ለመድኃኒት አምራቾች-ልዩ ትኩረት

ኢትዮጵያ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር ውስጥ ከምታስገባቸው ምርቶች መካከል መድኃኒቶችና የሕክምና ግብዓቶች በዋናነት ከሚጠቀሱት ተርታ ይመደባሉ፡፡ ከእነዚህ ምርቶች ብዙዎቹ ማለትም ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት የሚያስገቡት ከውጪ ሀገር ነው፡፡

በ2023 በተደረገ የአፍሪካ ጥናት እንደተመላከተው፤ ለመድሀኒትና ለሕክምና ቁሳቁስ በዓመት በዓለም ላይ አንድ ነጥብ ስድስት ትሪሊዮን ዶላር ይወጣል። በአፍሪካ ደግሞ 26 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም በኢትዮጵያ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዶላር ወጪ ይደረጋል፡፡ ይህ ሁኔታ በሀገር ውስጥ ምርት አቅርቦት ቢሸፈን ኖሮ ብዙ ችግሮችን መፍታት ያስችል እንደነበር መረዳት ይቻላል፡፡ በተለይም ከጊዜና ከመድሀኒት ጥራት እንዲሁም ከማጓጓዣ ጋር የሚወጡ ወጪዎች ራስን በከፍተኛ ሁኔታ ከመታደግ አንጻር የማይተካ ሚና ይኖረዋል፡፡

ለዚህም ነው መንግሥት ለሀገር ውስጥ የመድሀኒት አምራቾችና የሕክምና ግብዓት አቅራቢዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ የሚገኘው፡፡ ይህ ትኩረቱ ደግሞ ኢትዮጵያ ከመድሀኒት አንጻር ያላትን ሽፋን በእጅጉ እንድታሳድግ አግዟታል፡፡ ለአብነት የሀገር ውስጥ አምራቾች በጥሬ እቃ አቅርቦትና የውጪ ምንዛሬ ችግር የተነሳ ከአቅማቸው በታች በማምረታቸው በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መድሀኒቶች እና የሕክምና ግብአቶች ከአጠቃላይ ፍላጎቱ አንጻር የነበራቸው ሽፋን ስምንት በመቶ ብቻ ነበር፡፡ አምራችነታቸውም 25 በመቶ ያህሉን ብቻ የሸፈነ ነው፡፡ ይህ ግን በተሰሩ ጠንካራ ሥራዎች የተነሳ በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት አቅርቦቱን ከስምንት ወደ 36 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል፡፡

ይህ ቁጥር ሀገሪቱ ከአላት ፍላጎት አንጻር እጅግ ያነሰ ቢሆንም ልዩነቱ ግን ከጊዜ ወደጊዜ ብዙ መሻሻሎች የታየበት እንደሆነ ይገለጻል፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት እና የጤና ሚኒስቴር በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የመድኃኒት እና የሕክምና ግብአት አምራቾች የሚፈጸም ግዥን በሚቀጥሉት ከሦስት እስከ አምስት ዓመታት እስከ 60 በመቶ ለማድረስ አቅደው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በ2016 በጀት ዓመት በመድኃኒት፣ የሕክምና መሳሪያዎች እና መገልገያዎችን፣ የላቦራቶሪ ኬሚካሎችን ጨምሮ በጥቅሉ ከ29 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የሕክምና ግብአቶችን ገዝቶ 5 ሺህ ለሚጠጉ የመንግሥት ጤና ተቋማት የማከፋፈል ሥራ ሰርቷል፡፡ ይህም የሀገር ውስጥ ምርት ሽፋኑን ከፍ ከአደረጉት ሥራዎች መካከል እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡

የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርትን ለማሳደግና አምራቾችን ለመደገፍ ከፖሊሲ ማሻሻያ ጀምሮ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል። በተለይም ለመድሃኒት አምራቾች ምቹ መሰረተ ልማት ከማሟላት አንጻር መንግሥት ቁርጠኛ ሆኖ የተሻሉ አማራጮችን ፈጥሯል፡፡ አንዱ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ ይናገራሉ፡፡ ለሌሎች አምራቾች ጭምር ትልቅ ሚና እየተጫወተ የሚገኝ እንደሆነና በቀጣይ ደግሞ በዘርፉ የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ያስረዳሉ፡፡

የፋርማስቲካል ዘርፍ የጤናን ሁኔታና የሀገርን እድገት ለማፋጠን እንዲሁም የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመጨመር ትልቅ አቅም የሚሆን ነው፡፡ በዚህም በተቋማዊ አደረጃጀት መደገፍ ይኖርበታል፡፡ እርሱን ከፍ የሚያደርጉ መደላደሎችም ሊፈጠሩለትም ይገባል፡፡ ከእነዚህ መካከል የፋርማሲዩቲካል ፎረም መቋቋም አንዱ ሲሆን፤ ለሀገርም ሆነ ለጤናው ዘርፍ የሚኖረው አስተዋጽኦ እጅጉን የጎላ ነው፡፡ በተለይ ፎረሙ ሲመሰረት 13 የመንግሥት ተቋማት እና ዘጠኝ የግል ሴክተሮች የተካተቱበት በመሆኑ ብዙ ለውጦችን እንደሚያመጣ ይታመንበታል።

የሀገር ውስጥ የመድኃኒት አይነቶች ፍላጎቱ እጅግ ብዙ ነው፡፡ በዚህም ካለፉት ጊዜያት ጀምሮ ጥሩ መሻሻሎች እየታዩበት የመጣ ነው፡፡ ለአብነትም ካለፉት ጊዜያት አንጻር ከፍታው የ28 በመቶ ጭማሬ የታየበት ነው፡፡ ነገር ግን ምርቱ አሁንም በቂ አይደለምና ብዙ መሥራን ይጠይቃል፡፡ አምራቾች አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ ማገዝም ይገባል፡፡

የፋርማሲዩቲካል ፎረም መቋቋሙ ደግሞ ለችግሩ እልባት ከመስጠት አንጻር ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ ምክንያቱም ፎረሙ የሀገር ውስጥ መድሀኒት አምራቾችን የሚገጥሟቸውን ችግሮች በመለየት የመድሃኒት አቅርቦት እጥረትን ለመፍታት ያግዛል፡፡ የሀገር ውስጥ የመድሃኒት አቅርቦትን ለማሻሻል ከሚመለከታቸው አምራቾችና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ያስችላል፡፡

የፋርማሲዩቲካል ዘርፍ አቅምን በማሳደግ የኢንቨስትመንት ፍሰትን እንዲጨምር፣ የአምራቾችን ችግሮች በተቋማዊ አደረጃጀት እንዲፈታም ሁነኛ ሚናን ይጫወታል፡፡ ለፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪው የተሰጠው ትኩረትም ያሳድጋል፡፡

እስካሁን ባለው ሂደትም ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ከሚፈልጉት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንዲሁም ሀገር ውስጥ እስከሚደርሱ ከሚወስዱት ጊዜ አንጻር ባለፉት ዓመታት የሀገር ውስጥ አምራቾችን ማጠናከር ላይ ትኩረት አድርጎ መስራቱ አዋጭነት እንዳለው ሁሉም ተረድቷል፡፡ በመሆኑም ግብዓቶችን ለማሟላት ከሚያስፈልጋቸው የውጭ ምንዛሪ 55 በመቶውን ለመሸፈን ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡ ይህም የመድሀኒት አምራቾችንም ሆነ ግብዓት አቅራቢዎችን የምርት አቅማቸው እንዲያሳድጉ በእጅጉ እንዳገዛቸው ሚኒስትር ዴኤታዋ አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት 97 የሚጠጉ የመድሀኒት አይነቶች በሀገር ውስጥ አምራቾች የሚቀርቡ ሲሆን፤ አጠቃላይ ዋጋቸውም አምስት ቢሊየን ብር ድረስ የሚያወጡ ናቸው፡፡ የሕክምና ቁሳቁሶችን ሳይጨምር መሰረታዊ የሚባሉ ከ362 በላይ መድሀኒት በመንግሥት እየቀረበ እንደሚገኝና ከዚህ ውስጥ ደግሞ በሀገር ውስጥ አቅርቦት በአይነት እና በመጠን ባለፉት ቅርብ ዓመታት በርካታ መሻሻሎች ታይተዋል ሲሉም ይናገራሉ፡፡

መንግሥት ለተኪ ምርቶች ልዩ ትኩረት መስጠቱን የሚናገሩት ደግሞ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ መንግሥት ተኪ ምርትና ከፍተኛ ወጪን እየጠየቀ ነው ብሎ ከፈረጃቸው መካከል መድሃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ እንዲሁም ግብዓቶች ናቸው። ስለሆነም በብዙ መልኩ እንዲደገፉ ውጤታማ የሚያደርጉ የፖሊሲ ማሻሻያና ሌሎች የድጋፍ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ጭምር ትኩረት እንዲሰጠው አድርጓል፡፡ አሁንም የመድሃኒትና ሌሎች የሕክምና ግብአቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመጠቀም ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዲኖረው ማድረግ ላይ ልዩ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡

የሀገር ውስጥ አምራቾች እንዲበረታቱና አዳዲስ ኢንቨስተሮች በዘርፉ እንዲሰማሩ በማድረጉ ዙሪያ ለስኬታማነቱ የሚሆኑ ቁልፍ ተግባራት ተቀርጸዋል፤በመድሃኒት ልማትና አቅርቦት ከሀገር ውስጥ ባለፈ ወደ ውጭ በመላክ ለአህጉራዊ ተደራሽነት ጭምር ለመስራትም ከባለድርሻ አካላት ጋር ልዩ ልዩ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡ ሆኖም ቅድሚያ የሚሰጠው ምርቱ በምን ይደገፍ፤ አምራቾች በዋናነት ያሉባቸው ችግሮች ምን ምን ናቸው የሚለውን መለየት ላይ ይሆናል፡፡ ለዚህም ችግሮችን ይፈታሉ ተብሎ እንደ ሀገር ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ቡድን ስለተቋቋመ በትኩረት እንዲሰራበት ይደረጋል ሲሉ ይናገራሉ፡፡

ፎረሙ ተናቦና ተግባብቶ ዋና ዋና የሚላቸውን ችግሮች ማቅረብ ከቻለ እንደ ሀገር መድረስ ያለብን ምርት ላይ እንደርሳለን፡፡ ለዚህም መንግሥት ቁርጠኛ ሆኖ እየሰራ እንደሆነ የሚያመላክቱ ነገሮች አሉ፡፡ አንዱና ዋነኛው በኢኮኖሚ ማሻሻያው የሰራቸው ተግባራት ናቸው፡፡ በዚህ ማሻሻያ የውጪ ምንዛሬ እጥረት በብዙ መልኩ ተፈትቶ ታይቷል፡፡ አሁንም አምራቾች ይህ ችግራቸው በብዙ መልኩ መፍትሄ እንደሚያገኝ እምነት እንዳላቸው ያስረዳሉ፡፡

ዶክተር ዳንኤል ዎክቶሌ የኢትዮጵያ የመድሀኒት እና የሕክምና መገልገያ አምራቾች ማሕበር ፕሬዚዳንትና የክሊችትሮ መድሃኒት ፋብሪካ ባለቤት ናቸው። ቅንጅታዊ ሥራዎች በይፋ የሚጀመሩበት ፎረም መቋቋሙ እንዳስደሰታቸው ይናገራሉ። ፎረሙ በችግሮቻቸው ዙሪያ ለመወያየት እድል የሚሰጥና ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ የመስራቱን እድል የሚያሰፋ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡

አምራቹን የሚያጋጥሙት ተግዳሮቶች በበቂ ሁኔታ መፈታት ከተቻለ የሀገር ውስጥ አምራቾች የሕክምና ግብአቶችንም ሆነ መድኃኒቶችን ለማምረት የሚያግዳቸው ምንም ነገር እንደማይኖርም ያመላክ ታሉ፡፡ ምክንያቱም ክትባቶችን ጨምሮ የቲቢ እና የኤችአይ ቪ መድሀኒቶች በዋናነት ከውጭ በድጋፍ እና በግዥ የሚቀርቡ ቢሆንም ከዚህ ውጪ ያሉ መሰረታዊ የሚባሉ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸውን መድኃኒቶችንና የሕክምና ግብአቶችን የሚያመርቱ የሀገር ውስጥ አምራቾች ናቸው፡፡ ችግሩ በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ መደላደሉ አለመፈጠሩ በመሆኑ ይህንን መፍታት ላይ ሁሉም መረባረብ እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ የመድኃኒት እና የሕክምና መገልገያ አምራቾች ማሕበር ውስጥ የታቀፉ 24 አምራቾች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል 12ቱ መድሀኒቶችን ብቻ የሚያመርቱ ሲሆኑ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ግብአቶችን እና የሕክምና መገልገያ ቁሳቁሶች አምራች ናቸው። እነዚህን በበቂ መልኩ በመደገፍ ያንሳል ከተባለም ሌሎች ተጨማሪ ኢንቨስተሮችን በመሳብ ለዜጎቻቸው የሥራ እድልን፤ የጤና ሁኔታን ማመቻቸትና የሀገሪቱን የውጪ ምንዛሬ አቅም ከፍ ማድረግ ይቻላል ሲሉ ይመክራሉ፡፡

ዶክተር ዳንኤል፤ መንግሥት እያደረገ ያለውን ድጋፍና ትኩረትም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ ይህም የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት 55 በመቶ የውጭ ምንዛሪ ከመንግሥት እንድናገኝ አድርጓል ይላሉ። የቀረውን ገንዘብ ከባንኮች ለማግኘት በሚደረገው ጥረት አንዳንድ ጊዜ በቂ ምንዛሪ አናገኝም፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ምንዛሪውን ለማግኘት ገቢ እንዳናደርግ የምንጠየቀው ገንዘብ እጥረትም በተፈለገው ልክ እንዳንቀሳቀስ አድርጎናል፡፡ ስለሆነም የመንግሥት ድጋፍ እንዳለ ሁሉ ባንኮችም ይህንን እድል የሚያሰፉበት ሁኔታ ቢመቻች የበለጠ ያነሳሳልና ቢታሰብበት በማለት ሀሳባቸውን ይገልጻሉ፡፡

ዶክተር ዳንኤል፤ አሁን ላይ በተቋቋመው የፋርማሲዩቲካል ፎረም አማካኝነት ብዙ ችግሮቻቸው እንደሚፈቱላቸው አምነዋል፡፡ በተለይም በመሳሪያዎች ላይ ያለውን እጥረት ለመፍታት፣ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችን ቁጥር ለማሳደግ፣ ሀገር ውስጥ ተሰርተው ለአገልግሎት ብቁ ሊሆኑ የሚችሉ እና ከውጭ የሚገቡትን ማስቀረት ላይ ዓላማ ያደረገ ሥራን እንዲሰሩ እንደሚያግዛቸውም ተስፋ አድርገዋል፡፡ አምርተው የሚሸጡበትን እድል እንደሚያሰፋላቸውም ያስባሉ፡፡ ምክንያቱም ብዙውን የመድሀኒት ግዢ የሚፈጽመው መንግሥት በመሆኑ ከውጪው ይልቅ የሀገር ውስጥ ምርትን በብዙ መስፈርት ይመረጣል፡፡

የመጀመሪያው ምርትን በእውቀትና በፍላጎት መጠን ለይቶ ማምረት ሲሆን፤ መንግሥትን መጠየቅ ያለባቸውን ነገር በአግባቡና የሄዱበትን ርቀት አሳይተው መሆን እንዳለበት ነው የገለጹት፡፡

የአፍሪኪዩር ኢትዮጵያ የመድሃኒት ፋብሪካ ባለቤት ዶክተር ታደሰ ተፈሪ እንደሚሉት ደግሞ፤ መንግሥት ለጤናው ዘርፍ የሰጠው ትኩረት እጅግ የሚበረታታ ነው፡፡ ከመድሀኒቶች ጋርና ከሕክምና ግብዓቶች ጋር ተያይዞ ያሉትን ችግሮች በመረዳት የሚያነቃቃ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ በተለይም ለመድሃኒት አምራቾች የውጭ ምንዛሬ በማቅረብ ረገድ መልካም ተሞክሮዎች እየታዩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አምራቹ ጥራቱ የጠበቀና አቅሙን ሙሉ ያፈሰሰበትን መድሃኒት እንዲያመርት ያግዘዋል፡፡ ስለዚህም ጅማሮው ተጠናክሮ ይቀጥል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢዎች አገልግሎት መረጃ እንደሚያሳየው፤ በአጠቃላይ 1020 መድኃኒቶች እና የሕክምና ግብአቶች ለሀገር ውስጥ መሰረታዊ እንደሆኑ በዝርዝር ውስጥ የተካተተ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ ከ200 በላይ የሚሆኑት ምንም አቅራቢ የሌላቸው ናቸው።

የዓለም አቀፍ መድኃኒት አቅራቢዎች ብዛት 185 ቢሆንም አሁንም በሀገሪቱ ያለውን የመድኃኒት አቅርቦትና ፍላጎት ማጣጣም አልተቻለም፡፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ብዙ መሻሻሎች እየታየ ስለመጣ ቀሪ ሥራዎቹ ላይ የሀገር ውስጥ አምራቾች በስፋት ቢሳተፉ ለሀገር የተሻለውን እድል እንደሚፈጥር ታምኖበታል፡፡

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ጥር 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You