በሊቢያ የ28 ስደተኞች የጅምላ መቃብር ተገኘ

አዲስ አበባ፡- የሕገ-ወጥ ስደተኞች መተላለፊያ በሆነችው ሊቢያ ስደተኛ መሆናቸው የተገመተ የ28 ሰዎች የጅምላ መቃብር መገኘቱን ቢቢሲ ዘግቧል።

የጅምላ መቃብሩ የተገኘው፤ በደቡብ ምስራቅ ሊቢያ ኩፍራ በተባለች ከተማ አቅራቢያ ሲሆን ከቀናት በፊት በዚችው ከተማ ላይ አስራ ዘጠኝ የሚደርሱ አስከሬኖችን የያዘ ሌላ የጅምላ መቃብር መገኘቱ አይዘነጋም፡፡

የአካባቢው ባለሥልጣናት የሕገ-ወጥ ሰዎች ዝውውር ይፈጸምበታል የተባለውን ቦታ ከተቆጣጠሩ በኋላ የተገኘ የጅምላ መቃብር እንደሆነ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ገጹ አጋርቷል። በዚሁ ሥፍራ በአጋቾች ቁጥጥር ስር የነበሩና በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ የቆዩ 76 የሚሆኑ ስደተኞችን መታደግ እንደተቻለ የባለሥልጣናቱ ልሳን አስታውቋል። በዚህ ሕገ-ወጥ ተግባር ላይ ከተሳተፉት ውስጥ አንድ ሊቢያዊ እና ሁለት የውጪ ዜጎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል፡፡

መግለጫው አያይዞም ‹ይህ ወሮበላ ቡድን በሕገ-ወጥ መንገድ በገቡ ስደተኞች ላይ ግፍና መከራ በማድረስ ነፃነታቸውን በመቀማት፣ ስቃይና ጭካኔን በመፈጸም ለውርደትና ለሰብዓዊ ጥቃት ዳርጓቸዋል› ብሏል። በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋሩት የፎቶ እና የቪዲዮ ምስሎች የሕግ አካል እና በጎ ፍቃደኞች በአሸዋማ ስፍራው ላይ ቁፋሮ ሲያካሂዱ እንዲሁም አስከሬኖችን በጥቁር ፕላስቲክ ላይ ሲያስቀምጡ አሳይቷል፡፡

ሊቢያ ብዙዎች ከተስፋቸው ተስተጓጉለው ባዷቸውን የቀሩባት፣ በሞትና በብዙ ስቃይ በረሃ ላይ የቀሩ ስደተኞችን ታሪክ የያዘች መሆኗ ይታወቃል። የአፍሪካ ወጣቶች የተሻለ ኑሮ ፈልገው በሚያደርጉት ሕገ-ወጥ ስደት የበረሃ እና የባሕር ሲሳይ ሲሆኑ ማየት የተለመደ ነው። በኩፍራ አቅራቢ የተገኘው የጅምላ መቃብርም የዚህ ታሪክ አንድ ምዕራፍ ነው። ከሊቢያ መዲና ትሪፖሊ በአንድ ሺህ ሰባት መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በዚችው ከተማ አቅራቢያ እየተካሄደ ያለው ቁፋሮ መቀጠሉ ተነግሯል፡፡

በጅምላ መቃብሩ የተገኙት አስከሬኖች ለምርመራ መወሰዳቸውን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ያስታወቀ ሲሆን ባለሥልጣናቱ ከአደጋው የተረፉ ስደተኞችን ምስክርነት እየሰሙ እንደሚገኙ ነው የተገለጸው። የዛሬ ዓመት በዚሁ ወቅት የስልሳ አምስት ስደተኞችን አስከሬን የያዘ የጅምላ መቃብር መገኘቱን ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ማስታወቁ ይታወሳል። በወቅቱ ተቋሙ ይሄን ክስተት ለመግለጽ ‹በጣም አስደንጋጭ› የሚል የኅዘን ስሜትን ነበር የተጠቀመው፡፡

ስደተኞቹ በምን ምክንያት እንደሞቱ እና የየት ሀገር ዜጋዎች እንደሆኑ እስካሁን ያልታወቀ ሲሆን በሊቢያ በኩል ወደሜዲትራኒያን ባሕር ሲወሰዱ እንደሞቱ ግን መላ ምት አለ። የብዙዎቹ ስደተኞች ዕጣ ፈንታ በረሃ ላይ መቅረትና ባሕር ላይ ሰምጦ መቅረት በመሆኑ የነዚህ ሟች ስደተኞች ዕጣ ፈንታም ከዚህ የተለየ አለመሆኑ ተነግሯል፡፡

ሊቢያ ብዙ ስደተኞች በአደገኛው የሜዲትራኒያን ባሕር በኩል በማቋረጥ ወደ አውሮፓ ለመግባት የሚፈልጉ ስደተኞች ከሚጠቀሙበት አማራጭ መካከል ዋነኛው መሆኑ ይታወቃል። በተለይ የሊቢያውን መሪ መሐመድ ጋዳፊ ከሥልጣን መገርሰስ ተከትሎ በሀገሪቱ የተፈጠረውን መከፋፈልና ግጭት እንደጥሩ አጋጣሚ በመቁጠር በርካቶች ሊቢያን መሸጋገሪያ አድርገው ይመርጧታል። በዚህ አደገኛ ውሳኔያቸውም ለሞት የሚዳረጉት ጥቂቶች አይደሉም።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ መረጃ ከሆነ በባለፈው የአውሮፓውያኑ 2024 ብቻ ወደአውሮፓ ለመድረስ ሜዲትራኒያን ባሕርን ሲያቋርጡ የጠፉ ሰዎች ቁጥር ከሁለት ሺህ ሁለት መቶ መብለጡን በመግለጫው ማስታወቁ ይታወሳል። በርካታ ስደተኞች ለሕገ-ወጥ ስደት መሸጋገሪያነት የሚመርጧት ሊቢያ እንደምትታሰበው ሳይሆን ብዙዎችን በበረሃዋ አስቀርታለች። መረጃውን ከቢቢሲ እና ከሌሎች የዜና ምንጮች አግኝተነዋል፡፡

በሚያዚያ 2007 ዓ.ም ሊቢያን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት ያሰቡ 30 ኢትዮጵያውያን በአይኤስ አይኤስ ታግተው በግፍ መገደላቸው የሚታወስ ነው፡፡

ዘላለም ተሾመ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You