
– 250 ቦቴዎች ለስድስት ወራት ከሥራ ውጪ እንዲሆኑ ቅጣት ተጣለባቸው
አዲስ አበባ፡- መንግሥት ቤንዚንን በሊትር 21 ብር፣ ናፍጣን በሊትር 28 ብር እየደጎመ እንደሚገኝ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ሰው ሰራሽ የገበያ እጥረት እንዲፈጠር ያደረጉ 250 ቦቴዎች ለስድስት ወራት ከሥራ ውጪ እንዲሆኑ መደረጉን ተጠቆመ፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ተስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት ከነዳጅ ምርቶች ግብይት፣ ከዋጋ ክለሳ ጋር በተያያዘ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ መንግሥት ከሰሞኑ በነዳጅ ምርቶች ካደረገው የዋጋ ክለሳ በኋላ ቤንዚንን በሊትር 21 ብር ፣ ናፍጣን በሊትር 28 ብር እየደጎመ ነው፡፡
ከዋጋ ክለሳ በፊት ባለፈው ታኅሣሥ ወር አንድ ሊትር ቤንዚን 91 ነጥብ 14 ፣ ነፍጣ 90 ነጥብ 28 ብር ሲሸጥ እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ገበያ አንድ ሊትር ቤንዚን 123 ብር ፣ አንድ ሊትር ናፍጣ በዓለም ገበያ 126 ብር እንደሆኑ ገልጸዋል። መንግሥት ባደረገው ድጎማ ባለፈው ታኅሣሥ ወር በቤንዚን ላይ ወደ ግለሰቦች መሄድ የነበረበትን 31 ብር ከ81 ሳንቲም እንዲሁም በናፍጣ ላይ 35 ብር ከ32 ሳንቲም ሲደጉም ቆይቷል ብለዋል፡፡
ቤንዚን ላይ 33 በመቶ ብቻ ወደ ተጠቃሚው በማስተላለፍና 67 በመቶ የሚሆነውን ከዓለም ገበያ ጋር ያለውን ልዩነት መንግሥት ተሸክሞ እንደሚገኝ አመልክተዋል። ናፍጣም እንዲሁ 25 በመቶ የሚሆነው ለተጠቃሚዎች ተላልፎ ቀሪውን 75 በመቶ መንግሥት የተሸከመው እዳ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዳይጎዱ ሰፋፊ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ መንግሥት በጥቅል የነዳጅ ድጎማ ወደ 137 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ደጉሟል ብለዋል፡፡
ከጥቅል ድጎማ ውጪ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ በሚባለው ማለትም፤ ባለፉት ስድስት ወራት ለሕዝብ ትራንስፖርትና ለከተማ አውቶቡሶች በሚደረግ ድጋፍ በአንድ ሊትር ወደ 19 ብር ልዩ ድጎማ በማድረግ ወደ 463 ሚሊዮን ብር ብቻ መንግሥት ድጎማ ስለማድረጉም ተናግረዋል፡፡ የዋጋ ጭማሪዎች ሲደረጉ በጭማሪ ዋጋዎቹ ላይ ኤክሳይዝ ታክስ፣ ቫት፣ የተለያዩ ቀረጦችና አሹራዎች እንዳይኖሩ በማድረግ መንግሥት ማግኘት የሚገባውን ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ መተውንም ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ በሊትር 1 ነጥብ 3 የአሜሪካ ዶላር እንደሆነ ጠቅሰው፤ በጎረቤት ሀገር ጂቡቲ 1ነጥብ 74 ፣ በኬንያ 1ነጥብ 4 የአሜሪካ ዶላር እየተሸጠ እንደሚገኝና በኢትዮጵያ የ1 ሊትር ነዳጅ ዋጋ 0 ነጥብ 8 የአሜሪካ ዶላር እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
ከሰሞኑ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ ከዓለም ዋጋ ጋር ሲነጻጸር በብዙ መልኩ ቅናሽ የሚታይበት እንደሆነና መንግሥት ቤንዚንን በሊትር 21 ብር ፣ ናፍጣን በሊትር 28 ብር እየደጎመ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ የዋጋ ማሻሻያ እየተደረገ ሲመጣ ጉዳዩን የማስጮህ፣ የፖለቲካ አጀንዳ የማድረግ፤ ፍላጎቶችና ዝንባሌዎች እየተስተዋሉ መሆኑን አንስተው፤ አድራጎቱ ፍጹም ስህተትና ትክክለኛ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
በነዳጅ አቅርቦት ፣ ስርጭት እና የግብይት ሥርዓት የሚስተዋለውን ችግር ባለሀብቶችና ነጋዴዎች ጫናውን ካልተጋሩ መንግሥት ብቻውን ተሸክሞ ለመጓዝ የሚቸገር መሆኑን ገልጸው፤ ይህ ካልሆነ መንግሥት ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የጀመራቸውን ትልልቅ ብሮጀክቶች ለመገንባት የሚቸገር እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
መንግሥት ደረጃ በደረጃ ከጫና ውስጥ ለመውጣት የዋጋ ማሻሻያዎችን ሲያደርግ፤ አንዳንዶች በአቋራጭ ለመክበር በመፈለግ ነዳጅን በመሰወርና ስርጭቱን በማስተጓጎል ሰው ሰራሽ የገበያ እጥረት እንዲፈጠር ሲያደርጉ ይስተዋላልም ብለዋል፡፡
250 ቦቴዎች ከ10 እስከ 15 ቀናት ጢሻ እና ዱር ውስጥ ቆመው በተክኖሎጂ በተደረገ ክትትል ከክልል ንግድ ቢሮዎችና ከጸጥታ መዋቅሮች ጋር በመሆን ርምጃ እንዲወሰድባቸው መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በተጣለባቸው ቅጣት ቦቴዎቹ ለስድስት ወራት ምንም አይነት ምርት እንዳያጓጉዙ ተደርጓል፡፡ 19 ተባባሪ ማደያዎችም ከነዳጅ ግብይቱ ለስድስት ወራት እንዲታገዱ መደረጉንና ከ100 ሚሊዮን በላይ የገንዘብ ቅጣት እንደተጣለባቸው አስታውቀዋል፡፡
በሕገ ወጥ ንግድ 385ሺህ ሊትር ነዳጅ ተወርሶ 27 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት ገቢ መሆኑን ገልጸዋል። የተጀመሩ ርምጃዎች በማደያዎች ከግብይት ሥርዓቱ እንዲወጡ በማድረግ፤ ቅጣቱን የማጠናከር ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም