በሸኔ ላይ የተጀመረው የተቀናጀ ዘመቻ የሀገራቱን ሁለንተናዊ ትብብር ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው!

ዓለማችንን እየተፈታተኗት ካሉ ወንጀሎች በዋንኛነት የሚጠቀሱት ጽንፈኝነት ፣ ሽብርተኝነት ፣ ሕገወጥ የሰው እና የጦር መሳሪያ ዝውውር ፣ የኮንትሮባንድ ንግድ ወዘተ ናቸው። ወንጀሎቹ በተለይም በማደግ ላይ ባሉ እና ነገዎቻቸውን ብሩህ አድርገው እየተንቀሳቀሱ ለሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ከፍ ያሉ ተግዳሮቶች ስለመሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።

ወንጀሎቹን ለመከላከል ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በተቀናጀ መንገድ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም፤ ከወንጀሎቹ ስፋት ፣ ጥልቀት፣ ውስብስብነት አኳያ የሚጠበቀውን ያህል ስኬታማ መሆን አልተቻለም። ዛሬም በነዚህ ወንጀሎች የሚፈተኑ ሀገራት እና ሕዝቦች ጥቂት አይደሉም። አጠቃላይ በሆነው ማኅበራዊ ፣ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎቻቸው ላይ እየተፈጠረ ያለውም መንገጫገጭ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ወንጀሎቹ በአንድም ይሁን በሌላ በሀገራቱ እና በሕዝቦቻቸው ሰላም እና መረጋጋት ፣ የመልማት እና የማደግ መሻት ላይ አሳሳቢ ፈተና ሆነዋል። በአንዳንድ አጋጣሚዎችም ሀገረ- መንግሥትን ስጋት ውስጥ በመክተት ሕዝቦችን ለበዛ መከራ እና ስቃይ ፣ ሞት እና ስደት እየዳረጉ ያሉበት ሁኔታ የዕለት ተዕለት ዜናዎቻችን አካል ከሆነ ውሎ አድሯል።

እነዚህ በባህሪያቸው ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ወንጀሎች ፣ ሊፈጥሩት የሚችሉት አደጋ በአንድ አካባቢ /ማኅበረሰብ ታቅቦ የሚቆይ አይደለም፣ በተገኘው አጋጣሚ በሙሉ የአደጋ አድማሳቸውን እያሰፋ ስጋትነታቸውን እያገዘፉ የሚሄድ ጭምር ናቸው።

ችግሩን በአግባቡ በመከላከል ሊያስከትል የሚችለውን ዘርፈ ብዙ አደጋ ማስቀረት የሚቻለው በተቻለ መጠን ሀገራት የችግሩን አሳሳቢነት ተረድተው በጋራ መንቀሳቀስ ሲችሉ ነው። በተለይም ሰፊ ድንበር የሚጋሩ ሀገራት ችግሩ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የብሔራዊ ደህንነታቸው የጋራ ስጋት መሆኑ የማይቀር ፤ ሊያስከፍላቸው የሚችለውም ዋጋ የከፋ እንደሚሆን ይታመናል።

ሀገራቱ ይህንን ብሔራዊ የደህንነት ስጋት ተሻግረው የሕዝቦቻቸውን ሰላም እና ደህንነት ፣ የመልማት እና የማደግ ፍላጎት እውን ለማድረግ ፣ ወንጀሎቹን ለመከላከል በተናጠል ከሚያደርጓቸው ጥረቶች በተጓዳኝ ያላቸውን አቅም አቀናጅተው መንቀሳቀስ ፣ ለዚህ የሚሆን ቁርጠኝነት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።

የኢትዮጵያና የኬንያ መንግሥታት ለአካባቢው ሰላም እና መረጋጋት ስጋት እየሆነ ያለውን አሸባሪውን የሸኔ አሸባሪ ቡድን በጋራ ለመደምሰስ የጀመሩት ጥረት የዚሁ እውነታ ተጨባጭ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፤ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል በዓለም አቀፍ ፈረጃ ለሚደረጉ ጥረቶች መልካም ተሞክሮ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

አሸባሪው የሸኔ ታጣቂ ቡድን መንግሥት እና ሕዝብ የሰጡትን የሰላም ዕድል በመርገጥ ላለፉት ሦስት ዓመታት በሽብር ተግባራት ላይ ተሰማርቶ ቆይቷል። ንጹሐንን ከማገት እና ከመግደል ጀምሮ፤ የመንግሥት እና የሕዝብ ንብረትን በመዝረፍ እና በማውደም ላይ ተሠማርቷል። አሰቃቂ ወንጀሎችን በመፈጸም ሽብርን ሲያስፋፋ ፣ በሕዝቦች መካከል አለመተማመንን በመፍጠር ግጭቶችን ሲፈጥር እና ሲያራግብ ቆይቷል።

ድንበር በመሻገርም በሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ እና የሰዎች ዝውውር፤ በኮንትሮባንድ ንግድ ከዛም ባለፈ የጎሳ ግጭቶችን በመቀስቀስ ለጎረቤት ሀገር ኬንያ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ሆኗል፡፡ በሀገራቱ የድንበር አካባቢዎች ለዘመናት ሰፍኖ ለቆየው ሰላም እና መረጋጋት ፈተና ሆኗል።

በሽብር ቡድኑ ላይ ፈጥኖ እርምጃ መውሰድ ካልተቻለ ፤ ከቡድኑ ተጨባጭ ባህሪ አኳያ ላለፉት ሦስት ዓመታት በሀገር ውስጥ የፈጸሟቸውን ወንጀሎች ኬንያውያን ወንድሞቻችን ላይ የማይቀጥልበት ምንም ምክንያት አይኖረውም።

የቡድኑን ተፈጥሯዊ ባህሪ እና የጥፋት መንገድ፣ ቀጣይ ስጋት በአግባቡ በመረዳት የኢትዮ -ኬንያ የደኅንነትና የጸጥታ ተቋማት በቡድኑ ላይ የተቀናጀ ዘመቻ ማካሄድ መጀመራቸው ፣ ለሕዝቦቻቸው ሰላም እና መረጋጋት ትልቅ አቅም ነው፤ በሀገራቱ መካከል ያለውን ወዳጅነት እና ሁለንተናዊ ትብብር ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው!

አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You