የምንገኝበት 21ኛው ክፍለዘመን ከሚታወቅባቸው ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ ስልጣኔ እንደሆነ ሁላችንም እንገነዘባለን። አዳዲስ ነገሮችን ወይም ክስተቶችን ባየን ቁጥርም “አይ የ21ኛው ክፍለዘመን ሰው” ማለት የተለመደ ነው። በተለይ በቴክኖሎጂው መስክ ይህ ክፍለዘመን የደረሰበት ደረጃ ክፍለዘመኑን በበጎ ጎኑ እንዲዋጅ ያደርገዋል።
የዚህ የሰለጠነ ዘመን ባለቤት ደግሞ የሰው ልጅ ነው። ምክንያቱም የስልጣኔውም ዋነኛ መንስኤና ተጠቃሚ ራሱ የሰው ልጅ ነውና። ይህ ሃቅ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን የስልጣኔ መገለጫው ምንድነው? ለሚለው ጉዳይ የተለያዩ ጉዳዮች ሊነሱ ይችላሉ። ለዛሬው ግን ከነዚህ የስልጣኔ ማሳያ መንገዶች ውስጥ ጥቂቱን ብቻ ላንሳ።
ስለስልጣኔ ሲነሳ በቅድሚያ በአእምሮአችን የሚመጣው ከተማና ከተሜነት ነው። ምክንያቱም በከተሞች ለስልጣኔ መንስኤ የሆኑት አብዛኞቹ የተማሩ ሰዎች፣ ቴክኖሎጂውና ሌሎችም ሉአላዊነትን የሚያሳዩ መንገዶች በቀላሉ ይገኛሉና። በዚህ የተነሳም በአገራችን ይህ “ከተሜ” ነው ሲባል በአብዛኛው የሚገልፀው ወይም ቃሉን የምንጠቀምበት ለስልጣኔ ነው። “የሰለጠነ” ለማለት። ይህንን ትርጉም በአእምሮአችን ይዘን እስኪ አንዳንድ ተግባራትን እንመልከት።
መቼም አዲስ አበባ ለአገራችን ምን ያህል የከተሜነት ትልቋ መገለጫ እንደሆነች መናገር ለቀባሪ ማርዳት እንዳይሆን እንጂ ሁሉም የሚያውቀው ሃቅ ነው። አዲስ አበባ በብዙ ነገር የከተማችን ትልቋ ከተማ ናት(ከእድሜ በስተቀር)። አዲስ አበባ ከታናሿ ድሬዳዋ በአስር እጥፍ የምትበልጥ፣ የአገሪቱ ዋና ከተማ፣ የአፍሪካ መዲና፣ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች መቀመጫ፣ ከአንድ መቶ በላይ ኤምባሲዎች መናኸሪያ፣ ወዘተ ከተማ ናት። ከዚህ ባሻገር አዲስ አበባ ለአገራችን ከተሞች ሁሉ ተምሳሌት መሆን ያለባት መሪያቸው ናት።
ነገር ግን “አዲስ አበባ እንደስሟ ናት ወይ” የሚል ጥያቄ ሲነሳ በርካታ ጥያቄዎች ይነሱባታል። ነዋሪዎቿም ቢሆኑ ከዚህ ትልቅ ከተማ የሚጠበቀውን ተግባር የማከናወን አቅም አላቸው ወይ ሲባል ብዙዎቹ ጥርጣሬ ይገባቸዋል። ለምሳሌ በሌሎች ከተሞች ከምናየው በተለየ ሁኔታ ስልጣኔን የሚገዳደሩ ድርጊቶች ጎልተው የሚታዩባት ከተማ አዲስ አበባ ናት። ከነዚህ ውስጥ አንዱ ፅዳት ነው።
በአዲስ አበባ በመንገድ ላይ መሽናት እንደነውር መታየት የቀረ እስከሚመስል ድረስ ቆሞ መሽናት የተለመደ ነው። አንዳንዱ ሱፉን ለብሶና ከረባት አስሮ(በአብዛኛው የተማረ ወይም የሀብታም መገለጫ ስለሆነ) መንገድ ዳር አጠገቡ ከቆመው ጓደኛው ጋር እያወጋ ያለምንም ሃፍረት የሚሸናባት ከተማ አዲስ አበባ ናት።
በመንገድ ዳር አፋቸውን ከፍተው የተቀመጡ ቱቦዎች ሁሉ መፀዳጃ ቤት እስከሚመስሉ ድረስ ማንም አላፊ አግዳሚ ቆሞ የሚሸናበት ከተማ አዲስ አበባ ነው። በዚህ የተነሳ አንድ መንገደኛ በድንገት አንድ ቱቦ ሲያገኝ ቆሞ ቢሸና እሱ የአዲስ አበባ ነዋሪ ነው ለማለት ያስደፍራል።
ይህ ድርጊት ግን ከአዲስ አበባ ውጪ ብዙም አይታይም። አብዛኞቹ ትናንሽ ከተሞቻችን እንኳን በዚህ ደረጃ የወረደ ተግባርን ሲያስተናግዱ አይታይም። ታዲያ ስልጣኔ ያለው የት ነው? የሚል ጥያቄን ያስነሳል።
ሁለተኛው ጉዳይ የትራፊክ ህግን ስለማክበር ነው። በአገራችን የትራፊክ አደጋ የአብዛኛውን ህይወት እየቀጠፈ ያለ ትልቅ ፈተና ነው። በዚህ ላይ መንግስትም ሆነ የተለያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶች ችግሩን ለመግታት ጥረት ያደርጋሉ። ይህን አደጋ ለመከላል ዋነኛ መፍትሄ ተደርገው ከሚወሰዱ ጉዳዮች አንዱ ደግሞ እግረኞች ግራቸውን ይዘው እንዲጓዙ ማስተማር ነው። በዚህ ረገድም በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።
ነገር ግን ይህንን ተግባራዊ ማድረግ ላይ በርካታ ውስንነቶች እንዳሉ ይታወቃል። በተለይ በአዲስ አበባና በሌሎች የአገራችን ከተሞች እንዲሁም በገጠር ቀበሌዎች ያለው ልዩነት አስገራሚ ነው። በአንፃሩ የስልጣኔ ደረጃቸው ላቅ ይላል ተብሎ በሚጠበቅበት አዲስ አበባ ከመኪና ጋር እየተጋፉ መሄድ የስልጣኔ መገለጫ እስከሚመስል ድረስ የተለመደ ነው። በአዲስ አበባ ከመኪና ጡሩምባ ይልቅ ከመንገድ ዳር የማይጠፉ አህዮች ይፈራሉ።
በርግጥ አንዳንድ አሽርካሪዎችም ከትራፊክ ህጉ ይልቅ ትራፊክ ፖሊሱን ይበልጥ የሚፈራበት ሁኔታ ይስተዋላል። ለምሳሌ ቀይ መብራት “ቁም” የሚል ህግ መሆኑን ማንም አሽከርካሪ የሚያውቀው ህግ ነው። ነገር ግን ይህንን ህግ የትራፊክ ፖሊስ አለመኖሩን አይቶ የሚጥስ አሽከርካሪ አለ። የ”ዜብራ” መንገድም ለእግረኞች ቅድሚያ ስጥ የሚል ምልክት ነው። ነገር ግን ይህንን ከሚያከብረው አሽከርካሪ ይልቅ የማያከብረው ይበዛል።
በአንጻሩ ወደገጠር ወጣ ስልን የምናገኘው ደግሞ ከዚህ የተለየ ነው። ከአዲስ አበባ በተለይ ወደምእራብ እና ሰሜን አቅጣጫ ወጣ ሲባል ሁሉም ሰው ግራውን ይዞ ሲጓዝ ማየት አዲስ አይደለም። በነዚህ አካባቢዎች ቀኙን ይዞ የሚሄድ ሰው ከተገኘ እሱ ለአካባቢው እንግዳ ነው ማለት ነው። ወይም በአብዛኛው ከአዲስ አበባ የሄደ ሰው ነው ማለት ነው። ታዲያ የትኛው ነው ስልጣኔ የገባው የሚለው ጥያቄ እዚህጋ ይነሳል።
በአጠቃላይ ስልጣኔ ማለት በቴሌቪዥን መስኮት የምናየውን የባህር ማዶ ባህል እንዳለ ገልብጦ እዚህ መጠቀም ከሆነ ከተሜው ሻል የሚልበት መንገድ ብዙ ሊሆን ይችላል። ለምሳ የፀጉር ስታይል፤ አለባበስ፣ እርቃን መሄድ፣ ወዘተ። ስልጣኔ ግን ከዚህ ውጪ ብዙ ነገር ማለት ነው። እናም በተለይ በከተሞች አካባቢ፣ በተለይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ስለስልጣኔ ትንሽ መለስ ብለን ራሳችንን ማየት ያለብን በርካታ ጉዳይ መኖሩን ልብ እንበል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 15/2011
ወርቁ ማሩ