
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ለሀገር ስፖርት እድገት ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተገለጸ። አካዳሚው ከየካቲት 03-04/2017 ዓ.ም በአርባምንጭ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባዘጋጀው የምክክር መድረክ፣ ለኢትዮጵያ ስፖርት እድገት የጎላ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተጠቁሟል። “ለሀገራችን ስፖርት እድገት፣ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሚና የላቀ ነው” በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው የምክክር መድረክ የአካዳሚውን የአስር ዓመታት ጉዞ በተመለከተ ሰነድ ያቀረቡት እውቁ የ3ሺ ሜትር መሰናክል ውድድር አሰልጣኝ ተሾመ ከበደ፣ አካዳሚው በነዚህ ዓመታት በተለያዩ ስፖርቶች ከክለብ ጀምሮ እስከ ብሔራዊ ቡድን በርካታ ስፖርተኞችን ማስመረጥ እንደቻለ ጠቁመው፤ አካዳሚው ያፈራቸው ስፖርተኞች በርካታ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ክብረወሰኖችን መስበር እንደቻሉ አስረድተዋል። በውጤት ረገድም ከሀገር ውስጥ እስከ ተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮችና ኦሊምፒክ ድረስ ኢትዮጵያን ማስጠራት እንደቻሉም አሰልጣኙ ባቀረቡት ሰነድ ገልጸዋል።
እንደ አሰልጣኝ ተሾመ ገለፃ፣ አካዳሚው በነዚህ ዓመታት ለታዳጊዎችና ወጣቶች በአስር የስፖርት አይነቶች ስልጠና እየሰጠ ውጤታማ መሆን የቻለው ተሰጥኦ ከመለየት ጀምሮ እስከ ምልመላና ስልጠና ባለው ሂደት ሳይንሳዊ መንገድ በመከተሉ ነው።
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 249/2003 ከተቋቋመ በኋላ ተተኪ ስፖርተኞችን የማፍራት ግብ ይዞ በአስር የስፖርት አይነቶች ከመላ ሀገሪቱ ታዳጊዎችን በመስፈርት እየመለመለ የተጓዘበትን መንገድ አሰልጣኝ ተሾመ ባቀረቡት ሰነድ በዝርዝር አሳይተዋል። አካዳሚው በነዚህ ዓመታት አዲስ አበባና አሰላ በሚገኙ የማሰልጠኛ ማዕከላቱ በርካታ ስኬቶችን እንዳስመዘገበው ሁሉ የተለያዩ ፈተናዎችን ማሳለፉንም አሰልጣኙ ጠቁመዋል።
የታዳጊዎች ምልመላን በተመለከተ አካዳሚው በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢ ተሰጥኦን በመለየት እንደየአካባቢው እምቅ የስፖርት አቅም በሳይንሳዊ መስፈርት ብቻ እየሠራ እንደሚገኝ አሰልጣኙ አስረድተዋል። ያምሆኖ እንደ ሀገር አብዛኞቹ የታዳጊ ፕሮጀክቶች ከ17 ዓመት በታች ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው መሥራታቸው የራሱ ችግር አለው። እንደሌላው ዓለም ከስድስት ዓመት ጀምሮ ሕፃናት ላይ(Grass root) ላይ እየተሠራ አይደለም። በዚህ እድሜ ላይ የሚገኙ ሕፃናት ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በአካዳሚዎችና ፕሮጀክቶች ውስጥ ለመሥራት ቤተሰብም ፍቃደኛ አይሆንም። ሕፃናቱ ከቤተሰብ ሳይለዩ የሚሰሩበት ሥርዓት አለመኖሩም ለዚህ አንዱ ምክንያት መሆኑን አሰልጣኙ ገልጸዋል።
የስፖርት መሰረተ ልማትን በተመለከተ እንደ ሀገር ባለፉት አራት ዓመታት የአዲስ አበባ ስቴድየም እድሳቱ ባለመጠናቀቁ ምክንያት አትሌቶች ልምምድም ይሁን ውድድር የሚያደርጉበት መም ማጣታቸው ይታወቃል። በዚህም ምክንያት ሀገር አቀፍ ውድድሮችና ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ዝግጅቶች የሚደረጉት በአካዳሚው መም ላይ ነው። ይህም የአካዳሚው መም ሥራ እንዲበዛበትና እንዲጎዳ ማድረጉን አሰልጣኝ ተሾመ ጠቅሰዋል። ይህ ደግሞ የአካዳማው ተልዕኮ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል። ስለዚህም የአዲስ አበባ ስቴድየም እድሳትንና የሌሎች ስቴድየሞችን ግንባታ በፍጥነት በማጠናቀቅ አካዳሚው ላይ ያለውን ጫና ማስተንፈስ እንደሚያስፈልግ አሰልጣኙ አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ የቤት ውስጥ መም(ትራክ) ሳይኖራት በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከዓለም አንደኛ ሆና ያጠናቀቀችበትን ውጤት ያስታወሱት አሰልጣኝ ተሾመ፤ አካዳሚው ያሉት ጅምናዚየሞች አነስተኛ የመሮጫ መም ሊያሠሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል። ይህም ኢትዮጵያ የቤት ውስጥ መም ያላት የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት እንድትሆን ከማስቻሉ በተጨማሪ በቤት ውስጥ ዓለም አቀፍ ውድድሮችም ይበልጥ ስኬታማ እንደሚያደርጋት በማስረዳት ለሚመለከተው አካል የቤት ሥራ ሰጥተዋል።
አካዳሚው ባለሙያዎች በትምህርትና ዓለም አቀፍ ስልጠናዎች ራሳቸውን እንዲያጎለብቱ በርካታ ሥራዎችን ማከናወኑን የጠቆሙት አሰልጣኝ ተሾመ፣ አካዳሚው ይበልጥ እውቀቶችን ማስፋት እንዳለበትም አስረድተዋል። የውጪ ተሞክሮ አለመኖር፣ የስፖርት ትጥቅ ጥራትና መጠንም የአካዳሚው ፈተናዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በምክክር መድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ፣ አካዳሚው ተተኪ ስፖርተኞችን በማፍራት፣ የሀገሪቱን የስፖርት ሙያተኞች በማሰልጠንና ችግር ፈቺ የሆኑ የስፖርት ጥናትና ምርምሮችን በመሥራት ለኢትዮጵያ ስፖርት እድገት እያበረከተ የሚገኘውን የላቀ አስተዋፅኦ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመደገፍ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ማገዝ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ፣ልማት እና የባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቀሰሙ ማሞ በበኩላቸው፣ “ስፖርት የሕዝብ ነው፣ ስፖርት እንደ ሀገርና ዓለም የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳው ከፍ እያለ በመሆኑ አካዳሚው እንደ ሀገር እየሠራ ያለው ሥራ የሚያስመሰግነው ነው በማለት የተናገሩ ሲሆን፤ አካዳሚው ሕዝብና መንግሥትን እንደ ድልድይ ሆኖ እያገለገለ በመሆኑ መሰል የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረኮችም የስፖርቱን ስብራቶች ለመጠገን ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ አብራርተዋል።
የአካዳሚው ዳይሬክተር አቶ አንበሳው እንየው ባደረጉት ንግግርም፣ አካዳሚው በመንግሥት የተሰጠውን ተተኪ ስፖርተኞች የማፍራት ተልዕኮ በአግባቡ እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 5 ቀን 2017 ዓ.ም