
አዲስ አበባ፡- እዚህ የቆምኩት የዓድዋ ድል በፈጠረው የነፃነት ጮራ ነው፤ የዓድዋ ድል ለአፍሪካ ነፃነት ትግል እንደ ችቦ ማቀጣጠያ ሆኖ ማገልገሉን በአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ እየተሳተፉ ያሉት የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞተሊ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ እዚህ የቆምኩት የዓድዋ ድል በፈጠረው የነፃነት ጮራ ነው፤ እዚህ የቆምኩት በፓን አፍሪካኒዝም መሥራች አባቶቻችን ትግል ምክንያት ነው ብለዋል።
የዓድዋ ድል መንፈስ በቀጣይ ለአፍሪካ ሁለንተናዊ ለውጥ እንደ ስንቅ መጠቀም እንደሚገባ አመልክተው፤ አፍሪካ በቀድሞው መሪዎች ትግል ከቅኝ ግዛት መላቀቅ ብትችልም፤ ሕልሞቻቸውን እውን ለማድረግ ከውጭ ጥገኝነት በመላቀቅ በትብብር መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል።
አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በብድር አቅርቦት፣ በብድር አመላለስ እና በሌሎች ዘርፎች የተጋረጠባትን አግላይና ኢ-ፍትሐዊ አሠራሮችን ለማስወገድ፤ አፍሪካውያን ከዲያስፖራው ጋር በትብብር መሥራት አለባቸው ብለዋል።
በዓለም ላይ ያለውን ኢ-ፍትሐዊነትንና አግላይነትን ለመታገል ንግግርን ወደ ተግባር መቀየር በቁርጠኝነት መሥራት ተገቢ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የዓለምን መፃኢ ጊዜ ካለ አፍሪካ ሰላም ማሰብ አይቻልም ብለው፤ ይህም በአፍሪካ ውስጥ ያሉ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያሉ አፍሪካውያንንም ይመለከታል ነው ያሉት።
እኛ በካሬቢያን ሀገራት የምንገኝ ዜጎች ከእናንተ አፍሪካውያን ጋር ከዘር ባሻገር ብዙ የሚያገናኙን ነገሮች አሉ፤ ይህን ማጠናከር እንፈልጋለን ሲሉም ተናግረዋል።
ይህ ዓለም ለሕዝቦቿ እንዲሁም ለተፈጥሮዋ ትኩረት እንድትሰጥ፣ ወደ ቀልቧም እንድትመለስ መልዕክትን የሚያስተላልፍም ጭምር ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሯ።
የታሪክን ጠባሳዎች ሽረን ወደ ተሻለችው ዓለም እንሻገር፤ ከኋላችን ያለፈው በድጋሚ ሊረብሸን አይገባም፤ ከዚህ በኋላ ለሚኖረን ጊዜ ከራሳችን ውጭ የሚያስቆመን መኖር የለበትም ማለታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።
የሕዝቦቻችንን መፃኢ ዕጣ ፋንታ የተሻለ ማድረግ ዛሬ በእኛ እጅ ነው፤ እኛም ዛሬ የዓድዋ ጀግኖችን ትግል ማድረግ፣ የነሱን ወጤት ማምጣት ይጠበቅብናል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2017 ዓ.ም