
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ተሳታፊዎች ያደረገችው አቀባበል የሚደነቅ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ አስመልክቶ ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ በየዓመቱ እያደረገች ያለችው የእንግዶች አቀባበልና ዝግጅት በተሳታፊዎች አድናቆት እንደተቸረው ተናግረዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤን ለመታደም ከ12 ሺህ በላይ እንግዶች ኢትዮጵያ ገብተዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ መለወጥም መደነቃቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ደኅንነት ምክር ቤት አባል ለመሆን ያደረገችው ጥረት ተቀባይነት አግኝቷል። በቀጣይ ሁለት ዓመታት ታገለግላለች ብለዋል።
የመሪዎች ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሦስት ጉዳዮች ላይ ንግግር አድርገዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ኅብረትና ለፓን አፍሪካኒዝም ጽንሰ ሀሳብ መጠናከር ያደረገችውን አስተዋፅዖ አንስተዋል።
ፍትሕ ለአፍሪካና ለዘረዓ አፍሪካውያን አስፈላጊ መሆኑን በማንሳት ከምንም በላይ ግጭትን ማስቀረት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍሪካ የርስ በርስ ትብብር በማጠናከር የነፃ ንግድ ቀጣናን በመተግበር ጥራት ያለው የትምህርት ሥርዓት በመዘርጋት የሰው ሠራሽ አስተውሎትን ለመጠቀም አፍሪካ ካለችበት ችግር ማላቀቅ እንደሚያስፈልግ ማስረዳታቸውን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ዘርፍ የተሻለ ውጤት እያስመዘገበች መሆኑን መግለጻቸውን ጠቅሰው፤ የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ ማደጉን ተናግረዋል። የመንግሥት የግብር አሰባሰብ ገቢ በእጥፍ ማደግ መቻሉን ተናግረዋል። በቀጣይም ለአፍሪካ ከምንም በላይ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት መስጠታቸውንም ተናግረዋል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2017 ዓ.ም