ከግብይት ማዕከላት ውጪ በሚደረጉ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፡የተለያዩ የእህል ምርቶች ከሚሸ ጡባቸው ሕጋዊ የግብይት ማዕከላት ውጪ የሚደረጉ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ተገቢው ቁጥጥር ሊደረግ እንደሚገባ የአዲስ አበባ የእህል ነጋዴዎች ማህበር ምክትል ሊቀመንበር አቶ ይመር ሙሄ ገለጹ።

የአዲስ አበባ የእህል ነጋዴዎች ማህበር ምክትል ሊቀመንበር አቶ ይመር ሙሄ በእህል ገበያው የጤፍ፣ የስንዴ እና የጥራጥሬ እህሎች በቂ የምርት አቅርቦት እና የዋጋ ቅናሽ እያሳየ መሆኑ ገልጸዋል። ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡ እህሎች ወደ ሕጋዊ የግብይት ማዕከላት ሳይደርሱ በሕገ-ወጥ መንገድ ያለደረሰኝ የሚሸጡበትን አሠራር ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ ምክትል ሊቀመንበሩ አሳስበዋል።

በሕገ-ወጥ መንገድ ተሠማርተው የሚሸጡ ነጋዴዎች ላይ ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር ቢደረግ የተሻለ የዋጋ ቅናሽ ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል።

እንደ ምክትል ሊቀመንበሩ ገለጻ ፤በያዝነው ሳምንት የጤፍ ዋጋ ቅናሽ የታየበት ሲሆን የነጭ ጤፍ ዋጋ በኩንታል 11 ሺህ ብር ፣ ሰርገኛ ጤፍ በ10 ሺህ 500 ብር እና ቀይ ጤፍ በዘጠኝ ሺህ 100 ብር በገበያው ላይ ይገኛል። የስንዴ ዋጋ አንደኛ ደረጃ በኩንታል ከአምስት ሺህ 300 ብር ሲሆን ሁለተኛ ደረጃ ስንዴ በሶስት ሺህ 500 ብር በኩንታል እየተሸጠ ይገኛል።

የጥራጥሬ እህሎችን በተመለከተ ባቄላ ከዘጠኝ ሺህ 500 ብር ጀምሮ አንደኛ ደረጃ ባቄላ 10 ሺህ 500 ብር በኩንታል እንደሚሸጥ ጠቁመው፤ የበቆሎ ዋጋ ከባለፈው ሳምንት ብዙም ጭማሪ ያላሳየ ሲሆን በሶስት ሺህ 200 ብር በኩንታል ለገበያው ላይ ቀርቧል። የገብስ፣ የአተር እና ሩዝ በተመሳሳይ ጭማሪ ያላሳዩ ምርቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

አቶ መሀመድ አሊ በእህል በረንዳ የተለያዩ የጥራጥሬ ምርቶችን የሚሸጥ ሲሆን በገበያው ላይ በቂ የምርት አቅርቦት እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።

በምርቶቹ ላይ የሚታየው የዋጋ መዋዠቅ አሁን የተረጋጋ እና በቅናሽ ዋጋ እየቀረበ መሆኑን የገለጸው መሀመድ፤ በግብይት ማዕከላቱ ከተለያዩ ቦታዎች ላይ አምጥተው በሕገ-ወጥ መንገድ ደረሰኝ ሳይቆጥሩ የሚሸጡ ነጋዴዎች በሕጋዊ መንገድ ለሚሠራው ነጋዴ ፈተና እንደሆኑበት ገልጸዋል ።

የእህል ምርቶቹን ተረክበው ለመግዛት ቢፈልጉም ነጋዴዎቹ ደረሰን የሌላቸው በመሆኑ አማራጭ የታክስ ሥርዓት መፈጠር አለመቻሉ አዳጋች እንዳደረገው አስገንዝበዋል።

ምርቶች ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገቡ ሲሆን ምርቶቹ ወደ ገበያው የሚሰራጩበትን ከታች ጀምሮ ያለውን ሰንሰለት ማጤን እንደሚገባ የገለጹት አቶ መሀመድ፤ የሚመለከተው አካል ከነጋዴዎች ጋር ቀርቦ ውይይት ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ምርቶቻቸው ከሕጋዊ የገበያ ማዕከላት ውጪ የሚሸጡ ነጋዴዎች አሉ ያሉት ምክትል ሊቀመንበሩ፤ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ የእህል ምርቶች ወደ ሕጋዊ የግብይት ማዕከላቱ ሳይገቡ በገበያው ላይ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚደረገው ግብይት በሕጋዊ መንገድ የሚሠሩ ነጋዴዎች ላይ ጫና የሚፈጥር መሆኑን አብራ ርተዋል።

ይህንን ሕገ-ወጥ ሥርዓት መቆጣጠር ካልተቻለ የተረጋጋ ገበያ ሥርዓት ለመፍጠር የሚደረገውን እንቅ ስቃሴ ውጤታማ እንዳይሆን እንቅፋት እንደ ሚሆንበት ገልጸዋል።

በአራት የተለያዩ አቅጣጫዎች በአቃቂ ፣ ኮልፌ፣ በእህል በረንዳና በአሸዋ ሜዳ ለማስተንፈሻ የተገነቡ እና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ አራት የግብይት ማዕከላት መኖራቸውን ያስታወሱት አቶ ይመር፤ የግብይት ማዕከላቱ ያለውን ሰፊ የሸማች ቁጥርና ምርት ያገናዘቡ በመሆናቸውም እንዲሁም ሁሉም ሰው በየአካባቢው በቅርበት ሊያገኘው የሚችል መሆናቸውንም ጠቅሰዋል ።

ማንኛውም ሸማችም ሆነ ሻጭ በእነዚህ ማዕከላት ብቻ በመገበያያት በየጊዜው የሚፈጠረውን የዋጋ ንረት ከመግታት ባለፈ ሀገር ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ማግኘት እንደሚቻል ገልጸዋል።

አቶ ይመር ሙሄ ምርቶቻቸውን ይዘው በገበያው ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ከሌሎች በገበያ ማዕከላት ከሚገኙ ሕጋዊ ነጋዴዎች ጋር በተመሳሳይ ሕጋዊነታቸው ተጠብቆ መክፈል የሚገባቸውን ግብር እንዲከፍሉ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You