አዲስ አበባ፡– ሀገራዊ ምክክሩ የፖለቲካ እና የሃሳብ ልዩነቶችን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አቶ ኩማ ደመቅሳ ገለጹ፡፡ በርካታ የፖለቲካ ጥያቄ ባለበት እና ሰፊ ክልል በሆነው ኦሮሚያ የአጀንዳ ልየታና የተሳታፊዎች ምርጫ በጥሩ ሁኔታ መጠናቀቁ ለኮሚሽኑ አንዱ ትልቅ ስኬት መሆኑን አመለከቱ፡፡
አቶ ኩማ ደመቅሳ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በትጥቅ ትግል የፖለቲካ ሃሳብ ማሳካት አይቻልም፤ ሀገራዊ ምክክሩ ያሉትን የፖለቲካ እና የሃሳብ ልዩነቶች በውይይት ለመፍታት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
የአስተሳሰብ እና የአመለካከት ልዩነቶች ተፈጥሯዊ መሆናቸውን የሚገልጹት አቶ ኩማ፤ እስከአሁን በኢትዮጵያ ታሪክ የፖለቲካ እና የሃሳብ ልዩነቶችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ በመሣሪያ መዋጋት የተለመደ ችግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህ ደግሞ እንደ ሀገርም ጥፋት እንጂ ልማትን የማያመጣ በመሆኑ ለድህነታችን አንዱ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት የብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት የሚሉት አቶ ኩማ፤ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር መቀጠል የምትችለው ብሔር ብሔረሰቦች በመፈቃቀድ በእኩልነት አንዱ የበላይ አንዱ የበታች ሳይሆኑ መኖር ከቻሉ ብቻ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
በክልል ደረጃ በተደረገው የአጀንዳ ልየታ መድረክ በእኩልነት እና በመከባበር ጥሩ ምክክር መደረጉን መታዘባቸው ተናግረው፤ በዋናው ሀገራዊ ምክክር ላይም የሌላውን ሃሳብ በማድመጥ እና በመከባበር ወደ ሠላም ማምጣት እንደሚቻልና ጠንካራ ሀገር መገንባት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
ማንኛውንም ጥያቄ በሠላማዊ መንገድ በውይይት መፍታት የሚቻልበት ዘመን ላይ ነን ያሉት አቶ ኩማ፤ ለዘመናት የቆየውን የኢትዮጵያ ችግር ለመፍታት ሀገራዊ ምክክሩ ትልቅ ዕድል ይዞ መጥቷል፤ ይህን ዕድል በአግባቡ መጠቀም ከሁሉም ወገን እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡
እንደ አቶ ኩማ ገለጻ፤ የትጥቅ ትግል አቋርጠው በሠላማዊ መንገድ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ብለው ወደ ሠላም የመጡ ኃይሎች ውሳኔ ጥሩና የሚደገፍ ነው፡፡
ከእነዚህ ኃይሎች ሌሎችም ትምህርት በመውሰድ አክሳሪ ከሆነው ግጭት ወጥተው በሠላማዊ መልኩ ችግሩን በውይይት መፍታት የሚቻልበትን አማራጭ ሊከተሉ ይገባል፡፡ ከዚህ ቀደም በሠላማዊ መንገድ ለመወያየት ዕድሎች ባለመመቻቸታቸው እሳቸውም በትጥቅ ትግል መሳተፋቸውን አስታውሰው፤ አሁን ላይ ችግሮች በመሣሪያ የሚፈቱበት ጊዜ ያበቃና በሀገራዊ ምክክሩ የቀረበው የሠላም አማራጭ ታሪካዊ ዕድልን ይዞ የመጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ወገኖች በቀረበው ትልቅ እና ታሪካዊ ዕድል ተጠቅመው ወደ ሠላም መምጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
ምክክርን የማካሄድ ሥራው ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑም አዲስ መሆኑን የተናገሩት አቶ ኩማ፤ ኮሚሽኑ እስከአሁን እየሠራው ያለው ሥራ የተሳካ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በርካታ የፖለቲካ ጥያቄ ባለበት እና ሰፊ ክልል በሆነው ኦሮሚያ የአጀንዳ ልየታና የተሳታፊዎች ምርጫ በጥሩ ሁኔታ መጠናቀቁ ለኮሚሽኑ አንዱ ትልቅ ስኬት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
መዓዛ ማሞ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 24 ቀን 2017 ዓ.ም