«ጀቢና» ከእውነት የተዘገነ ሕይወት …

ታላቅ የፈተና መንገድ፣ ሰፊ የጭንቅ ጎዳና፣ በሀዘን የሚሻገሩት፣ በችግር የሚያልፉት አስፈሪ የ|ሕይወት ድልድይ፡፡ በጸሀይና ጨለማ የተዋዛ፣ በደግ ክፉ የሚታገሉት ማንነት፡፡ ዕንባና ሳቅ ተዳብለው ፣ ታሪክ የወለዱበት፣ ጉልበት ከፍቅር ፣ መዋደድ – ከጥላቻ የተፋጠጡበት ፣ ሀያል እውነት፡፡ ‹‹ጀቢና››

ወግና ባሕል፣ ቂም ጥላቻን ሽረው፣ በቀል ሞትን አሸንፈው የቆሙበት ጥብቅ ምሰሶ ፡፡ ታሪክ በታሪክ የተቀየረበት፣ በደልና ብሶት ዕንባና ሥብራት፣ ጥንካሬን የወለዱበት፣ መሸነፍን ድል ነስተው ‹‹ነበር›› የተሰኙበት አይረሴው ሀቅ ፡፡ እነሆ ! ይህ የማንነት ግማድ ዛሬ በአንድ ተጣምዶ ፣ በሕብር ተዋዶ ‹‹ጀቢና ›› ይሉት ታሪክን አምጦ ወልዷል ፡፡

‹‹ ጀቢና›› ማለት በአፋን ኦሮሞ ፅናት ፣ ብርታትና ጥንካሬ ይሏቸውን ትርጓሜዎች ይወክላል፡፡ ይህ ቃል ከያዘው ፍቺ ባሻገር ታሪክ ሆኖ ሲወለድ ደግሞ ከዘመናችን ድንቅ የፊልም እይታዎች መሀል አንዱ ሆኖ እናገኘዋለን። ‹‹ጀቢና›› መነሻውን በእውነተኛ የሕይወት ታሪክ ላይ ያጸና ልብ አንጠልጣይ ፊልም ነው፡፡ ይህ እውነት ዛሬ ሥጋ ለብሶ፣ ነፍስ ዘርቶ፣ ዕውን ሲሆን ማረጋገጫው የራሷ የባለታሪኳ እማኝነት ነው፡፡ ‹‹ጀቢና›› ፊልም ሆኖ ለዕይታ ሲበቃ በበርካታ የሕይወት ስንክሳሮች፣ በአይረሴ የፈተና አጋጣሚዎች ተጠላልፎ ነው፡፡

በነዚህ የሕይወት ሰንሰለቶች ትስስር ፍቅርና ፈተና፣ ክፋትና ደግነት፣ ከሕይወት ውጣውረድና አሸናፊነት ፣ ከጥብቅ ባሕልና ታሪክ ፣ ጋር የጎንዮሽ ተጣምረዋል፡፡ በደራሲ ሳሙኤል ተሻገር /የእማዬ ልጅ/ ዳይሬክተርነት ተዘጋጅቶ የቀረበው ጀቢና በአሁን ፊልም ፕሮዳክሽን አማካኝነት ቀረጻው ተካሂዷል፡፡

አንድ ሰዓት ከሀምሳ ሶስት ደቂቃ የሚፈጀው ይህ ፊልም ዋና ባለታሪኳ ሔለን እሸቱ ኤክዝኪዩቲቭ ፕሮዲዩስር ሆናበታለች፡፡ ቀለም ፊልምስና ጴጥሮስ እሸቱም ፕሮዲዩሰር በመሆን ከውነውታል፡፡ የፊልሙ የሥራ ቆይታ በግዜ መጠን ሲተመን አንድ ዓመት ከአንድ ወር ያህል ፈጅቷል፡፡

‹‹ጀቢና›› የፊልም ታሪክ ሆኖ ፣ ስሜት ሰቅዞ፣ ትርጉም ሰጥቶ ለተመልካች እይታ ይበቃ ዘንድ የፈጀው የበጀት መጠንም ስድስት ነጥብ አንድ ሚሊየን ብር ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የፊልሙን ታሪክ ከእውነተኛው የሕይወት ቀለም ጋር ለማቀናጀት በተመረጡ ሥፍራዎች ቀረጻዎችን ማካሄድ ግድ ነበር፡፡

ለፊልሙ ታሪክ መከወን ወንጂ ስኳር ፋብሪካ፣ ቆቃ፣.ሞጆና አዲስ አበባ ታላቅ ድርሻ አበርክተዋል፡፡ አንድ ወር በፈጀው የቀረጻ ቆይታም ታሪክን ከእውነታ አመሳስሎ ፣ ባሕልን ከማንነት አስታርቆ ለማሳየት የቦታ ምርጫዎቹ ልየታዎች ስኬታማ ሆነዋል፡፡

ጀቢና ፊልም ላይ በመተወን ታሪኩን ሕይወት የዘሩበት ተዋናዮች ከጅማሬ አስከፍጻሜ ልብ እንዳንጠለጠሉ ተጉዘዋል፡፡ ካሳሁን ፍስሀ /ማንዴላ/፣ ቤተልሄም ሸረፈዲን፣ እታፈራሀ መብራቱ፣ አስራት ታደሰ፣ ሉሊት ይሳቅ፣ ናትናኤል መኮንን እና ሕጻን አሜን ሚኪያስ ወይም ትንሽዋ ኑኑ በዋና ተዋናይነት ታሪኩን መርተዋል። ሌሎች ከሁለት መቶ በላይ የሚቆጠሩ ተዋንያኖች ደግሞ በአጃቢነት ተሳትፈዋል፡፡

በጀቢና ፊልም ስኬት ከጀርባ ያሉ ባለሞያዎች አስተዋጽኦ ደግሞ ለፊልሙ ድንቅ ሆኖ መጠናቀቅ የላቀ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ፊልሙን ፊልም አድርጎ ለመልካም ዕይታ ለማብቃትም የተለያየ ዕውቀትና ችሎታ ያላቸው ሁለት መቶ ሰላሳ ባለሙያዎች ተሳትፎቸው የጎላ ነው፡፡

የጀቢና ፊልም ታሪክ መነሻ ‹‹ምሰሶዋ ›› የተባለ መጽሀፍ ሲሆን የመጽሀፉ ደራሲና ባለታሪክ ደግሞ የፊልሙ ኤክዝኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰር ሄለን እሸቱ ናት። ሄለን ፊልሙ ዕውን ሆኖ ለዕይታ ከመብቃቱ በፊት ‹‹ምሰሶዋ›› በሚለው መድብሏ በራሷ ላይ የሆነባትን እውነት ገጽ በገጽ፣ አንድ በአንድ ከትባ ለንባብ አቅርባለች፡፡

የደራሲዋ የመጽሀፍ ሀቅ በልጅነት ዕድሜዋ ማንነቷ የተፈተነበት፣ ሴትነቷ፣ የተደፈረበትና በድንገት የፍቅር ታሪኳ የተቀየረበትን ክፉ አጋጣሚ ይተርካል፡፡ በዚህ ስብራት መሀል የበጎ ሰዎች ደግነት ተንጸባርቋል፡፡ የባሕልና ወግ ጥንካሬ፣ የእርቅ ስርዓት ኃይልና የበቀል ሽንፈት ታይቷል፡፡ አይበገሬ ብርታት፣ የሕይወት ትግልን ወልዶ የማንነት ጽናትን መስክሯል፡፡ የሄለን እሸቱ ታሪክ ክፋይ፣ የውስጠቷ እውነትም ይኸው ነው፡፡

ባለታሪኳ ሄለን ከዓመታት በፊት በምሰሶ መድብል የታሪኳን እውነት ቁልጭ አድርጋ ከተበችው፡፡ ለእሷ እንዲህ መሆኑ ብቻ ግን አልበቃትም፡፡ በማንነቷ ላይ የደረሰው ክፉ የሕይወት ንቅሳት በሌሎች እህቶቿ እንዳይደገም ተጨማሪ መንገዶችን አሰላች፡፡

ይህ በብዙዎች ቤት ያለ እውነት፣ በበርካታ ሴቶች ልቦና ያልሻረ ቁስል ዛሬም ሥር ሰዶ ሕመሙ በርትቷል። አሁንም ጥቂት አይሏቸው ሕጻናት፣ እናቶችና መሰል እህቶቿ በዚህ እሾሀማ መንገድ እየተራመዱ ነው። ሄለን ይህን ጠንቅቃ ማወቋ ሕመሙን እንድትጋራ፣ ችግሩን እንድትካፈል አስገደዳት፡፡ መጽሀፉ ዳግም በፊልም ተሰርቶ በርካቶችን እንዲያስተምር ልቦናዋ ከልብ ፈቀደ።

በፊልሙ የሕይወቷ ውጣረድ፣ የማንነቷ ትግልና የአሸናፊነቷ ድል ተንጸባረቀ፡፡ የበርካታ ሴቶች ውስጣዊ ቁስል፣ የክፉ ደግ ማንነቶች ጥግ ተገለጠ፡፡ የኦሮሞ ገዳ ሥርዓት ለሴት ልጅ ያለው ቦታና ክብር በግልጽ ታየበት፡፡ እነሆ! ‹‹ጀቢና›› የታሪኳ ክፋይ፣ የብዙሀኑ መልክና መስተዋት ሆኖ ዕውንነቱን አወጀ፡፡

ሄለን እንደምትለው መጽሀፉን አሳትማ ማውጣቷ የእሷም የሌሎችም እውነታ ነውና መልካምነቱ ይጎላል። መጽሀፍ ብቻውን ግን ከብዙሀን ደጅና ጓዳ አንኳኩቶ ለመግባት በቂ የሚባል ኃይል የለውም ፡፡ ፊልም ደግሞ በአንድ ግዜና ቦታ ለበርካቶች ለመድረስ ጠንካራ ይሉት ጉልበት ይዟል፡፡

እንደ ሄለን ዕምነት የእሷ ታሪክ በትንሹ ለአንዲት ሴት ሕይወት መለወጥ ፣ ለሌሎችም መመሪያና ማስተማሪያ እንዲሆን ተደርጎ ተከውኗል፡፡ መጽሀፏን ወደ ፊልም ለመቀየርም የብዙዎች ልፋትና ድካም አርፎበታል፡፡ ጀቢና ሄለን የኖረችበት፣ ያለፈችበት እውነተኛ የሕይወት ታሪክ ነው፡፡ ዛሬ የጨለመ ሁሉ ነገ ሲያልፍ ብርሀንና ተስፋ እንደሚሆን በወጉ ይጠቁማል፡፡ ፊልሙ የብርታት፣ ጥንካሬና ትዕግስትን ኃያልነት በተግባር ያንጸባርቃል፡፡

በጀቢና ፊልም የባለታሪኳን ገጸ ባሕርይ ተላብሳ የሰራችው ቤተልሄም ሸረፈዲን እውነታውን አሳምራ በማሳየት ብቃቷን በአግባቡ ተወጥታለች፡፡ ቤተልሄም እንደምትለው ዋና ባለታሪኳ ሄለን የራሷን ሕይወት ሳትደብቅ በመጽሀፍና በፊልም ማድረሷ በእጅጉ ያስመሰግናታል፡፡ በተለይ ይህን እውነታ ወደ ፊልም እንዲቀየር ዋጋ መክፈሏ ለብዙዎች ሕመምና ቁስል መሻር እንደ መድሀኒትነት ይቆጠራል፡፡

ጀቢና ብዘዎች ከልብ በሆነ የሙያ ትጋት የተሳተፉበት ፊልም ነው፡፡ ፊልሙን በስኬት የተዋጣለት ለማድረግም የባለታሪኳ ድርሻ ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል፡፡ ለዚህ እውነት ደግሞ ቤተልሄም ሁሉንም ተሳታፊዎች ከልብ ታመሰግናለች፡፡

ፊልሙን በዋና ተዋናይነት ከመሩት መካከል ናትናኤል መኮንን አንዱ ነው፡፡ ናትናኤል በጀቢና ላይ የተንጸባረቀው ታሪክ በብዙ ሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚደርሰው እውነታ ስለመሆኑ ይናገራል፡፡ በርካቶች በያዙት ዓላማና ዕቅድ ካሰቡት እንዳይደርሱ ዕንቅፋት የሚሆናቸው በየቤቱ የሚፈጸመው በደልና ጥቃት ነው። ይህ አይነቱ ሀቅ ደግሞ በበርካታ እናቶችና ሴቶች ላይ ጫናውን ጥሎ ክንዱን አፈርጥሟል፡፡

በናትናኤል አገላለጽ በተለያዩ ተፅዕኖዎች አንገታቸውን ደፍተው በየቤቱ ቀርተዋል ለሚባሉ ነፍሶች ‹‹ ጀቢና››ተገቢ የሚባል መልስ አለው፡፡ ፊልሙ እያንዳንዳቸው ‹‹ተሰብሪያለሁ፣ ወድቂያለሁ›› ከሚሉበት መንፈስ አላቆ ኃይልና ጉልበት ለመስጠት የሚያግዝ ነው፡፡ ፊልሙን እንደ ሀገር፣ እንደቤት፣ እንደ እናትና እህት መርምሮ ላስተዋለው ደግሞ ትርጓሜው ግልጽና እውነት ሆኖ ይገኛል፡፡

ናትናኤል በጀቢና ፊልም ላይ ዋና ተዋናይ ሆኖ መሳተፉ በእጅጉ ያኮራዋል፡፡ የተቀረጹት ገጸ ባሕርያት እውነተኞች በመሆናቸው ሥፍራው ድረስ በመሄድ ታሪኩን ለመሳል ተሞክሯል፡፡ ያለፉበትን ዘመን አሻራ፣ አለባበስ፣ ወግና ባሕል ሳይቀር በጥንቃቄ መቀረጹ ለፊልሙ በወግ መሳካት ምክንያቱ ነበር፡፡

ለእሱ ፊልሙ የተለመደው አይነት ፊልም አይደለም፡፡ እውነተኛ ታሪክና ትክክለኛ ስሜትን ያንጸባርቃል፡፡ የብዙዎችን ሕይወትና ያልሻረ ቁስል ያስታውሳል፡፡ እንዲያም ሆኖ በዕንባና ሀዘን ብቻ የሚቋጭ አይሆንም። መፍትሄውን ጠቁሞ፣ ብርታት ጽናትን አሳይቶ ደማቅ ምሳሌነቱን ያጎላል፡፡

ናትኤል የዚህን ፊልም ዓላማ የሚለካው ሲኒማ ቤት ገብቶ ተመልካች ተዝናንቶበት እንዲታይ በማድረግ አይደለም፡፡ የጀቢና ፊልም ዋንኛ ግብ በየቤቱ ያሉ ተበዳይ ነፍሶችን በወግ በአግባቡ መድረስ ነው፡፡ ከሕመማቸው ፈውሶ፣ ከስብራታቸው ጠግኖ ዳግም ትንሳኤያቸውን ማወጅ ነው፡፡ ይህ እውነታ ደግሞ በፊልሙ ሙሉ ታሪክ ተንጸባርቆ ሕያውነቱ ተረጋግጧል፡፡

በሳሙኤል ተሻገር /የእማዬ ልጅ/ ደራሲና ዳይሬክተርነት ዕውን የሆነው ‹‹ጀቢና›› የበርካቶችን ሕይወትና ያልተነገሩ ድብቅ ሚስጥራትን ይነካካል፡፡ ብዙዎች ወደ ውስጥ አልቅሰው የቆሰሉበትን፣ ሕመም አመላክቶ መፍትሄውን ለመጠቆምም ጠንካራ ጉልበት አለው፡፡

ደራሲና ዳይሬክተሩ ሳሙኤል ተሻገር /የእማዬ ልጅ/ እንደሚናገረው ደግሞ ‹‹ጀቢና ››ከርዕሱ ጀምሮ ተጽዕኖ ፈጣሪነቱ በገሀድ ጎልቶ ይስተዋላል፡፡ ባለታሪኳ ሄለን እሸቱ ያለፈችባቸውን የሕይወት መንገዶች ‹‹ምሰሶዋ›› በተሰኘው መጽሀፏ ካስነበበች በኋላ ታሪኩን ወደ ፊልም ቀይሮ ለዕይታ ለማብቃት በርካታ የጥበብ ባለሙያዎች ሊጣመሩ ግድ ብሏል፡፡

ሳሙኤል መፅሀፉን መነሻ አድርጎ ወደ ፊልም የተቀየረው ‹‹ጀቢና›› ዛሬም ድረስ በሀገራችን ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጾታዊ ጥቃትና በደል ለማሳየት መስታወት መሆኑን ይናገራል፡፡ ፊልሙ ከክፉ ወንዶች ባለፈ መልካም ልቦና የተቸራቸው አጋሮች መኖራቸውን ጭምር አመላካች ነው፡፡

ትናንት በ ‹‹ነበር ›› ቀርተዋል የሚባልላቸው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችም አሁን ድረስ ነፍስ ስለመዝራታቸው የጀቢና ፊልም በዋንኛ እማኝነት ተቀርጻል፡፡ ባለታሪኳ ካለፈችባቸው ሻካራማ የሕይወት መንገዶች ባሻገር ሴት ልጅ በአካባቢው የገዳ ሥርዓት ተዳኝታ ስለ በደሏ ፍትህ የምታገኝበት እውነታም ምስክርነቱ ታይቷል፡፡

የፕሮዳክሽን ማናጀር አብርሀም ማዕረግና ሲኒማቶግራፊ ጋድ ክፍሎም የተሳተፉበት በድራማ ይዘት የተቀረጸው ‹‹ጀቢና›› በኢትዮጵያ የፊልም ፕሮዲሲዩሰሮች የዘርፍ ማኅበር ተገቢውን የማረጋገጫ ዕውቅና አግኝቷል።

ስለ ፊልሙ አጠቃላይ ይዘት ጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም ሙሉ ጋዜጣዊ መግለጫ በጎልደን ቱሊፕ ሆቴል የተሰጠ ሲሆን ለፊልሙ ስኬት አስተዋጽኦ የነበራቸው አካላት በሙሉ ምስጋና ተችርዋል፡፡

ከመግለጫው መልዕክት ለማወቅ እንደተቻለው ፊልሙ ከተመረቀ በኋላ በተለመደው መልኩ በሀገር ውስጥ ሲኒማቤቶች የሚታይ አይሆንም ፡፡ ‹‹ጀቢና ›› በኢንተርናሽናል የፊልም ዘርፍ በዓለም አቀፉ ካታሎግ የፊልም ገበያውን እንዲቀላቀል ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። ከዓለም አቀፍ ባለሙያዎች በመጣ ሀሳብ መሰረትም ለተወሰኑ ወራት በማንኛውም ሲኒማ ቤት እንዳይታይ ከስምነት ተደርሷል፡፡

ወደፊት መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓ.ም በሚኖረው መርሀ ግብር ደግሞ የኢትዮጵያ ባለሀብቶች፣ ባለሥልጣናት፣ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችና ታዋቂ ሰዎች በሚገኙበት በጀቢና ሥም ለሚቋቋመው ፋውንዴሽን ታላቅ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ይካሄዳል፡፡ በዚህ ዕለትም የተለያዩ የውጭ ሀገራት ፊልም ሰሪዎች፣ የሀገር ውስጥና የዳያስፖራ ባለሙያዎችና በርካታ እንግዶች እንደሚገኙ ተጠቁሟል።

‹‹በሕይወት ያለነው ከዕጣ ፈንታችን ጋር ለመታገል ነው›› የሚል መርህን ያንጸባረቀው ‹‹ጀቢና›› የተሰኘው እውነታዊ ፊልም ዕለተ ሰኞ ጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም በሀገር ፍቅር ቲያትር በርካታ የጥበብ ቤተሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በቀይ ምንጣፍ ሥነሥርዓት በታላቅ ድምቀት ተመርቋል፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You