የኦሮሚያ ክልል የቱሪዝም ዘርፍ አበረታች አፈፃፀም

የቱሪዝም ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ይታመናል። በሥራ ዕድል ፈጠራ ከሚታወቁ የምጣኔ ሀብቱ ዘርፎች አንዱ መሆኑም ይታወቃል።

የቱሪዝም ገቢ የማይገባበት ቤት እንደሌለ ተደርጎም ይታሰባል። ከዚህ ዘርፍ የሚቋደሰው ብዙ ነው። የቱሪስት ቁሳቁስ ከሚሸጡት፣ እንደ ፈረስና የመሳሰሉትን የትራንስፖርት አማራጮች ከሚያቀርቡት ጀምሮ፣ ባለኮከብ ሆቴሎች፣ አየር መንገዶች፣ መንግሥታት.ወዘተ ከዘርፉ ገቢ በእጅጉ ተጠቃሚ ናቸው።

የሀገር ገቢን በማሳደግ፣ ድህነትን በመቀነስ በኩል ከፍተኛ ሚና እንዳለው መረጃዎች ያመለክታሉ። ለእዚህም ሲባል ሀገሮች ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ያላቸውን እምቅ የቱሪዝም ሀብት በማልማት፣ በማስተዋወቅ እና ለገበያ በማቅረብ ይሠራሉ።

በቱሪዝም ሀብታቸው ከሚታወቁት የዓለም ሀገሮች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለእዚህ ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መሆኗ ይታወቃል።

እንደሚታወቀው ሀገሪቱ አያሌ ባሕላዊና ታሪካዊ እንዲሁም ተፈጥሯዊ መስሕቦቿ አሏት። የሰው ዘር መገኛ መሆኗ፣ ብሔራዊ ፓርኮቿ፣ ደማቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶቿ፣ የአያሌ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እናት መሆኗ የፈጠረላት ቱባ ባሕል፣ የአየር ንብረቷ ምቹነት በዘርፉ እምቅ ሀብት ያላት እንድትሆን አድርገዋታል።

ከእነዚህ የቱሪዝም ሀብቶቿ መካከልም በርካታዎቹ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች በመባል በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ የባሕል ተቋም /ዩኔስኮ/ ተመዝግበውላታል። ይህም ሁኔታ እነዚህ የቱሪዝም ሀብቶች ከእሷም አልፈው የዓለም ቅርስ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

እነዚህ የተፈጥሮ፣ የባሕልና የታሪክ ሀብቶች ከመላ ዓለም በሚመጡ ተመራማሪዎች፣ ጎብኚዎች እንዲሁም በሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ይጎበኛሉ። ሀገሪቱም ዓለምም በስስት የሚመለከቷቸው የኢትዮጵያ መገለጫ ብቻ የሆኑ ጥቂት የማይባሉ የቱሪስት መስሕቦች ያሉባት እንደመሆኗ በዓለም አቀፍ ደረጃም በጎብኚዎች ልብ ውስጥ ትገኛለች።

እነዚህ መስሕቦች በሀገር ውስጥና በውጭ ቱሪስቶች የሚጎበኙ ቢሆንም፣ ካላቸው የመጎብኘት አቅም አኳያ ሲታይ ግን የጎብኚዎቹ ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል ሳይሆን ቆይቷል። ይህን ለመለወጥና ከቱሪዝም ዘርፉ መገኘት ያለበትን ትሩፋት ለማግኘት የለውጡ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል።

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የአስር ዓመቱ መሪ እቅድ የምጣኔ ሀብቱ ምሰሶ ካላቸው አምስት ዘርፎች አንዱ የቱሪዝም ዘርፉ እንዲሆን ሲያደርግም ይህ እምቅ ሀብት ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ያለውን ከፍተኛ ፋይዳ ታሳቢ በማድረግ ነው።

በዚህም ሀገሪቷ ከቱሪዝም ሀብቱ የሚገባትን ገቢ እንድታገኝ የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። በመዲናዋና በክልሎች በመንግሥት ደረጃ በቱሪስት መዳረሻ ልማት እንዲሁም በቅርሶች እድሳት ላይ የተከናወኑትና እየተከናወኑ ያሉት ሰፋፊ ሥራዎችም ይህንኑ ያመለክታሉ።

በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ለቱሪስት መዳረሻ ሊሆኑ የሚችሉ የተለያዩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል፤ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከልም በገበታ ለሸገር ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ከተማ ተገንብተው ወደ ሥራ ከገቡ ዓመታት የተቆጠሩት የአንድነት፣ የወዳጅነትና የእንጦጦ ፓርኮች ይጠቀሳሉ። መዳረሻዎቹ እንደታለመላቸውም የከተማዋና የሀገሪቱ የቱሪስት መስሕቦች መሆን ችለዋል። የከተማዋንም የሀገሪቱንም ገጽታ በእጅጉ እየቀየሩ ይገኛሉ።

መንግሥት ይህን ተነሳሽነቱን ወደ ክልሎች በማስፋት በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቱ ደግሞ በወንጪ ዳንዲ ኢኮ ቱሪዝም፣ በጎርጎራ፣ በኮይሻ /የሀላላ ኬላ ሪዞርትና የጨበራ ጩርጩራው የዝሆን ዳና ሎጅ/ ደረጃቸውን የጠበቁ መዳረሻዎችን ገንብቶ ወደ ሥራ እንዲገቡ አርጓል፤ በግሉ ዘርፍ የተገነባው የቤኑና መንደር ሌላው የቱሪዝም ዘርፉ ትኩረት ውጤት ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአዲስ አበባ ተጀምሮ ወደ ክልል ከተሞች እየተስፋፋ ያለው የኮሪደር ልማት የአዲስ አበባንም የክልል ከተሞችንም፣ የሀገሪቱንም ገጽታ በእጅጉ እየቀየረ ከመሆኑም በተጨማሪ ለቱሪዝም ዘርፉም ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት እምነት እየተጣለበት ይገኛል።

እነዚህ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች መልማታቸው የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር እያደረገው ስለመሆኑ እየተገለጸ ነው።

ክልሎችም የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን በማልማት ቱሪስቶችን በመሳብ ገቢያቸውን በመጨመር ላይ ይገኛሉ። በቱሪዝም እምቅ አቅማቸው ከሚታወቁ ክልሎች አንዱ የኦሮሚያ ክልል ነው። ክልሉ በርካታ የተፈጥሮና የታሪክና የባሕል የቱሪዝም ሀብቶች እንዳሉት ይታወቃል።

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ፣ የሶፍ ዑመር ዋሻ፣ የበርካታ አእዋፋት መገኛ የሆኑት የአቢጃታና ሻላ ሐይቆች፣ የዝዋይ፣ የላንጋኖ እንዲሁም የወንጪ ሐይቆች፣ በበርካታ አካባቢዎች የሚገኙ ፍል ውሃዎች፣ የጅማ አባ ጅፋር ቤተመንግሥት፣ ወዘተ በብዙዎች ዘንድ ከሚታወቁ የክልሉ የቱሪዝም መስሕቦች መካከል ይገኙበታል።

የኦሮሞ ብሔር የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ የተመዘገበው የገዳ ሥርዓት፣ የብሔረሰቡ ባሕላዊ አለባበሶች፣ ጨዋታዎች፣ የዳኝነትና የመሳሰሉት ሥርዓቶች ከክልሉ የቱሪዝም ሀብቶች ጥቂቶቹ ናቸው።

እነዚህን የክልሉን የመስሕብ ሀብቶች በማልማት፣ በማስተዋወቅ፣ መስሕቦቹን ለመጎብኘት የሚያስችሉ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በመገንባት ነባሮቹን በማደስ ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ ሥራዎች በመሥራት ክልሉ ከዘርፉ የሚያገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።

መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ ክልሉ የቱሪስት መስሕብ ሀብቶቹን በተለያዩ መንገዶች እያስተዋወቀ ይገኛል። በኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት፣ በቪዚት ኦሮሚያና በሚስ ኦሮሚያ መርሐ ግብሮች መስሕቦቹን ያስተዋውቃል።

እንደ ጥምቀት፣ ኢሬቻ ያሉትን የአደባባይ በዓላት የቱሪዝም ፋይዳ በሚገባ በመገንዘብና ለእዚህም በቂ ዝግጅት በማድረግ ቱሪስቶችን ለመሳብ የሚደረገው ጥረትና እሱን ተከትሎ እየታየ ያለው ለውጥም እንዲሁ ከዓመት ዓመት እየጨመረ መጥቷል።

በክልሉ የቱሪዝም ዘርፍ እንቅስቃሴ በተለይ ባለፉት ስድስት ወራት የዘርፉ አፈጻጸም ላይ ያነጋገርናቸው የክልሉ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ነጋ ወዳጆ ያገኘነው መረጃም ይህንኑ ክልሉ ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረትና በዘርፉ እየተመዘገበ ያለውን ለውጥ ያመለክታል።

ምክትል ኮሚሽነሩ፤ በተያዘው በጀት ዓመት ያለፉት ስድስት ወራት በክልሉ የቱሪዝም ዘርፍ አበረታች እንቅስቃሴ መታየቱን ይገልጻሉ። የፌዴራል መንግሥት ባለፉት ዓመታት የቱሪዝም ዘርፉን ከማሳደግ አንፃር ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ በርካታ ሥራዎችን ማከናወኑን እሳቸውም ጠቅሰው፣ በኦሮሚያ ክልልም በተለያዩ ቦታዎች ላይ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን የማልማትና የነበሩ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች የማደስ ሥራዎች ተከናውነዋል ሲሉ ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። ለእዚህም በወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም እና በቤኑና መንደር የተከናወኑትን ሥራዎች ጠቅሰዋል።

የክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ይበልጥ እንዲነቃቃ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባሮች እየተከናወኑ መሆናቸውንም አመልክተው፣ ለእዚህም አዳዲስ ሆቴሎችና ሪዞርቶች እንዲገነቡና ነባሮቹም ታድሰው ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉንም ገልፀውልናል።

የቱሪዝም ዘርፉ ከሚያስገኘው ገቢና የሥራ ዕድል በተጨማሪም የሀገሪቷንም ገፅታ ከመገንባት አንፃር የሕዝብ ለሕዝብ ቅርርብን በመፍጠር ከፍተኛ ድርሻ አለው ያሉት አቶ ነጋ፣ ጎብኚዎች ጎብኝተው መሄድ ብቻ ሳይሆን ዘመድ አፍርተው እንዲመለሱ ጭምር ማድረግ ላይም እንደሚሠራ ገልጸዋል። ስለኢትዮጵያ ያላቸው እውቀት እንዲሰፋና ተመልሰው እንዲመጡ የሚያደርግ መስተንግዶ አግኝተው ወደመጡበት እንደሚመለሱ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ምክትል ኮሚሽነሩ እንደ የዓለም አቀፍ የቱሪዝም ድርጅት ትርጓሜ አንድ ሰው ከመኖሪያ ቀዬው ርቆ የ24 ሰዓታት ቆይታን ሲያደርግ እንደ ቱሪስት ሊቆጠር ይችላል ሲሉ ጠቅሰው፣ ከዚህ ትርጓሜ አንጻር በኦሮሚያ በ2017 የበጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት ከሃይማኖት በዓላት፣ ከቢዝነስ እና የተለያዩ እቅስቃሴዎች ጋር በተያያዘ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች ክልሉን ጎብኝተዋል ሲሉ አስታውቀዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ቁጥር መጨመሩን ያስታወቁት ምክትል ኮሚሸነሩ፣ በዕቅድ ከተያዘውም 120 ሺህ ውስጥ 112 ሺህ 395 የሚሆኑ የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች ክልሉን መጎብኘታቸውንም አስታውቀዋል። ይህ በእቅድ አፈፃፀም ሲታይ 93 ነጥብ ሰባት በመቶ መሆኑንም ገልጸዋል።

የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን በተመለከተም ሲያብራሩ ክልሉ በስምንት ሚሊዮን ጎብኚዎች ይጎበኛል ተብሎ መታቀዱን ጠቅሰው፣ ከ18 ሚሊዮን 593 ሺህ በላይ ጎብኚዎች ክልሉን እንደጎበኙም አስታውቀዋል።

ምክትል ኮሚሽነሩ እንዳስታወቁት፤ የቱሪዝም ዘርፉ እንደ ሀገር ከፍተኛ ገቢ የሚገኝበት ነው፤ በክልሉ በስድስት ወራት ውስጥ ከዘርፉ ከ31 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል። ይህም ከእቅድ አንፃር ሲታይ ከውጭ ሀገራት ቱሪስቶች አንድ ቢሊዮን 709 ሚሊዮን 997 ሺህ ብር ለማግኘት ታቅዶ ሁለት ቢሊዮን 171 ሚሊዮን 112 ሺህ 530 ብር ተገኝቷል። ከሀገር ውስጥ ጎብኚዎች 12 ቢሊየን 709 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዶ 29 ቢሊዮን 619 ሚሊዮን 842 ሺህ 975 ገቢ ማግኘት ተችሏል።

በክልሉ ያሉ የቱሪስት መስሕቦችንና ሀብቶችን ለመመልከት በርካታ ቱሪስቶች ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች እና ከሀገሪቱ ልዩ ልዩ አካባቢዎች ይመጣሉ ያሉን አቶ ነጋ፣ የእነዚህን ቱሪስቶች የቆይታ ጊዜ ለማራዘም እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በተለይ የውጪ አገር ጎብኚዎች የቱር ኦፕሬተሮችንና የጎብኚዎችን ምክረ ሀሳብ ተከተለው፤ የክልሉን ታሪክ፣ ባሕልና ሃይማኖት ነክ የሆኑ መስሕቦች ላይ ይታደማሉ፤ በቡና ማሳዎች ውስጥ በመገኘት የቡና ምርት ሂደቶችን እንዲያስተውል በማድረግ የቆይታ ጊዜአቸው እንዲራዘምና ጥሩ ጊዜን እንዲያሳልፉ በመደረግ ላይ ይገኛል።

አስጎብኚ ባለሙያዎች አንድ ቱሪስት በአግባቡ መስተንግዶ አግኝቶ፣ ክልሉን ተዋውቆ ወደ ሀገሩ እንዲመለስ ሙያዊ ድርሻቸውን መወጣት ይገባቸዋል ያሉን ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ለዛም የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በዘርፉ የሠለጠኑ ባለሙያዎችን እንዲያፈሩ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል። ቱሪስቱ አገልግሎት የሚያገኝባቸውን ስፍራዎች ምቹ በማድረግ የጎብኚዎች የቆይታ ጊዜ እንዲረዝምና ምቹ እንዲሆንላቸው መሠራቱንም አስታውቀዋል።

በክልሉ አዳዲስ ቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች መፈጠራቸውንም ጠቅሰው፣ ይህም ለጎብኚዎች ቁጥር መጨመር ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል። በተለያዩ የክልሉ ከተሞች እየተካሄደ ባለው የኮሪደር ልማት፣ ከተሞችን የማስዋብና የመንገድ መሠረተ ልማቶች የማስፋፋት ሥራ የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንዲያድግ የበኩሉን አስተዋፅዖ እንደሚያበረክትም ገልጸዋል።

ሃይማኖት ከበደ

አዲስ ዘመን  ጥር 25 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You