
ቡታጅራ፡- ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሰባቱም የክልሉ ማዕከላት ላይ ከ4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የቢሮዎችን እና የቤተ መንግሥት ግንባታ ለማካሄድ ስምምነት ተፈራረመ።
ስምምነቱ የተፈረመው ከተለያዩ ሥራ ተቋራጮች ጋር ሲሆን፤ አጠቃላይ የቢሮዎቹና የቤተ መንግሥቱ ግንባታ ወጪያቸውም አራት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ተገልጿል። ፕሮጀክቶቹ ከስድስት ወራት እስከ ሁለት ዓመታት ይጠናቀቃሉ ተብሏል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማና ኢንዱስትሪ ክላስተር አስተባባሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል፤ ግንባታዎቹ በከተሞች መነቃቃትን የሚፈጥሩ፣ ፍትሐዊ እድገትን የሚያሰፍኑ ናቸው ብለዋል።
ግንባታዎቹም በወራቤ፣ በሳጃ፣ በወልቂጤ፣ በቡታጅራ፣ በዱራሜ፣ በሆሳዕና እና ሃላባ ከተሞች የሚከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የሚገነቡት ሕንጻዎችም ወቅቱን የሚመጥኑ፣ ዘመናዊነትን የተላበሰ፣ የከተማን ገጽታ በመቀየር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ይሆናሉ ነው ያሉት። ባህላዊና ዘመናዊ የሕንጻ ግንባታ ጥበብን ያካተቱ እንደሚሆኑም ተገልጿል።
ለዚህም የቦታ ዝግጅት መጠናቀቁን፣ በፍጥነት ወደ ትግበራ እንደሚገባ አቶ ስንታየሁ ለሥራ ተቋራጮቹ አሳስበዋል።
የክልሉ መንግሥት የገባውን ቃል የሚፈጽም መሆኑን የሚያሳይ፣ መተማመንንም የሚያሳድግ መሆኑን ጠቁመው፤
ተቋራጮቹ የተመረጡትም ፕሮጀክቶችን በጊዜና በጥራት የመጨረስ ብቃታቸው እንደመለኪያ መታየቱንም አንስተዋል።
ድጋፍና ክትትል የሚደረግበትና አፈጻጸማቸውም በከፍተኛ አመራር ደረጃ ክትትልና ግምገማ የሚደረግበት መሆኑን አቶ ስንታየሁ ተናግረዋል።
ክልሉ በ2018 ዓ.ም የሚከበረውን 20ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል አዘጋጅ እንደመሆኑ አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶቹ ተጠናቅቀው ለበዓሉ እንዲደርሱ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም