
አዲስ አበባ፡- አፍሪካ ያሉባትን የፋይናንስ ክፍተት ለመሙላት የአፍሪካ መንግሥታት አዳዲስ አጋሮችን በአስቸኳይ መፈለግ እንዳለባቸው በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ የብሉ ኢኮኖሚ እና የዘላቂ አካባቢ ልማት ኮሚሽነር ገለጹ፡፡
ኮሚሽነሯ ጆሴፋ ሊዮን ኮሬያ ሳኮ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የአፍሪካ ሀገራት በአህጉሪቱ ላይ የሚደርሰውን ተፅእኖ ለመቋቋም እና ለመቀነስ እንደ ቻይና እና የአረብ ሀገራት (ኩዌት፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኦማን…) ያሉ አዳዲስ ለጋሾችን በአስቸኳይ መፈለግ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የአፍሪካ ኅብረት በለጋሾች የገንዘብ ድጋፍ ላይ ጥገኛ መሆኑ ትልቅ ፈተና እንደሆነ የጠቀሱት ኮሚሽነሯ፣ ምንም እንኳን መጠነኛ እድገት ቢያሳይም አባል ሀገራት ለአፍሪካ ኅብረት እቅዶች ማስፈጸሚያ የሚያበረክቱት የገንዘብ ድጋፍ አሁንም አነስተኛ እንደሆነ ተናግረዋል:: ‹‹አሁንም 75 በመቶ የሚሆነው የገንዘብ ድጋፍ የሚገኘው ከውጭ አጋሮች በተለይም ከአውሮፓ ኅብረት እና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ነው። በርካታ አባል ሀገራት ለዓመታዊ መዋጮ ክፍያ ውዝፍ እዳ አለባቸው›› ብለዋል።
እ.ኤ.አ. በ2016 የአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት ወደ አህጉሪቱ በሚገቡ ምርቶች ላይ የዜሮ ነጥብ ሁለት በመቶ ቀረጥ ተግባራዊ ለማድረግና የአፍሪካ ኅብረትን ፋይናንስ ለማድረግ ታሪካዊ ውሳኔ ማሳለፋቸውን ያወሱት ኮሚሽነሯ፣ ‹‹ይህ ውሳኔ ገና ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ካልሆነና የገንዘብ እጥረቱ በዚሁ ከቀጠለ የአፍሪካ ኅብረት የፋይናንስ ነፃነት አይረጋገጥም:: ይህም አፍሪካ የራሷ አጀንዳዎች ባለቤት የመሆኗ ጉዳይ አሳሳቢ ሆኖ ይቀጥላል›› ብለዋል::
በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአህጉሪቱ ሕዝብ በረሃብ የተጠቃ መሆኑን ጠቁመው፤ የውስጥ ግጭቶች፣ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የዋጋ ንረት የምግብ አቅርቦትን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ የነጻ ንግድ ስምምነትን በመጠቀም የምግብ ሸቀጦችን አቅርቦት ከፍ ማድረግ እና የአህጉሪቱን የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል:: ለአፍሪካ የግብርና ሥርዓት ለውጥ ትኩረት የሚሰጠውንና ለዘርፉ እድገት አዎንታዊ ሚና ያላቸውን በርካታ ተግባራት የያዘውን ‹‹ሁሉን አቀፍ የአፍሪካ ግብርና ልማት መርሃ ግብር›› (CAADP) በአግባቡ መተግበር የአህጉሪቱን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ እንደሚያግዝም ኮሚሽነሯ ተናግረዋል::
የፕሬዚዳንት ትራምፕ ውሳኔ ለኤችአይቪ/ኤድስ ሕክምና ድጋፍ ሲያገኙ በቆዩ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ላይ ብዙ አሉታዊ ተጽእኖዎች እንደሚኖረው ጠቁመው፤ የአፍሪካ ሀገራት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሀገሪቱ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (ዩ.ኤስ.ኤይድ/USAID) በኩል የሚቀርቡ ርዳታዎችን ለማገድ መወሰናቸውን ተከትሎ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሸፈንም አዳዲስ የልማት አጋሮችን መፈለግ እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል::
ግርማቸው ጋሻው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም