በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት መጀመሪያ ጥር 23 በአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ እራሱን የቬንዝዌላ ፕሬዚዳንት አድርጎ የሾመው የተቃዋሚ መሪ የሆነው ጇን ጓኢዶ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የሆነውን ኒኮላስ ማዱሮን ከሥልጣን ማውረድ ቀላል እንደሆነ ተናግሮ ነበር። ጓኢዶ ሦስት እቅዶች ያዘጋጀ ሲሆን የመጀመሪያው የማዱሮን ፕሬዚዳንትነት ሕገወጥ እንደሆነና ወደ ሥልጣን የመጣው ምርጫ አጭበርብሮ እንደሆነ መናገር፣ ሁለተኛው በአገሪቱ የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረት ማድረግ እንዲሁም ሦስተኛው ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ በማድረግ ወደ ሥልጣን መምጣት ናቸው።
ነገር ግን ጓኢዶ ነገሮችን አስተካክላለሁ ብሎ ከተናገረ ስድስት ወራት ቢያልፉትም እስካሁን የማዱሮን ሥልጣን መቀነስ አልቻለም። የ35 ዓመቱ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪ የሆነው ጓኢዶ ማዱሮን ከሥልጣን ማውረድ ያልቻለው እንደ ቻይና ያሉ አገራት ለማዱሮ ጠንካራ ድጋፍ በማድረጋቸው ምክንያት ነው። ቻይና በአሁን ወቅት ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስና ወታደራዊ ትብብር ከቬንዝዌላ ጋር የምታደርግ አገር ነች። በዚህም የጓኢዶን ፕሬዚዳንትነት አልቀበልም ያለች ሲሆን ቬንዝዌላ ያለማንም አገር ጣልቃ ገብነት ነፃ አገር ሆና መቀጠል አለባት የሚል እምነት አላት።
የጓኢዶ ደጋፊ ከሆኑት መካከል የአሜሪካ መንግስት ቻይና ለማዱሮ አስተዳደር እያደረገች ያለችውን ድጋፍ የነቀፈ ሲሆን በቀጣይ በቬንዝዌላ ለሚከሰቱ ማናቸውም ችግሮች ተጠያቂ ቻይና መሆንዋንም ተናግሯል። በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ሚያዝያ 13 ቺሊን የጎበኙት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማይክ ፖምፔዮ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ቻይና ከኋላ ሆና ለማዱሮ መንግስት እያደረገችው ያለው ድጋፍ በአገሪቱ ችግሮች እየተባባሱ እንዲመጡ አድርጓል። በቅርቡ ደግሞ የአሜሪካ ደቡባዊ ክፍል ወታደራዊ መሪ የሆኑት አድሚራር ክሬጅ ፋለር የማዱሮ አስተዳደር ህዝቡን የሚቆጣጠርበት ቴክኖሎጂ ከቻይና በድጋፍ ማግኘቱን ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቬንዝዌላ ላለው ችግር የቻይና ከፍተኛ ሚና እንዳለ እውቅና የተሰጠው ጉዳይ ሲሆን ጓኢዶ ቻይና ለማዱሮ መንግስት እያደረገችው ያለውን ድጋፍ እንድታቆም ከፍተኛ ቅስቀሳ እያደረገ ይገኛል። ፖምፔዮ በቻይና ላይ ትችት ከሰነዘሩ በኋላ የሽግግሩ መንግስት ፕሬዚዳንቱ ጓኢዶ በብሉንብግ ላይ ለምን ቻይና ለቬንዝዌላ ማገዝ ፈለገች የሚል ፅሁፍ አሳትሟል። በፅሁፉ ጓኢዶ ማስረፅ የፈለገው ተቃዊሚ ፓርቲዎች የቻይናን ፍላጎት እና ኢንቨስትመንት ተሳትፎ ከማዱሮ መንግስት በበለጠ እንደሚያሳድጉና ለቻይና መንግስት የተሻለ የፋይናንስ ገቢ እንደሚፈጥሩ ነው። ነገር ግን ይህ እንዲሆን ቻይና ለማዱሮ የምታደርገውን ድጋፍ መቀነስና ማቆም ስትችል ነው። የጓኢዶ ፅሁፍና የፖምፔዮ ንግግር የሚያሳየው የቬንዝዌላን ጉዳይ የሚከታተሉ አገራት ቻይና በቬንዝዌላ የውስጥ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ መግባቷን ማመናቸውንና በቀጣይ ቻይና የቬንዝዌላን እጣ ፈንታ መወሰን እንደምትችል የተቀበሉ መሆናቸውን አሳይቷል።
ቬንዝዌላ ለቻይና ለምን
አስፈላጊ ሆነች?
ቻይና በኢኮኖሚና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ለቬንዝዌላ በጣም አስፈላጊ አገር ነች። ቬንዝዌላም በተመሳሳይ ለቻይና በላቲን አሜሪካ ወሳኝ አገር ናት። ቻይና በነዳጅ የበለፀገችውና የሶሻሊስት ርዕዮት ዓለም ተከታይ ከሆነችው ቬንዝዌላ ጋር ከንግድ ትብብር በተጨማሪ በመልከአምድር አቀማመጥም ምክንያት ቻይና ከአሜሪካ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ፉክክር እንድታሸንፍ ይረዳታል። በተጨማሪም ቻይና እያደረገችው ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ቬንዝዌላ ለቻይና ቀጣይ የኢኮኖሚ መዳረሻዋ እንደምታደርጋት ማሳያ ነው።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት የተጀመረው እአአ 1999 ሂውጎ ቻቬዝ ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ ነው። እአአ 2013 ቻቬዝ ከሞተ በኋላም የሁለቱ አገራት ግንኙነት በማዱሮ አስተዳደርም ቀጥሏል። እአአ 2000 እስከ 2018 ድረስ በሁለቱ አገራት መካከል በተደረገው የንግድ ልውውጥና ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ስድስት ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። በተጨማሪም ቻይና ለቬንዝዌላ በብድር መልክ የሰጠቻት ገንዘብ አጠቃላይ 60 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።
አብዛኛው የቻይና ብድር እና ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ያተኮረው በነዳጅ ዘርፉ ላይ ነው። እአአ 2007 ላይ ቻይና-ቬንዝዌላ የትብብር ፈንድ በማቋቋም ቬንዝዌላ አምስት ቢሊዮን ብር ብድር በቀጥታ እንድታገኝ ያደረገች ሲሆን ቬንዝዌላ ብድሩን በድፍድፍ ነዳጅ መልክ ከፍላለች። የትብብር ፈንዱ የቻይና መንግስት በኦርኖኮ ነዳጅ ማምረቻ ድርጅት ውስጥ እንድትሳተፍና እንድትመራ አድርጓታል። የነዳጅ ድርጅቱ በአለም ትልቁ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቦታ ነው።
ቻይና ከማዱሮ ጎን መሆን የፈለገችው ለምንድነው?
በአጠቃላይ የቬንዝዌላ የብድር እዳ ባለፉት ሃያ ዓመታት የጨመረ ሲሆን፤ የነዳጅ ዘይት ማውጣቱ ስራ በአገሪቱ በተፈጠረው ብጥብጥ በመስተጓጎሉ ምክንያት ቬንዝዌላ ብድሩን መክፈል እያቃታት ይገኛል። ይህ ደግሞ የቻይና የኢኮኖሚና የሃይል ማመንጨት ስራ ላይ አደጋ ደቅኗል። በተመሳሳይ ሁኔታም በአገሪቱ ባለው የንግድ እንቅስቃሴ መዳከም አብዛኛው የቻይና ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የተወሰኑት ባሉበት እንዲቆሙና የተቀሩት ደግሞ ከነጭራሹ እንዲቆሙ ተደርጓል።
በአሁኑ ወቅት በቬንዝዌላ ላይ በተጋረጠው ችግር ምክንያት ቻይና ለመሰረተ ልማት ግንባታዎች የሚውል ገንዘብ በብድር መልክ ለመስጠት አልቻለችም። ቻይና ዋነኛ ትኩረት ያደረገችው በመንግስት የተያዙ ድርጅቶች ላይ ሲሆን በተለይ የነዳጅና የሀይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ ነው። በዚህ አይነት መልክ አጠቃላይ ቬንዝዌላን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገች ትገኛለች። ከላይ የተቀመጡት ችግሮች እና ኢኮኖሚው ላይ አደጋ ቢጋረጥም ቻይና አሁን ድረስ ከማዱሮ መንግስት ጎን ነች። ይህ ደግሞ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ቻይና እራሷን እያስተዳደረች በምትገኝ አገር ውስጣዊ ችግር ውስጥ ጣልቃ መግባት ስለማትፈልግ ነው። ይህ ግን ቻይና እስከመጨረሻው የማዱሮን መንግስት እየደገፈች ትቆያለች ማለት አይደለም።
ያልተረጋገጡ ምክንያቶች እንዳሉ ሆነው ቻይና አሁንም ድረስ ከማዱሮ መንግስት ጋር እየሰራች ትገኛለች። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በአካባቢው ባለው የንግድ እንቅስቃሴ ከአሜሪካ ጋር ለመፎካከር ፍላጎት ስላላት ሲሆን ይህ ደግሞ በቬንዝዌላ ችግሮች እንዲባባሱ አድርጓል። በተጨማሪም ‹‹የደቡብ ደቡብ ትብብር›› በአሁኑ ወቅት የቻይና የውጭ ፖሊሲዋ ሲሆን ይንን ትብብር ማጣት አትፈልግም። ለዚህ ደግሞ የንግድና የኢንቨስትመንት ተባባሪዎቿን መክዳት ፍላጎት የላትም። በአሜሪካ የሚደገፉ ተቃዋሚ ቡድኖችን ፍላጎት ለማሟላት ብቻ ነፃ የሆነች አገር ላይ ህጋዊ ያልሆነ እርምጃ መውሰድ ላይ እምነት የላትም።
በሌላ በኩል ጓኢዶ የትኛውም ጥረት ቢደርግ ቻይና የቬንዝዌላ ተቃዋሚዎችን በምንም ምክንያት አታምንም። ተቃዋሚ ፓርቲዎች በቬንስዌላ ስልጣን ቢያገኙ የቻይናን ብድር የመክፈላቸው ሁኔታ አጠራጣሪ ነው። ነገር ግን ቻይና ተቃዋሚዎች ስልጣን ቢይዙ ብድሩን ለመክፈል ላይስማሙ ይችላሉ ብላ እንድትጠራጠር ያደረጋት ምክንያት እስካሁን አይታወቅም። የቬንዝዌላ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ተቀራርበው እየሰሩ የመሆናቸው ጉዳይ በቻይና እንዳይታመኑ ያደረጋቸው ይመስላል። በዚህም ቻይና የማዱሮን መንግስት የመደገፍ ስራዋን ቀጥላለች። የቻይና መንግስት የቬንዝዌላ ምሁራንን ከማመን የተቆጠበው ምሁራኑ ከትራምፕ አስተዳደር ጋር በትብብር እየሰሩ ስለሚገኙና የቬዝዌላንና የአካባቢውን ጥቅም ለማስጠበቅ የአሜሪካን አላማ አስፈፃሚዎች በመሆናቸው ነው።
ቻይና አሁን ያለችበት ሁኔታ ብዙም አዳጋች አይደለም። ጓኢዶ እና ደጋፊዎቹ ቻይና ሀሳቧን እንድትቀይር ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ሲሆን እራሳቸውን ከትራምፕ አስተዳደር በማራቅ እና ቬንዝዌላ ያለባትን እዳ ለቻይና እንዴት መክፈል እንዳለባቸው እቅድ እያዘጋጁ ይገኛሉ። የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎቹ የቻይናን እምነት ማግኘት የሚችሉ ከሆነ የማዱሮን መንግስት ለማውረድ ከፍተኛ እድል ይኖራቸዋል። በዚህም አገሪቱን የማስተዳደር እድል ያገኛሉ ማለት ነው። መረጃውን ያገኘነው ከቢቢሲና አልጀዚራ ነው።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 15/2011
መርድ ክፍሉ