አዋጁ የኢኮኖሚ ወንጀሎችን ውጤታማ በሆነ መልኩ መከላከል የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ ፡- የንብረት ማስመለስ አዋጅ መፅደቁና ተግባራዊ መሆኑ የኢኮኖሚ ወንጀሎችን በውጤታማ መልኩ መከላከል ያስችላል ሲሉ የፍትሕ ሚኒስትር ወይዘሮ ሐና አርዓያሥላሴ ገለጹ።

የፍትሕ ሚኒስትር ወይዘሮ ሐና አርዓያሥላሴ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ አዋጁ ሲተገበር ለተወሰኑ ወንጀሎች ብቻ ተፈጻሚ ይሆን የነበረው የንብረት ማስመለስ ለሁሉም በማድረግ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ ጤናማና ፍትሐዊ የሆነ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ሥርዓት እንዲኖር ያግዛል ብለዋል።

ሚኒስትሯ የንብረት ማስመለስ አዋጅ ከፀደቀ በኋላ የተፈጠሩ ብዥታዎችን ለማጥራት የአዋጁን ይዘት እና የአተገባበር ሁኔታ አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ንብረት ማስመለስን የተመለከቱ ሕጎች ቢኖሩም የተወሰኑ ወንጀሎችን ብቻ የሚመለከትና ሁሉንም አይነት የኢኮኖሚ ወንጀሎች ያካተተ ባለመሆኑ አይደለም ብለዋል። ይህም የኢኮኖሚ ወንጀል የፈጸመ ግለሰብ ከወንጀል ተጠያቂነት ባለፈ ንብረቱ የሚመለስበት ሥርዓት እንዳልነበረ አውስተዋል።

ይህ ክፍተት እንደ ሙስና ያሉ እና ሌሎች የኢኮኖሚ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት የተሟላ እንዳይሆን አድርጎታል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ከተጠያቂነት ባለፈ ከወንጀሉ ያገኙት ንብረት ተመላሽ ተደርጎ ለሕዝብ ጥቅም የሚውልበት ሥርዓት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

እንደ ወይዘሮ ሐና ገለጻ፤ አዋጁ የንብረት ምርመራ ሂደት ማገድ እና ማስተዳደር በአዋጁ የሰፈረ ጉዳይ ነው።አዋጁ ተቋማት በየደረጃው ያላቸውን ኃላፊነት ወጥ በሆነ መልኩ ያስቀመጠ ሲሆን የዓለም አቀፍ ትብብርንም ያካተተ ነው።

የኢኮኖሚ ወንጀሎች በባሕሪያቸው ውስብስብ እና ድንበር ተሻጋሪ ናቸው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ወንጀሉን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጸመ ወንጀል በሌላ ሀገር ንብረት የተፈራበት ከሆነ ከሌሎች ሀገራት ጋር በመተባበር ወንጀሉን እንዴት መከላከል ይቻላል የሚሉ ድንጋጌዎችን የያዘ እንደሆነ አብራርተዋል ።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ አስፈጻሚውን ሥልጣን በተመለከተ በዘፈቀደ የሚተገበር ሳይሆን የንብረት ማስመለስ ሂደት ውሳኔ ተፈጻሚነት በወንጀል ጥፋተኝነት ላይ የተመሠረተ ነው።በፍርድ ቤት ውሳኔ ሀብቱ በወንጀል ድርጊት የተፈራ ሀብት መሆኑ ሲረጋገጥ የንብረት ማስመለስ ሥራ የሚከናወን ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል ።

ሌላኛው የሦስተኛ ወገኖችን ጥበቃ ማለትም ንብረቱን በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘ መሆኑን ሳያውቁ ተገቢውን ክፍያ ከፍለው ያገኙት የቅን ልቦና ገዢዎች መሆናቸው ከተረጋገጠ ንብረቱ እንዳይወረስ ለፍርድ ቤቱ ማመልከቻ ማቅረብ የሚቻል በመሆኑ አዋጁ ለቅን ልቦና ገዢዎች ተገቢውን ጥበቃ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ምንጩ ያልታወቀ ንብረትን በተመለከተ አዋጁ 10 ዓመት ወደኋላ ሄዶ መሥራቱ እና የ10 ሚሊዮን ብር ገደብ መቀመጡ ሌላኛው ብዥታ የተፈጠረበት መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሯ፤ ይህ በሌሎች ሀገራት የንብረት ማስመለስ ሕግ ላይ ያለ ተሞክሮ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ምንጩ ያልታወቀ ሀብትን የሚመለስበት ሥርዓት የፍትሐ ብሔር ተጠያቂነት ብቻ በመሆኑ ከሕጋዊነት መርሕ ጋር ተጣጥሞ የሚተገበር መሆኑን ሚኒስትሯ ጠቁመው፤ የወንጀል ተጠያቂነት ላይ የተመሠረተ የንብረት ማስመለስ ሂደት አዋጁ ከተወጣበት ጊዜ ጀምሮ ያለ መሆኑን አንስተዋል።

ምንጩ ያልታወቀ ንብረትን በተመለከተ የሚቀርቡ ማስረጃዎች የሰነድ ብቻ ናቸው የሚል የተሰራጨው መረጃ ስህተት መሆኑን ገልጸው፤ አዋጁ በየትኛውም ሁኔታ የንብረቱን ሕጋዊነት ያስረዳልኛል የሚላቸውን የሰውና ሌሎች ማስረጃዎችን ተጠቅሞ ሕጋዊነቱን ማስረዳት ይችላል ብለዋል።

የአዋጁን አተገባበር አስመልክቶ በጥንቃቄ እንዲተገበር ልዩ አደረጃጀቶች እንደሚኖሩ አመልክተው፤ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም በነበሩ የንብረት ማስመለስ ሂደቶች ያሉ ተሞክሮዎችን መነሻ በማድረግ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የንብረት ማስመለስ አዋጅ ቁጥር 1364/2017 በያዝነው የጥር ወር መጀመሪያ 2017 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁ ይታወሳል ።

ሰሚራ በርሀ

 

አዲስ ዘመን ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You