
የትግራይ ሕዝብ ባለፉት ሁለት ዓመታት ጦርነት ላይ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ በዚህ አክሳሪ ጦርነትም ብዙ ዋጋ ከፍሏል፡፡ ሰላሙን ባወጀበት ማግሥት ጦርነት ቆስቋሽ ለሆኑ የዛቻና የይዋጣልን ድምጾች ምላሽ መስጠት የለበትም፡፡ ባላገገመ ሥነ ልቦና እና ባልሻረ ጠባሳ ለእንዲህ ዓይነቱ ሰላም አደፍራሽ ሰጣ ገባ እድል መስጠት ማለት ትላንትን መድገም ማለት ነው፡፡ የነበረን በማስቀረት ውስጥ እንጂ የነበረን በመድገም ውስጥ ጀግንነት የለም፡፡
በሰላም ወዳድነቱ ለብዙዎች ምልክት የሆነው የትግራይ ሕዝብ አንድነቱን አጠናክሮ ወደነበረበት ከፍታው እንዲመለስ ችግሮች በውይይት መፈታት ይኖርባቸዋል፡፡ የትግራይ ሕዝብ አሁን ባለው ቁመና ከሰላም ውጭ ምንም አስፈላጊ ነገር የለውም፡፡ እየተፈጠሩ ያሉ አለመግባባቶች በአጭሩ ካልተቀጩ እንዳለፈው ጊዜ ወደ ከባድ ክስረት የሚወስዱ ናቸው።
በሁለት ዓመት ጦርነት ብዙ ነገሩን ባጣ ሕዝብና ወጣት መሀል ለዳግመኛ ነውጥ ነገሪት መጎሰም የሚያዋጣ አይደለም፡፡ ያለፈው ይበቃል፣ የነበርንበት የስቃይና የመከራ ጊዜ ተደግሞ አይደለም ሲታሰብ የሚያም ነው፡፡ በመጣው የሰላም ጮራ ትግራይ ወደቀደመ ሰላሟ እየተመለሰች ባለበት ሁኔታ ለሌላ ንትርክ መሰናዳት በትግራይ እናቶች እንባ መቀለድ ነው የሚሆነው፡፡
ተማሪዎች እየተማሩ ነው፡፡ ወጣቱ በተገኘው ሰላም በአፍላነቱ ለለውጥ እየተጋ ነው፡፡ አርሶ አደሩ እያረሰ ነው፡፡ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀያቸው በመመለስ ላይ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የትግራይ ሕዝብ ወደቀደመ ሰላሙ በመመለስ ላይ ይገኛል፡፡ ይሄ ሁሉ በሆነበት ሁኔታ የትግራይ ሕዝብን ዳግመኛ ወደ እሳት ለመክተት የሚደረግ የይዋጣልን ርምጃ በምንም መልኩ የሚደገፍ አይደለም፡፡
የተጀመረውን ሰላም ማስቀጠል ሁሉም ዜጋና አመራሮች ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የሚሰሙ ግጭት ቀስቃሽ አሉባልታዎች ለማንም እንደማይጠቅሙ በባለፈው ጊዜ አይተናል፡፡ ትግራይ በጦርነት ብዙ ወጣቶቿን አጥታለች፡፡ እናቶች አልቅሰዋል፡፡ ሕፃናት ያለ ወላጅ ቀርተዋል፡፡ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ርቀው የሰነበቱበት ያ ዘግናኝ የጦርነት ጊዜ በሁላችንም ትውስታ ውስጥ በመጥፎነቱ የሚነሳ ነው። አሁናዊ የሁለት ቡድኖች አለመግባባት ትላንትን ለመድገም ካልሆነ በስተቀር የሚያመጣው ትርፍ የለም፡፡
ቁጭ ብለን በጦርነት በከረምንባቸው ጊዜያቶች ያገኘናቸውን ትርፍ እና ኪሳራዎቻችንም ማስላት ብንችል በእውነቱ ከማንም ቀድመን የምናፍረው እኛ እንሆን ነበር፡፡ አላስተዋልንም እንጂ በጦርነት የብዙ ሀፍረት ባለቤቶች ነን፡፡ ሰው ሰላምን ለማምጣት ጦር ከጨበጠ ውርደት ውስጥ ነው፡፡ አንድ ቡድን አሊያም አንድ የፖለቲካ ድርጅት አላማውን ለማሳካት በሀገርና ሕዝብ ላይ ጨክኖ ለጦርነት ከተሰናዳ በእውነቱ ያ የመጨረሻው የሰው ልጅ የጥፋት ጥግ ነው፡፡
ውርደትና ክብር ሥፍራ አላቸው፡፡ ሥፍራቸውን ካላጤንን በርግጥም ክብር ውርደት ውርደት ክብር መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ሰላም ለማምጣት ጦር መማዘዝና ድንጋይ መወራወር ቀርቷል፡፡ በበላ ልበልሀ ወግ ችግሮችን ከምንጩ አድርቆ በእርቅና በይቅርታ መተቃቀፍ የሚቻልበት ዘመን ላይ ነን፡፡ ገሎ ለመሞት ካልሆነ እና በትውልዱ መሀል የጥላቻ ዘር ለመዝራት ካልሆነ በስተቀር ማንም ማንንም በጦርነት ማሸነፍ አይችልም፡፡ ሰላማዊ ሰዎች ሰላምን ለማምጣት ጦርነት አይገጥሙም፡፡ ሰላማዊ ትግል ነው የሚያደርጉት፡፡ የተሳሳትንው ሰላምን በኃይል ለማምጣት የምናደርገው ሙከራ ልክ እንዳይደለ አለማወቃችን ላይ ነው፡፡
በሰላማዊ ትግልና በጦርነት የተፈጠረች ሀገር አንድ ዓይነት አይደለችም፡፡ እስከ ዛሬ በጦርነት ሀገር ፈጥረናል፣ ለመፍጠርም ሙከራ አድርገናል። የሚያዋጣን ነፍጥ አንግቦ መንቀሳቀስን ትቶ ሰላማዊ ትግል ማድረግ ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ ራሱን ከጦርነትና ከመሰል አለመግባባቶች ለመታደግ ለሰላም ቅድሚያ በሰጠ የእርስ በርስ ጉርብትና መበልጸግ አለበት፡፡ ወጣቱ ካለፈው ተምሮ መንቃት አለበት፡፡
ስሜት ክፉ ነገሩ ኪሳራዎቻችንን እንድንቆጥር እድል አለመስጠቱ ነው፡፡ ጦርነት የስሜታዊነት ምላሽ ስለሆነ ስሜታዊ ሰው ደግሞ የሚሆነውን ቀድሞ ለመረዳት አቅም አይኖረውም፡፡ ብስለት ማለት ከአንድ ውሳኔ በፊትና በኋላ ያለውን ውጤት ቀድሞ መረዳት ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ የጦርነትን አስከፊነት የሚያውቅ፣ ስለሰላም ዘብ የቆመ ሕዝብ ነው፡፡ ስሜታዊ የሆኑ ቡድኖችና ግለሰቦች ዋጋ እንዳያስከፍሉት በብስለት ሀይ ሊል ይገባል፡፡
አንድ ጊዜ ሰላም ከደፈረሰ እስኪጠራ ዓመታት ይፈጃል፡፡ አስቀድመን የምንወስዳቸው የብስለት ውሳኔዎች ናቸው ከነገ ቁጭትና እዬዬ ሊታደጉን የሚችሉት፡፡ ሰላምን ረግጦ የሚመጣ ድልና እድል የለም፡፡ ድሎቻችን ያሉት በሰላማችን ውስጥ ነው። ልክ ያልሆነ እና ዋጋ የሚያስከፍል ነገር ከሆነ በቃ ስንል ነውጥ ፈጣሪዎችን ልናስቆም ይገባል፡፡
አንድ የቢዝነስ ሰው ኢንቨስት ባደረገው ሀብቱ ላይ ያመጣውን ትርፍና ኪሳራ ማስላቱ የተለመደ ነው። ከትርፉ ኪሳራው ካመዘነ ለሁላችንም እንደሚገባን ወደዛ የቢዝነስ መስክ ዳግመኛ አይመለስም፡፡ በአዲስ ጉልበት እና የታደሰ ኃይል ወደሌላ አቅጣጫ ይመለከታል እንጂ፡፡ ይሄ የቢዝነስ ሰው በብስለት የሚኖር እንደሆነ የምናውቀው ትርፍ ለሌለው ነገር ላለመድከም በመወሰኑ ነው፡፡
ከዚህ ግለሰብ በመነሳት የሀገራችንን ስሜት ወለድ እሽቅድምድም በንጻሬ መመልከት ይቻላል፡፡ እንደ ሀገር ትልቁ ችግራችን ከጦርነት በኋላ ያገኘንውንና ያጣነውን ለማስላት ጊዜ ማጣታችን ነው፡፡ ጊዜ ቢኖረን ኖሮ ዳግመኛ ወደ ጦርነት እንዳንገባ የሚያደርጉ አስተማሪ ታሪኮች ይኖሩን ነበር፡፡
በርግጥ ጦርነት ትርፍ እንደሌለው ብዙዎቻችን እናውቃለን፡፡ ትልቁ ጥያቄ ግን ትርፍ ለሌለው ነገር ሰው ልጅ እንዴት ይደክማል? የሚለውን መመለስ ነበር፡፡ ለማይጠቅመንና ትርፍ ለሌለው ነገር በመድከም የጋራ ውበቶቻችንን፣ የአብሮነት እሴቶቻችንን እየናድን ነው፡፡ ትርፍ ለሌለው ነገር መድከም ስናቆም ዋጋችንን እያወቅን እንመጣለን፡፡ ዋጋችንን ስናውቅ ደግሞ ለስሜት መገዛት እንተዋለን።
ጦርነት አዋራጅ ነው፡፡ ለማንም የማይበጅ ከማጉደል ባለፈ ለማይሞላ፣ ከመሽረፍ ባለፈ ለማይጠግን ብኩርናን መሸጥ ነው ፡፡ በገድሎ መሞት ጅጋኔውን ያደረገ ምን ውበት አለው? ለምክክርና ውይይት ያልጀገኑ ሃሳቦች ለጥሎ መወደቅ የበረቱ ከሆነ ሀገሬ እዳ አለባት፡፡ ትውልዱ ውርደት ጎሳሚ የሞት ነጋሪት ሳይሆን ነፃ አውጪ የእርቅ ሸንጎ ያስፈልገዋል፡፡
ሸንጎዎቻችን ሃሳብ አጥተው በተወለወሉ ጠረጴዛ አጊጠው ጦርነትን መሻር ሲያቅታቸው እናውቃለን። በሱፍና በከረባት የተከሸኑ የሕዝብ ነፃ አውጪ ነን የሚሉ ፖለቲከኞች ሩቅ ማየት አቅቷቸው በቅርብ አዳሪ አፈ ታሪክ አብሮነትን ሲሸረሽሩም እናውቃለን። ሸንጎዎቻችን ሽማግሌ የተቀመጠባቸው፣ እውነትና ሀቅ የጸናባቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡ እርቅ ደም ያድርቅ በሚል ኢትዮጵያዊ ወግ አስተቃቅፈው በሚሸኙ አባቶች ሥፍራ ሊኖረው ግድ ይላል፡፡ ለሰላም የተሰው፣ ጥልን በፍቅር የሻሩ አስታራቂ ፊተኞች ያልሰመሩ ህልሞቻችን ሆነው በሁላችንም ንጋት ላይ ተሰቅለዋል፡፡
እንዲነጋልን አንጊ ባለራዕይ ያስፈልገናል፡፡ ጨለምተኞች ንጋታችን መሀል ምንም አይሠሩም። ከእዳ ወደ ምንዳ በሆነ የአብሮነት ወግ ስለ ሰላም ጦርነትን በቃን የምንልበት የጋራ ድምጽ እጅግ ያስፈልገናል፡፡ በለው ሲሉና ደግ አደረክ ሲሉ የነበሩ የሞት ልሳኖች በትህትና አጎንብሰው ስለፍቅር ተረከዝ ሊይዙ ይገባል፡፡ እንዲህ ስንሆን ንጋታችን ከጨለማዎቻችን መሀል ያፈነግጣሉ፡፡ በንጋታችን መሀል የተሰገሰጉ ጨለምተኞች በብርሃን ሸኮናቸውን ተብለው ይፍረከረካሉ፡፡
ህልም አለን? የመዳን፣ የመታረቅ፣ ነፃ የመውጣት። የመታረም፣ የመተቃቀፍ፣ የመዋደድ፡፡ ህልሞቻችን ግን ሰላም ተኮር ባልሆነ ውንብድና ጨንግፈዋል፡፡ ህልሞቻችን ለሰላም ቅድሚያ በመንፈግ ቀንጭረዋል። ደመናው ውስጥ ነን ብርሃን እየሻትን፡፡ ጨለማው መሀል ነን ውጋግ እየናፈቅን፡፡ የቆምንበት አውድማ እንደትላንቱ ያለ በደም የደደረ ነው፡፡ ቦታ ካልቀየርንና የአስተሳሰብ ለውጥ ካላደረግን ከብርሃናችን መድረስ አይቻለንም፡፡
ለየትኛውም ሀገርና ሕዝብ የሰላም ዋጋ በቀላል ተመን የሚታይ አይደለም፡፡ ብቸኛ የህልውና ዋስትና ሆነው ለሰው ልጆች ከተሰጡ የሕይወት ጸጋዎች መሀል ሰላም አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ በዚህ የሰላም መንገድ ተጉዘው አብሮነትን ከማጽናት በላይ አስፈሪና የታፈሩ የሆኑ ሀገራት ብዙ ናቸው፡፡ የድል ጎዳናቸውን ትተው በንትርክና በሰጣ ገባ ድላቸውን ወደ ውርደት የቀየሩን እንደዚሁ ብዙ ናቸው፡፡ አሁን ላለችው ኢትዮጵያ የሰላም ዋጋ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡
የዝሆኖች ጥል ለሳሩ እና ለእንግጫው አደጋ ሲሆን እናውቃለን፡፡ ታች ያለው የማህበረሰብ ክፍል ያለ እዳው ፍዳውን እንዳይበላ ከላይ ያሉ አመራሮች ስለ ሰላም ዋጋ መክፈል አለባቸው፡፡ የትግራይ ሕዝብ የመማር፣ የመነገድ፣ አርሶ የመብላት፣ እንደቀደመው የእርስ በርስ ትስስሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ወደቀደመ ሰላሙ መመለስ ምርጫ ውስጥ የማይገባ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ እየተሰሙ ያሉ የሁለት ጎራ የግጭት ነጋሪቶች ለማንም የሚበጁ አይደሉም፡፡ የፈሰሰው ታፍሶ ሳያበቃ፣ የጠወለገው እየለመለመ ባለበት ሁኔታ ላይ ሌላ ድርቅና መከራን ለመውለድ ማማጥ በምንም መመዘኛ የማይለካ ጭካኔ ነው፡፡
የትግራይ ሕዝብ ሰላማዊ ሕዝብ ነው፡፡ ስስት የማያውቅ፣ አካፍሎና ተካፍሎ የሚበላ የርህራሄ ምልክት ነው፡፡ በኢትዮጵያዊነት ውስጥ የከፈለው ውለታም በምንም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ይሄ ሰላማዊ ሕዝብ ወደቀደመ የሰላም ተምሳሌትነቱ እንዲመለስ እና ከሌላው ወገኖቹ ጋር ተዋዶና ተፈቃቅዶ እንዲኖር ስለሰላም ማውጋት እንጂ ስለጠብ ቆስቋሽ መሆን ትርጉም አይሰጥም፡፡
ንትርክና ሰጣ ገባ ከትርፋችን ላይ የሚቆ ርስ፣ ከሙላታችን ላይ የሚያጎል እንደሆነ ባሳለፍናቸው የጦርነት ዘመኖቻችን አስተውለናል። ምን እንደሚሻለን እናውቃለን፡፡ የመረጥናቸው መንገዶቻችን ከንጋት ሰውረው ጨለማ ውስጥ ጥለውን እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ በነጋ ሰማይ ላይ ስለጨለማ መዘመር አያስፈልግም፡፡ በፈካ ቀዬ መሀል ስለሞት መደስኮር አላስፈላጊ ነው፡፡ ትግራይ እንደነጋላት መቀጠል ነው የሚኖርባት፡፡ ለዳግም ዝቅታ መንገድ ከፋች የሆኑ የአንድ ወገን ንትርኮች ጦርነትን ካለሆነ ሰላምን አያምጡም፡፡
ምጦቻችን ሰላምን እንዲያስታቅፉን በፍቅር መሥራት ብቸኛው አማራጫችን ነው፡፡ በጥላቻ የተጠቃ አእምሮ ሰላምን ማማጥ አይቻለውም። በጦርነት በተጠቃ ልብ አብሮነትን መጸነስ አይሆንለትም፡፡ እያማጥን ከሆነ ሰላምን ለመውለድ እናምጥ፡፡ ክንዶቻችን መከራን መሸከም አቅቷቸዋል። ጉያዎቻችን ሞትን እሽሩሩ ማለት ከብዷቸዋል፡፡ ትከሻዎቻችን ስለጥላቻ ዝለዋል፡፡
ምርጫችን ያሻንን ሀገርና ትውልድ እንዲሰጠን የታመነ ነው፡፡ በእስካሁኑ ግስጋሴያችን የምርጫችንን እየበላን ነው፡፡ በላያችን ላይ ያንጃበቡ የመከራ ደመናዎች፣ የጦርነት ነጋሪቶች የምርጫዎቻችን ውጤቶች ናቸው፡፡ እያየናቸው ያሉ እና እየሰማናቸው ያሉ ከአብሮነት ያፈነገጡ ብቻነቶች በፍቃዳችን የወረስናቸው ምርጫዎቻችን ናቸው። ፍቅር የጠወለገበት አውድማችን፣ እንደጎለጎታ በርባንን ፈተን ክርስቶስን የወነጀልንበት አብራካችን በምርጫችን የተወረሰ ነው፡፡
ነገን የተሻለ ለማድረግ ምርጫችንን ማስተካከል ይኖርብናል፡፡ ጦርነት በቃን፣ ጥላቻ በቃን ስንል ውርሳችን እውነት ይሆናል፡፡ መገፋፋት በቃን፣ መበላላት ይብቃን ስንል ክብራችን አብሮነት ይሆናል፡፡ ዘረኝነት መጠላላት በቃን ስንል ቀለማችን ኢትዮጵያዊነት ይሆናል፡፡ ውርስ እንደ እናትና አባት ቤትና ንብረት ሁሉ ከራሳችን ለራሳችን የምንወርሰው የአስተሳሰብ ልምምድ ነው፡፡
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 29 ቀን 2017 ዓ.ም