«የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያ ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ያመጣል» -የኢትዮጵያ የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያ የቦርድ አባል እሌኒ ገብረመድህን (ዶ/ር)

እሌኒ ገብረመድህን (ዶ/ር) አንደኛ፣ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ያገኙት በኢኮኖሚክስ ነው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አሜሪካን ሀገር ከሚገኘው ኮርኔል ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከሚችንጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።

የዓለም ባንክን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ በኃላፊነት ሠርተዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢኮኖሚስት ሆነው እንዲሁም የምርት ልውውጥ ኤክስፐርት በመሆን ሠርተዋል። በዓለም አቀፉ የምግብ ፖሊሲዎች ምርምር ተቋም ውስጥም አገልግለዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት /UNDP/ የፈጠራ ሥራዎች ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሠርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት መሥራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ በመሆንም ለዓመታት አገልግለዋል። ከምርት ገበያው ከተለዩ በኋላም በስማቸው የሚጠራ ተቋም በመመሥረት በምርት ገበያ ዙሪያ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የማማከር ሥራዎች ተሰማርተዋል። በዚህም በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የእርሻ ሰብል ግብይት አሠራሮችንም በመፍጠር በሚሊየን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ አድርገዋል፡፡

ገለልተኛ ከሆኑ ምሁራንና ባለሙያዎች ሃሳብ በመቀበል የፖሊሲን አካታችነት ከመጨመር ባለፈ ያልታዩ ጉዳዮችን ለማየት፣ ኢትዮጵያ ያለችበትን ውስብስብ የሆነ የድህነትንና ሌሎች ማኅበራዊ ችግሮችን ለመረዳትና ውጤታማ የፖሊሲ አማራጮችን ለመመርመር ያስችላል ተብሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የተቋቋመው ገለልተኛ ብሔራዊ የኢኮኖሚ ምክር ቤት አባል በመሆንም አገልግለዋል፡፡

ብሉ ሙን የተሰኘ ወጣት የሥራ ፈጣሪዎችን የሚደግፍ ተቋም በመመሥረት በግብርና ዘርፍ አዋጪ የንግድ ሃሳብ ይዘው ለሚመጡ ወጣት የሥራ ፈጣሪዎች ሥልጠና እና መነሻ ፋይናንስ የሚሰጥ ድርጅት መሥርተው ትልቅ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይም ይገኛሉ።

በአሁኑ ወቅት ኩባንያዎችና ባለሀብቶች የአክሲዮን ድርሻዎችን የሚሽጡበት፣ የሚገዙበት፣ በቋሚነት ልውውጥ የሚደረግበትና ለመንግሥትና ለግሉ ዘርፍ የገንዘብ ምንጭ በመሆን ለምጣኔ ሀብት እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት እየተመሰከረለት የሚገኘው የኢትዮጵያ የሰነደ መዋለ ንዋይ ገበያ (Ethio­pian Securities Exchange – ESX) የቦርድ አባል ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም ከእኚሁ አንጋፋ ባለሙያ ጋር ቆይታ አድርጓል። መልካም ንባብ፡፡

 አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መሥራች እና የመጀመሪያዋ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነበሩ። አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ ከሌሎች አፍሪካ ሀገራት አንጻር ዘግይታ ያቋቋመችው የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያ የቦርድ አባል ሆነው ከምሥረታ ሂደቱ አንስቶ እየተሳተፉ ስለሚገኙ፣ የሁለቱን የኢትዮጵያ ርምጃዎች በንጽጽር እንዴት ይመለከቷቸዋል ?

እሌኒ (ዶ/ር)፡– የኢትዮጵያ ምርት ገበያን የመመሥረት ሃሳብ ይዤ ስመጣ አፍሪካ ላይ ተሞክሮዎች ነበሩ፣ ነገር ግን ውጤታማ አልነበሩም። ውጤታማ ያልሆኑት የውጭ ሀገራት አሠራር ሞዴል በቀጥታ ወስደው በመተግበራቸው ነው። ይሄ በቀጥታ መገልበጥ እንደማያዋጣ በመረዳት በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ተስተካክሎ በልካችን የተነደፈ የምርት ገበያ መፍጠር ችለናል። በዚህም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ስኬታማ የሆነ የምርት ገበያ መፍጠር ችላለች።

ወደ የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያ ስንመጣ በአፍሪካ ውስጥ ናይጄሪያ፣ ኬኒያ፣ ጋና፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮ እና ግብጽ ውስጥ ትልልቅ ገበያዎች አሉ። ሆኖም ግን ብዙ ጊዜ ከእኛ የምርት ገበያ እንኳን በንጽጽር ስንመለከታቸው ያን ያህል ጠለቅ ያለ ግብይት አልነበራቸውም። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በነበርኩበት ጊዜ ለጉብኝት ጋና ሄጄ ነበር። በወቅቱ የጋና የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያን ስጎበኝ በቀን ምን ያህል ዶላር ትገበያያላችሁ ብዬ ስጠይቃቸው በሰጡኝ ምላሽ በጣም ተገርሜያለሁ። ከአርባ ዓመት በፊት በጀመሩት ገበያ በቀን የሚገበያዩትን የገንዘብ መጠን ከተመሠረተ ገና ሦስት ዓመቱ የነበረው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በአስር እጥፍ ይበልጠው ነበር። ለምንድን ነው ይሄ የሆነው ግብይታቸው በሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያ ሆነ እንጂ ኢኮኖሚያቸው ለሽያጭ ለመቅረብ የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን የሚያሟሉ ብዙ ድርጅቶች አልነበሩትም።

ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያ በማቋቋም ረገድ ጀማሪ ሳይሆን የመጨረሻ ከሚባሉት ሀገራት ተርታ መሰለፋችን የራሱ ጥቅሞች አሉት ብዬ አስባለሁ። የቀደሙት ሀገራት የሠሯቸውን ስህተቶች ላለመድገም እና ትምህርት በመውሰድ የተሻለ መንገድ መከተል እንድንችል ያደርገናል። የኢትዮጵያ ምርት ገበያን ከኬኒያ የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያ ጋር ብናወዳድረው በቀን በሰባት እጥፍ የሚበልጥ ግብይት ያካሂዳል። ይህ ለምን ሆነ ብለን በመፈተሽ የወሰድነው ትምህርት አለ።

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ምርት ገበያን አሁናዊ ቁመና እንዴት ይገመግሙታል ?

እሌኒ (ዶ/ር)፡– በቅርብ በጣም አልተከ ታተልኩትም ፤ ነገር ግን እንደተረዳሁት ሥራው በጥሩ ሁኔታ ቀጥሏል፤ ከቴክኖሎጂው ጋር እየተራመደ ነው። በእኔ አመለካከት እኔ በነበርኩበት ጊዜ ጊዜያቸው ገና ነው ብለን በይደር ያቆየናቸው እንደ ፊዩቸር ማርኬት ያሉ ጉዳዮች አሁን የሚጀመሩበት ሁኔታ ቢታይ ደስ ይለኛል። እንደ እኔ ሥርዓቱን ለመዘርጋት የምንችልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም ማንኛውም ነገር አንድ ቦታ ላይ ሊቆም አይችልም። ሁልጊዜም ራሱን መፍጠር መቻል አለበት። ምርት ገበያው ሥራ ሲጀምር የስማርት ፎን ተጠቃሚዎች ቁጥር ከጠቅላላ ስልክ ተጠቃሚው ስድስት በመቶ ገደማ ነበረ፤ ዛሬ ከስድሳ በመቶ ደርሷል። ይሄ ማለት በስማርት ፎኖች ላይ ብዙ ዓይነት የተሻለ አሠራር መፍጠር እንችላለን።

ሌላው የምርት ገበያው የተጀመረው አሠራሩ አዲስ በመሆኑ ግንዛቤው እስኪፈጠር እና የግሉ ዘርፍ እምነት ማሳደር እስኪችል ድረስ ተብሎ በመንግሥት መቶ በመቶ ይዞታ ነው። ፕሮጀክቱ ሲቀረጽ ግን መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በሂደት ተመጣጣኝ የባለቤትነት ድርሻ እንዲኖራቸው መሳብ እንችላለን ተብሎ ነበር። አሁን 17 ዓመታት አስቆጥሯል። የግሉ ዘርፍ ባለድርሻ ሊሆን ይገባ የነበረበት ጊዜ ዘግይቷል። የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ መኖር የተሻለ አሠራር እና ቴክኖሎጂ እንዲኖርና የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮም መውሰድ ያስችላል። በሌሎች ሀገሮች ያለው አሠራር እንደዚህ ያለ ነው። የኢትዮጵያ ምርት ገበያም በቀጣይ ወደዛ ያመራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

አዲስ ዘመን፡- የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያውን ዘግይታ በመጀመሯ ኢትዮጵያ ከወሰደቻቸው ትምህርቶች አንድ ሁለቱን መጥቀስ እንችላለን?

እሌኒ(ዶ/ር)፡– ግብይቱን ቀድመው ከጀመሩ ሀገራት በትልልቅ ድርጅቶች ግብይት ብቻ የተወሰኑ ሆነው ቆይተዋል። እኛ ሁለት ዓይነት ገበያ ነው የምናስጀምረው። ትላልቅ የሚባሉትን እንደ ኢትዮ ቴሌኮም እና አየር መንገድ ያሉትን ድርጅቶች በአንድ በኩል እናገበያያለን። በሌላ በኩል ደግሞ አነስተኛ ኩባንያዎችን ማስተናገድ የሚችል የግብይት መድረክም እንፈጥራለን። ምክንያቱም በአነስተኛ ኩባንያዎች ብዙ ግብይት ይካሄዳል የሚል አመለካከት ስላለን። ይሄ ትልቅ ለውጥ ነው። የኢትዮጵያ የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲወዳደር የሚኖረው አንዱ ትልቅ ልዩነት ይሄ ይመስለኛል፡፡

ግብይቱን ቀድመው የጀመሩት የአፍሪካ ሀገራት ከአርባ ወይም ከሃምሳ ዓመታት በኋላ የደረሱበትን ሼር ላይ ብቻ መገበያየትን ብቻ ሳይሆን በቦንድ የመገበያየት የብድር አሠራር ከመጀመሪያውም ማስኬድ መቻላችንም ወደ መጨረሻው ገበያውን በመጀመራችን ያገኘነው ሌላው ጥቅም ነው። በሚቀጥሉት ዓመታት እየተማርን ራሳችንን እያሻሻልን በመሄድ የምናገኘው ልምድ ደግሞ ይበልጥ ያግዘናል ብዬ አምናለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያ ነበረ ወይስ አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የተጀመረው ?

ዶ/ር እሌኒ፡– ኢትዮጵያ የሰነደ መዋዕለ ንዋዮች ገበያ ሊኖራት ይገባል ወይስ አይገባም በሚል ውይይቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል። ከዚህ ቀደም የመዋለ ንዋዮች ገበያ እንደነበረን እና አሁን እንደገና እንደተጀመረ ተደርጎ ሲነገርም ሰምቻለሁ። ከዚህ ቀደም የድርጅቶችን ሼር የምንገዛበት ሁኔታ ነበረ ነገር ግን ሼሮችን የምንገበያይበት መድረክ አልነበረንም። ስለዚህ የሰነደ መዋለ ንዋይ ገበያው ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረ እና አዲስ ነገር ነው። የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው አካል የሆነው የኢትዮጵያ ሰነደ መዋለ ንዋይ ገበያ በካፒታል ገበያ አዋጁ መሠረት በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ ትብብር በአክሲዮን ኩባንያነት እና በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ በመቋቋሙ እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ። ከፍተኛ የሆነ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤ ለኢኮኖሚያችንም መተማመኛ ይሰጣል።

አዲስ ዘመን፡- የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያው በውጭ ሀገራት ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምን ዓይነት ዕድል ይሰጣል ?

እሌኒ(ዶ/ር)፡– ኢትዮጵያ የጀመረችው የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያው ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የሌሎች ሀገራት ዜጎች ዕድል የሚሰጥና የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው። ብዙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና ስለኢትዮጵያ የሰሙ የሌሎች ሀገራት ዜጎች በትናንሽ ገንዘብም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ እየፈለጉ መንገድ አጥተው ቆይተዋል። አሁን ግን የሰነድ መዋለ ንዋዮች ገበያው ስለተጀመረና በየትኛውም ሀገር የሚኖሩ ሰዎችን ስለሚያስተናግድ ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ያደርጋል።

አዲስ ዘመን፡- የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያው ውጤታማነት ላይ ከግራ ቀኝ የሚሰጡ አስተያየቶችን እርስዎ እንዴት ይመለከቷቸዋል ?

እሌኒ(ዶ/ር)፡- የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያው ውጤታማ ይሆናል የሚል ትልቅ እምነት አለን አለኝ። ከተለያዩ ሀገራት ተሞክሮ ልምድ በመውሰድ አቅማችንን አሳድገን ዝግጅት አድርገን ነው የጀመርነው። ከውጭ ሀገራት ተሞክሮዎች ብዙ ልምድ የወሰደ ጠንካራ ባለሥልጣን ድርጅት መፈጠሩ ትልቅ መተማመኛ የሚሰጥ ነገር ነው። በኢትዮጵያ የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያ እውን ለማድረግ የካፒታል ገበያን በማቋቋም፣ አዋጅ በማውጣትና ሌሎች ሁኔታዎችን በማሟላት መንግሥት የወሰዳቸው ርምጃዎች በጣም ጠቃሚ ናቸው። ከኢትዮጵያ ምርት ገበያም በርካታ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ወደ የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያው ገብተዋል።

አዲስ ዘመን፡- ገበያውን ከዚህ ቀደም ተቋማዊ ባልሆነ መንገድ ይካሄድ ከነበረው የሼር ሽያጭና ግዢ እንዲለይ የሚያደርገው ምንድን ነው ?

እሌኒ(ዶ/ር)፡- እስካሁን ባለው አሠራር ሰዎች ድርሻ የሚገዙትና የሚሸጡት ከሚያውቁት ሰው ወይም ባንክ ሄደው ነው። ይሄ ደግሞ ጊዜ የሚወስድ እና ውጤታማ ያልሆነ ነው። ሁሉም ሰው ድርሻ መግዛትና መሸጥ የሚችልበት የጋራ መገበያያ መድረክ እንዲሁም ግልጽ፣ ዋስትና የሚሰጥና ቀልጣፋ የሆነ የግብይት ሁኔታ መፍጠር አለበት። ገዢዎቹን እና ሻጮቹን የምናውቅበት የተደራጀ የሰንደ መዋለ ንዋዮች ያስፈለገን ለዚህ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ስለ ሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያ ሕዝቡ በቂ ግንዛቤ ይዟል ብለው ያምናሉ ?

እሌኒ (ዶ/ር)፡– አሁን ገበያው ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል። ቀጣዩ ሥራ ገበያውን በስፋት ከሕዝብ ጋር ማስተዋወቅ ነው የሚሆነው። አሁን በዚህ ቃለ መጠይቅ በጉዳዩ ዙሪያ ከእኔ ጋር ቆይታ እንዳደረጋችሁት ሁሉ ሌሎችንም የዘርፉ ባለሙያዎች በስፋት በሚዲያዎች እያቀረባችሁ ይህ አዲስ አሠራር ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ለሕዝብ መተላለፍ አለበት። የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያ ማንም ሰው ኢንቬስተር እንዲሆን ዕድል የሚፈጥር ነው። በእኛ በኢትዮጵያኖች አመለካከት ኢንቬስተር ሲባል ትልቅ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ ሰዎችን ብቻ ነው የምናስበው ነገር ግን ትናንሽ ድርሻዎችን ከኢትዮ ቴሌኮም ወይም ከሌሎች ድርጅቶች የገዛ ዜጋም ኢንቨስት አድራጊ ነው። የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያው ለእያንዳንዱ ዜጋ ትልቅ ሀብትን የማጎልበቻ መንገድ ነው፡፡

አነስተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መቆጠብ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ወደ ባንክ ነው የሚሄዱት። ገንዘቡን በባንክ ሲያስቀምጡት በዓመት የሚያገኙት ስምንት በመቶ ወለድ ነው። ይህ የወለድ መጠን የባንክ ሼር በመግዛት ከሚያገኙት 30 በመቶ ትርፍ አንጻር አነስተኛ ነው። ለምን ጥቂት ሰዎች ብቻ ሼር እየገዙ 30 በመቶ ትርፍ እያገኙ ብዙሃኑ ሰምንት በመቶ ወለድ ያገኛል ? አንድ ሰው ግድ የለም የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያው አልገባኝም በለመድኩትና በማውቀው መንገድ ስምንት በመቶ ወለድ ማግኘት ይበቃኛል ብሎ ሊወስን ይችላል። ሌላው ደግሞ ይሄን ድርጅት እየተከታተልኩት ነው፤ አውቀዋለሁ ውጤታማነቱን ተመልክቻለሁ፤ እያደገ ነው፤ ትርፋማ መሆኑን በተጨባጭ አውቃለሁ ብሎ ሼር መግዛትን ሊመርጥ ይችላል። ገንዘብን በባንክ ውስጥ ከማስቀመጥና የሚያድግ ሼር ለመግዛት ኢንቨስት ከማድረግ የትኛው እንደሚሻል ለእያንዳንዱ ሰው የሚተው ውሳኔ ሆኖ፤ ምርጫ መኖሩ ጥሩ ነገር ነው።

የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያ የገንዘብ አቅም ያላቸው ጥቂቶች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሼሮችን መግዛት የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥርላቸዋል። ከ30 ዓመታት በፊት እናቴ ለልጆቼ በጊዜ ሂደት እያደገ የሚሄድ ድርሻ መግዛት እፈልጋለሁ ብላ ለእኔ እና ለእህቴ አነስተኛ ሼር ገዝታልን ነበር። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በአነስተኛ ገንዘብም ቢሆን የኢትዮ ቴሌኮምን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ወይም የሀበሻ ሲሚንቶን ሼር መግዛት እችላለሁ ብሎ መናገር መጀመር አለበት። ይህም ማለት እያንዳንዱ ዜጋ ምንም ዓይነት መጠን ያለው ገንዘብ ቢኖረኝ የሂሳብ ቁጥር ከፍቼ ባንክ ከማስቀምጠው ይልቅ የአንድ ትርፋማ ድርጅትን ሼር ብገዛበት ተጠቃሚ ሆናለሁ ብሎ ማሰብ ይጀምራል ማለት ነው። የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያ ለመላው የሀገራችን ሕዝብ የሚጨምረው እሴት ይህ ነው።

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ከዓመታት በፊት የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያ ለማቋቋም ሃሳብ አቅርበው ነበር። ቀደም ብሎ ባለመከፈቱ ይቆጫሉ ?

እሌኒ (ዶ/ር)፡– አዎ ቀደም ብለን የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያን ጀምረን ቢሆን ኖሮ እንጠቀም ነበር ብዬ አስባለሁ። መጀመር ከነበረብን ጊዜ ዘግይተናል፤ ጊዜው አልፏል ባይ ነኝ። የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያው አስፈላጊነት ልክ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሚያስፈልግበት ደረጃ የነበረ ነው። ማንም ሰው ምርት ገበያው እውን ይሆናል ብሎ አልጠበቀም ነበር። ነገር ግን ችግሮች ስለነበሩብን እና የግድ ልንፈታቸው የሚገቡ ስለነበሩ እውን አድርገነዋል። ዝግጁ አልነበርንም፤ ነገር ግን ደግሞ ምርጫ አልነበረንም። አንድ ችግር ካለ መፍትሔው መኖር አለበት። የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያውም ተመሳሳይ ነው።

እውነታው የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያ በሌለበትም ሼሮችን እንገዛና እንሸጥ ነበር። እስካሁን በወረቀት ማስረጃ ሼሮችን ስንገዛ እና ስንሸጥ ቆይተናል። ድርሻ የገዛንበት የወረቀት ማስረጃ ሊጠፋ ወይም ቤታችን በእሳት ሊቃጠል ቢችል ዋስትና መስጠት የሚችል የተደራጀ ሥርዓት አልነበረንም። የተደራጀ፣ ዘመናዊ እና ዲጂታል የሆነ የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያ መኖር መተማመን እንዲፈጠርና ሰዎች በቀላሉ ሼሮችን እርስ በርስ እንዲገበያዩ የሚያደርግ ነው። ሼራቸውን ለሽያጭ የሚያቀርቡ ድርጅቶች ትክክለኛ የፋይናንስ ታሪካቸውና አትራፊነታቸው ተጣርቶ ገበያው ላይ ስለሚሳተፉ ገበያተኞች አስተማማኝ መረጃ ላይ ተንተርሰው ውሳኔዎች ላይ እንዲደርሱ ያግዛል።

አዲስ ዘመን፡- ባንክ እና የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያ የአሠራር ግንኙነት እንዴት ያለ ነው ?

እሌኒ(ዶ/ር)፡– የባንክ አሠራርና የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያ ተሻሚ አካሎች ሳይሆኑ አብረው የሚሠሩ ናቸው። ከባንኮች ወደ የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያው የተላለፈ ብር ተመልሶ ወደ ባንክ ነው ለገዢው የሚተላለፈው። የአንዱ ማደግ ሌላውን ያሳድጋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- አስተማማኝነቱ እንዴት ይታያል ?

እሌኒ(ዶ/ር)፡- የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያው ለእያንዳንዱ ዜጋ ትልቅ ሀብት የማጎልበቻ መንገድ ነው። ይሄ እንዲሆን ከቁጥጥርና ሕግ ማሕቀፍ እንዲሁም ከአሠራር ሥርዓት አንጻር አንድ ሰው ገንዘቡን ያለ አግባብ እንዳያጣ ለመከላከል ጠንካራ ሥራ መሰራት አለበት። እነዚህን ነገሮች ደግሞ በምርት ገበያው አሳይተናል። አሁንም በሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያው ያለው አሠራር ለማንም ሰው ዋስትና የሚሰጥ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያውን መመሥረት ተከትሎ ባንኮች እያቋቋሙ ይገኛሉ። ከዚህ አንጻር የኢንቨስትመንት ባንክ የሚኖረው ሚና ምንድን ነው ?

እሌኒ (ዶ/ር)፡– አዎ የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያው መምጣት አብሮ የኢንቨስትመንት ባንኮች ይዞ መጥቷል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲቢኢ ካፒታል በሚል የራሱን ኢንቨስትመንት ባንክ እያቋቋመ ነው። ሌሎች ባንኮችም ተመሳሳይ መንገድን እየተከተሉ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን አዋጅን መሠረት በማድረግ ባንኮች ኢንቨስትመንት ባንክ በማቋቋም ላይ ይገኛሉ።

የኢንቨስትመንት ባንክ የሰነደ መዋለ ንዋይ ሽያጮችን በውክልና የሚሸጥ ገዢ እና ሻጭን የማገናኘት ሥራ የሚሠራ ተቋም ነው። ባንኩ በሰነደ መዋለ ገበያ ውስጥ ሰነደ መዋለ ንዋይ አቅራቢዎችን ከገዢዎች ጋር በማገናኘት የግብይት ሥርዓቱ እንዲፋጠን የሚያደርግ ተቋም ነው። የመዋለ ንዋይ ገበያው አማካሪ በመሆን ድርጅቶችን ይደግፋል፤ መዋለ ንዋዮችን የመግዛት እና የማሻሻጥ ሥራ ይሠራል። የሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያው ለባንክ ዘርፉ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ብዙ ለውጦች እንዲመጡ የሚያደርግ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።

እሌኒ(ዶ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ተስፋ ፈሩ

 

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You