«አፍሪካ የራሷን ችግር በራሷ መፍታት መቻል አለባት» -አምባሳደር ተፈራ ሻውል

ኢትዮጵያ ከጥንት እስከ ዛሬ የነጻነት ተምሳሌት ሆና ዘልቃለች፡፡ መላው አፍሪካ እና ጥቁር ሕዝብ በቀኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ ሲማቅቅ ከመላው ከጭቁኖች ጎን ተሰልፋ በርካታ ትግሎችን ያቀጣጠለች እና አፍሪካውያን ለነጻነታቸው እንዲታገሉ መንገድ ያመላከተች ብቸኛ ሀገር ነች፡፡ ዛሬም ይኸው ሚናዋ ጎልቶ ቀጥሏልበቀጣዩቹ ቀናትም 38ኛውን የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤን በተሳካ መልኩ ለማስተናገድ እንግዶችን በመቀበል ላይ ትገኛለች፡፡

የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ወቅታዊ የሆነውን የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ስብሰባን እና ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት እስከ አፍሪካ ሕብረት መቋቋም ድረስ የተጫወተችውን ሚና በተመለከተ ከአምባሳደር ተፈራ ሻውል ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

አምባሳደር ተፈራ ሻውል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ከጸሐፊነት እስከ አምባሳደርነት አገልግለው በኋላም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ አገልግለዋል፡፡ ከአምባሳደሩ ጋር የተደረገው ቃለመጠይቅም እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ወቅት ጋዜጠኛ ሆነው ሂደቱን በመዘገብ የታሪኩ አካል ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ላይ የነበራትን ሚና እንዴት ይገልጹታል?

አምባሳደር ተፈራ፡– መጀመሪያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት ጋዜጠኛ ሆኜ ተሳትፌያለሁ። አፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲቋቋም በካዛብላንካ እና በሞኖሮቪያ በተደረጉ ስብሰባዎች የተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች በቡድን ተከፋፍለው ነበር፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ በፕሬዚደንት ታፕ ማን ወደሚመራው ቡድን መልዕክተኞችን በመላክ ነጻ ያልወጡ ሀገራትን ነጻ የማውጣትና አፍሪካን አንድ የማድረግ ጉዳይ ሕብረት ከሌለ በቀር ሊሳካ እንደማይችል በማስረዳት እንዲሁም በሴኩ ቱሬ የሚመራውን ሁለተኛውን ቡድን በማግባባት በመጨረሻ የአዲስ አበባው ስብሰባ እንዲካሄደ ማድረግ ችለዋል፡፡

ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ ሚኒስትሮቻቸውን አቶ ከተማ ይፍሩ፣ አያሌው ማንደፍሮ፣ ጌታቸው መካሻ እና ሌሎች እውቅ ዲፕሎማቶቻቸውን በአኅጉሩ በማሰማራት ለመሪዎች ልዩ መልዕክቶችን በመላክ እና ራሳቸውም ሄደው ጉብኝት በማድረግ በማሳመን ነው በአውሮፓውያን አቆጣጠር ግንቦት 25 ቀን 1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መመስረት ያስቻለው የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ አዲስ አበባ ላይ እንዲካሄድ ያደረጉት፡፡

ቀደም ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንን ጽህፈት ቤት በአዲስ መልክ አሰርቶ ቁልፉን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አስረክቦ ስለነበር ኢትዮጵያ የመገናኛውን መንገድ አዘጋጀች፡፡ በወቅቱ ከነበሩት 32 የአፍሪካ መሪዎች 31 በሥብሰባው ላይ ተገኙ፡፡ የቶጎ መሪ በተቃዋሚዎቻቸው በመገደላቸው ምክንያት በሥብሰባው አልተወከለችም፡፡

ከዚያ በኋላ ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ በጣም የታወቁ የሕግ ባለሙያ በነበሩት አቶ ተሾመ ገብረማርያም አርቃቂነት እና በሌሎች ተባባሪነት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተር ረቂቅ ተዘጋጀ፡፡ ንጉሰ ነገሥቱ ካስተናገዱት ታሪካዊ ሥብሰባ በኋላ ቻርተሩ ተፈረመ። ለቻርተሩ መፈረም ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱት ጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ፣ ከተማ ይፍሩ፣ ጌታቸው መካሻ፣ ዶ/ር ስዩም ሀደጎት፣ አያሌው ማንደፍሮ፣ አምባደር መንግሥቴ ደስታ እና ሌሎችም ነበሩ፡፡

ንጉሡ በሥብሰባው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ከዚህ አዳራሽ አንድ የመስማሚያ ሰነድ ሳንፈርም አንወጣም ብለዋል፡፡ አፍሪካን ነጻ ለማውጣት እኛ አፍሪካውያን ከሌላው የምንጠብቀው ምንም ነገር የለም፤ ራሳችንን በራሳችን መርዳት አለብን የሚል ጥሪም አቅርበዋል፡፡ ከዚያም ስምምነት ላይ ደርሰው ለመፈራረም በቁ፡፡

የስምምነት ሰነዱ የመጨረሻ ገጽ ላይ የሁሉም የአፍሪካ መሪዎች ስምና ፊርማ አለ፡፡ መሪዎቹ ለአፍሪካ ክብር ለመስጠት ሲሉ በመጀመሪያ የፈረሙት በአማርኛ ቋንቋ የተዘጋጀው ሰነድ ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ በጽሁፍም ሆነ በሥነጽሁፍ በደምብ የተደራጀው ብቸኛው የአፍሪካ ቋንቋ አማርኛ ነበር፡፡ ይህ በአማርኛ የተዘጋጀው ሰነድ በእንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ ተተርጉሟል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ባሕል ለድርጅቱ መመስረት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡

ከመጀመሪያው ሥብሰባ በኋላ ብዙ ሂደቶች ታልፈው የአፍሪካ ነጻ አውጪ ኮሚቴ ተቋቁሞ ነጻ ሳይወጡ ቀርተው የነበሩ ሀገሮች ነጻ እንዲወጡ ተደረገ፡፡ በተለይም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ በቅኝ ግዛት ስር ያሉ ሀገራትን ነጻ እንዲያወጣ የተመሰረተው ኮሚቴ ሊቀመንበርነትን ለረጅም ጊዜ ይዘው የቆዩት የኢትዮጵያ መንግሥት መልዕክተኞች ነበሩ፡፡

አዲስ ዘመን፡የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተልዕኮውን አጠናቆ የአፍሪካ ሕብረት ሲመሰረት ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ባለሙያ ሆነው በሰብአዊ መብትና የፖለቲካ ጉዳዮች ቃል አቀባይነት በመድረኩ ተሳትፈው ነበርየሕብረቱን መመስረት ዛሬ ላይ ቆመው እንዴት ይገመግሙታል ?

አምባሳደር ተፈራ፡የአፍሪካ ሀገራት ነጻ ከወጡ ከብዙ ዓመታት በኋላ ደግሞ የአፍሪካ ሕብረት መመስረት አለበት የሚል ሀሳብ ቀርቦ በ2002 በደቡብ አፍሪካ ደርባን የአፍሪካ ሕብረት ተመሰረተ፡፡ እኔ በጣም እድለኛ ሰው ነኝ፡፡ እንደጠቀስከው በደቡብ አፍሪካ ደርባን የአፍሪካ ሕብረት ሲመሰረት ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቀጣሪ ሆኜ የሰብአዊ መብት እና የፖለቲካ ጉዳዮች ቃል አቀባይ ስለነበርኩ የምስረታ ሂደቱን መመልከት ችያለሁ፡፡

የመጀመሪያው የጋና ፕሬዚደንት ዶ/ር ክዋሚ ኑኩርማ የጋራ ሰራዊት፣ የጋራ ፖለቲካ እና የሀገራት ሕብረት ያለው መንግሥት እንመስርት ብለው ነበር፡፡ ያን ጊዜ ብዙዎች እርሳቸውን ከጊዜው የቀደሙ እብድ አድርው ነበር የሚመለከቷቸው፡፡ አሁን ቀስ በቀስ የተናገሩት ነገር ሁሉ እየመጣ ነው፡፡ በሕብረት ደረጃ የአፍሪካ ሕብረት ተመስርቷል፡፡ አሁን ብዙ ነገሮች በጋራ እየተሰሩ ነው። የቀጣናዊ የንግድና ኢኮኖሚ ድርጅቶችም ተፈጥረው እየተጠናከሩ መጥተዋል፡፡ በተለይ አሁን ባለንበት አሉታዊ የሶሻል ሚዲያ ዘመን መደበኛው የሚዲያ ሥራ የሕብረቱ ሀገራት የጋራ ሀገር ለመፍጠር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የማገዝ ኃላፊነት አለበት፡፡

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወራሽ የሆነው የአፍሪካ ሕብረት ለአፍሪካ ሕዝብ ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ ያደረገ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረትና መጠናከር የነበራት ጉልህ ሚና በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስርም ሳይጓደል ቀጥሏል፡፡

አዲስ ዘመን፡አዲስ አበባ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቀመጫ እንድትሆን ሲወሰን ሶማሊያ ጥያቄ አንስታ ነበር ?

አምባሳደር ተፈራ፡ሁለተኛው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሥብሰባ ካይሮ እንዲካሄድ ተደረገ፡፡ ካይሮ ላይ የተሰበሰቡት መሪዎች አዲስ አበባ የድርጅቱ መቀመጫ እንድትሆን እና በቅኝ ግዛት ዘመን የነበሩት ድንበሮች ሳይጣሱ እንዲቆዩ የሚሉ ሁለት ትልልቅ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት ያደረገችው አስተዋጽኦ፣ የአፍሪካ ሀገራት ከቀኝ ግዛት ነፃ ሲወጡ ለ 200 ሰዎች ነፃ የትምህርት ዕድል የሰጠች ሀገር መሆኗ እንዲሁም የአፓርታይድ ሥርዓት እንዲገረሰስ ኔልሰን ማንዴላን ከማሰልጠን ጀምሮ ደማቅ ታሪክ የሠራች ሀገር መሆኗ ለድርጅቱ መቀመጫነት ተመራጭ እንድትሆን አድርጓታል፡፡

በዚያን ጊዜ ሶማሌዎች ኢትዮጵያ ግዛታችንን ነጥቃለች ብለው ክርክር አንስተው ነበር፡፡ ጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ተነስተው በትክክል ታሪኩን በማስረዳት ተቀባይነት አግኝተው የኢትዮጵያን ጥቅም አስከብረዋል።

አዲስ ዘመን፡የቀድሞ አፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ አዲስ አበባ መሆን የለባትም የሚል ጥያቄ በተለያዩ መድረኮች ተነስቷል። የኢትዮጵያ መሪዎችና ዲፕሎማቶች ዋና መስሪያ ቤቱ ከአዲስ አበባ እንዳይወጣ ያደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ተጋድሎ ምን ይመስል ነበር ?

አምባሳደር ተፈራ፡አዲስ አበባ ላይ በተደረገው 10ኛው የመሪዎች ሥብሰባ ሊቢያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና መስሪያ ቤት ከኢትዮጵያ መነሳት አለበት የሚል ሀሳብ አቀረበች፡፡ በወቅቱ ዶ/ር ምናሴ ኃይሌ አፍሪካ ለሽያጭ የምትቀርብ አኅጉር አይደለችም፡፡ የመላው አፍሪካ መሪዎች የወሰኑት ውሳኔ በመሆኑ ሊቢያ ስላለች ብቻ አይቀየርም ብለው ባቀረቡት ሀሳብ ተሸንፋ ሙከራው ከሸፈ፡፡

እንደገና መሀመድ ጋዳፊ ከስልጣን ሊወርዱ ሦስት ዓመታት ሲቀራቸው አሩሻ ላይ በተካሄደ የሕብረቱ መሪዎች ሥብሰባ ላይም ተመሳሳይ ጥያቄ ሲነሳ በሙሉ የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት የሕብረቱ ጽህፈት ቤት አዲስ አበባ ሆኖ እንዲቀጥል ወስነዋል፡፡ ከዚያ በኋላ የሕብረቱ ጽህፈት ቤት ተስፋፍቶ በቻይና መንግሥት ድጋፍ ትልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ያካተተ ግዙፍ ሕንጻ ተገንብቶ ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና ሆና ቀጥላለች፡፡

በቡርኪናፋሶ በተደረገ ሌላ የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ላይም የሊቢያው መሪ መሀመድ ጋዳፊ የአፍሪካ ሕብረት ዋና መሥሪያ ቤት ከኢትዮጵያ እንዲነሳ ክርክር ሲያቀርቡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገች ሀገር ናት፡፡ ማነው ማንዴላን ለነጻነት እንዲዋጋ ያሰለጠነው? ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ አይደሉም ወይ? ማን ነው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲጠናከር ያደረገው? መንግሥቱ ኃይለማርያም አይደለም ወይ? ስለዚህ የምታቀርቡት ክርክር ውሃ አይቋጥርም ብለው በጠራ የዲፕሎማቲክ ቋንቋ እና በጥሩ እንግሊዘኛ አስረድተው የኢትዮጵያ ሀሳብ አሸንፏል፡፡

ስለዚህ በዘመናት የመጡ የኢትዮጵያ መሪዎች ሁሉ ስለአፍሪካ የሚያቀነቅኑት ሀሳብም ሆነ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ወሰን የለሽ እና ለድርድር የማይቀርብ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ የአፍሪካ ብሎም የዓለም ሰላም እንዲጠበቅ ያበረከተችው እና በማበርከት ላይ ያለችው አስተዋጽኦ ምን አንድምታ አለው ?

አምባሳደር ተፈራ፡– አገራችን በኮሪያ፣ ኮንጎ፣ ላይቤሪያ፣ ሩዋንዳ እና ሶማሊያ ሠላም አስከባሪ በመላክ የሚስተካከላት የለም። ኮንጎ ነጻነት እንድትጎናጸፍ ከማድረግ እና ነጻ ከወጣች በኋላም የነበረውን ችግር ለማረጋጋት ኢትዮጵያ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበራት፡፡

በኮንጎ የተሰማራውን ሰላም አስከባሪ ኃይል ይመሩ የነበሩት የጦር አዛዥ ጄኔራል ከበደ ገብሬ ነበሩ፡፡ የኮሪያ ታሪካችን እንደተጠበቀ ሆኖ አፍሪካን በተመለከተ ከኮንጎ በመጀመር በርዋንዳ፣ ላይቤሪያ፣ ብሩንዲ፣ ዳርፉር ሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን አብዬ እና ሶማሊያ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ተሰማርቶ የተባበሩት መንግሥታትን እና የአፍሪካ ሕብረትን ጥረት ደግፏል፤ አሁንም እየደገፈ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአትዮጵያን መከላከያ ኃይል በጣም ያከብራል፡፡

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአባል ሀገራቱ ቀጣናዎች የሰላም መጠባበቂያ ኃይል እንዲቋቋም አድርጓል፡፡ በምስራቅ አፍሪካ በተቋቋመው የቀጣናው ተጠባባቂ ኃይል ውስጥ እኔም ተሳትፌያለሁ፡፡ ወታደራዊ ክንፉ አዲስ አበባ እንዲሁም ማስተባበሪያ ቢሮው ደግሞ ናይሮቢ ሆኖ አሁንም ድረስ ያለ ኃይል ነው፡፡ ለዚህም ቀጣናዊ ኃይል መቋቋም ኢትዮጵያ የበኩሏን ድርሻ ተወጥታለች፡፡

አዲስ ዘመን፡የአፍሪካ ሕብረት እንደ አውሮፓ ሕብረት አይነት የጠነከረ አንድነት ለመፍጠር የሚያደርገው ጉዞ አንዳይፋጠን ያደረጉት ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው? መፍትሔውስ ምንድን ነው?

አምባሳደር ተፈራ፡የአፍሪካ ሕብረት አንድ ችግር አለበት፡፡ ሀገራቱ ቢሰባሰቡም ለድርጅቱ ሥራ ማስኬጃ የሚያስፈልገውን በጀት በማዋጣት ረገድ ጥቂት ሀገሮች ናቸው ወቅቱን ጠብቀው የሚከፍሉት። የተቀሩት በወቅቱ የሚጠበቅባቸውን አይከፍሉም፡፡ ይሄ ትልቅ ተግዳሮት ነው፡፡ መሀመድ ጋዳፊ በሕይወት በነበሩ ጊዜ የአንዳንድ ሀገራትን መዋጮ ይሸፍኑ ነበር። የእነዚህን ሀገራት ድጋፍ አገኛለሁ ብለው ነው በተደጋጋሚ የሕብረቱ መቀመጫ ከአዲስ አበባ እንዲነሳ ይጠይቁ የነበረው፡፡

የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ሀገራት ነጻ እንዲወጡ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ጥሩ ታሪክ ያለው ድርጅት ነው። እንደ አውሮፓ ሕብረት የተጠናከረ ድርጅት እንዲሆን አፍሪካውያን ራሳቸውን በራሳቸው ካልረዱ ማንም አይረዳቸውም፡፡ አንዳንድ ሀገራት የሚያደርጉት ርዳታም የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም የሚጠቀሙበት ሊሆን ይችላል፡፡

ሌላው የዴሞክራሲ እና የሕግ የበላይነት ነገር ነው፡፡ እያንዳንዱ የአፍሪካ መሪ የሕግ የበላይነት እና ዴሞክራሲ በሕሊናው እንዲሰርጽ ካላደረገ አህጉሩ ከችግር ሊወጣ አይችልም፡፡ በሌሎች ርዳታ ላይ ተንጠልጥሎ ሳይሆን ሕዝብን በማስተባበር በራስ አቅም ደህንነትን ማሸነፍ ይገባናል፡፡

አንድ ሕብረት ሲቋቋም ጥንካሬው የሚወሰነው በአባላቱ ጥንካሬና ቆራጥነት ነው፡፡ እያንዳንዱ የሀገር መሪ የግል ጥቅሙን እስካስቀደመ ድረስ እንቅፋት ይኖራል። በኤሲያ እና ላቲን አሜሪካም ተመሳሳይ ድርጅቶች አሉ፡፡ የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራት አንድ አይነት ገንዘብ ይጠቀማሉ፡፡ ዜጎቻቸው እንደልባቸው ከአንዱ ሀገር ወደሌላው ይጓዛሉ፡፡ አፍሪካውያን እዚህ ደረጃ ለመድረስ ራሳችንን ታግለን ማሸነፍ አለብን። ያለበለዚያ ለሚቀጥለው ትውልድ የምናወርሰው ዕዳ ከፍተኛ ነው የሚሆነው፡፡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳሉት ከዕዳ ወደ ምንዳ ለመሸጋገር ትልቅ ጥረት መደረግ አለበት፡፡

አፍሪካውያን ብዙ ፈተናዎች አሉብን፡፡ የውስጥ ሕብረት የሌላቸው የአፍሪካ ሀገራትና መንግሥታት በውጪው ዓለም ከአውሮፓ፣ ከኤሲያ፣ ከቻይና፣ ከአሜሪካ እና ከሌሎችም ጋር የሚያደርጉት ትብብር መስመር ሊይዝ አይችልም፡፡ መጀመሪያ የራሳቸውን ችግር ማሸነፍ አለባቸው፡፡ በኢትዮጵያም ውስጥ ቢሆን መቻቻልን፣ መነጋገርን፣ መወያየትን እና መመካከርን በማስቀደም ኃይልን ከመፈለግ ይልቅ ፖለቲካዊ መፍትሄ በመፈለግ ለተቀረው አፍሪካ ምሳሌ መሆን ይጠበቅብናል። ምክንያቱም አፍሪካ እኛን ነው የሚመለከተው፤ እኛ ገደል ከገባን አፍሪካም ገደል ገባ ማለት ነው፡፡

የኮንጎን ወንዝ ምሳሌ አድርጌ ባነሳልህ በብራዛቢል እና በኪንሻሳ መካከል ያለው ትንሹ ርቀት ሦስት ኪሎ ሜትር ነው፡፡ እኔ በመካከለኛው ምስራቅ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኃላፊ ሆኜ ስብሰባ በምናደርግበት ጊዜ የሁለቱን ኮንጎዎች ውጭ ሚኒስትሮች ይህችን ሦስት ኪሎ ሜትር ድልድይ ሰርታችሁ ማገናኘት ያቃታችሁ ለምንድን ነው ብዬ ጠየቄያቸው ነበር፡፡ ኮንጎ ብራዛቢልም ሆነች ኮንጎ ኪንሻሳ ነዳጅ አላቸው፡፡ የአንድ ቀን የነዳጅ ምርታችሁን ለዚህ ድልድይ ብታውሉት ምን አለበት ስላቸው፣ እኛ ምን እናድርግ ፕላኑ አለ ነገር ግን መሪዎቻችን እምቢ አሉ ነው ያሉኝ፡፡ ስለዚህ መሪዎች ራሳቸውን ለልማትና ለነጻነት እስካላሰለፉና የግል ጥቅምን በማሳደድ እስከተሰማሩ ድረስ የአፍሪካ ችግር በቀላሉ አይቀረፍም፡፡

አዲስ ዘመን፡ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጀት የጸጥታው ምክር ቤት ውክልና እንድታገኝ የሚጠይቅ የአፍሪካ መሪዎች ድምጽ ከፍ ብሎ እየተሰማ መጥቷል፡፡ አፍሪካ በምክር ቤቱ የምትወከል ከሆነ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረትም ሆነ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ካላት ታሪካዊ ሚና አንጻር ውክልናውን ለማግኘት ዝግጅት ማድረግ አይኖርባትም?

አምባሳደር ተፈራ፡በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ውስጥ አፍሪካ ውክልና ማግኘት አለባት፡፡ ምክንያቱም በምክር ቤቱ የትኛውም ውሳኔ የሚተላለፈው ቻይናን ጨምሮ በአምስቱ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት አሸናፊ ሀገራት ነው፡፡ ይሄ የጥቂት ሀገራት ሥብስብ የሆነ ቡድን ብቻ ወሳኝ ሆኖ መቀጠል የለበትም፡፡ አሁን ጀርመን ትልቅ ሀገር ነው አውሮፓን ሊወክል ይችላል፤ ሌሎች ሀገራትም አሉ፡፡ አፍሪካን የመሰለ ትልቅ አኅጉር በተባበሩት መንግሥታት ምክር ቤት እስካሁን አለመወከሉ ትክክል ባለመሆኑ መሻሻል ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

ኢትዮጵያ መጀመሪያ የአፍሪካ ነጻነት እንዲረጋገጥ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በፊት በነበረው ሊግ ኦፍ ኔሽንስ ውስጥ ደቡብ አፍሪካ ላይ ይደረግ የነበረውን ጭቆና ለማስወገድ የተከራከረች ሀገር ከመሆኗ አንጻር ለጸጥታው ምክር ቤት እጩ መሆን አለባት፡፡ ይሄ እንግዲ በራሳችን ዲፕሎማቶች ጥረትና አጋሮቻችን ድምጽ ሲሰጥ በሚያደርጉልን ድጋፍ የሚወሰን ይሆናል፡፡ የሌሎች ሀገራትን ድጋፍ ለማግኘት ደግሞ እያንዳንዱ ዜጋ ለሀገሩ ዲፕሎማት ሆኖ በተቻለው መጠን የማግባባት ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡

አዲስ ዘመን፡ኢትዮጵያ በታሪክ ተጠቃሽ የሆኑ ስመ ገናና ዲፕሎማቶች የነበሯት ሀገር ናት፡፡ የዚህ ዘመን ዲፕሎማቶቿ የአባቶቻቸው ልጆች ናቸው ብለው ያምናሉ?

አምባሳደር ተፈራ፡አሁንም በጣም በሳል ዲፕሎማቶች አሉን፡፡ እነዚህ ዲፕሎማቶች የሚያደርጉትን ጥረት እስካሁን እንደሚያደርጉት አጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡ እነ ከተማ ይፍሩን መልሰን መውለድ፤ እነ ጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉን መልሰን ማምጣት አንችልም። ነገር ግን የእነርሱ ታሪክ ለዚህ ትውልድ ምሳሌ ሆኖ ለዲፕሎማሲ ባሕላቸው አጋዥ ሊሆን ይችላል፡፡

አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ በባሕር በር ጉዳይ ከሶማሌ ላንድ ጋር ባደረገችው ስምምነት ችግር ሲፈጠር ሶማሊያ ብዙ እንቅስቃሴ አድርጋ ነበር፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ከቱርክና ከሌሎች ሀገራት ጋር ባላት ጥሩ ግንኙነት ሁኔታው ቶሎ ሊረግብ ችሏል፡፡ ይሄ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ባሕል ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር ያደረገችውን ስምምነት በአንድ በኩል «በሳል የዲፕሎማሲ አካሄድ» በሌላ በኩል ደግሞየዲፕሎማሲ ኪሳራ ያስከተለብለው የሚገልጹት ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ጉዳዩን እንዴት ይመለከቱታል?

አምባሳደር ተፈራ፡ፖለቲካ ተለዋዋጭ ነው። ኢትዮጵያ እስከዛሬም ከዲፕሎማሲ ማማ ላይ ወርዳ አታውቅም፡፡ የጂኦፖለቲካ ሁኔታ በየጊዜው ተለዋዋጭ ነው፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ በመካከለኛው ምስራቅ ኢራን ትልቅ ሚና ትጫወታለች፡፡ እስራኤልም እንዲሁ ከፍተኛ ሚና አላት፡፡ ግብጽ ብዙ ጊዜ በአደራዳሪነትና በድለላነት ትሰራለች፡፡ አሜሪካ ደግሞ አሁን በዘመነ ትራምፕ ሁሉን ልወስን ትላለች፡፡ ዓለማችን በተለዋዋጭ የጂኦፖለቲካ ውስጥ እንደመሆኗ ኢትዮጵያም ያንን እየተከተለች እየሰራች ነው፡፡ ስለዚህ በዲፕሎማሲያዊ አቅሟ ወረደች ወጣች የሚል ጥያቄ ሳይሆን መነሳት ያለበት፣ አሁን ያሉት የፖለቲካ ተዋንያን እነማን ናቸው እንዲሁም እንዴት ነው እነሱን መቋቋም በሚያስችል መንገድ የዲፕሎማሲ አካሄዳችን ማሻሻል ያለብን የሚለው ነው፡፡

ብዙ ነገር መሥራት የሚገባው በግብታዊነት ሳይሆን አስቦና ተጨንቆ ነው፡፡ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው ብትል ጨዋታውን ማወቅ አለብህ፡፡ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ በዘመናቸው ከፋሺስቶቹም ኮሚኒስቶቹም ከካፒታሊስቶቹም ጋር ይደራደሩ ነበር፡፡ ምክንያቱም ያሳስባቸው የነበረው የኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም ነው። አሁንም የአፍሪካ መሪዎች የአኅጉሪቱን ዘላቂ ጥቅም ለማስከበር በመተባበር ከሁሉም ኃይሎች ጋር መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ በፖለቲካና ዲፕሎማሲ ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ወዳጅ የለም፡፡ የአኅጉሪቱ አንድነት የሁሉንም የአፍሪካ መንግሥታት ትብብር ይጠይቃል፡፡

አዲስ ዘመን፡ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ መሆኗን ምን ያህል ተጠቅማበታለች ?

አምባሳደር ተፈራ፡በደምብ ተጠቅማበታለች። በኮንፍረንስ ቱሪዝም ብዙ አትርፋለች፡፡ በዚህ ዘመን ደግሞ የአፍሪካ ቪሌጅ እየገነባን ነው፡፡ አሁን በቅርቡ በቡራዩ በተከፈተው ኩሪፍቱ ሆቴል ላይ የተሠራው ሥራ የሚያስደንቅ ነው፡፡ በእነ ከተማ ይፍሩ እና ጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ስም አዳራሾች መሰየማቸው የሚያስመሰግን ነው፡፡ የዳግማዊ ምኒሊክ እና የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ቤተመንግሥት ታድሶ የኢትዮጵያ ታሪክ አሸብርቆ መታየት አሁን ላለው የለውጡ ኃይል የሰራው ትልቅ ውለታ ነው፡፡ አሁን ያለው መንግሥት ብዙ ነገር አጥፍቷል ብለው የሚከራከሩ ወገኖች ሊኖሩ ይችላሉ ነገር ግን የተሰራውን ተጨባጩን ሀቅ መሬት ላይ እያየን ነው፡፡ ይሄ መቀጠል ነው ያለበት፡፡

አዲስ ዘመን፡አዲስ አባባ በአራቱም ማዕዘናት እየተሰራ የሚገኘው የኮሪደር ልማት አዲስ መልክ እየያዘች ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ገጽታ መላበስ በአፍሪካ መዲናነቷ ላይ ምን አይነት እሴት ይጨምራል ?

አምባሳደር ተፈራ፡ኢትዮጵያ ሁልጊዜ ቀድማ ነው የምትሄደው፡፡ ለአፍሪካ ሕብረት ስታደርግ የኖረችው አስተዋጽኦም ይሄ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ሆቴሎች በደምብ ተስፋፍተዋል፡፡ መንገዶችም ሰፍተዋል፡፡ መሃመድ ጋዳፊ አንድ ሰሞን ‹‹አዲስ አበባ ቆሻሻ ከተማ ናት፡፡ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫውን መቀየር አለበት›› ብሎ ሰድቦን ነበር፡፡ ጋዳፊ ዛሬ በሕይወት ኖሮ የአዲስ አበባን አሁናዊ መልክ ቢመለከት ደስ ይለኝ ነበር፡፡

አዲስ አበባ ተለውጣለች፤ እየተለወጠችም ነው፡፡ ይሄ ለውጥ ደግሞ የሚያስከፍለው ብዙ መስዋዕትነት አለ። በከተማዋ ላይ እየተሰሩ ያሉ የልማት ሥራዎች ለቱሪዝም ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በዚህ መኩራት አለብን፡፡ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ልዩነቶች ቢኖሩንም እንኳን በአፍሪካ ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግሥታት እስከዛሬ ድረስ ላደረጉት አስተዋጽኦ እውቅና መስጠት አለብን፡፡

ለሥብሳባው የሚመጡ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እና ዲፕሎማቶቻቸው ወደፊት ቤተሰቦቻቸውንም ይዘው የአፍሪካ መዲና የሆነችውን አዲስ አበባ ለመጎብኘት እንዲነሳሱ በሚያደርግ ደረጃ አማላይ እንድትሆን የማድረግ ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ እያንዳንዳችን ደጃችንን በመጥረግና ቤታችንን በማሳመር የምንተባበርበት ጉዳይ ነው፡፡

አዲስ ዘመን:- ለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ስም አመሰግናለሁ?

አምባሳደር ተፈራ፡እኔም አመሰግናለሁ?

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ሐሙስ የካቲት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You