
አዲስ አበባ ፦ በሀገር ውስጥ የተመረቱ የግንባታ ግብዓቶችን የመጠቀም ልምድን ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በኢንስቲትዩቱ የስልጠናና ብቃት ማረጋገጫ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ቅድስት ማሞ በሀገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች አጠቃቀም ላይ የሚመክር ውይይት በተካሄደበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው የግንባታ ግብዓት የሚመጣው ከውጭ ሀገራት ነው። ከዚህ መነሻነትም መንግሥት በሀገሪቱ ያለውን የግንባታ ግብዓት ፍላጎት እስከ 2022 ዓ.ም 80 በመቶ በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን እቅድ ተይዟል። ለዚህም ከወዲሁ በሀገር ውስጥ የግንባታ ግብዓቶችን የመጠቀም ልምድን ለማሳደግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
የተቀመጠውን እቅድ ለማሳካት እንደ መሰናክል የሚሆኑትን ጉዳዮች ለመለየት ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ አሶሴሽን ጋር በመተባበር ጥናት ማከናወኑን አንስተው፤ በጥናቱ ውጤትም የሀገር ውስጥ ምርቶችን በመጠቀም ረገድ የሚታዩት ክፍተቶች ከአምራቾችም ሆነ ከተጠቃሚዎች በኩል እንዲለዩ መደረጋቸውን ገልጸዋል።
ይህንንም መሠረት በማድረግ ለቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫ ሊሆን የሚችል የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችሉ ግኝቶችም ይፋ እንደሆኑ አመልክተው፤ እነዚህን ግኝቶች መሠረት በማድረግና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት ከፖሊሲ ጀምሮ መሰናክል የሚሆኑ ነገሮችን በማስወገድ የሀገር ውስጥ የግንባታ ግብዓት ምርት ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እንደሚሠራ አመልክተዋል።
ጥናታዊ ጹሑፍ ያቀረቡት የዘርፉ ተመራማሪ ሲሳይ ደበበ (ዶ/ር)፤ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት የሀገር ውስጥ የግንባታ ግብዓት አምራቾች እያመረቱ ያሉት ከአጠቃለይ አቅማቸው ከ22 እስከ 45 በመቶ ብቻ ነው። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚቀመጠው የመሬት፣ የኤሌክትሪክ፣ የውሃ፣ የላብራቶሪ፤ የቴክኖሎጂ ተደራሽነትና የሀገር ውስጥ ምርትን ያለመጠቀም ልምድ በመኖሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሀገር ውስጥ የግንባታ ግብዓት አምራቾች የግንባታ ምርቶችን በጥራት ለማምረት የተሻለ እድል አላቸው ያሉት ተመራማሪው፤ ለሀገር ውስጥ አምራቾች የቴክኖሎጂ ድጋፍ ማድረግ፣ ሀገር-በቀል የግንባታ ምርቶችን አጠቃቀም ፍላጎት ማሳደግ፤ እንዲሁም አመራረታቸውን በቴክኖሎጂ ማስደገፍና ዘርፉን ለማሳደግ የተደነገጉ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በሀገር ውስጥ ግንባታ ምርቶች እንዲገነቡ ለማድረግ አቅጣጫ ማስቀመጥ የሚጠበቅ ይሆናልም ብለዋል።
በተጨማሪም በሀገሪቱ ሰላም እጦት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ፣ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የግንባታ ግብዓቶች በእጥፍ መጨመር የሀገር ውስጥ አምራቾችን እያጋጠማቸው ያሉ ችግሮች መሆናቸውን በመጥቀስ፤ ለዚህም የሀገር ውስጥ መሠረታዊ የግንባታ ግብዓቶችን አጠቃቀም ለማሳደግ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም