያነሳል።

ጋሽ ፍሬው ሁለንተናዊ እውቀትና መረዳትን ገንዘቡ ያደረገው ገና በታዳጊነቱ ነው። ሰዓሊነት፣ ሙዚቃ፣ እንጨት ስራ፣ ጥልቅ ንባብ፣ የቆዳ ሥራ እና ሌሎች የእጅ ሥራ ውጤቶችን ጨምሮ ጠንካራ የሥራ ባህል እንዲኖረው እናትና አባቱ ከግራና ቀኝ ሚዛኑን ጠብቆ እንዲያድግ ምክንያት ሆነውታል።

ከእድሜው የቀደመ መሆኑና ለንባብ መሰጠቱ ግን ብስለትን ብቻ ሳይሆን ጉሸማንም አድርሶበታል። ገና በታዳጊነቱ የፖለቲካ ተሳታፊ መሆኑ ለእስር ዳርጎታል። የአፍላነት እድሜውን ጠንከር ባሉ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ንባቦችና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ላይ ማድረጉ ዙሪያ ገባውን ጠንቅቆ እንዲረዳና ያለ እድሜው እንዲበስል ምክንያት ነበር። በዚህ ሂደት አልፎ ነው በዳንግላ እስከ 12ተኛ ክፍል ያለውን ትምህርቱን ያጠናቀቀው፤ ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመግባቱ በፊት መሠረተ ትምህርት ዘመቻ ያቀናው።

መሠረተ ትምህርትአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

የጋፈራ ቀበሌ (አዲስ ቅዳም ከተማ አቅራቢያ) ጎረምሳውን ጋሽ ፍሬውን እጆቿን ዘርግታ ተቀበለች። በአፍላነቱ የገበየውን እውቀትና ጉልበቱን ሳይሰስት ለመስጠት ጓዙን ጠቅልሎ መሠረተ ትምህርት ዘመቻ በጋፈራ ከተመ። በውስጡ ገበሬው መማር አለበት፣ ንፅህናውንና አካባቢውን መጠበቅ አለበት፣ ደኖችን መትከልና መሠረተ ልማት መሥራት መማር ይኖርበታል የሚል ቁጭት ተወለደ። ወጣትነቱ፣ ንባቡና የፖለቲካ ትኩሳቱ በጊዜው ለነበረው የተነቃቃ ስሜት ምክንያት ሆነው። በአካባቢው ደኖች በመትከል፣ ኅብረተሰብን በማንቀሳቀስና ራስን በመምራት የተሳካ ጊዜ አሳለፈ። ለአራት ወራት በዚህ ተግባር ቆይቶ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ገባ። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋሽ ፍሬው ሌላ የሕይወት ክፍል የተገለጠበት ምዕራፍ ሆነ።

ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት እንዳመጣ በታዳጊው ፍሬው አዕምሮ ውስጥ የስሜት መደበላለቅ ተፈጥሮ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ለዩኒቨርሲቲ የነበረው ከፍ ያለ ግምትና ፍራቻ ነበር። በወቅቱ ጋወን የለበሱ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ትላልቅ መጻሕፍት ቤቶች እና ብዛት ያላቸው ተማሪዎች በአንድ ስፍራ መገኘታቸው የፍርሀት ምንጩ ነበሩ። በዚህ ምክንያት ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት እንዳመጣ ቤተሰቦቹን አለማሳወቅ ድረስ የዘለቀ ትኩረት ማጣት ውስጥ ገብቶ ነበር። በተለይ በወቅቱ ለተማረ ሰውና ለመምህራን ይሰጥ የነበረው ክብርና ግምት በተወሰነ መልኩ ጫና ፈጥሮበት ነበር። ይህ እሳቤው ግን ብዙም ሳይቆይ ነበር ከውስጡ የጠፋው።

ጋሽ ፍሬው ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲገባ በጊዜው ከተለመደው የፀጉር ቁርጥ (ጆንትራ ቮልታ) ፋሽን እና የአለባበስ ቅንጦት ተለይቶ ነው። ቁምጣና በረባሶ አድርጎ፤ ኮራ ብሎ ደረቱን ነፍቶ ነው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ወጣቱ በምእራባዊያን ፋሽን እና

 

ከሀገር ባህል አለባበስ አፈንግጠው መታየታቸው (በድህነት ውስጥ ያሉ ቤተሰቦቻቸውን አስጨንቀው ማጌጣቸው) ለእርሱ አስደሳች ስላልነበር ነበር። በመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ወቅት ሙሉ ልብስ ቢኖረውም የእርሱ ምርጫ ግን ባለ ቁልፉን ቁምጣና ሸሚዝ በበረባሶ አድርጎ ወደ ዩኒቨርሲቲ መዝለቅ ነበር።

አፈንጋጭነቱ እና በጊዜው ለነበረው ፋሽን ጀርባ መስጠቱ በግቢው ማህበረሰብ ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ ያደረገ ነበር። በድርጊቱ የሚስቅ፣ እንደ አላዋቂ የሚቆጥረውና የሚያሾፍ ቢኖርም እርሱ ግን በውሳኔው ፀንቶ በማንነቱ ኮርቶ ይንቀሳቀስ ነበር። ‹‹አንዳንዱ ድርጊቴን ተመልክቶ አብረን ተፈትነን ባለፍነው እንግሊዘኛ ሊተርበኝ ይሞክራል›› ይላል የጉዳዩን አዝናኝ ጎን መለስ ብሎ እያስታወሰ።

በዩኒቨርሲቲው ያገኘው እውቀት የጠበቀውን እና የተጨነቀበትን ያክል አልሆነለትም። ‹‹ዩኒቨርሲቲ ፈትቶ የሚገጥመኝ፤ አዲስ ነገር የሚያሳውቀኝ ነበር የመሰለኝ›› ይላል ጋሽ ፍሬው፤ ሁኔታው በተቃራኒው ሆኖ በእጅጉ ቀሎት እንደነበር ሲናገር። 11ኛ እና 12ተኛ ላይ የተማረውን መልሶ ሲያገኘው የጠበቀው ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆነበት። አንዳንዱም ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል በንባብ የሚያውቀው ነበር። ሁኔታው ይበልጥ ትኩረቱን ወደ ሌላ ነገር እንዲያደርግ አደረገው። ወደ ከተማ መውጣትና አካባቢውን መቃኘት፤ አዳዲስ ነገሮችን መሞከር ልማዱ ሆነ። ቀለል ባለ ንባብ ፈተናውን በማለፍ ሳይኮሎጂ ዲፓርትመንት ተቀላቀለ። ከ40 ተማሪዎች ውስጥ የሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍልን በፍላጎት ከእርሱ ውጪ የመረጠ አልነበረም። አባቱ በጻፉለት ደብዳቤ ሕግን እንዲያጠና ፍላጎት እንዳላቸው፤ ምርጫው ግን የእርሱ መሆኑን ገልጸውለት ነበር። እርሱም ውስጡን በማዳመጡ ‹‹ሕግን ያወጣው የሰው ልጅ ነው፤ እኔ የማጠናው ሰውን ራሱን ነው›› የሚል ጠንካራ አቋም በመያዝ ወደ ትምህርት ክፍሉ ተቀላቀለ።

ትኩስ ጉልበትከአስመራ

እስከ ዩኤስ

ጋሽ ፍሬው ለራሱ ቃል በገባው መሰረት በአቋሙ ፀንቶ የሰውን ልጆች በጥልቀት የሚያጠናውን የሳይኮሎጂ ሳይንስ ለሦስት ዓመታት ተከታትሎ በድል አጠናቀቀ። የወዳጅ ዘመዶቹ ‹‹ሥራ አታገኝበትም ይቅርብህ›› የሚል ማስፈራሪያን፤ የአባቱ ‹‹ሕግ ብታጠና ምርጫዬ ነው›› የሚሉ ጉትጎታዎችን ወደጎን ትቶ ህልሙን ማሳካት ቻለ። ማስፈራሪያውን ከቁብ ያላስገባው የያኔው ተማሪ እንደተመረቀ ማእከላዊ ፕላን ስሙ ተልኮ እንደሌሎቹ ተመራቂዎች በምደባ የመምህርነት ሥራ ቀይባሕር በሚባል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ (Guidance and Coun­seling) አገኘ፤ ቦታው በቀድሞው የኢትዮጵያ ግዛት ስር በነበረችው ኤርትራ አስመራ ከተማ ነበር።

ከንባብና ከትምህርት ያገኘውን ዕውቀት ተግባር ላይ የሚያውልበት ጊዜ አሁን ነው። በኤርትራ-አስመራ የሚያውቀው ሰው አልነበረም። እንደቀድሞው የቤተሰብ ድጎማ የማይታሰብ ነው። በከተማው ኑሮ ውድ ነው፤ መኖሪያ ቤት ማግኘትም አይታሰብም። በመሆኑም ከዚህ ፈተና ጋር ተጋፍጦ ራሱን ማሸነፍና ሕይወቱን መምራት መጀመር አለበት።

በአስመራ ከተማ በሥራ የቆየባቸውን አራት ዓመታት ‹‹ወርቃማ ጊዜያት›› ይላቸዋል። ተማሪዎች ትምህርታቸውን የሚያውክ የሥነ ልቦና ችግር ሲያጋጥማቸው ከጎናቸው ሆኖ በሙያ ከማገዝ ባሻገር በቆይታው ገንዘብ አጠቃቀም፣ ራስን መግዛት እና ሙያው የሚጠይቀውን እውቀት ተግባር ላይ የማዋል ጥረት ወደ መሬት ማውረድ የቻለው በዚያ ነበር።

አብዛኛውን ጊዜውን በማንበብ ያሳልፋል፤ አልፎ አልፎ ጥናትና ምርምሮችን ይጽፋል። እውቀቱን በተመደበበት ሙያ በትክክል መተግበሩ ደግሞ ደጋግሞ ያረጋግጣል። ከዚህ የተነሳ ‹‹በአስመራ የሕይወትን ሀሁ የቆጠርኩበት፤ ማህበራዊ ሕይወትን ያጣጣምኩበትና ገንዘብ አጠቃቀም የተማርኩበት›› ነው ይላል።

በአስመራ ከተማ ቃኘው ጦር ሰፈር ውስጥ የሚኖሩ ፀሀይነሽ ቸኮልና ባሻ ታከለ ዳኘው (አሁን በሕይወት የሌሉ) የሚባሉ በጎ ኢትዮጵያውያን ማረፊያ አመቻችተውለት ነበር። እነዚህን ባለውለታዎቹን ዛሬም ድረስ ያመሰግናቸዋል። ከእነርሱ ጋር ከሁለት ዓመት ከመንፈቅ በላይ በፍቅርና በመተሳሰብ ቤተሰባዊ ጊዜን ልክ እንደ ልጅ አሳልፏል።

የያኔዋ የኢትዮጵያ ግዛት አስመራ ጋሽ ፍሬውን ብስለት አስተምራ፤ ራስን መምራትና ለሙያ መሰጠትን አስታጥቃ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት ላከችው። በዚያ ለአራት ዓመታት ቆይታ አድርጎ አጠናቀቀ። የማስተርስ ዲግሪውን እንደያዘ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ኮርክ (UCC) በኢትዮጵያ በነበረው ቢሮ ውስጥ ተቀጠረ፤ በኋላም ዳይሬክተር ሆኖ መሥራት ጀመረ። የፒኤች ዲ ትምህርት በዚያው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለአራት ዓመት ተከታተለ።

ሕይወት አልጋ በአልጋ ባይሆንም በጥረቱና ሥራን በመውደድ ትጋቱ ምክንያት ለበርካታ ዓመታት መሥራት ችሏል። የአይሪሽ ዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ውጤታማ ሥራውን ተመልክቶ ሩዋንዳ ከተከሰተው ግጭት በኋላ በዚያ ቢሮ እንዲከፍትና እንዲያደራጅ ስለመረጠው በሥነልቦና ማማከር እና ድጋፍ የሚያደርጉ ባለሙያዎችን በማሰልጠን እንዲሁም በሀገሪቱ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ለአራት ዓመት ቆየ። ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ብዙም ሳይቆይ ወደ ሴቭ ዘ-ችልድረን ግብረ ሰናይ ድርጅት ተቀጥሮ መቀመጫውን ኬንያ በማድረግ ለደቡብ ሱዳን የሕፃናት መብት፣ በጦርነት የተፈናቀሉትን ታዳጊዎች ድጋፍ ፕሮግራም ዙሪያ በናይሮቢ ለስድስት ዓመታት ሲሠራ ቆየ።

ጋሽ ፍሬው ትምህርቱን ለሰው ልጆች ሰብዓዊና ድጋፍ ማዋል ከጀመረ ዓመታት ተቆጠሩ። ከሀገራዊ ጉዳይ ያለፈ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ባላቸው ሰውኛ ጉዳዮች ላይ ተፅእኖ መፍጠር ጀመረ። በጦርነት፣ ርሀብ ፣ የእርስ በእርስ ግጭት እና በሌሎች ማህበራዊና ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎሽ ምክንያት ተጎጂ ለሆኑ የሰው ልጆች በሚደርሱ ድጋፎች ላይ አሻራውን ያሳርፍ ጀመር።

ከሥራዎቹ መካከል የሚጠቀሰው በዩኒሴፍ በደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ከተደረገ ወዲህ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀዬያቸው መመለስና ማቋቋም ላይ የሚያተኩረው ነው። በዚህ ፕሮግራም ላይ በኃላፊነት ለሁለት ዓመት አገልግሏል። ብዙም ሳይቆይ ከባለቤቱ ማርታ አለማየሁ (አሁን በዩክሬን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትሠራለች) ባላቸው የትዳር ጥምረት የአብ የሚል ስም ያወጡለትን ልጃቸውን ወለዱ።

አዲሱ የቤታቸውን እንግዳ ሲቀበሉ ጋሽ ፍሬው የዩኒሴፍ ሥራውን ለቅቆ ለተወሰኑ ጊዜያት ከሥራ ዓለም ተራርቆ ነበር። ዳግም ወደ ሥራ ሲመለስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለአንድ ሴሚስተር ሲያስተምር ቆይቶ፣ አይ አይ አር አር (IIRR) በሚባል ኢንስቲትዩት ውስጥ ሰዎች አቅማቸውን መጠቀም እንዲችሉ ማብቃት ላይ የሚሠራ ፕሮግራምን ለ9 ዓመታት በካንትሪ ዳይሬክተርነት መርቷል።

የጋሽ ፍሬው የሙያና የሥራ ትጋት ቀጥሎ በአሜሪካን ሀገር በሚገኘው ፊውቸር ጀነሬሽን ዩኒቨርሲቲ ተደገመ። በዚያ የአፍሪካ ሪጅን ዳይሬክተር በመሆን ከጋና፣ ከኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳንና ኡጋንዳ ተማሪዎችን በማህበረሰብ ለውጥ ላይ በሚያተኩር የማስተርስ ፕሮግራም (Applied Community Change) ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በማስተማር አስመረቀ። ይህንን ሥራ ለጊዜው በመግታትና በዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር አባል በመሆን ወደ ሌላ ሥራ አምርቶ የስዊድን ድርጅት በሆነው Life and Peace Institute የአፍሪካ ሪጅን ኃላፊ በመሆን ለሁለት ዓመታት አገለገለ። ወቅቱ የኮቪድ ወረርሽኝ የተከሰተበት ጊዜ በመሆኑ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስር የተቋቋመ ብሔራዊ ካውንስል (የምሁራን ስብስብ) ውስጥ በመግባት በአባልነት አገልግሏል። የፖላንድ ሀገር ድርጅት የሆነው የፖሊሽ ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅት አማካሪና የኢትዮጵያ ተወካይ፣ ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ደግሞ በጦርነትና ግጭት የሥነ ልቦና ጫና ለሚደርስባቸው ማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ ለሚያደርግ ድርጅት (Center for Victims of Tor­ture – CVT) የኢትዮጵያ ኃላፊ በመሆን ያገለገለ ሲሆን፤ በትግራይና በአማራ ክልል በነበረው የሰሜኑ ጦርነት ወቅት ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች ፕሮግራም በመምራትና በአካል በመሄድ በማገልገል ሙያዊ ግዴታውን ተወጥቷል።

ፕሎጊንግ ኢትዮጵያ

ላለፉት 37 ዓመታት እርሱ ሳያርፍ ለሰው ልጆች ግን እረፍትን በሚሰጡ ሙያዊ ግዴታዎች ውስጥ ሲያገለግል ቆይቷል። ዛሬ ራሱን የቢሮ ኃላፊነት ከሚጠይቁ የየእለት ሥራዎች ቢያርቅም አዕምሮውና ጠንካራው ሰውነቱ ደከመኝ አላሉም። ቤተሰቡ አዕምሮውን ማሳረፍ፣ ለቤተሰብ ጊዜ መስጠትና ጫናን መቀነስ እንዳለበት በተደጋጋሚ ጉትጎታና ምክር ስለሰጡት በግል የመንፈስ እርካታን በሚሰጠው የበጎ ፍቃድ ላይ ተሠማርቶ ይገኛል። ቀደም ባሉት ጊዜያት ተግባሩን ቢፈፅመውም አሁን ግን በቋሚነት እየሠራው ይገኛል።

ጋሽ ፍሬው ከድሮም ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ፋታ ሲያገኝ ከከተማው ጩኸትና ሁካታ መራቅ ያስደስተዋል። ከተፈጥሮ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት አለው። ይህንን ልምዱን ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ ከባለቤቱና ከልጆቹ ጋር ይፈጽማል። ይህ አጋጣሚ ታዲያ አሁን በፍቅር ከሚሠራው የፕሎጊንግ (በሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች፣ እንጦጦ ፓርክና ጉለሌ የእፅዋት ማእከልን በመሳሰሉ ቦታዎች የእግር መንገድና የአካል እንቅስቃሴ በማድረግ የሚጣል ፕላስቲክ ቆሻሻን ማንሳት፤) በጎ ፍቃድ አገልግሎት ጋር አስተዋውቆታል። በተለይ በዚህ በጎ ፍቃድ ሥራ ላይ በትኩረት እንዲሠራ ያደረገው ጉዳይ የትንሹ ልጁ አምነን ፍሬው ‹‹ሰዎች ግን ለምን ንፁህ ቦታ ላይ ቆሻሻ ይጥላሉ›› የሚል ቀላል የመሰለ ነገር ግን የሰው ልጆች ቸል ባይነትን የሚሞግት ጥያቄ ነበር።

የአምነን ጥያቄ አባትን አንቅቶ በቀጣይ የእረፍት ቀን ከልጆቹ ጋር በእንጦጦ ፓርክና መሰል አካባቢ ጥበቃ ልዩ ትርጉም ያላቸው ቦታዎች ላይ የሚጣሉ የፕላስቲክ ኮዳና ተረፈ ምርቶችን መሰብሰብ ጀመሩ። እግረ መንገድ ረጅም ኪሎ ሜትሮችን በመጓዝ የአካል እንቅስቃሴ (በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ) ያደርጋሉ። ብዙኃኑን ለማስተማር ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያን እንደ አማራጭ ይጠቀማሉ። ከዚህ መነሻ ‹‹ለቆሻሻ የተዘጋጀ ማጠራቀሚያ እያለ ሰዎች ፕላስቲክ ኮዳዎችንና ፌስታሎችን አላግባብ በየቦታው መጣል የለባቸውም›› የሚለውን እሳቤ በጽሑፍና በምስል እያስደገፉ ማስተማርን ተያያዙት።

በእረፍት ጊዜ የጋሽ ፍሬው ቤተሰብ የሚከውነው የበጎ ፈቃድ ተግባር በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ጀመረ። የሃሳቡ ደጋፊዎች ከማህበራዊ ሚዲያ በመመልከት ተቀላቀሏቸው። ጓደኛ፣ ወዳጅ ዘመድ እንዲሁም ሌሎች ከርቀት ስለ በጎ ፈቃድ ሥራው የሰሙ ሁሉ የሃሳቡ ተጋሪ ሆነው ፕላስቲክ ቆሻሻዎችን ከእንጦጦ ፓርክና መሰል መዝናኛ ቦታዎች ላይ በየጊዜው መሰብሰብና ማስተማር ጀመሩ። ይህን መሰል ተግባር በዓለም አቀፍ ደረጃ ‹‹ፕሎጊንግ›› የሚል ስያሜ አለው። በቤተሰቡ ተነሳሽነት የጀመረው ይህ እንቅስቃሴም ስያሜውን ከዚያ በመውሰድ ‹‹ፕሎጊንግ ኢትዮጵያ›› ተባለ።

ጋሽ ፍሬው ይህ የፕሎጊንግ እሳቤ በመላው ዜጎች ላይ እንዲሰርፅ ተጨማሪ የህይወት ግብ አንግቦ መንቀሳቀሱን ተያያዘው። የዘመቻና የአንድ ሰሞን ሆይሆይታ እንዳይሆን በጥንቃቄ ያዘው። ሰዎች በበጎ ፍቃድ ብቻ በተግባሩ ላይ እንዲሰማሩ የሚያስችል ሁነት ‹‹Informal Event›› እንዲሆን አመቻቸ። እሁድ ቀን የፕሎጊንግ አባላቱ የሚገናኙበት መንገድ በመፍጠር ፕላስቲክ ኮዳዎችና ቆሻሻዎችን በማንሳት ያፀዳሉ፤ ተጨማሪ ቆሻሻ እንዳይጣልም ያስተምራሉ።

‹‹የፕሎጊንግ በጎ ፍቃድ ሥራን ከጀመርን አራት ዓመት ሊሆነን ነው። ብዙ ሺህ ሰዎች በበጎ ፍቃድ ተግባሩ አባል ናቸው›› ይላል ጋሽ ፍሬው ስለ እንቅስቃሴው ሲናገር። ላለፉት አራት ዓመታት በማስተማርና የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን በማፅዳት ተምሳሌት እየሆኑ ነው። በሳምንት በበጎ ፍቃድ ተግባሩ ላይ በአማካኝ 70 እና 80 ሰዎች ተሳታፊ ናቸው። ይህንን ልምድ ወደ ሀዋሳ፣ ጋምቤላ (በሽሬና ጋምቤላ ሙከራዎች ተደርገዋል) ባህርዳርና ሌሎች ከተሞች ለማስፋት እየሠሩ ነው። ከአምነን ፍሬው የተነሳው ጥያቄ አድማሱን አስፍቶ ዜጎች በአካባቢ ጥበቃ ላይ ተቆርቋሪ እንዲሆኑና ባህል ሆኖ እንዲሰርፅ መንገዱ ተጀምሯል። ፕሎጊንግ ኢትዮጵያ ዛሬ ከጋሽ ፍሬው ቤተሰብ አልፎ ብዙዎችን በበጎ ፈቃድ እያሳተፈ ይገኛል።

ይህንን የበጎ ፍቃድ ተግባር በአጋጣሚ እንጦጦ ተገኝተው የተመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ የጋሽ ፍሬውን ተምሳሌታዊ ሥራ በአንድ ወቅት የፓርላማ እንደራሴዎች ስብሰባ ላይ በምሳሌነት በማንሳት ምስጋና እስከ ማቅረብ ደርሰዋል። ከ40 በላይ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ሚዲያ ስለ ፕሎጊንግ ኢትዮጵያ ተግባር ሰፋፊ ሽፋን ሰጥተዋል።

ጋሽ ፍሬው ከልብ በመነጨ ስሜት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጥ ዜጋ እየቀነሰ መምጣቱን ይናገራል። ይህ እሳቤ በፖለቲካና መሰል አጀንዳዎች እንዳይጠለፍ በመሥራት (promoting organic vol­unteerism) መሥራት ያስፈልጋል ይላል። በቀጣይ ልዩ ትኩረት የሚያደርግበት የሕይወት ግቡ በጎ ፍቃድ ‹‹በቅን ፍቃድ›› ላይ ተመስርቶ እንዲስፋፋ ማድረግ ነው። በተለይ ዲያስፖራ ማህበረሰቡ ለዚህ እሳቤ ተባባሪ እንዲሆን እቅድ ይዟል።

የሕይወት ዘመን ተግሳፅ

‹‹ወጣቱ አቋራጭ አይውደድ›› ይላል ጋሽ ፍሬው፤ ዛሬ የተዘራ ነገ ፍሬ እንደማያፈራ ሁሉ በተለያየ ሙያ መስክ የተሰማሩ ወጣቶች ስኬታማ ለመሆን ትዕግስትን ገንዘባቸው እንዲያደርጉ ሲመክር፤ ሁሌም በትምህርት ላይ መሆን፣ አዳዲስ ነገሮችን ለማወቅ በመጣር ውስጥ ለውጥ እንደሚገኝ ይህ ትውልድ መገንዘብ እንዳለበትም ከደረሰበት የሕይወት ልምድና ተሞክሮ ተነስቶ የአባትነት ምክሩን ይለግሳል።

ለጊዜ ልዩ ቦታና ከብር አለው። ዛሬን በአግባቡ መጠቀም ከነገ ፀፀት እንደሚያድን ጠንቅቆ ያውቃል። በዚህ መርህ እየተገዛ ኖሯል። መጪውም ሆነ የአሁኑ ትውልድ ጊዜን የሚጠቀምበትንና የሚረዳበትን አስተሳሰብ ማስተካከል እንዳለበት ከዝግጅት ክፍላችን ጋር በነበረው ቆይታ አበክሮ አንስቶልናል። መልካም እለተ ሰንበት!!

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

 

 

 

 

 

Recommended For You