አንዳንድ ጊዜ የምንሰማቸው አንዳንድ መረጃዎች ወይም ዜናዎች አስቂኝ፣ አስደንጋጭ፣ አስፈሪ፣ አዝናኝ ወይም ከዚህ በተለየ ሁኔታ አስተማሪም ሊሆኑ ይችላሉ። በተለይ ከፖለቲካው ወሬ ውጭ የምናገኛቸው አንዳንድ ዜናዎች በአብዛኛው አስገራሚ የሚሆኑባቸው አጋጣሚዎች ይስተዋላሉ።
ሰሞኑን ኦዲቲ ሴንትራል የተባለውና ለስላሳ ዜናዎችን በመዘገብ የሚታወቀው ድረገጽ ይዞ የወጣው ዜናም ትንሽ ለየት ያለ በመሆኑ ልናካፍላችሁ ወደድን።
መቼም በዚህ ዘመን በሰለጠኑ አገራት የሚገኙ አንዳንድ ሰዎች የሚፈጽሟቸው ተግባራት አስገራሚም አስደንጋጭም የሚሆኑባቸው ሁኔታዎችን አልፎ አልፎ አንመለከታለን። በተለይ ለየት ያለ ሥራ ሰርተው ስማቸውን በወርቃማው የጊነስ መዝገብ ለማስመዝገብ አስቂኝና አንዳንዴም የሞኝ ሥራ የመሰሉ ሥራዎችን ሰዎች ሲያከናውኑ እንሰማለን።
በርግጥ በአገራችንም በጊነስ መጽሐፍ ላይ ስማቸውን ያሰፈሩ ጥቂት ግለሰቦች እንዳሉ አይዘነጋም። ለምሳሌ የሳቁ ንጉሱ በላቸው ረጅም ሰዓት በመሳቅ ስሙን በጊነስ መዝገብ ማስፈር የቻለ ኢትዮጵያዊ ነው። እነኃይሌ ገብረሥላሴን የመሳሰሉት አንጋፋ አትሌቶቻችን ደግሞ በርካታ ሪከርዶችን በመሰባበር በላባቸው ስማቸውን በታላላቅ መዝገቦች ያሰፈሩ መሆናቸውን እናውቃለን።
ሰሞኑን የ48 ዓመቱ ጂሚ ዴ ፍሬኔ የተባለ ቤልጅየማዊ ያስመዘገበው የዓለም ሪኮርድ ግን ከዚህ ቀደም ከምንሰማው ለየት ያለና የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ነው። ጂሚ ሪከርዱን ያስመዘገበው ረጅም ሰዓት መፀዳጃ ቤት በመቀመጥ ነው። ኦዲቲ ድረገጽ እንደዘገበው ዴ ፍሬኔ ለአምስት ተከታታይ ቀናት መፀዳጃ ቤት በጎድጓዳው የመጸዳጃ ሳህን ላይ በመቀመጥ ነው ሪኮርዱን ያስመዘገበው።
ዴ ፍሬኔ ከዚህ ቀደም በዚህ ዘርፍ የሚደረግ ውድድር መኖሩን ምንም ግንዛቤ አልነበረውም። ሆኖም በዚህ ዘርፍ ለ100 ሰዓታት መፀዳጃ ቤት ውስጥ በመቀመጥ ሪከርድ ስላለው የቀድሞው የሪከርዱ ባለቤት በሰማበት ወቅት «እኔስ ይህንን እንዴት ማድረግ ያቅተኛል» በሚል መነሳሳቱን ገልጿል። በዚህም መሠረት 168 ሰዓት ወይም ለአንድ ሳምንት በመፀዳጃ ቤት በመቀመጥ የራሱን ሪከርድ ለመያዝ ወሰነ። ሆኖም ለ116 ሰዓት በመፀዳጃ ቤት ከተቀመጠ በኋላ ሰውነቱ ከዚህ በላይ መቀመጥ ስላልቻለ ከመፀዳጃ ቤት ቢወጣም ሪከርዱን ግን መጨበጥ ችሏል።
ዴ ፍሬኔ በውድድሩ ወቅት በእያዳንዱ አንድ ሰዓት ለአምስት ደቂቃ እረፍት የሚፈቀድለት ሲሆን ይህንንም እንደ እንቅልፍ ሰዓት ይጠቀምበት እንደነበር አስታውሷል። በዚህም መሠረት በአምስቱ ቀናት በአጠቃላይ ከሦስት ሰዓት ያልበለጠ የእረፍት ጊዜ ወይም የእንቅልፍ ሰዓት ብቻ እንደነበረው ለማወቅ ተችሏል። በዚህ ወቅት የጊነስ ሪከርዱን የሚዘግብ ሰው ባይገኝም ምስክሮችና የአካባቢው ሰዎች እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 15/2011
ወርቁ ማሩ