
/የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለትግራይ ሕዝብ በተለይ ለትግራይ ሊሂቃን ያቀረቡት ጥሪ ሙሉቃል/
በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደገለጽኩት፤ የትግራይ መሬትና ሕዝብ የስልጣኔ መነሻ፣ የሀገረ መንግሥት ዋልታና ጋሻ ናቸው። የትግራይ መሬትም የመንግሥት አስተዳደር፣ የአስተዳደር ሥርዓት እና የሀገር እሴቶች መፍለቂያና ማቀቢያ ነው። የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያን በመፍጠር እና በመንከባከብ ውስጥ ያለው ሚና ጥልቅ መሆኑን ፀሃይ የሞቀው ሀቅ ነው።
የትግራይ ሕዝብ በማይፋቅና በማይደበዝዝ ቀለም የተፃፈ ደማቅ ታሪክ ያለው ሕዝብ ብቻ አይደለም፤ ከምንም በላይ ደግሞ የሀገሩ ወዳጅ፣ የሰላምና የብልፅግና ወዳጅ የሥራ ወዳጅ መሆኑን ሁሉም የሚያውቀው ሀቅ ነው። ትግራይ ብዙ ሊቃውንት ምሁራንን፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ ፖለቲከኞችን፣ ሕዝባቸውንና ሀገራቸውን የሚጠቅሙ የሀገር ሽማግሌዎችን አፍርታለች።
የትግራይ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ የመንግሥትን ምንነት ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በመሆን ሀገረ መንግሥት የመሠረተ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ሀገረ መንግሥቱ አደጋ ላይ በወደቀበት ወቅትም ቢሆን ከባድ ዋጋ እየከፈለ ሀገረ መንግሥቱን ያቀበ ሕዝብ ነው።
ለዚህም ነው ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በመሆን ለሀገሩና ሉዓላዊነቱ ክብር ሲል ከድርቡሽ፣ ከግብፅ እና ከጣሊያን፣ በኋላም ከምዕራብ ወይም ከምሥራቅ እንዲሁም ከሰሜን ወራሪ ኃይሎች ጋር ተዋግቶ ለሀገሩ ሉአላዊነት መስዋእትነት የከፈለው። በተጨማሪም ለዴሞክራሲ፣ ለሰላምና ለልማት ዋጋ ከሌሎች ወንድማማች ብሔሮች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ልማትና እድገት ውስጥ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
ሌላው የትግራይ ሕዝብ መለያ ባህሪ የሀገር ፍቅር ነው።ልክ የትግራይ መሬት የኢትዮጵያ መሠረት እና ማዕከል ሆኖ እንዳገለገለ ሁሉ የትግራይ ሕዝብ ልብም በሀገር ፍቅር ስሜት የተሞላ መሆኑን የታሪክ ማስረጃዎች በመጥቀስ ለማረጋገጥ መሞከር “ለቀባሪ ማርዳት” ነው።
የትግራይ ሕዝብ ሀገሩን በሰላሟም ሆነ በችግር ጊዜ ኪዳኑን ሳይክድ ዋጋ እየከፈለ የአባቶቹን አደራ ጠብቋል።
በተለያዩ ዘመናት ማእከላዊ መንግሥት እንቅፋት ሲገጥመው ሀገሪቱን በማዳን እና ክፍተቶችን በመሙላት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
ከአክሱማዊ መንግሥት ውድቀት በኋላ የተፈጠረውን ክፍተት በመዝጋት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። በዘመነ መሳፍንት ጊዜ ክፍተቶችን በማስተካከል ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ሀገራዊ አንድነትን በማረጋገጥ ረገድም ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
የትግራይ ሕዝብ ታታሪና ሥራ ወዳድ ነው። የትግራይ ሕዝብ ኮረብታ ላይ ወጥቶ ያለማል፣ ድንጋይ ሰንጥቆና ፈልፍሎ የሚገነባ ሕዝብ ነው። ይህንን ግልጽ እና የታወቀ እውነታ ለማሳየት ማስረጃ ማቅረብ አያስፈልገኝም። የትግራይ ሕዝብ ትንሽ ሰላም በነበረበት ወቅት በንግድ፣ በግብርና፣ በሕንፃ፣ በኪነጥበብ፣ በቴክኖሎጂ መስክ ያከናወኗቸው ተግባራት መንገደኞች የሚገነዘቡት ሃቅ ነው። ከዚህም በላይ በፈተናዎች ውስጥ የማይናወጥ በመንፈስ የጠነከረ ሕዝብ ነው።
እንደ አለመታደል ሆኖ ግን በተለይ ባለፉት መቶ ዓመታት በተለያዩ አጋጣሚዎችና ምክንያቶች በተለይም ከማእከላዊ መንግሥት ጋር ባለው ግጭት የትግራይ መሬት የጦር አውድማ ሆኗል፤ የትግራይ ሕዝብም የጦርነት መጠቀሚያ ሆኗል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን መነሳት ያለበት ጥያቄ የትግራይ ሕዝብ ባለፉት መቶ ዓመታት ጦርነት ምን አይነት ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፀጥታዊ ጥቅሞች አገኘ፤ ምንስ ከሰረ ? ብለህ መጠየቅና ማሰላሰል ይገባል።
በዚህ ጊዜ አንድ አስተዋይ የትግራይ ሊሂቅ ትግራይና ሕዝቦቿ ከጦርነቱ ያገኙት ወይስ ያጡት ጥቅም ይበዛል ብሎ መጠየቅና መልስ ማግኘት አለበት። ሌላው ሊነሳ የሚገባው ጦርነት ብቸኛው አማራጭ ነበር ወይ? ሌላ መፍትሔ አልነበረውም? የሚለው ጥያቄ ነው። እና ከአሁን በኋላ ጦርነት እንዳይነሳ ለመከላከል ምን ማድረግ ይሻላል? የሚል ጥያቄውን መጠየቅ እና መልሱን ማግኘት አስፈላጊ ነው።
በጣም የሚያሳዝነው የትግራይ ሕዝብ የትናንት ቁስሉን ሳያገግም አሁንም ሰላምና መረጋጋት አግኝቶ ሠርቶ እንዳይገባና እንዳይለማ በጦርነት ወሬ ፍርሃት ሽብር እየኖረ መሆኑ ነው። እንዲህ ዓይነቱን አደጋ እንዴት መቋቋም እንደሚቻል ተረጋግቶ መወያየት ያለበት ጉዳይ መሆኑ ከጠቢብ የተሰወረ አይደለም።
ስለዚህ የትግራይ ተወላጆች በፖለቲካ፣ በቢዝነስ፣ በፀጥታ ፣ በአካዳሚክ እና በሚዲያ እና በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ምሁራን ለትግራይ ሕዝብ እስካሁን የተከፈለው ዋጋ ይበቃዋል፤ ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ የለም ብላችሁ መጀመሪያ በውስጣችሁ ያለው ልዩነት በሰላም በውይይትና በመረዳዳት የትግራይ ሕዝብን አንድነት በሚያረጋግጥ መንገድ ጉዳያችሁን እንድትጨርሱ እጠይቃለሁ።
ቀጥሎ ከፌዴራል መንግሥትና ከሌሎች ኃይሎች ጋር ያላችሁን አለመግባባት በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት እና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ እንድትሆኑ ጥሪ አቀርባለሁ።
በፌዴራል መንግሥት በኩል በሁሉም ጉዳዮች ላይ መወያየት፣ የሃሳብ ልዩነቶችን እንደ የአመለካከት ልዩነት ወስዶ ግን በተግባባንባቸው ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተስማምተን እንድንሠራ የሚያደርግ ሁኔታ እንዳለ በመገንዘብ ሕዝብን ከስጋት እናቶች እንቅልፍ ከማጣት፣ወጣቶችን ከመሰደድ ማዳን ላይ እንድትሠሩ ከሁሉም በላይ ግን ሕዝብ ወደ ልማትና ማገገም እንዲመለስ አብረን እንድንሠራ በድጋሚ ጥሪ አቀርባለሁ።
ሰላምና መረጋጋት ለትግራይ ሕዝብ
ጥላቻና ጦርነት ይበቃል ! ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ትኖራለች!! ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም