እኛ ኢትዮጵያዊያን በተረት ሀብታሞች ነን:: እንደው በትክክል ከተጠቀምንባቸው አገራዊ ሀብቶች ዋንኛው የሚመስለኝ ተረት ነው፡፡ አጠቃቀሙ ለበጎ አልሆነም እንጂ፡፡ ምክንያቱም አብዝተን የምንጣላው፤ ርዕስ በርዕስ የምንነታረከው በተረት ነው፡፡ የምሬን ነው ወዳጆቼ እንደውም ሳስበው ተረት ነው የሚመራን፤ የሚነዳንም ጭምር:: በድሮ ዘመን እንዲህ አደረጉህ፤ እንዲያ ነበርን …..እያሉ ይተረትሩልናል እኛም ተረት አክባሪ ተረት አማኝ ነንና ርዕስ በርዕስ እንተራተራለን፡፡
ሚስኪን ስናሳዝን! በተረት አድገን ተረት እየሰማን ኖረን በተረት የምንጋጭ ጉደኞች ነን:: ተራቹ ብዙ ነው የሚተረትለትም እልፍ፡፡ አባባሎቻችን ገላጭና ድንቅ ናቸው፡፡ ግን ውዶቼ የበዛ ሀብታችን መሃል አንዳንዴ የበዛ ስህተት አያለሁ፡፡ ለምሣሌ “ወደሽ ከተደፋሽ ቢረግጡሽ አይክፋሽ!” ይባላል፡፡ አባባሉ ግን ትክክል ነው?
ቆዩኝማ ይህቺ አባባሉን ያደመቁባት ሚስኪን ተደፊ (በነገራችን ላይ ሁሌም አባባሉን ስሰማ እግር ስር ድፍት ብላ ትታየኛለች ስታሳዝን!) ለመረገጥ ነው እንዴ የተደፋችው? እኔ ግን በፍፁም አይመስለኝም፡፡ አጎምብሼ ሌላውን ላቅና ተነጥፌ ለሌላው ክብር ልስጥ ማለትዋ ነበር፡፡ ለምን እርግጫን አሜን ብላ ትቀበል ታዲያ? እኛስ “ቢረግጡሽ አይክፋሽ” ማለትን ምን አመጣው:: ስለ ተረትና አባባሎቻችን ብዙ ማለት ይቻለል:: እኔ ዛሬ ላወራችሁ ያሰብኩት ከዚህ የተለየ ሆነ እንጂ በተረትና አባባሎቻችን መነሻነት ዓመት ማውራት ይቻላል፡፡ ወደው የተደፉ ግን ያላግባብ እየተረገጡ ያሉ የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና ወላጆቻቸው አጠቃላይ ሁኔታ ላወጋችሁ ነው::
አቤት አንዳንዴ የሚገጥም የሚሳካ ስያሜ ከሁነቱ ጋር ሲገጥም ደስ ሲል፡፡ እኔ ምለው ስንቶቻችን ነን በሰጠነው የምንቀጣ? ወደን ባደረግነው የማንወደው የሚገጥመን? ሳንፈቅድ እና ሳንወድ የምንቀጣበት ሞልቷል፡፡ ብዙ ገፍቶ መትቶ የሚቀጣን፤ ርቆ ቀርቦ የሚያሳጣንማ ብዙ ሞልቷል:: ወደን ባደረግነው በፍቃዳችን በፈፀምነው መቀጣት ህመሙ ከባድ ነው፡፡ ከፍሎ መሞት ይሉሀል ወዳጄ ይሄኔ ነው፡፡ እንደው ይሰውረንና አንዳንዴ ይገጥማል ፍሬን አልመው ገለባ የሚሆንበት፤ የተሻለን ፈቶ የባሰ የሚያገቡበት ገጠመኝ አለ፡፡
በእረፍቴ ቀን ያየሁት “ከፍሎ ሟች” የተሰኘ ፊልም ከፍሎ ሟቾችን አሳየኝ፡፡ ውይ ሲያሳዝኑ! እንደው እንባዬ በማይረቡ ነገሮች ፈሶ አለቀላችሁ እንጂ ከፍሎ ሟቾቹ እያሰብኩ ብዙ ባነባሁ ነበር፡፡ ስለ ፊልሙ ላወራችሁ አይደለም፡፡ የፊልሙ ሀሳብ ዛሬ እኔ ላወራችሁ ከፈለኩት ርዕስ ጋር ስለገጠመ እንጂ፡፡የተሻለ ለማግኘት ቀርበው ስለሚጎልባቸው ወላጆችና ተማሪዎች፤ የተሻለ እናቅርብ ብለው ይብስ ስለሚያጎድሉት የግል ትምህርት ቤቶች እናውራ፡፡
እርግጥ ወላጆች ወደ ግሎቹ ትምህርት ቤቶች የሚያቀኑት በምርጫ ወደውና ፈቅደው ነበር፡፡አጀማመራቸውም ውድድር ነበረና መልካም ነበር፡፡ የዛሬ ገፅታቸውን መላበስ ከመጀመራቸው በፊት ትምህርት መስፋፋትና ተደራሽ እንዲሆን በማድረግም ለመንግሥትም ጥሩ እረፍት ሰጥተዋል ትምህርት ቤቶቹ:: እየዋለ እያደር መልካቸውን ቀይረው ትኩረታቸው የሚሰበስቡት ገንዘብና የሚያገኙት ጥቅም ላይ አዋሉት እንጂ፡፡
ውዶቼ ሰው መሥራት ከምንም በላይ ጥንቃቄን ይሻል፡፡ ሰው መፍጠር ትልቅ ሥራ ነው:: ህንፃ ተንጋዶ ቢሠራ ድጋይ ነውና አፍርስው መልሰው ይገነቡታል፡፡ መንገድ ተሠርቶ ቢበላሽ መልሶ ጠግነው ለአገልግሎት ያውሉታል፡፡ አፍርሰው ሊሠሩ የማይችሉት፤ ጠግነው ሊመልሱት የማይችሉት ሰው ሲሆንስ? አዎ ሰው ሲሆን ችግር ነው ውዶቼ፡፡ አያፈርሱት አይጠግኑት ነገር ሰው ነዋ፡፡ ምክንያቱም ስብዕና ወይም ሰው መሆን በራሱ ሂደት ነዋ አንዴ ከተገነባ የሰውዬው ዘመን ማብቂያ ድረስ የሚዘልቅ:: ሰው አገር አይደል? አገር መገንባት ከስር ነው፤ ሰው መፍጠር ከጅምር ነው፡፡ የተቃና ትውልድ የቀናን አገር ይፈጥራልና የሰው አዕምሮ ላይ የሚሠራ ሥራ ከሁሉ ቀዳሚው እና ትኩረት የሚሰጠው ነጥብ ነው፡፡
እኔ የምለው የግል ትምህርት ቤቶች ግን ወዴት እያመሩ ነው? ጉዞና መድረሻቸው አውቀውት ይሆን? ከሚሰጡት አገልግሎት በላይ ክፍያን የሚጠይቁ ከሚሰጡት በላይ የሚወስዱ ቀማኞች ሆነዋል፡፡ ከተማሪ ወላጅ በሰበብ አስባቡ እየነጠቁ ኪሳቸው እንደሞሉት ለወላጆች ቃል ገብተው ልጅህን በስነ ምግባር ኮትኩቼ አስተምሬና አብቅቼ ለወግ ለማዕረግ አደርስልሀለሁ ያሉት ቃል ቢያከብሩ ምን አለ? የሞሉት ኪሳቸው ያህል የተማሪዎቹን አዕምሮ በሀገር ፍቅር ስሜትና እውቀት ቢሞሉት?
ስለሚሰበስቡት ገንዘብ እንጂ ስለሚያስተምሩዋቸው ተማሪዎች ግድ የሌላቸው ትምህርት ቤቶቹ እንዳሻቸው ከተማሪ ወላጅ ያለ እቅድና ጊዜ ባሻቸው መልኩ የገንዘብ ጭማሪ ሲያደርጉ፣ ያለ ወላጅ ውይይትና ውሳኔ በራሳቸው ህጎችን አውጥተው ወላጅና ተማሪን ሲያስከነዱ፣ ሲፈልጉ የተከራዩትና የሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት አድራሻ ሲቀይሩ ብቻ በተማሪዎችና በተማሪ ወላጆች ላይ የኑሮን ጫና አክብደው ለራሳቸው ህይወትን ማቅለሉን ተያይዘውታል፡፡
ባህሉን አክባሪ፤ አገሩን አፍቃሪ፤ ቤተሰቡን ጧሪ፣ ለወገን መከታ የሚሆን ትውልድ እናፈራለን:: ለልጅዎ ወላጅ ሆነን ተንከባክበን አንፀን እናስረክባለን በሚል የተከሸኑ ቃላት የዓመቱ መጀመሪያና መጨረሻ ላይ በየመገናኛ ብዙሐኑ የሚጎሉት እነዚህ ትምህርት ቤቶች ተግባራቸው ከቃላቸው ተቃራን ሥራቸው ከኪዳናቸው የራቀ ሆኗል፡፡ እርግጥ አገራዊ ዜጋን ኮትኩቶ በማፍራት የተወደሱ መልካም ትውልድን በማነፅ የታወቁ የግል ትምህርት ቤቶች የሉም ለማለት አልደፍርም፡፡
እያወራሁ ያለሁት ስለ ብዙዎቹ ነው፡፡ እረግጥ ነው መልካም ነገር በርክቶ አይገኝም ስለ ግድፈታቸው በዝቶ የሚወራ ምክንያት የበዙት ስህትት ላይ መገኘታቸው ነው:: ለምዝገባ ብለው ከአቅም በላይ በየዓመቱ እንደ ችግኝ የሚያድገው ክፍያቸው የግቢያቸው ማህበረሰብ ጋር እንኳን ሳይደርስ የትምህርት ባለቤቶቹን ካዝና ብቻ የሚሞላ ነው፡፡
ተማሪዎቹን በማቅናት እውቀትን በማስጨበጥ ብዙ የሚለፉት የግል ትምህርት ቤት መምህራን የሰው ልጅ መብት በተከበረበት በዚህ ዘመን መብታቸው የተጣሱ ሆነዋል:: የትምህርት ቤት ባለቤቶቹ እንዳሻቸው የሚለዋውጡዋቸው፣ ወር ለማቆየት እንኳን የማትበቃ ክፍያ የመምህራኑ የሚገባቸውን አለማግኘት ማስረጃ ጥቂት ማሳያ በደሎች ናቸው::
በሰበብ አስባቡ በትምህርት ቤቱ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ የሚዘጋጅላቸው እነዚህ ትውልድ ቀራጭ መምህራን ለትምህርት ቤቱ አሰሪዎችና አለቆች ካላጎበደዱ ጥሩ ማስተማር አለማስተማራቸው ለነሱ ዋስትና አይሆንም፡፡ የልፋታቸውን ያህል እንኳን ሳያገኙ በምን መለኪያ የተማሪዎቹን ፍላጎት ማሳካት ይችላሉ፡፡ የትምህርት ቤቶቹ እዚህ ደረጃ መድረስ የተቆጣጣሪው አካል ለዘብተኝነት ማሳያ ነው፡፡
ትምህርት ቤቶቹ የሚሰሩት ታላቅ የሆነው የሰው ፍጡርን ነው፡፡ ትምህርት ቤቶቹ የሚቀርፁት ነገ ሀገር ተረካቢውን ትውለድ ነው፡፡ የትምህርት ቤቶቹ ዝንጉነት በዚህ ከቀጠለ የሚቀጥለውን ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል ለመተንበይ ነብይ መሆን አይሻም፡፡ የሚያመርቱት ፈር የለቀቀ ትውልድ የሚገነቡት ግድ የለሽ ዜጋ የነገን መቅናት የማይወድ የአገር መለወጥ የማያሳስበው መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡
አገር ማለት ሰው ነው! እያልኩ አላደርቅህም ወዳጄ ምክንያቱም ኗሪው ከሌለ መኖሪያው ባዶ ነውና:: ተማሪን ማነፅ አገር መገንባት አገርን ማነፅ ነው:: ነገ የሚረከብና ወደሌላ የሚያሻገረው ትውልድ የዛሬ መዋያው ትኩረት ነውና፡፡ ያደጉት አገራ የመጀመሪያ ሥራቸው ሁሌም ትውልድ መገንባት ጠንካራ መሰረት ላይ ማኖር ነው ግብና ሥራቸው:: ያኔ ዜጋቸው አገሩን የሚጠቅመውና የሚጎዳውን ይለያል፡፡ ተኮትኩቶ ያደገው በሥነ ምግባር የተቀረፀው በመልካም ስብዕና ነውና የሥራቸው ውጤት ፍሬው ያማረ ይሆናል፡፡
ትምህርት ቤቶቻችን ያለባቸው ዘርፈ ብዙ ችግር ማያ መስታወት ከትምህርት ቤቶቹ እየወጡ ማህበረሰቡን የሚቀላቀሉ ተማሪዎቻቸው ናቸው:: እነዚህ ተማሪዎች በእውቀትና በመልካም ሥነ ምግባር ታንፀው ከወጡ ለማህበረሰቡ ጠቃሚ የሆነ ለራሳቸው ለተማሪዎቹም ስኬታማ ውጤት ማስመዝገባቸው አይቀሬ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ በተለየ መልኩ ትምህርት ቤቶቹ የሚቀርፁዋቸውና ለፈለገው መልካም ግብና ውጤት ከማብቃት ይልቅ የሚያገኙት ትርፍ ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው ትውልድን የሚገሉ ብሎም አገርን የሚያከስሙ ስግብግቦች ሲሆኑ ውጤቱ የከፋ ነው፡፡
በትምህርት ቤቶቹ ልኬታ ያለፈ ተግባር የተማሪ ወላጆችና ተማሪዎች ተማረው ሲናገሩ ይሰማል:: ሰሚ ማጣት ለችግሩ አለሁ ባይ አካል መጥፋትና ቢኖርም ሙከራዎች እንጂ የተሳካ ማስተካከያ የማድረግ አቅሙ ውስን መሆን ዛሬ ላይ የችግሮቹ ዋንኛ መዳረሻ የተማሪዎች ወላጆችና ቤተሰብ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ውዶቼ ሰው መሥራት ከምንም በላይ ጥንቃቄን ይሻል፡፡ ሰው መፍጠር ትልቅ ሥራ ነው:: ህንፃ ተንጋዶ ቢሠራ ድጋይ ነውና አፍርስው መልሰው ይገነቡታል፡፡ መንገድ ተሠርቶ ቢበላሽ መልሶ ጠግነው ለአገልግሎት ያውሉታል፡፡ አፍርሰው ሊሠሩ የማይችሉት፤ ጠግነው ሊመልሱት የማይችሉት ሰው ሲሆንስ? አዎ ሰው ሲሆን ችግር ነው፡፡
አያፈርሱት አይጠግኑት ነገሩ ሰው ነዋ፡፡ ምክንያቱም ስብዕና ወይም ሰው መሆን በራሱ ሂደት ነው፡፡ ከጅምር እስከ እደገት የሚገሩት አንዴ ከተገነባ ደግሞ የሰውዬው ዘመን ማብቂያ ድረስ የሚዘልቅ፡፡ ሰው አገር አይደል? አገር መገንባት ከስር ነው፤ ሰው መፍጠር ከጅምር ነው፡፡ የተቃና ትውልድ የቀናን አገር ይፈጥራልና የሰው አዕምሮ ላይ የሚሠራ ሥራ ከሁሉ ቀዳሚው እና ትኩረት የሚሰጠው ነጥብ ሊሆን ይገባል! ቸር ያሰማን፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ 12/2011
ተገኝ ብሩ