የመጽሐፉ ርእስ ታላቁ ጥቁር ኢትዮ-አሜሪካ ዘዳግማዊ ምኒልክ
ደራሲ ንጉሤ አየለ ተካ
የገጽ ብዛት 474
የመጽሐፉ ዋጋ 225 ብር
ኅትመት ኢክሊፕስ ማተሚያ ቤት፤ አዲስ አበባ፤
ታላቁ ጥቁር ኢትዮ – አሜሪካ ዘዳግማዊ ምኒልክ የሚለውን መጽሐፍ ያነበብኩት በተለየ ስሜት ነው። በእኔ አረዳድ ዳግማዊ ምኒልክ በዘመናቸው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያደረጉት ከጀርመን፤ ከጣሊያን፤ ከእንግሊዝ ፣ ከፈረንሳይና ከመስኮብ ጋር እንጂ እንደዚህ ስፋት በአለው ሁኔታ ከአሜሪካ ጋር የነበራቸውን የዲፕሎማሲ ወዳጅነት የሚገልጽ መጽሐፍ አግኝቼ በስፋት ያነበብኩበት ጊዜ የለም። የዚህን ጽሑፍ ርእስ የምኒልክ ዱካ በአሜሪካ ያልኩትም ለካ ዱካቸውና ፈለገ መንግሥታቸው እስከአሜሪካ ድረስ ደርሶና ታውቆ ኖሯል ለማለት ነው።
ደራሲ ንጉሤ አየለ ተካ ወደ ድርሰቱ ዓለም ከተሰማራ ብዙ ዘመናትን አስቆጥሯል። በዚህ ዓይነት ቀደም ሲል ሐኖስ ጣዝማ(በደራስያን ሕይወት ላይ ያተኮረ)፤ፍካት( ግጥሞችና ወጎች በጋራ የተሠራ)፤ አራተኛው መልስ( በተለይ ለሕጻናት የተዘጋጀ)፤የገራዶ ዋሽንት (ሥነ ግጥም) የተሰኙ የድርሰት ሥራዎቹን ለንባብ አብቅቷል። በቅርቡ ደግሞ “ታላቁ ጥቁር ኢትዮ- አሜሪካ ዘዳግማዊ ምኒልክ” በሚል ርእስ ያሳተመውን አዲስ መጽሐፍ በአራት ኪሎ ቅርስና ጥበቃ ባለሥልጣን የስብሰባ አዳራሽ ማስመረቁና ለአንባብያን እንዲሰራጭ ማድረጉ ይታወሳል። መጽሐፉ ከሚታወቀው ወደማይታወቀው የሀገር ታሪክ የሚያሸጋግርና በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን የኢትዮ-አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዴት እንደነበር ያትታል።የመጽሐፉ ዝግጅት ከ12 ዓመታት በላይ እንደወሰደና በጥናትና ምርምር ዙሪያ እንደሚያተኩር ደራሲው ይናገራል።
ሥራው በሁለቱ አገሮች ረገድ ከተጻፉት መጻሕፍት የመጀመሪያው እንደሆነም ተመልክቷል።መጽሐፉ 474 ገጽ ያለው ሲሆን መጠኑም ከፍተኛ ነው።ከመጽሐፉ የኅትመት ጥራትና የገጽ ብዛት፤ ከያዘው መሠረታዊ ቁም ነገር አንጻር ሲታይ ዋጋው አነስተኛ ነው። ዛሬ 100 ገጽ የማትሞላና የውሻ ምላስ የምታህል መጽሐፍ ከ100 እስከ 150 ብር ስታወጣ የዚህ ትልቅ መጽሐፍ ዋጋ 225 ብር መሆኑ የደራሲውን ሚዛናዊነት ያመለክታል።የመጽሐፉ ደራሲ ኢትዮጵያ ከዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጀምራ ከአሜሪካ ጋር የነበራት የወዳጅነትና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ምን እንደሚመስል የጻፈልን በአሜሪካ ልዩ ልዩ ሙዚየሞችና አብያተ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙና ስለ ኢትዮጵያ የሚ ያስረዱትመጻሕፍትን፤ጋዜጦችን፤ልዩልዩየፕሮቶ ኮልናየታሪክ፡ሰነዶችን፤ፎቶግራፎችን፡በማሰስና ያለመታከትም ሰፊ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ነው።
ደራሲ ንጉሤ አየለ እስከ ዛሬ ድረስ አብዛኛው ሕዝብ የማያውቃቸውን አዳዲስ መረጃዎችንና ታሪካዊ ክንውኖችን ተንትኖ እነሆ ብሎናል።የአሜሪካ ጋዜጦችና የዲፕሎማሲ ባለሙያዎች ዳግማዊ ምኒልክን ብልህና ገናና የአፍሪካ ንጉሥ ናቸው በማለት ከማድነቅ አልፈው «የዓለም ታላቁ ጥቁር ሰው ምኒልክ የፓን አፍሪካን የክብር ፕሬዚዳንት መሆን አለባቸው» ማለታቸውን ደራሲ ንጉሤ (56)ያስነብበናል።
ደራሲ ንጉሤ ለብዙ ዓመታት የደከመበትንና የለፋበትን የታሪክ ትሩፋቱን ያቀረበልን መንግሥት ወይንም የግል ድርጅት ባጀት መድቦለት ሳይሆን በራሱ ገንዘብ በአሜሪካ ልዩ ልዩ ግዛቶች መረጃ ለማግኘት በመዘዋወር ነው።በዚህ ዓይነት እስከዛሬ የተሰወሩትን ጥልቅ መረጃዎችን ከመላ አሜሪካና ከአንዳንድ ደሴቶች ውስጥ ከሚገኙ የተወቁ አብያተ መጻሕፍት፤ታላላቅ ሙዚየሞች፤በየቤተ መጻሕፍቱ በጥንቃቄ ከተቀመጡ ሰነዶች፤ጋዜጦችና መጻሕፍት ጭምር በመሰብሰብና የተሰወረውን ጉዳይ ወደ ብርሃናማው መድረክ በማምጣት ነው።በዚህ አይነት በሁለቱ አገሮች መካከል የተጀመረው የቆየ ግንኙነት በኋላ ጊዜ ለተከናወኑት በርካታ ቁም ነገሮች ዋነኛ መሠረት እንደሆነ ከመጽሀፉ ለመረዳት ይቻላል።
እንደሚታወቀው ዳግማዊ ዓፄምኒልክ በዘመናቸው ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር የዲፕሎማሲና የወዳጅነት ግንኙነት ያደርጉ የነበረው አንድም በደብዳቤ ወይንም እንደራስ መኮንን የመሰሉ ታማኛቸውንና ባለሟላቸውን ወክለውና ሌሎች መልእክተኞቻቸውን አስከትለው በመላክ ነበር።
በዘመኑ ከነበረው የግንኙነት ቴክኖሎጂ ውሱንነት የተነሣ በባሕር ላይ በመርከብ ይደረግ የነበረው ጉዞ አሰልቺና ጊዜም ወሳጅ ስለነበር ለአንድም ጊዜ ቢሆን ወደ ውጭ አገር ሄደው የማያውቁት ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ በመልእክተኛ ደረጃ በ1984 ዓ.ም የውጭ አገር ግንኙነቱን የጀመሩት በራስ መኮንን ተጠሪነት በእንግሊዝዋ ንግሥት ቪክቶርያ ልጅ በኤድዋርድ 7ኛ የዘውድ በዓል ላይ እንዲገኙ እነመምህር ገብረ እግዚአብሔርን፤ፊታውራሪአባ ታቦርን፤ትርጁማን ሚካኤል ብሩን፤ፊታውራሪ ኃይለ ሥላሴ ዓባይነህን( የራስ እምሩ አባት) ከንቲባ ገብሩን ወደ እንግሊዝ (መርስኤ ኀዘን1999፡84) በመላክ ነበር። ከእነዚህ መልእክተኞች ውጭ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ከሀገሩ ርቀት የተነሣም ሊሆን ይችላል ሌሎች ሰዎችን ወደ አሜሪካ አልላኩም።
ይሁን እንጂ ዳግማዊ ምኒልክ አሜሪካ እንደ ሌሎች የአውሮፓ አገሮች ወደ አፍሪካ መጥታ የሰው አገር የማትወርርና ድንበርም የማታፈርስ መሆኗን በሚገባ ተረድተዋት ስለነበረ ወዳጅነቷን አጥብቀው ይፈልጉት ነበር።በፕሬዚዳንት ቴዎዶር ሩዝቬልት ዘመን ለአሜሪካና ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መሠረት የጣለውም ቆንሲል ጄ ሮበርት ስኪነር ነው። ዓፄ ምኒልክ በዘመናቸው አሜሪካንን የገለጽዋት“ ሌሎች አገሮች ወደ አፍሪካ የሚመጡት ልክ ልጆች ወደ አባታቸው መጥተው ‘አባየ ኑዛዜ ፈጽመህ አንዳች ነገር ትተውልናለህ?’ እንደሚሉ ዓይነት ነው። አሜሪካ ብቻ ናት በአፍሪካ መሬት የሌላትና ሜዝም የማትፈልግ ። የአሜሪካ ፍላጎቷ የመነገድ ፈቃድ ብቻ ነው» በማለት ነው።
ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ይህንን የተናገሩት ፕሬዚዳንት ቴዎዶር ሩዝቬልት ደስ የሚሰኘውን የወዳጅነት ደብዳቤ እንዲህ ሲል ስለጻፈላቸው ነው።« ለትንሹም ሆነ ለትልቁ አገር ያለን አመለካከት እኩል አክብሮት የተሞላውና በእውነተኛ ወዳጅነት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል። የሌሎችን መብትና ፍላጎት አክብረን ሐቀኛ ወዳጅነት መመሥረት ተገቢና ፍትሐዊ ነው።ይህንንም በቃላት ብቻ ሳይሆን በተግባር የምንገልጸው መሆን አለበት »:: በመሆኑም ንግሥት ሳባ በጠቢቡ ሰሎሞን ጥበብ ተደንቃ፤ ተመስጣና ጥበብን፤ ዕውቀትን ለመቅሰም ፈልጋ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዛ እንደነበረ ሁሉ ዓፄ ምኒልክም በመላው አውሮፓ በእግረ ልቡናና በመንፈስ ተጉዘውና መልእክተኞቻቸውንም ወደ ፈረንሳይ፤ ጣሊያንና እንግሊዝ ልከው ሀገራቸው የሥልጣኔ ባለቤት እንድትሆን ብዙ ጥረት አድርገዋል፤ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ለሀገራችን ያስገኙትም ይኸው የጥበብና የሥልጣኔ አፍቃሪነታቸው ነው።
ደራሲው ንጉሤ አየለ ስለአሜሪካና ኢትዮጵያ ወዳጅነት ለብዙ ዓመታት ያልተቋረጠ ጥናትና ምርምር በማድረግና ከዚህ በፊት በአንባብያን ዘንድ የማይታወቁ አዳዲስ መረጃዎችን ይዞልን ስለመጣ መጽሀፉን በበለጠ ተጠቃሽ ባለታሪክ ያደርገዋል።ደራሲው ኢትዮጵያዊነት በአሜሪካ ምን እንደሚመስል፤በጉብኝት፤ በንባብና በፍለጋ አማካይነት የሁለቱን አገሮች ወዳጅነት በተመለከተ ምን ዓይነት ውጤት እንዳገኘ፤ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን በሁለቱ አገሮች መካከል ስለነበረው ንግድና ወዳጅነት፤ የኢትዮጵያ ጉዳይ በኋይት ሐውስ ቤተ መንግሥት እንዴት አጀንዳ እንደሆነ፤አሜሪካዊው ቆንሲል ሮበርት ፒን ስኪነር የሁለቱን አገሮች ወዳጅነት ለማጠናከር ስለአደረገው ጥረት፤ ስለመጀመሪያው የሩዝቬልት ካምፕ በድሬዳዋ ፤ዊልያም ኤሊስ በኢትዮጵያ ፍቅር እንዴት እንደተነደፈ ያስረዳናል።
በተጨማሪ በምኒልክ አደባባይ የሩዝቬልትን መልእክተኛ ለመቀበል ስለተደረገው አቀባበል፤ ስለታላቁ ጥቁር ሰው ስለ ዓፄ ምኒልክ ባሕርያትና በአሜሪካውያን ዘንድ ስለነበራቸው ተወዳጅነት ፤ በስጦታ መልክ በመርከብ ወደ አሜሪካ የተጓዘው የምኒልክ አንበሳ በመርከበኞች አጠራር ቴዲ በዋሺንግተን ዲሲ እንዴት እንዳገሳ ከቦረና ተነሥተው አሜሪካ ስለገቡት የጥንት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፤በአሜሪካ ኢትዮጵያውያውያን ስለሠሩት ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን በፎቶግራፎች ጭምር በታጀበ አቀራረብ አዳዲስ ክስተቶችን ያሳየናል።አንድሬይ ካርኔጌ በበኩሉ ዳግማዊ ምኒልክን በዓለም ላይ ምን እየተከናወነ እንደሆነ የሚያውቁ፤መልካም ሆኖ ላገኙት ነገር ግርማ ሞገስ ያለውን አድናቆታቸውን የሚሰጡ ታላቅና ጠቢብ ንጉሥ በዚህ ዘመን በአቢሲኒያ ነግሠው እንደነበር ይመሰክር ዘንድ ( ይህ የምኒልክ ደብዳቤ) ለመጭው ትውልድ ይቀመጣል ሲል አድናቆት ቸሯቸዋል። የኢትዮጵያ ወጣቶች ዘመናዊ ትምህርት የሚማሩበት ዘመን መምጣቱንም ለአሜሪካው ቆንሲል ለሮበርት ስኪነር መናገራቸው ዘመናዊ ሥልጣኔ ወደ ሀገራችን እንዲገባ የጸና እምነት የነበራቸው መሆኑን ያሳያል።
እንደ እውነቱ ከሆነ ስለሁለቱ አገሮች ብዙ ሰው ገና ያልተረዳውንና ያላወቀውን ታሪክ አስፍቶ የጻፈውና የጎደለውን ነገር የሞላው ደራሲ ንጉሤ አየለ ብቻ ስለሆነ ታላላቅ የታሪክ ሥራዎችን እንዳቀረቡልን የጥንት ደራሲዎቻችን ሊመሰገኑና ሊታወስ የሚገባው ኢትዮጵያዊ ነው ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 13/2011
ታደለ ገድሌ ጸጋየ ዶ,/ር