ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያደረገችውን አስተዋጽኦ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በኩራት የመግለጽ ኃላፊነት አለበት

አዲስ አበባ፦ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያደረገችውን ሁሉን አቀፍ አስተዋጽኦ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በኩራት ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም ሀገራት ዜጎች የመግለጽ ኃላፊነት እንዳለበት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለኢፕድ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያደረገችውን አስተዋጽኦ ሚዲያዎች፣ ምሁራን፣ የመንግሥት አመራርም ግለሰብም ጭምር በኩራት ለሌሎቹ የመግለጽ ኃላፊነት አለባቸው።

‹‹ነገር ግን እኛ ስለራሳችን ማውራት እንቆጠባለን›› ያሉት አምባሳደር ዲና፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻነትና እኩልነት በግንባር ቀደምትነት በመሳተፍ የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር የከፈለች ሀገር መሆኗን አንስተዋል።

ይህም በታሪክ የተመዘገበ ቀደምት የአፍሪካ ሀገራትም የሚያውቁትና እውቅና የሚሰጡበት ሁኔታ አለ፤ ነገር ግን ባደረገችው አስተዋጽኦ ልክ እውቅና አግኝቷል ለማለት አስቸጋሪ መሆኑን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል።

እንደ አምባሳደር ዲና ገለጻ፤ ኢትዮጵያ አፍሪካን በሃይል ለማስተሳሰር ለሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ጂቡቲ እንዲሁም በቅርቡ ከታንዛንያ ጋር አስፈላጊውን ሂደት አጠናቃ የሃይል አቅርቦት እየሰጠች መሆኑ የሚበረታታ ነው፤ ይህም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥራች አባቶች የተነበዩትን እና የተመኙትን የአፍሪካን አንድነት ያፋጥናል።

የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ አፍሪካ ህብረት እውን እንዲሆን የኢትዮጵያ ሚና ጉልህ እንደነበር የሚያስታውሱት አምባሳደሩ፤ ‹‹በዚህ ብቻም ሳይቀር አፍሪካ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ልማት በውህደት ላይ ማተኮር አለባት የሚለውን አጀንዳ በማንሳትና በማስጨበጥ ረገድ በላቀ መልኩ ሚናዋን ተወጥታለች›› ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻነት ሲደረግ በነበረው ትግል ለደቡብ አፍሪካ፣ ለዝምባብዌ፣ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን የነበሩ የአፍሪካ የነጻነት ታጋዮች እንዲጠናከሩ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፎችን ስታደርግ እንደነበርም አውስተዋል።

እንዲሁም በሰላም ጥበቃው በኮንጎ፣ ሩዋንዳ፣ ላይቤሪያ፣ ቡሩንዲ፣ ሱማሊያና ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ከሌሎች አፍሪካውያን ጋር በመሆን መሥራቷን አስታውሰው፤ አሁን ደግሞ ለውህደት፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለሚደረገው ትግል ከቃል የላቀ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑን አምባሳደሩ ጠቁመዋል።

በአፍሪካ ሀገራት በተለይም በጎረቤት ሀገራት መካከል የሚስተዋሉ ልዩነቶች በኢትዮጵያ በኩል እንዲቀረፉ በየጊዜው ጥያቄዎች እንደሚቀርቡና ጥረቶች ተደርገው ውጤት የመጣባቸው እንዳሉ አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።

‹‹አፍሪካን በኋላ ቀርነት ያስፈረጁ ነገሮች መቀየር አለባቸው፤ እራስን መቻል በመፈክር ሳይሆን በትግበራ ነው የሚመጣው›› የሚሉት አምባሳደር ዲና፤ የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ ለየት ባለ መልኩ አፍሪካን መካስ ላይ እንደሚያተኩር አመላክተዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You