«ስምንት ዓመት ገዳ»

በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ዜጎች ከልጅነታቸው ጀምሮ የሀገር አለኝታ፤ መከታ እንዲሆኑ ኃላፊነት ይሰጣቸዋል። ተግባርና ኃላፊነታቸው የሚወሰነው ደግሞ በሥርዓትና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ነው፡፡ ሥርዓቱ ሲበጅም እድሜ መለኪያ በማድረግ ነው፡፡ የሥርዓቱ መሠረት የገዳ ሥርዓት ሲሆን፤ መደቡ እያንዳንዱ ‹‹ስምንት ዓመት ገዳ›› እየተባለ ይጠራል፡፡ በጠቅላላው የሥርዓቱ ስም ደግሞ ‹‹ገዳ›› ይባላል፡፡ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ እያንዳንዱ የእድሜ እርከን ዋጋ ይሰጠዋል፡፡ በዓመታት ልዩነቶች ውስጥ ኃላፊነትም ተለይቶ የሚቀመጥበት ነው፡፡ ከዚህ አኳያም ዝርዝር መረጃውንና ሥርዓቱ ለሀገር ያለውን አበርክቶ በተመለከተ የኦሮሚያ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የባሕል ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ደራራ ከተማን አነጋግረናቸዋል፡፡

የገዳ እርከን በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ስማቸው ልዩ ልዩ ነው፡፡ ሆኖም ተግባሮቻቸው አንድ ዓይነት በመሆኑ በቋሚነት ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉትን እናነሳለን። ከዚህ አንጻር እርከኑ ክፍፍሉን የሚጀምረው ‹‹ደበሌ›› የሚል ስያሜ ከተሰጠው ሲሆን፤ ይህም እስከ 8 ዓመት ድረስ ያሉ ልጆችን ያካትታል፡፡ በዚህ የሥልጣን እርከን ውስጥ ያሉት ልጆች በመሆናቸው ኃላፊነታቸው ውስን ነው፡፡ ከቤተሰባቸው ብዙም ሳይርቁ ጎረቤትና መሰል የአካባቢውን ማኅበረሰብ እንዲያገለግሉ እነርሱም እንክብካቤን እንዲያገኙ የሚደረግበት ነው፡፡

ሁለተኛው የገዳ እርከን ‹‹ጋሜ ጥጥቃ›› የሚሰኘው ክፍል ሲሆን፤ ከ8 ዓመት እስከ 16 ዓመት ድረስ ይዘልቃል፡፡ በዚህ እርከን ውስጥ የሚመደቡት ልጅነት ባሕሪም ቢኖራቸው ከመጀመሪያው የተለየ የሥራ ኃላፊነት የሚጣልባቸው ናቸው፡፡ ይህም እንደላይኞቹ ከመንደራቸው ሳይርቁ ቀለል ያሉ ሥራዎችን እንዲለማመዱ የሚደረግበት ነው፡፡

ሦስተኛው እርከን ‹‹ቆንዳላ›› ወይም ‹‹ጋሜ ጉርጉዳ›› የሚባለው ሲሆን፤ ከ16 እስከ 24 የእድሜ ክልል ላይ ያሉ ወጣቶች የሚመደቡበት ነው፡፡ ይህ እድሜ ለአደን የሚመረጡበት ጊዜ ሲሆን፤ ከዚያም ባሻገር ከባድ ሥራ ለመሥራት ረጅም ርቀት እንዲሄዱ ይፈቀድበታል፡፡ የቆንዳላ ዘመን ከማብቃቱ ከሶስት ዓመት በፊት ደግሞ የጋዳ ክፍል አባላት ተሰብስበው የወደፊት የቡድን መሪዎችን (የሀዩ ምክር ቤት) ሹመት ይሰጡና በመጨረሻም መሪ እና አስፈፃሚ ፣ የፍትህ እና የሥርዓት ባለሥልጣናት ይሆናሉ። ከመጨረሻው ምርጫ በፊት ግን ብዙውን ጊዜ ረዘም ያለ የድርድር ዘመቻ ይካሄዳል። እጩዎቹ ከምርጫ በፊት የሕዝቡን ድጋፍ ለማግኘት በደጋፊዎቻቸው ታጅበው ማኅበረሰቡን እንዲጎበኙ ይደረጋል፡፡ ግለሰቦቹ በጥበብ፣ በጀግንነት፣ በጤና እና በአካል ብቃት ላይ ተመርኩዘው ይመረጣሉ።

አራተኛው እርከን ‹‹ኩሳ›› የሚሰኘው ሲሆን፤ እድሜው ከ24 እስከ 32 የሚደርሱ ዜጎችን ያሳትፋል፡፡ ቀደም ሲል የተመረጡት መሪዎችን ከራሳቸው ቡድን በስተቀር ሙሉ ሥልጣን ባይዙም በይፋ የሚቀላቀሉበት ደረጃም ነው። በግለሰብ ሕይወት ውስጥ እና በሁሉም የገዳ ሥርዓት ውስጥ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ክስተቶች አንዱ ሆኖም ይቆጠራል። የኩሳ ክፍል ሙሉ ሥልጣንን ለመገመት የዝግጅት ጊዜን ያስፈልገዋልና ቀጣዩን ክፍል ማለትም ‹‹ሪባ ዶሪ››ን ለመቀላቀል ዝግጁ የሚሆኑበትና አባል ሆነው እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

አምስተኛው የገዳ ደረጃ ‹‹ሪባ ዶሪ›› የሚባለው ሲሆን፤ ከ32 እስከ 40 ዓመት ያሉ የማኅበረሰቡ ወንዶች ይሳተፉበታል፡፡ ዋና ሥራው የክፍል አባላቱ ወደ ሉባ ወይም ገዳ የሚገቡበት ጊዜ ነው፡፡ የሥርዓቱ በጣም አስፈላጊ ክፍል የሚባሉት ሲሆኑ፤ ሙሉ ደረጃ ላይ የደረሱ ናቸው፡፡ እንደ ገዥ የገዳ ክፍል በዚህ ደረጃ ሥርዓቱ ለአፍታ ይቆማልና ሁሉም ዜጎች የመጨረሻውን ክፍል በመልቀቅ ወደ ሂደቱ ክፍል ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ይህም በአዲሱ የወጣት ክፍል ወዲያውኑ የተያዘው እና የሥርዓቱን መሰላል መውጣት ይጀምራል።

ስድስተኛ እርከን ላይ የሚቀመጠው ‹‹ጋዳ›› እየተባለ የሚጠራው ክፍል ነው፡፡ ይህ እርከን ከ40 እስከ 48 ዓመት ድረስ ያሉ ዜጎችን በማሳተፍ የተለያዩ ኃላፊነቶችን ወስዶ የሚሠራበት ነው፡፡ ይህ ክፍል ሉባ እየተሰኘ ይጠራልም። ይህንን እርከን ያለፈ ዜጋ የሚገባው ዩባ ላይ ነው፡፡ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ዩባዎች ሦስት የእድሜ እርከኖች ተሰጥተውት የሚሠራበት ነው፡፡ እነዚህም የመጀመሪያው ዩባ ከ48 እስከ 56 ያለው ሲሆን፤ ሁለተኛው ዩባ ከ56 እስከ 64 የሚቀመጠው ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ከ64 እስከ 72 የእድሜ ክልል ላይ ያሉ ዜጎች እንዲሳተፉበት የሚደረግ ነው፡፡

ዩባዎች እነዚህን በሦስት የተለያዩ የስምንት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ካለፉ በኋላ ደግሞ ወደ ‹‹ጋዳሞጂ›› ክፍል ከፍ ይላሉ፡፡ ይህም ከ72 እስከ 80 ዓመት ድረስ የሚዘልቀው የገዳ ደረጃ ክፍል ነው፡፡ ከዚያም ‹‹ጃርሳ›› የሚባል የመጨረሻ ክፍል ገብተው ሙሉ በሙሉ ጡረታ እንዲወጡ የሚደረግበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

በገዳ ሥርዓት ክፍሎች ሽግግር

በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ የገዳን መለወጥ ማክበር የግድ ነው፡፡ ስለዚህም በየስምንት ዓመት ኮርማ፣ ድልብ፣ ሰንጋና መሲናዎችን በብዛት አርዶ በትልቅ ድግስ ‹‹ቡታ›› በማለት ትልቅ በዓል ይከበራል፡፡ ‹‹ሉባ›› የሚል ስያሜ የተሰጣቸውና ትልልቅ ኃላፊነቶችን ወስደው የሚሠሩት ዜጎች ሥልጣናቸውን እንዲረከቡ ይደረጋል፡፡ ሥልጣኑ እውን የሚደረገው በእያንዳንዱ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ዜጎች 40 ዓመት ሲሞላቸው ነው፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለም ሥርዓቱ እስከ መጨረሻው ይከናወናል፡፡ ከአንድ ሰው ደረጃ ወደ ሌላው ሲሸጋገርም በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው ተግባርና አኗኗሩ ይለወጣል። ለምሳሌ፣ በቆንዳላ፣ ኩሳ እና ራባ ዶሪ የክፍል ደረጃ ግለሰቦቹ በ24 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የጦር ስልትን፣ የኦሮሞ ታሪክን፣ ፖለቲካን፣ ሥርዓትን፣ ሕግንና አስተዳደርን ይማራሉ።

በ40 ዓመት እድሜያቸው ወደ ገዳ ክፍል ወይም ሉባ ሲገቡ ሀገሪቱን የማስተዳደር እና የአምልኮ ሥርዓቶችን ማክበር ኃላፊነትን ለመወጣት ሁሉንም አስፈላጊ እውቀት አግኝተው ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ጡረታ በመውጣት ያበቃል፡፡ የሽማግሌዎች ቡድን ወደ አማካሪ እና የዳኝነት አቅም ይለወጣል፡፡

በቱላማ ገዳ አሠራር መሠረት የገዳ ባለሥልጣናት የሚባሉት የሚከተሉት ሲሆኑ፤ አባ ቦኩ ፕሬዚዳንት፤ አባ ቦኩ – የመጀመሪያ ምክትል ፕሬዚዳንት፤ አባ ቦኩ-ሁለተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት፤ አባ ጨፌ – የጉባዔው ሊቀመንበር (ቻፌ)፤ አባ ዱቢ የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ ለጉባዔው የሚያቀርብ አፈ-ጉባኤ፤ አባ ሴራ የሕጎች ማስታወሻ እና የጉባኤው የውይይት ውጤቶች፤ አባ አላንጋ – ውሳኔውን የሚያስፈጽም ዳኛ፤ አባ ዱላ – የሠራዊቱ ኃላፊ፤ አባ ሳ – በኢኮኖሚው ውስጥ ኃላፊ በሚል ይቀመጣሉ፡፡

የገዳ መለወጫ ጊዜና የአረካከብ ሥርዓቱ

የኦሮሞን ሕዝብ የሚያስተዳድር አባ ቦኩ የተባለው ዋናውን ሥልጣን የያዘው ሹም ይለወጣል። ደግሞም መማክርቶችና ዳኞች የሚለዋወጡት በገዳ መለወጫ ጊዜ ነው። ገዳቸው ያለፈ አባ ቦኩ፣ መማክርቶችና ዳኞች ከአዲሱ ባለገዳዎች መካከል ለሚመረጡ ሹማምንት የሕዝብን ማስተዳደር ሥልጣን ያስረክባሉ። ከዚያ በኋላ ‹‹ዩባ›› ወይም ‹‹አካካዩ›› ተብለው ከአዲሱ ባለገዳዎች ጀርባ ተቀምጠው በሽምግልና ይፈርዳሉ። የሥልጣን አረካከብ ሥርዓት በሚከተለው አካኋን ይፈጸማል።

ገዳ የሚለወጥበት የቡታ በዓል ከመድረሱ ሁለት ዓመት አስቀድሞ ሕዝቡ ‹‹ኦዳ›› ከሚባል ከተከበረው ዛፍ ዙሪያ ይሰበሰባል። ስብሰባው ላይ ሥልጣን የያዘው አባ ቦኩና መማክርቶቹ፣ ዳኞችና ከሁለት ዓመት በኋላ ቡታ ለማረድ ተረኛ የሆኑት ባለገዳዎች በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ይደረጋል። በስብሰባውም ቦታ የቦረና ዘር የሆነ አባትና እናቱ ያልሞቱ፣ ሚስቱ በሕይወት የምትገኝ፣ የበኩር ልጁም ያልሞተበት፣ አካላቱ ያልጎደለ፣ የአባቱና የልጆቹ ስም መልካም ስም የሆነ ደግ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተመርጦ ‹‹አባ ኮርማ›› ተብሎ ይሾማል።

ሕዝቡ በበኩሉ ከባለገዳዎች መካከል ሁነኛውን ሰው መርጦ ‹‹አባ ቦኩ›› ብሎ ይሾማል። ቀጥሎም መማክርትና ‹‹ራባ ዶሪ›› የሚባሉ ዳኞች፣ አባ ዱላ የሚባል የጦር ሠራዊት መሪ ይመርጣሉ። ከምርጫው በኋላ አባ ኮርማው ለተሰበሰበው ሕዝብ ንግግር ካደረገ በኋላ ሕዝቡን መርቆ ሥርዓቱን ይፈጽማል። ከምረቃው በኋላ ሕዝቦቹ እየዘፈኑ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ያሰናብታቸዋል። የዚህ የስብሰባ በዓል የ‹‹ደጋጋ›› በዓል ይባላል።

ስምንት ዓመት ሲያስተዳድሩ ከቆዩት ሥልጣን የሚረከቡ ሹማምንት በሕዝብ ከታወቁ በኋላ የሕግና የሕዝብ አስተዳደር ጥበብ በጥልቀት ሲያጠኑ ይቆያሉ። በዚሁ ምክንያት ገዳ በተለወጠ ጊዜ የሥልጣን መረካከብ ቀላል ሥራ ይሆናል። ሹማምንቱም ሥራቸውን በደንብ አውቀውት ይገኛሉ።

በኦሮሞዎች ዘንድ ሕግ የማወጅ ኃላፊነት የተሰጠው ድርጅት የሉባዎች ጉባኤ የሚባል ሲሆን፤ ጉባኤው ሕግ ለማውጣት ተሰብስቦ የሚመክረው፣ በአንድ ጎሳ ውስጥ ከአባ ቦኩ ደጅ ነው። በሌሎች ጎሳዎች ውስጥ ጉባኤው የሚደረገው ኦዳ ከሚባል ከታላቅ ዛፍ ጥላ ስር ነው። የሉባዎች ሰብሳቢ አባ ቦኩ ሆኖ ዶሪና ‹‹ራባ›› የተባሉትም አለቆች አብረውት ይቀመጣሉ። አባ ቦኩ ብሉኮውን አጣፍቶ ቦኩውን ከብሉኮው ስር ደብቆ በርጩማ ከሚባል ወንበር ላይ ይቀመጣል። ሌሎቹ በጉባኤው ውስጥ ተካፋይ የሆኑት ሉባዎች ሁሉ በአባ ቦኩ ዙሪያ ይቀመጣሉ። የሚደነገገው የሕግ ሃሳብ ለጉባኤው ከተነገረው በኋላ ስለቀረበው ሕግ ሃሳባቸውን ለመስጠት የሚሹ ሉባዎች ሁሉ በየተራቸው ተነስተው በመደገፍ ወይም በመቃወም ይሳተፋሉ።

በጉባኤው ላይ ተራ የተሰጠው ተናጋሪ ከሸንጎው ፊት ሲቆም ጦሩን በግራ እጁ ጨብጦ በቀኝ የያዘውን አለንጋ ዋና ዋና ነገር በተናገረ ጊዜ እያስጮኸ ዲስኩር ያደርጋል። ተናጋሪው ዲስኩሩን ከጨረሰ በኋላ በንግግሩ ውስጥ ስህተት አድርጎ እንደሆን እንዲያርምና የረሳውም ነገር ካለ እንዲጨምርበት ሲባል ሌላ ሰው ንግግር ሳይጀምር ጉባኤው በጸጥታ ለተወሰነ ጊዜ ይጠብቃል። ንግግር ያደረገው አባል የማይቀጥል መሆኑ ሲታወቅ ለሚቀጥለው አባል ተራ ይሰጣል። ከዚህ ሥርዓት ወጥቶ ማንም አይናገርም። የቀረበውን ሕግ ለመቃወም ማንኛውም ሉባ መብት አለው። ነገር ይደር ለማለት የፈለገ ማንኛውም አባል ቀቤ /ያዝኩ/ ያለ እንደሆን ይደር ብሎ ጉባኤው ይነሳል እንጂ ንግግሩ አይቀጥልም፣ ውሳኔም አይወሰድም።

ሕጉ ሥርዓትን ተከትሎ ከተመረመረና የሚናገሩት ሉባዎች ሁሉ ከተስማሙበት በኋላ ጉባኤው ይዘጋል። በማግስቱ አባ ቦኩ ኮርማ አርዶ ቦኩውን የኮርማውን ደም ካስነካ በኋላ ‘’ሴራን ቱሜ’’ ሕግ ደንግጌያለሁ ሲል በጦሩ መሬቱን ከመታ በኋላ ሕጉ እንደ ታወጀ ይቆጠራል። ፍርድ የሚፈጸምበት ሥነ ሥርዓት በኦሮሞዎች ደንብ ሥርዓትን የሚያዩና ባላገሮችን የሚያሟግቱ አባ ቦኩ፣ ዶሪና ራባ የተባሉት የሉባዎች ዳኞች ናቸው። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ከሶስቱ ዳኞች ሌላ ከሳሹ ከሌሎች መካከል ‹‹ሸኔ›› የተባሉ አምስት ሕግ አዋቂዎች ሲቆጥር ተከሳሹ አራት ቆጥሮ በጠቅላላው ሶስት ዳኞች፣ ዘጠኝ ሸኔዎች ሆነው እንዲሟገቱ ይደረጋል፡፡

ከእነዚህ ሌላ የፈቀደ ሰው ሁሉ በአደባባዩ ላይ ተገኝቶ የፍርድ ሂደቱን ለመከታተል መብት አለው። ከተሟጋቾቹ አንዱ ሌላው የቆጠረውን ሸኔ አልቀበልም ለማለት ሶስት ጊዜ ደጋግሞ ሸኔው አይገባም ማለት አለበት። በሶስተኛው ጊዜ አይገባም ብሎ ከተናገረ በኋላ ይህ ተቃውሞ የቀረበበት ተቆጣሪ ጠላቱ መሆኑን ወይም የባላጋራው ዘመድ መሆኑን ካላስረዳ በቀር ተቃዋሚው ለተቆጣሪው ሸኔ ዘጠኝ ላም ካሳ እንዲከፍል ይፈረድበታል። ሸኔዎች ከተቆጠሩ በኋላ ከሳሽና ተከሳሽ ‹‹አባ አለንጋ›› የተባሉ ጠበቃዎች ያቆማሉ።

ሕግ አዋቂ ሉባዎች ካልሆኑ በቀር ነገረተኞች ራሳቸው እንዳይሟገቱ ክልክል ነው። ሙግት፣ ክርክር በዚህ አካኋን ከተከናወነ በኋላ “ተሬ” ከሚባል አደባባይ ተሰብስበው ችሎት ያደርጋሉ። ሕግ በሚያወጡ ጊዜ እንደሚደረገው ሁሉ ሙግት ሲደረግ ማንኛውም ሰው ተነስቶ ቀቤ ወይም ያዝኩ ያለ እንደሆን ሙግቱ ማደር አለበት። ተሟግቶ የተፈረደበት ሰው ይግባኝ ያለ እንደሆንም ይግባኙ በጎሳው ፍርድ ቤት ሊታይ አይችልም። የሚበዛውን ጊዜ ይግባኝ ፍርድ ከአንዱ ጎሳ ፍርድ ቤት ወደ ሌላው ጎሳ ፍርድ ቤት ይላካል።

ኦሮሞዎች ሁሉ በአንድ ሰፈር ወላቡ ዙሪያ በነበሩ ጊዜ ነገርን ከአንዱ ፍርድ ቤት ወደ ሌላው ጎሳ ዳኝነት መውሰድ ቀላል ነበር። በኋላ ግን ነገዱ ተከፋፍሎ ጎሳዎቹ ከተራራቁ በኋላ ለምሳሌ ከሜጫ ነገድ ፍርድ ቤት ወደ ቱለማ ለመላክ አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጠረ። ይህን ችግር ለማስወገድ የሚከተለው ደንብ ተደነገገ። ሥርዓታቸውን ወደ ሌላ ጎሳ ፍርድ ቤት ለይግባኝ የሚወስዱ ነገረተኞች ሁሉ በዘንጋቸው ላይ ጨርቅ እንደ ባንዲራ እያሠሩ እንዲጓዙ፣ በጉዟቸውም ጊዜ ይህን ምልክት ያየ የኦሮሞ ቤተስብ ሁሉ ተቀብሏቸው አብልቶ፣ አጠጥቶ፣ አሳድሮ እንዲሸኛቸውና መንገድም እንዳይሳሳቱ እንዲመራቸው ተደረገ። በሚያልፉበት ሀገር ቀማኛ ወይም ወንበዴ ከጎዳና ላይ የሚገኝ የሆነ እንደሆነ የሀገሩ ሞቲ ሰዎች አስከትሎ ከአደገኛው ቦታ እንዲያሳልፋቸው በሴራ ቱማ ተደነገገ። ይግባኝ ባይ በሚጓዝበት መንገድ ባንዲራውን ይዞ ከተጓዘ ችግር እንዳያገኘውና ፍርዱም በሥርዓት እንዲታይለት ጥብቅ ሕግ ሆኖ የቆየ ነው፡፡

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You