
1.እስፒናች፡- የቫይታሚን ኤ እና ሲ ክምችት ያለው ሲሆን እነዚህ ቫይታሚኖች የአንቲኦክሲዳንት ባህሪ ስላላቸው ቆዳችንንም ሆነ ሰውነታችንን ከፍሪ ራዲካሎች ይከላ ከላሉ፡፡ ማግኚዢየም፣ ሴሌኒየም፣ እና ዚንክን መያዙ ደግሞ ለቆዳ መወጠር፣ ለደም ዝውውር፣ ለቆዳ ወዝ ቁጥጥር ወዘተ… ትልቅ ጥቅም ይሰጣሉ፡፡
2.ኪያር፡- ለቆዳ ውበት እና ጤንነት የሚጠቅም ሲሊካ የሚባል ማዕድን ይዟል። ኪያርን አዘውትሮ መመገብ እና የኪያር የፊት ማስክ መቀባት ቆዳን ብሩህ እና አንፀባራቂ የሆነ ውበት ያላብሰዋል፡፡ የቆዳን እርጅናም ያዘገያል፡፡
3. ቀዩ፣ ቢጫውና ብርቱካናማው የፈረንጅ ቃሪያ፡- የፈረንጅ ቃሪያ ቤታ ካሮቲን የሚባለው የአንታይኦክሲዳንት አይነት ባህሪ ያለው ቫይታሚንን የያዘ ሲሆን ይህም በቆችን ስባማ ክፍል ውስጥ ሟሙቶ ቦታ በመያዝ ይቀመጣል፡፡
በዚህም ምክንያት የቆዳን ህዋሳት ከፍሪ ራዲካል ለመከላከል ይረዳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የቆዳን የመለወጥ ባህሪ የመጠበቅ እና ሞላ ያለ እና ውብ እንዲሆን ያደርጋል፡፡
4.አቮካዶ፡- የቫይታሚን ኢ ይዞታው ከፍተኛ በመሆኑ የቆዳን ህዋሶች ከፍሪ ራዲካሎች ጥቃት ይከላከላል፡፡
5. ፐርስሊ፡- በውስጡ የያዘው ጠቃሚ ዘይት የማሸናት ባህሪ ያለው በመሆኑ፣ በውሃ ውስጥ የሚሟሙ ቆሻሻዎች እንዲወገዱ ያደርጋል፡፡ የኩላሊት ስራንም ቀልጣፋ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች እንደ ሊቲዮለን የመሳሰሉ የአንታይኦክሲዳንት አይነቶችን በውስጡ ይዟል፡፡
6. ሽንኩርት፡- ሽንኩርቶች አንድ የጋራ የሆነ የማዕድን ይዘት አላቸው፡፡ እርሱም ሰልፈር ነው፡፡ ሰልፈር የተባለው ማዕድን ደግሞ ቆዳ እንዳይሸበሸብ እና እንዲወጠር ያደርጋል፡፡
7.እንስላል፡- ለምግብ መፈጨት ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ሲሆን ዘሩ፣ ቅጠሉ፣ ሥሩም ጠቀሜታ ላይ መዋል የሚችል የአትክልት አይነት ነው፡፡ እንስላል ልክ እንደ ፐርስሊ ሁሉ የማሸናት ባህሪ አለው፡፡ ይህ ደግሞ ከሰውነታችን መውጣት ያለባቸውን በውሃ ውስጥ የሚሟሙ ቆሻሻዎችን በብዛት እና ቶሎ ቶሎ እንዲወገዱ ያደርጋል፡፡
ቆሻሻ ከሰውነታችን በበቂ ሁኔታ ተወገደ ማለት ደግሞ የቆዳ ጥራት እና ፍካት ይጨምራል ማለት ነው፡፡
8.ቲማቲም፡- ቲማቲም የተለያዩ አንቲኦክሲዳንት አይነቶችን የያዘ የምግብ አይነት ነው፡፡ ስለዚህ ቲማቲም ህዋሶቻችንን ከፍሪ ራዲካል ጥቃት ሊታደግ የሚችል በቀላሉ የሚገኝ አትክልት ነው፡፡ በመሆኑም ቲማቲም ባለው አንታይኦክሲዳንት ብዛት እና አይነት ሳቢያ የቆዳን እርጅና ፍጥነትን የመቀነስ ችሎታ አለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ
የኮላጂንን ጥንካሬ እና የመለጠጥ ችሎታ የመጨመር ኃይል ስላለው የቆዳ መሸብሸብን ፍጥነት ይቀንሳል፡፡
9. ቀይ ስር፡- ቀይ ስር በውስጡ ቤታ ሳያኒን የተባለ ቅመም የያዘ ሲሆን ይህ ቅመም ለቀይ ስር ደማቅ ሀምራዊ ቀለም መያዝ ምክንያትም ነው። ይህ ቅመም በዋነኛነት ከሚያከናውናቸው ሥራዎች ውስጥ የጉበትን ቆሻሻ የማስወገድ ሥራ ማገዝ ነው። ይህም ማለት በሰውነት ውስጥ የሚገኙ መርዛማ የሆኑ ቆሻሻዎችን ለማስወገድ የሚጠቅም ሲሆን መርዛማ ቆሻሻዎችን በመሰባበር ከሰውነት እንዲወገዱ ይረዳል። ከዚህ በተጨማሪ ዚያክሳቲን የተባለ አንታይኦክሲዳንት በመያዙ ህዋሶቻችንን ከፍሪ ራዲካሎች ሊታደግልን ይችላል። ይህ በአንፃሩ ቆዳ ቶሎ እንዳይሸበሸብ፣ ውብ እና ህይወት ያለው እንዲሆን ያደርጋል፡፡
10 .ስኳር ድንች፡- በውስጡ ቆዳ አፍቃሪ የሆነውን የአንቲኦክሲዳንት አይነት ቤታ ካሮቲንን በብዛት የያዘ ነው። ቤታ ካሮቲን ደግሞ በተደጋጋሚ በብዛት እንደተመለከትነው በቆዳችን ስባማ ክፍል ውስጥ በመጠራቀም የቆዳችንን ኮላጂንን እና ኢላስቲን የተባሉ ቆዳን የመለጠጥ እና የመወጣጠር ባህሪን የሚያላብሱ ክፍሎችን ከፍሪ ራዲካሎች ጥቃት ይከላከላል፡፡ በዚህም ሳቢያ ቆዳ ቶሎ እንዳይሸበሸብ እና እንዳያረጅ ያግዛል፡፡ ሌላው ቤታ ካሮቲን በ‹‹አንቲ ኢንፍላማቶሪ›› ባህሪው ምክንያት የቆዳን መቅላት፣ ማበጥ እና ህመም የማከም ችሎታ አለው፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 13/2011