ግንቦትን ለእናቶች ጤና

የግንቦትን ወር ስናስብ ቀድሞ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው «የእናቶች ቀን» ነው። በዚህም ቀን ሁሉም እናቱን ያስባል፤ የእናቱን ልፋትና ድካም ሁሉ ይቆጥራል። የእናት ውለታዋን እያስታወሰ የተለየ ስጦታ ያዘጋጃል፤ ይሰጣል። ስጦታ ካልሆነለት ደግሞ በምስጋና እና በሙገሳ ውለታዋን ይዘክራል። በእርግጥ ለእናት ምን ተደርጎ፤ ምን ተሰጥቶና ምን ተከፍሎ ይቻላል! እርሷ መተኪያ የሌላት፤ ዋጋ የማይተመንላት ናት። ከፅንስ ጀምሮ በሆዷ ተሸክማ፣ ማንም የማይጋራትን አስጨናቂ ምጥ አምጣና ወልዳ ለቁም ነገር የምታበቃ የፈጣሪ ጸጋ ነች። እህት፤ ሚስት፤ አሳዳጊም ሆና ነገን በብርሃን የምታሳይ፣ ሁሉ የማይከብዳት መሬት ናት። ከዚህ አንጻርም ስለእርሷ ጤና መጨነቅ ምንም ማለት እንዳልሆነ ማንም ይገነዘበዋል።

በእናት ጤና ላይ መስራት ሀገርንም ቤተሰብንም ማቆም ነው። ለዚህም ይመስላል እንደ ሀገር ግንቦት ወር የእናቶች ጤና ወር ተደርጎ መከበር የጀመረው። ‹‹ወሩን ለእናቶች ጤና መስጠቱ ምን ምን ጠቀሜታዎችን ያስገኛል?›› ካልን ይህንን ወር ታሳቢ አድርገው የእናትነት ቀን በሆነችው ግንቦት ሦስት በልዩ ልዩ ዝግጅቶችና ምርመራዎች ያከበሩት የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒዬም ሜዲካል ኮሌጅና የኔ ሄልዝ እንዲሁም ሌሎች አጋር ድርጅቶች ኃላፊዎች ጋር ቆይታ አድርገናል።

በመጀመሪያ ሀሳባቸውን ያጋሩን ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒዬም ሜዲካል ኮሌጅ ፕሮቮስት ዶክተር ሲሳይ ስርጉ ሲሆኑ፤ የእናቶች ጤና ወር መከበር በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ይናገራሉ። እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ይህ ወር ሲታሰብ እንደ እናቶች ጤና ሁለት መልክ ኖሮት ይታያል። አንደኛው ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚመጡ ችግሮቻቸው ትኩረት እንዲያገኙ ማስቻል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ እንደ ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚከሰቱ የጤና ችግሮቻቸው እንዲታዩ ማድረግ ነው።

እናቶች ከሚፈተኑባቸውና ለሞት ከሚዳረጉባቸው የጤና እክሎች መካከል እንደ ልብ ሕመም፣ የስኳር በሽታ እና ካንሰር ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ከዚያም በተጨማሪ አካላዊ እና አእምሯዊ የጤና ጉዳዮች ክፍት ውይይቶች ካልተደረጉባቸው ከፍተኛ የጤና ችግር ይሆኑባቸዋል።

የእናቶች ጤና ወር የመከበር ግብ እነዚህና መሰል ችግሮቻቸው ግንዛቤን በመጨበጥ ቀድመው እንዲከላከሉ ማድረግና ጤናቸውን በተሻለ ሁኔታ ለመጠበቅ እንዲችሉ ማበረታታት ነው። ከዚያም ባሻገር የጤና ባለሙያዎች እና ድርጅቶች እናቶች እንዴት ጤናማ ሕይወትን መምራት እንደሚችሉ መረጃ እና ምርመራ እንዲያደርጉ የሚጋበዙበት በመሆኑ ነጋቸውን እንዲያሳምሩ ጥሩ መደላደልን መፍጠር ነው። ይህም በመደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴና በምክር አልያም በተለያዩ ምርመራዎች የሚከወን ሊሆን እንደሚችል አንስተዋል።

እናቶችን ወደ ሞት ከሚመራቸው የጤና ችግር ውስጥ በዋናነት ከወሊድ ባሻገር የሚጠቀሰው የማህጸንና የጡት ካንሰር እንደሆነ የሚገልጹት ዶክተር ሲሳይ፤ ይህ ወር እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ሆስፒታል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራበት ምክንያት የሴቶች ልዩ የጤና ፍላጎቶችና ችግር ናቸው ተብለው የተለዩት በሽታዎች በተለያየ ምክንያት እየታሰቡ ወደ ቅድመ መከላከሉ እንዲያዘነብሉ ለማድረግ ነው። የተለያዩ መድረኮች ሲፈጠሩ ደግሞ ወደ ጤና ተቋም የመሄድ ልምድ የሌላቸው እናቶች በእነዚህ አጋጣሚዎች ተነሳሽነት እንዲኖራቸውና ምርመራ እንዲያደርጉ እንዲሁም አካላዊ እና አእምሮአዊ ደህንነታቸውን እንዲጠብቁ ለማድረግም እንደሚያስችል ይናገራሉ።

የማህበረሰብ ጤና ሲታሰብ ደግሞ ሰፊውን የሕዝብ ቁጥር የሚይዙት እናቶችን አስቀድሞ ማየት እንደ ሀገር በርካታ በረከቶችን መቀበል እንደሆነ የሚገልጹት ዶክተር አበበ፤ ጤናው የተጠበቀ ማኅበረሰብ አምራች ነው፤ ጤናው የተጠበቀ ማኅበረሰብ ሀገር ይጠብቃል። ከዚህ አንጻርም ባለድርሻ አካላትን ያካተተ የጤና ፕሮግራሞችን እንደ ሀገር በመዘርጋት እንደ ኢኮኖሚው ሁሉ ኢንቨስትመንት አድርጎ መስራት ይጠይቃል። ስለሆነም ሁሉም ሰው ለእናቶች ጤና ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ያስረዳሉ። በተለይም መንግሥት ብቻውን ይህን ማድረግ ስለማይችል አጋር አካላት በትብብር መስራት እንደሚገባቸውም ያስገነዝባሉ።

የእናቶች ጤና በባህል፤ በሃይማኖት አስተምሮና በቤተሰብ አስተዳደግ እንዲሁም በትምህርትና በመረጃ እጦት ችግር ይገጥመዋል። ይህ ደግሞ ከሁሉም በላይ በግንዛቤ መፍጠር መስተካከል ይኖርበታል። ሆኖም በየቀኑ ይህን የሚያደርገው ውስን አካል ነው። በዚህ መዘናጋት ውስጥ ብዙዎች ለሞት ሊዳረጉ ይችላሉ። ስለዚህ ግንዛቤ መፍጠር የራሱ ጊዜ ያስፈልገዋል። የግንቦት ወርም የተመረጠው ከዚህ አንጻር ይመስለኛል ያሉን ደግሞ የእኔ ሄልዝ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ቅድስት ተስፋዬ ናቸው።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ወሩ ስለእናቶች ጤና አስፈላጊነት ግንዛቤን ለማስጨበጥ እና ደህንነታቸውን እንዲቆጣጠሩ ለማስቻል ጠቀሜታው የጎላ ነው። እናቶች ጊዜውን አውቆ በሁሉም ቦታ ላይ እንዲታወሱም ያደርጋቸዋል። ይህ ወር እናቶች በየአካባቢያቸው የሚያበረክቱትን አስተዋጾ ለማጉላት፤ ክብር ለመስጠት፤ ራስን የመንከባከብ ባህልን ለማጎልበትና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን ለመፍጠርም የሚያስችል እድል የሚሰጥ ነው። ከሁሉም በላይ የእናቶች ጤና ላይ በማተኮር የረዥም ጊዜ ደህንነትን እና በሽታን መከላከልን ሥራ ለማከናወን ያስችላል፤ ጤናማ ልማዶችን ለማስፋፋትም ይበጃል።

የእናቶች ጤና ወር መኖሩ በማኅበረሰቡ ዘንድ ስለ ጤና ማውራት እጅግ የሚያሳፍርባቸው በርካታ ልምዶች ያሉበትም በመሆኑ የመነጋገር ባህልንም ለማዳበር ሁነኛ እድልን የሚፈጥር ነው የሚሉት ሥራ አስኪያጇ፤ ለአብነት የወር አበባ ጉዳይ ያነሳሉ። የወር አበባ ተፈጥሯዊ የሴትነት መገለጫ ነው። ነገር ግን ማኅበረሰቡ የሚያየው እንደ እርግማን በመሆኑ ሳይነጋገርበትና የልጆቹን ለውጥ ሳይከታተልበት በመቅረቱ እናቶችም ሆኑ አጠቃላይ ሴቶች ለከፋ የማህጸን አለያም ሌሎች ችግሮች እንዲጋለጡ ይሆናሉ። ስለሆነም እንደነዚህ አይነት ልዩ ቀናት እናቶች ጤና ላይ ትልቅ አሻራን አሳርፈው እንዲያልፉ ያደርጋሉ።

ወሮች ተለይተው በጤና ጉዳይ ላይ ሲሰሩ ምን አይነት መድኃኒት ያስፈልገኛል፤ ምን አይነት የሰውነት እድገት ውስጥ ነኝ፤ የሥነተዋልዶ ጤናን በምን መልኩ መከታተል እችላለሁና መሰል የጤና ሁኔታን ለመረዳትና ክትትል ለማድረግ እንዲሁ ወሳኝነት አላቸዋል። አሁን ላይ በጤናው ዘርፍ በተለይም በእናቶች ሞት ቅነሳ ዙሪያ በርካታ ለውጦች የመጡትም በእነዚህና መሰል ምክንያቶች መሆኑን ማንም ሊክደው አይችልም። ስለሆነም ለእናቶች ጤና ትኩረት መስጠቱ ከዚህም ባለፈ ሊሰራበት ይገባል ሲሉ ያሳስባሉ። የወንዶች አጋርነት ደግሞ ወሳኝነት እንዳለውም አበክረው ይናገራሉ።

የኤም ኤስ አይ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር አበበ ሽብሩ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በዓለም ላይ ብዙ እናቶች ከሚሞቱባቸው ሀገራት ተርታ ትመደብ ነበር። ሆኖም ለእናቶች ጤና በተሰጠው ትኩረት ብዙ ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ ሆነዋል። በተለይም ከወሊድ ጋር የተያይዙ ሕይወት ማጣት በብዛት መፍትሄ የተቸራቸው ሆነዋል። ብዙን ጊዜ የእናቶች ጤና ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው የሥነ ተዋልዶ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም የእናቶች ሞት ዋነኛ መንስኤ ይደረጋል። ስለዚህም እናቶችን ወደ ጤና ተቋም ሄደው ክትትል ማድረግ እንዲችሉና በዚያው እንዲወልዱ ለማድረግ ግንዛቤ ማስጨበጥ የግድ ይላል። ለዚህ እንደ እናቶች ጤና ወር አይነቶች ተለይተው የተሰጡ ቀናት ያስፈልጋሉ።

የጠራ አገልግሎት የማግኘት መብት ጉዳይ፤ በእውቀትና በልምድ የዳበሩ ባለሙያዎችን አግኝቶ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ እናትም ሆነ ልጅ ጤናማ ሆነው እንዲወለዱ ከማድረግ አንጻር ክፍተቶችን ለመቀነስ የግንዛቤ ማስጨበጫ፤ መረጃ መለዋወጫ እንዲሁም ምርመራ ማድረጊያ የተለዩ ቀናት ያስፈልጋሉ። ከእነዚህ ቀናት ውስጥ ደግሞ የእናቶች ጤና ወር አንዱ ነውና የሚጫወተው ሚና ቀላል እንዳልሆነ መወሰድ አለበት የሚሉት ዶክተር አበበ፤ እናት ሕይወት ለመስጠት ስትል ሕይወቷን ማጣት የለባትም። ስለሆነም የእናቶችን ሞትና ህመም ቅነሳ ላይ ተሳትፎ ለማድረግም ይህ ጊዜ ልዩ ዋጋ የሚሰጠው እንደሆነም ያነሳሉ። በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በማኅበረሰብ እንዲሁም በመንግሥት ደረጃ ትኩረት ተሰጥቷት የእናቶች ጤና ችግር መፈታት አለበት።

እናቱን፣ እህቱን እንዲሁም ቤተሰብን በወሊድ ምክንያት የሚያጣ ሰው ሊኖር አይገባም። ለዚህ ደግሞ እያንዳንዱ ዜጋ የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል። ለአብነት ደም በመለገስ በደም እጥረት ሕይወታቸው የሚያልፍ እናቶች እንዳይኖሩ መሥራት ያስፈልጋል። ይህንን እድል ለመፍጠር ደግሞ የእናቶች ጤና ወር መከበር ድርሻው ከፍተኛ እንደሆነም ያብራራሉ።

እናቶች የማይቻለውን ችለው፣ ማንም የማይከፍለውን ዋጋ ከፍለው፣ ምንም ዓይነት ፈተና ሳይበግራቸው በፅናት ልጆችን የማሳደግ ትልቁን ኃላፊነት የሚወስዱ ጠንካራ የማኅበረሰብ ክፍል በመሆናቸው በእነርሱ ጤና ላይ መሥራት ሀገርን ከችግሮቿ መታደግ ነው። ምክንያቱም ተተኪ ትውልድን በጥሩ ሥነምግባርና ሀገር ወዳድነት ይፈጥራሉ፤ ጤናማ ዜጋ እንዲሆኑ በማድረግም የሀገርን ብልጽግና ያረጋግጣሉ። ስለዚህ ለእነርሱ ጤና መጨነቅ የአንድ አካል ሥራ ብቻ መሆን እንደሌለበት ይመክራሉ።

እናቶች ላይ ከወሊድ ጋር የተዛመዱ በሽታዎች በርካታ ናቸው። አንዱና ዋነኛው ፊስቱላ ሲሆን፣ ያለእድሜ ከሚፈጠር እርግዝና እና ችላ ከተባለ ረዥም ምጥ ጋር ተዳምሮ የሚፈጥር እንደሆነ ይገለጻል። ስለሆነም እነዚህና መሰል ችግሮችን ለመከላከልና እናትን ጤናማ ለማድረግ ከሚያስችሉ መንገዶች ውስጥ በአብይነት የሚጠቀሰው ዘመናዊ የቤተሰብ ምጣኔን መጠቀም፣ ለእያንዳንዱ የተወሳሰበ ወሊድ ድንገተኛ የወሊድ እና የአራስ ህፃናት እንክብካቤን ማግኘት እንደሆኑም ዶክተር አበበ ያነሳሉ።

የእናቶች ጤና ሲነሳ ብዙ ጊዜ ሥራዎች የሚከናወኑት በውጪ ድርጅቶች በሚደረግ ድጋፍ ነው። አሁን ደግሞ እነዚህ ድጋፎች በብዙ መልኩ እየቀነሱ መጥተዋል። ስለዚህም እስከ አሁን የተደረገውን ውጤታማ ተግባር ለማጠናከር ከተፈለገ ያለንን የሰው ኃይል ከአለን ተፈጥሯዊ ሀብት ጋር አጣጥመን መጓዝ ይገባል የሚሉት ባለሙያው፤ ጤና ለአንድ ሀገር ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ ነው። ስለሆነም አሁን ያለውን የእናቶች ጤና ጉዳይ ቸል ልንለው አይገባም። መንግሥትና አጋር ድርጅቶች በትብብር እየሰሩ ጤናማ ማህበረሰብን መፍጠር እንደሚጠበቅባቸው ያስገነዝባሉ።

የእናቶች ሞት ዋና ምክንያት ተብለው ከሚወሰዱት መካከል ቀጥተኛ የወሊድ ችግሮች 85 በመቶን ይይዛሉ። በዚህም ከ2000ዓ.ም ጀምሮ በተሰሩ ተግባራት በርካታ ለውጦች መታየት ችለዋል። ባለፉት አስርት ዓመታት ብቻ በእናቶች ሞት ላይ አስገራሚ ለውጦች እንደነበሩ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። እንደ መረጃው ከሆነ፤ የእናቶች ሞት በ2000ዓ.ም 871 ከመቶ ሺህ የነበረ ሲሆን፤ በ2017ዓ.ም ይህ የሞት ቁጥር ወደ 401 ቀንሷል። ይህ በየዓመቱ ወደ 12ሺህ እናቶችን ከሞት መታደግ የተቻለበት እንደሆነም ያመላክታል። አሁንም ቢሆን እንደ ሀገር ይህንን አጠናክሮ በመቀጠል በኩል በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ በመሆናቸው ከፍተኛ የሆኑ መሻሻሎች እየመጡ መሆኑም ተመላክቷል። ይሁን እንጂ ሙሉ መደላደል ላይ የተቀመጠ አይደለምና የእናቶች ጤና ጉዳይ የሁሉም መሆን እንዳለበት ተጠቁሟል።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You