
በአዲስ አበባ የሚከሰቱ አብዛኛዎቹ የመንገድ የትራፊክ አደጋዎች በአሽከርካሪዎች ችግር ምክንያት የሚከሰቱ መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ። ለአደጋዎቹ መከሰት ምክንያት በመሆን በአብዛኛው የሚጠቀሰውም በፍጥነት ማሽከርከር ነው።
በመዲናዋ በመንገድ ትራፊክ አደጋ ተደጋጋሚ ሞት የተከሰተባቸው አምስት ቦታዎችም ተለይተዋል፤ እነዚህም በመገናኛ 13፣ ኃይሌ ጋርመንት 10፣ ቦሌ ሚካኤል ስምንት፣ ጦር ኃይሎች ሰባት፣ ቻይና ካምፕ ስድስት መሆናቸውን በ2022/23 የተካሄደ የመንገድ ደህንነት ጥናት ያመላክታል።
ከተሽከርካሪ አኳያ በአብዛኛው በሰው ሕይወት ላይ አደጋ እያደረሱ የሚገኙት የከባድ ተሽከርካሪዎች እና ሚኒባሶች መሆናቸውንም መረጃዎች ጠቁመዋል።
የመንገድ ደህንነት አደጋዎችን ለመቀነስም ብቁ አሽከርካሪዎችን ማፍራት፣ የቴክኒክ ችግር ባለባቸው እና የደህንነት ስጋት በሆኑ ተሽከርካሪዎች ላይ ቁጥጥር እና ክትትል ማድረግ የየራሳቸው ሚና እንዳላቸውም ተጠቁሟል። በቅርቡ የብሉምበርግ በጎ ፈቃደኞች እና የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን በመንገድ ደህንነት ላይ ያተኮረ አጠቃላይ ውይይት አድርገዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ምክር ቤት የመሠረተ ልማት እና ማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ግዛቸው አይካ (ዶ/ር)እንዳስገነዘቡት፤ መንገድ አንደ ሀገር ነው። መንገድ ላይ የማይወጣ መንገድን የማይጠቀም፣ ከመንገድ ጋር የተያያዘ ሕይወት የሌለው ሕዝብ የለም። ሕፃናት አዋቂዎች፣ በእድሜ የገፉ፣ የተማሩ፣ ያልተማሩ፣ በተለያየ የሕይወት ደረጃ ላይ የሚገኙ ሁሉ መንገድን ይጠቀማሉ።
መንገድ እንደ ሀገር ምሳሌ መሆን ይችላል። ሀገር በትክክል ከተመራ ለዜጎች ሰላም እንደሚሆን ሁሉ መንገድ ደግሞ በትክክል ከተመራ ደህንነቱ በትክክል ከተጠበቀ የዜጎች የሰላም መንገድ ይሆናል። አብዛኛውን ጊዜ ግን መንገዶች የዜጎች ስጋት፣ የዜጎች ፍርሃት እንዲሁም ባንጠቀምባቸው ወደማለት ደረጃ የሚደርሱበት ጊዜ አለ። መንገድ ላይ የሚፈጠሩ አደጋዎች ከሁሉም የራቁ እንዳልሆነም እርግጠኛ በመሆን ነው።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ በእሳቸውና በቤተሰባቸው ላይ የደረሰውን የትራፊክ አደጋ በማሳየት በመጥቀስ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ “በአንድ ወቅት ከበድ ያለ አደጋ እኔ እና እህቴ ደርሶብን ነበር። ስምንት አካባቢ እግረኞች ነን። በሰላም ከምናመልክበት ቤተእምነት እየወጣን ነው። ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ስምንታችንም ራሳችንን ያገኘነው ሆስፒታል ነው። ሰባታችን እድለኛ ሆነን የተወሰነ የአካል ጉዳት ደርሶብን ዛሬም ድረስ አለን። ስምንተኛዋ እህቴ ግን በሕይወት የለችም።” ሲሉ የመንገድ ደህንነት ሲነሳ ከሕይወት፣ ከኢኮኖሚ፣ ከሀገር ሰላም ጋር የተያያዘ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በመንገድ ደህንነት ላይ መሥራት ወላጆች እና ተማሪዎች ከትምህርት መልስ በሰላም እንዲገናኙ ማድረግ፣ በመንገድ ደህንነት ላይ ያሉ ባለሙያዎች፣ ጥናትና ምርምር አድራጊዎች፣ ሥራው ሕይወትን የሚያድን መሆኑን እንዲሁም ፕላንና ልማት ሚኒስቴርን ጨምሮ አጠቃላይ የከተማ እቅድ ሲወጣም የመንገድ ደህንነት ሥራም የህይወት አድን እቅድ መሆኑ ታሳቢ ሊሆን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
እሳቸው እንደተናገሩት፤ በ2016 በክረምት መግቢያ የከተማ አስተዳደሩ የመንገድ ደህንነትን ለማስጠበቅ እንዲያስችል በሚል የምክር ቤት አደረጃጀት እንዲቀየር አድርጓል። ከዚህም አንዱ የመሠረተ ልማት እና ትራንስፖርት ቋሚ ኮሚቴው ከመንገድ ደህንነትና ከትራንስፖርት ጋር የሚሰሩ መሠረተ ልማቶች በተቀናጀ መልኩ የሚሠሩበትን ሁኔታ ፈጥሯል። በዚህ ሂደት የትራንስፖርት ቢሮ፣ የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ የትራፊክ ማኔጅመንት፣ የመንገድ ባለሥልጣን፣ የመብራት አገልግሎትንና የውሃ አገልግሎትን አንድ ላይ በመሰብሰብ ወጥ በሆነ መንገድ እንዲሄድ መደረጉን አስታውቀዋል።
በከተማዋ ብዙ አደጋ የሚደርሰው ምሽት ላይ መሆኑን ታሳቢ በማድረግም የከተማ አስተዳደሩ የመንገድ መብራት አገልግሎት የሚሰጥ ራሱን የቻለ ተቋም አቋቁሟል። ማታ ላይ መንገዶች ብርሃን እንዲሰጡ፣ በየቦታው ያሉ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች እንዲሠሩ የሚያደርግ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚወስድ ተቋም ተፈጥሯል።
በተለይ ብሉምበርግ ይሄንን ሃሳብ ይዞ ከትራፊክ ማኔጅመንት እና አዲስ ከተቋቋመው የመንገድ መብራት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ጋር በመሆን ምሽት ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን በመቀነሱ ሥራ ላይ በስፋት እንደሚሠራ ታሳቢ እንደሚደረግም አመላክተዋል።
በሌላ በኩል የከተማዋ የጋራዥ አገልግሎት ሰጪዎች በሕግ እየተዳደሩ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ የሞተር ሳይክል ፍቃድ ያለው ከባድ መኪና አስገብቶ ያድሳል ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት አብነት ጠቅሰው አመልክተዋል። ከዚህ በኋላ ጋራዦች የሚሠሩበት የሥራ ብቃት እንዲኖራቸው፣ እያንዳንዱ ሥራ የሙያ ዲሲፕሊን ሊኖረው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ ማንኛውም ግጭት ደርሶበት የሚቀጣ ተሽከርካሪ የፖሊስ ሪፖርት ሳይኖረው እድሳት አይደረግለትም ብለዋል። የዚህ ዓይነት የፖሊሲ ማሻሻል ሥራ ቀጣይነት እንደሚኖረውም አመላክተዋል። በውሃና ፍሳሽ በኩልም እንዲሁ መክደኛ የሌላቸው የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች መስኮቶች እንዳሉም ጠቅሰው፤ በዚህ የተነሳ ፍሳሹ ወደ አስፓልት መንገድ እየወጣ የደህንነት ችግር ጭምር እየሆነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በመዲናዋ ከ1000 በላይ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ መስኮት ክዳኖች መሰረቃቸውን ጠቁመው፤ ይህም አደጋው መልሶ ለማህበረሰቡ መሆኑን አስገንዝበዋል። የመሰረተ ልማት እና ማዘጋጃ ቤት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በእነዚህ የጋራ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ ማስቀመጡንም አመላክተዋል።
የምክር ቤቱ ትልቁ ሚና የፖሊስ፣ የትራፊክ ፖሊስ እንዲሁም የሌሎች የመንግሥት አካላት አጠቃላይ የሥራ ሂደት መከታተል መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ምክር ቤቱ ተነሳሽነቱን በመውሰድ የዚህ ዓይነት ተግዳሮቶችን ለመከላከል የሚያስችል የጋራ መድረክ እንደሚያዘጋጅ ጠቁመዋል።
አሽከርካሪዎች የአሽከርካሪነት ሥልጠና ወይም መኪና የመንዳት ክህሎታቸውን በሚገባ ማጎልበት አለማጎልበታቸውን ለመከታተልም የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ክትትል እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
በመድረኩ ላይ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አማረ ታረቀኝ እንዳስታወቁት፤ የመንገድ ደህንነትን ለማስጠበቅ ከአጋር ድርጅቶችና ከመንገድ ደህንነት ምክር ቤት አባል ተቋማት ጋር ቅንጅት በመፍጠር መሥራት ያስፈልጋል። እያንዳንዱ እግረኛም ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል። ቅንጅታዊ የመንገድ ደህንነት ሥራ በመንገድ ደህንነቱ ላይ ሰላማዊና ከአደጋ የፀዳ እንቅስቃሴ ለመፍጠር ያግዛል፤ የግንዛቤ ማስጨበጥና ሕግ የማስከበር ሥራዎች በተናበበ መልኩ ሲሠሩ የትራፊክ አደጋን በስፋት መቀነስ ያስችላል።
ምክትል ኃላፊው እንዳስታወቁት፤ በመዲናዋ በ2013 በጀት ዓመት የትራፊክ አደጋ በ480 ያህል ሰዎች ላይ የሞት አደጋ አድርሷል፤ በ2016 ደግሞ በ401 ሰዎች ላይ የሞት አደጋ ተመዝግቧል። በሰው ሕይወት ላይ የሚደርሰውን አደጋ ይበልጥ ለመቀነስ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ ሥራዎች አጠናክሮ መቀጠል አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።
በተለይ አጋር ድርጅቶች ለድጋፍ እስከመጡ ድረስ በቴክኒክ እና በቁሳቁስ በአግባቡ መደገፍ ይገባቸዋል። አሁን ዓለም በደረሰበት ደረጃ ላይ የፍጥነት ቁጥጥር በማድረግ፣ ጠጥቶ ማሽከርከር ላይ ቁጥጥሮች የሚደረግባቸውን ጨምሮ ለትራፊክ አደጋ አጋላጭ የሆኑ ሁኔታዎችን የመከላከል ኃላፊነት አለባቸው።
የመንገድ ደህንነት ምክር ቤት አባላትም ሥራዎቻቸውን እንደ አንድ መደበኛ ሥራ ተቋሙ ከተቋቋመበት ራዕይ እና ተልዕኮ ጋር በማዛመድ የመንገድ ደህንነትን ጉዳይ አብሮ ማየት እና መምራት ይገባቸዋል። ለምሳሌ የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን በመንገድ ለሚፈጠሩ አደጋዎች በውጤትም በጉድለትም ቀላል የማይባል ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ብቃት ያለው አሽከርካሪ ወደ መንገድ ካልወጣ አደጋ የመከሰት ዕድሉ ሰፊ መሆኑንም አመልክተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ከዚህ አንፃር በከተማዋ ብቃት ያለው አሽከርካሪ አፍርቶ ለማውጣት የማሠልጠኛ ተቋማትን በበላይነት የሚመራው የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ቁጥጥር ባለሥልጣን በዚህ ላይ በአግባቡ እገዛ ማድረግ ይገባል። የተሽከርካሪ ብቃት ጉዳይም በተመሳሳይ ሁኔታ በዚሁ ተቋም በኩል የሚታይ በመሆኑ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ኃላፊነት ተሰጥቶታል። በዚህ ላይ እየሠራ መሆኑን ተከትሎ ለውጦች እየመጡ ቢሆንም በዚያው ልክ መደገፍ ይገባዋል።
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን በበኩሉ መንገዶች ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ለእግረኛው ምቹ የሆኑ ማቋረጫዎች፣ የእግረኛ መሻገሪያዎችን እና ተገቢ የሆኑ መሠረተ ልማቶች በማሟላት፣ በጥቅሉ የመንገድ ደህንነትን ከደህንነት እና ከእንቅስቃሴ አኳያ ሊያግዝ ይገባል በሚል ኃላፊነት የተሰጠው መሆኑን አስገንዝበዋል።
ሌሎች ተቋማትም እንደ ተቋማቱ ባህሪ ደንብ በማስከበር፣ ሕግ በማስከበር በኩል በጋራ የሚሠሩ ሥራዎችን በመሥራት፣ ሁሉም መንገዶች /የእግረኛም የተሽከርካሪም/ ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ በማድረግ ሕግ የማስከበሩን ሥራ በጋራ የመሥራት ኃላፊነት አለባቸው።
ግንዛቤ በሚፈጠርበት ሂደትም የትምህርት ቢሮ በተለይ ልጆች ላይ የሚሠራው ይኖረዋል፤ ረዳት የትራንስፖርት አስተናባሪ በሚል የሚሰጠው ሥልጠና በሥርዓተ ትምህርት ደረጃ በመንገድ ደህንነት ትምህርትነት በትምህርት ቢሮ የመጀመሪያ ደረጃ (እስከ ስምንተኛ ክፍል) ትምህርት ቤቶች በማህበራዊ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል። ይህ ትምህርት ቤቶች ላይ የሚሠራ ሥራ ተጠናከሮ መቀጠል አለበት።
በሚኒ ሚድያዎችም የመንገድ አጠቃቀም ምን መምሰል አለበት? ደህንነቱ የተጠበቀ የመንገድ አጠቃቀም እንዴት ተግባራዊ ሊደረግ ይችላል? በሚሉት ላይ ጭምር በልጆች ላይ መሥራት ከተቻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል አስታውቀዋል።
ጤና ቢሮም በተመሳሳይ የቅድመ መከላከል ሥራው እንደተጠበቀ ሆኖ አደጋዎች ከደረሱ በኋላ ተጎጂዎች በፍጥነት ወደ ጤና ተቋማት ተወስደው ሕክምና እንዲያገኙ በሚደረገው ጥረት ላይ ሚናውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል። በጥቅሉ 15 የሚሆኑ መሰል ተቋማት የየራሳቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የትራፊክ ማኔጅመንት እንዲሁ በበላይነትና በአግባቡ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችን እንደሚሠራ ጠቅሰው፤ አቅም ገንብቶ ብቁ የሆኑ ተቆጣጣሪዎችን በማሰማራት ሕግ የማስከበር ሥራውን እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ ይህን ኃላፊነት ዲሲፕሊን በጠበቀ መልኩ ከመፈፀም አኳያ የራሱን ሥራ አጠናክሮ ይሠራል ሲሉም አስታውቀዋል፡፡
እያንዳንዱ ተቋም ቅንጅታዊ አሠራሩን በማጠናከር፣ ባለድርሻውም፣ የመንገድ ደህንነት ምክር ቤት አባላትም እንዲሁም የብሉምበርግ በጎ ፈቃደኛ ድርጅትም የየራሳቸውን ኃላፊነት በሚወጡበት ሂደት መሆናቸውንም ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በመዲናዋ በአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ቁጥጥር ባለሥልጣን ሥር 137 ተቋማት ይገኛሉ። ባለሥልጣኑ ለተቋማቱ በየጊዜው ድጋፍና ክትትል ያደርጋል፡፡ አሁንም ጠንካራ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ የመንገድ ደህንነቱን ማረጋገጡ ላይ መሥራት ይገባል። ከባህሪ ጋር ተያይዞ ያሉ ጉድለቶች ለማረምም የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን እንደ አንድ የከተማ አስተዳደሩ ሴክተር መሥሪያ ቤት በጋራ እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።
የትራፊከ ደንብን በተደጋጋሚ በሚተላለፉት ላይም አስተማሪ የቅጣት እርምጃ መውሰድ አማራጭ እንደሌለው አስታውቀዋል፡፡ አሽከርካሪዎች እስከ አሁንም የትራፊክ ምልክቶችን ባለማክበር 100 ብር የሚያስቀጣውን ከመክፈል አቅም ጋር በማወዳደር አደባባይ ደርሶ ማዞር ሲገባ አላግባብ ሕግ እየተጣሱ ለአደጋዎች መንስኤ ሲሆኑ እየታዩ ያሉበትን ሁኔታም ለአብነት ጠቅሰዋል።
መሰል ችግሮችን ለመፍታት ሲባል የትራፊክ ሕግን በአግባቡ አለማክበር ለከፍተኛ ቅጣት የሚዳርግ ስለመሆኑ የሚያስገነዝብ እርምጃ መውሰድ ያለበት መሆኑ ሊለመድ እንደሚገባውም ጠቁመዋል። በዚህ ሂደትም የአፈፃፀም ችግሮች አሉ፤ አለአግባብ ተቀጥተናል የሚሉ አካላት ካሉም ማመልከት እንደሚችሉ ገልጸዋል። የቁጥጥር ባለሙያዎች ከዲሲፕሊን ውጪ የሆነ ተግባር ሲፈፅሙ ከተገኙም ከሥራ እስከ ማሰናበት የሚደርስ ቅጣት እንደሚወሰድባቸውም ተናግረዋል። በዚህ ሁኔታም በ2016 ዓ.ም ብቻ በ94 ያህል ተቆጣጣሪዎች ላይ የእርምት እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡
ከመዲናዋ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ጋር ተያይዞም በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ኮሪደሩ በለማባቸው አካባቢዎች ስምንት ደቂቃዎች አካባቢ ይፈጅ የነበረ ጉዞ በአራት እና አምስት ደቂቃዎች የሚፈጸምበት ሁኔታ መፈጠሩን አስታውቀዋል፡፡ መንገዶች ለተሽከርካሪዎች ክፍት መሆን ሲገባቸው ለተሽከርካሪዎች ማቆሚያነት መዋላቸውን አስታውሰው፣ በኮሪደር ልማቱ ከ120 በላይ የፓርኪንግ ተርሚናሎች መሠራታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ይህም መንገድ ላይ ይፈጠሩ የነበሩ መስተጓጎሎችን አስቀርቷል ብለዋል።
በእግረኛ መንገዶች ላይ የመጣውንም ለውጥ ጠቅሰዋል፡፡ በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት ከ90 ኪሎ ሜትር በላይ የእግረኛ መንገዶች መገንባታቸውን አመልክተዋል፡፡ በተጨማሪም ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ የብስክሌት መንገድ መሠራቱን ተናግረው፤ ይህ በመሆኑም ተሽከርካሪውም ፣ ሳይክል ተጠቃሚውም፣ እግረኛውም አንድ ላይ ይጓዙ የነበረበትን ሁኔታ ማስቀረቱን ገልጸዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ በለማባቸው አካባቢዎች በአሽከርካሪዎች ፍጥነት ላይ በራዳር ጭምር ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ይህም አሽከርካሪዎች ሕጉን አክብረው እንዲያሽከረክሩ እያገዘ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ጥር 24 ቀን 2017 ዓ.ም