በጉባዔው የኢትዮጵያን የባሕር በር ማግኘት መብት አጀንዳ ማድረግ ይገባል

አዲስ አበባ፡በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የኢትዮጵያን የባሕር በር መብት የማግኘት መብትን እንደ አንድ አጀንዳ ሊነሳና ዲፕሎማሲያዊ ሥራ ሊሠራ ይገባል ሲሉ የትግራይ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀመንበር አረጋዊ በርኸ (ዶ/ር) አስታወቁ።

አረጋዊ በርኸ (ዶ/ር) በጉዳዩ ዙሪያ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የባሕር በር የነበራት ታላቅ ሀገር ናት፤ ይሁንና ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት የባሕር በር አልባ ሆኖ እስከ ዛሬ ድረስ ዘልቃለች፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታጣ ያደረጋትና ዋና ተጠያቂው በሥልጣን ላይ የነበረው ኢህአዴግ ነው።

ቀድሞ የነበረው ኢህአዴግ አገዛዝ የመቶ ሚሊዮን ሕዝብ መብትን ግምት ውስጥ ሳያስገባ የሀገር መብት አሳልፎ ሰጥቷል ያሉት አረጋዊ (ዶ/ር)፣ እንደዚያ በማድ ረጉም በኢኮኖሚያችን ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል ሲሉ ገልጸዋል።

በወቅቱ በርካታ የአፍሪካ ህብረት መሪዎች እነ ማንዴላ፣ ኮፊ አናን፣ ዓለም አቀፍ ፖለቲከኞች እና ልሂቃን የኢትዮጵያ አካሄድ ትክክል እንዳልሆነ ተረድተው ቢቃወሙም ሰሚ አለማግኘታቸውንም ተናግረዋል።

አሁንም በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የኢትዮጵያን የባሕር በር መብት የማግኘት መብትን እንደ አንድ አጀንዳ ሊነሳና ጠንካራ ዲፕሊማሲያዊ ሥራ መሥራት እንደሚገባ አመልክተው፤ ይህ አጀንዳ ለአፍሪካ ነጻነትና አንድነት ጉልህ ድርሻ ላበረከተችውና እያበረከተች ለምትገኘው ኢትዮጵያ የህልውና ጥያቄ መሆኑን ወንድሞቻችን አፍሪካውያን እንዲገነዘቡት ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

በወቅቱ የነበሩት የኢትዮጵያ መሪ፣ የባሕር በር አያስፈልግም ብለው ፈርመው በማስረከብ ሀገሪቱን ችግር ውስጥ ከተዋታል ያሉት አረጋዊ (ዶ/ር)፤ የባሕር በር ጉዳይ ማንሳትም የማይታሰብና ያስወግዝ እንደነበር አስታውሰዋል።

ፓርቲያቸው ሰፊ ዓላማ እንዳለው የገለፁት አረጋዊ (ዶ/ር)፣ በታሪክ የነበረንን ሀብት በተገቢው መንገድ ጠይቆ ማግኘት የሀገር መብት ማስከበር በመሆኑ፤ በሰላማዊ መንገድ ጥግ ድረስ የዲፕሎማሲ ሥራ በመሥራት የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ እንሠራለን ሲሉም ተናግረዋል።

አረጋዊ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ የባሕር በር ጉዳይ በማንኛውም ጊዜ መነሳት ያለበት ጥያቄ ነው። ጥያቄው የሀገር ጉዳይ በመሆኑ በአፍሪካ ህብረት እና በሌሎች መድረኮች በሰላማዊ እና በሕጋዊ መንገድ ሊነሳ ይገባል። ይህ የሁሉም ድርሻ ቢሆንም በተለይ በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያ ታላቅነትና መብትን የሚያስከብር ጉዳይ ሊነሳ ይገባል።

የባሕር በር ጥያቄ ማንሳት ሌላውን ሀገር ከመጉዳት እና ግጭት ከማስነሳት ጋር በማያያዝ የሚያስቡ አካላት ልክ እንዳልሆኑ ጠቅሰው፤ ምክንያቱም የኢትዮጵያውያን መብት ማስከበር ማለት ሌላውን መጉዳት አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

በተገኘው አጋጣሚ እና መድረክ የሀገሪቱ ሕጋዊና ታሪካዊ ጥያቄ በተገቢው መንገድ በማንሳት ተፈፃሚ ሊሆን ይገባል ያሉት የፓርቲው ሊቀመንበር፣ ሁሉም ችግር በሰላማዊ መንገድ ዕልባት ሲያገኝ ውጤቱ መልካም ይሆናል ብለዋል።

ለዚህም የሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ይሁንታ እንደሚያስፈልግ በመግለፅ፤ ችግሮች እና ሀገራዊ ጥቅሞች በሰላማዊ መንገድ እና በቅንነት ሊፈቱ ይችላሉ ሲሉ አስረድተዋል።

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You