የሰው ልጅ የአዕምሮው ምጥቀት መለኪያው የስልጣኔው ጥግ ማሳያው ሳይንስ ነው፡፡ በሳይንስ ቀመር እገዛ የሚሠሩ ምርምሮች፣ አዳዲስ ግኝቶችና ፈጠራዎች በየ ዕለቱ ህይወትን በማቅለልና የሰው ልጅን የአኗኗር ሂደትን በመቀየር ላይ ይገኛሉ፡፡ የፈጠራ ወይም የምርምር ሥራ ሠርተው ለዓለም ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሰዎች ማግኘት የተለመደ ነው፡፡ ከዚህ በተለየ ደግሞ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች በአንድ ግለሰብ ተፈጥሮ ሲገኝ ማስገረሙ አይቀሬ ነው::
ዛሬ በሳይንስ አምዳችን ዘርፈ ብዙ የምርምርና የፈጠራ ውጤቶችን ያበረከቱ ትጉህ የፈጠራ ባለሙያና መምህር አነጋግርን::
በኦሮሚያ ክልል ኤሊባቦር ዞን ዳሪሞ ወራዳ ዳሪሞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ መምህር ተመራማሪና የፈጠራ ባለሙያ ናቸው መምህር ገረሙ አብዲሳ፡፡ በፈጠራ ሥራ የተዋጣላቸው ልዩ ክህሎተኛው መምህርና የፈጠራ ባሙያው ለተማሪዎቻቸው የቀለም ትምህርትን ከማስተማርና በሥነ ምግባር ኮትኩቶ ከማሳደግ ባለፈ ፈጠራን የተካኑ ለሀገራቸው የጠለቀ ፍቅር ያላቸውና ለለውጥዋ የሚታትሩ ታላቅ ህልም ያላቸው ተመራማሪ ናቸው፡፡
መምህርና የፈጠራ ሥራ ባለሙያው ፔሬስኮፕ፣ ማይሮስኮፕ፣ ቀላል የቤት ውስጥ ስልክ፣ የቡና ማሽን፣ ባለጉዳይና ጉዳይ ፈፃሚን ለማገናኘትና ሥራን ለማቀላጠፍ የሚረዳ መሣሪያ፣ በኤሌትሪክ የሚሠራ ወንፊት፣ የባጃጅ የትራክተርና የመኪና ሞዴል በምርምራቸው በመፍጠር ተግባራዊ አድርገዋል፡፡
የፈጠራ ሥራው መነሻ
ከተማሪዎቻቸው እጅግ በቅርበት የሚውሉት የፈጠራ ባለሙያው መምህር ገረመው ስለ ፈጠራ ሥራ አብዝተው በሬዲዮ የሚሰሙት ተማሪዎቻቸው ለፈጠራ ሥራዎቻቸው መነሻ ናቸው፡፡ ተማሪዎቹ ስለ ፈጠራ ሥራ ምንነት ተደጋጋሚ ጥያቄ ለመምህሩ ማቅረባቸውና እርሳቸውም ለፈጠራ ሥራ ልዩ ቦታ መስጠታቸው ዛሬ ላይ ለደረሱበት መነሻ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡
ለተማሪዎቻቸው ስለ ፈጠራ ሥራ ለማስረዳት ጥናትና ምርምር ማድረግ ጀመሩ ያ ጥናትና ምርምር ደግሞ ተግባራዊ ለመድረግ ሁሌም መሞከርና አዳዲስ ነገሮችን ማከል ያለመሰልቸት መጣርን አዘወተሩ የሚከውኑት ተግባር ሆነ፡፡ በዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ የሠሩት የባጃጅ ሞዴል ከንድፈ ሐሳብ ጀምረው ለተማሪዎቻቸው ማሳየት መቻላቸው እና ተማሪዎቻቸው የሰጡዋቸው መልካም አስተያየቶች ይበልጥ ጠንክረው እንዲሠሩ ምክንያት ሆናቸው፡፡ በመጨረሻም ዛሬ ድረስ የፈጠሩዋቸው የተለያዩ ማሽንና መገልገያ መሣሪያዎች ለማበርከት በቁ፡፡ ጥረት ውጤት ያስገኛልና ከተደጋጋሚ ልፋትና ጥረት በኋላ መምህርና ተመራማሪው አቶ ገረመው ምርምራቸው ትልቅ ውጤት አስገኘላቸው፡፡
የፈጠራ ሥራው አሁን ያለበት ደረጃ
በአሁኑ ወቅት በትምህርት ቤትና በራሳቸው መኖሪያ ቤት ለአገልግሎት በመዋል ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህ የፈጠራ ሥራዎች ከዚህ በሰፋ መልኩ ለማህበረሰቡ ለማቅረብና በስፋት ሠርቶ ለማከፋፈል ያለባቸው የገንዘብ አቅም ውስን መሆን በምክንያት ይጠቅሳሉ መምህሩ:: አሁን ድረስ የፈጠሩዋቸው ማሽንና መገልገያ መሣሪያዎች በተሻለ መልኩ ጥቅም ላይ ማዋል እንዲቻል የሚመለከተው አካል ድጋፍና ትብብር አጥብቀው ጠይቀዋል፡፡
በፈጠራ ሥራው የተገኘ እውቅና ሽልማት
ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እውቅናና የ2011 ዓ.ም የወርቅ ሜዳሊያና በወረዳ በዞንና በክልል ደረጃ የተለያዩ ሜዳሊያዎች የገንዘብ ሽልማት፣ ከተለያዩ ተቋማት እውቅናና የሜዳሊያ ሽልማት በፈጠራ ሥራቸው አግኝተዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን የፈጠራ ሥራ መብት ባለቤትነት በማረጋገጥ ሂደትና ከሥራዎቹ ማግኘት የሚገባን ጥቅም ለመቋደስ ያሉበት ቦታ ከዋና ከተማው መራቅና እነዚህ ሂደቶችን ለማለፍ የገንዘብ አቅም ውስንነት ወደፊት እንዳይራመዱ አድርጓቸዋል፡፡
በፈጠራና በምርምር ሥራው ከባዱ ፈተና
እኚህ ብዙ ፈጠራዎችን ማበርከት የቻሉት ታታሪ መምህር ፈጠራውን ሲያካሂዱና የምርምር ሥራው ለማከናወን ሲነሱን ከጅምር እስከ ዛሬ አልጋ ባልጋ ሆኖላቸው አልነበረም:: ይልቁንም የምርምር ሥራ ትዕግስትና ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረግ የሚጠይቅ ስለነበር ሳይሰለቹ መትጋትና በምርምር ሥራዎቹ የሚገጥሙ የበዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ማለፍ ከፈጠራው ባለሙያ የሚበቁ ነበሩ፡፡ ያሉበት አካባቢ ከከተማ መራቅ የመሥሪያ ቁሳቁስና ቦታ ችግር የገንዘብ እጥረትና ለምርምርና ፈጠራ ሥራው ወቅት የገጠማቸው ፈተና መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ዛሬ ድረስ ለምርምር ሥራቸው ተብሎ የሚለቀቅላቸው የማበረታቻና የምርምር ሥራ ማስኬጃ ገንዘብ በሳይንሱ ዘርፍ የሚሠሩ መሥሪያ ቤቶች በሚፈልጉት ሰዓት ማግኘት ያለመቻላቸው የተሻለ ውጤት ላይ እንዳይደርሱ አድርጓቸዋል፡፡
የፈጠራና ምርምር ባለሙያው በሀገር ደረጃ አሁን አሁን ለምርምር ሥራ የሚሠጠው ትኩርት በጣም ብዙ ይቀረዋል ባይ ናቸው፡፡ ዘርፉ ችግር ፈቺ እነደመሆኑና ለኢኮኖሚው ማበርከት የሚችለውን ታላቅ ጠቀሜታን በሀገር ደረጃ ለመቋደስ ለመስኩ ትኩረት መስጠትና ተገቢውን ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡
በተለይም የፈጠራ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች ያለባቸውን የእውቀትና ክህሎት ክፍተት፣ የገንዘብ እና የፈጠራ ሥራ ማድረጊያ ቦታና ቁሳቁስ እጥረት ዋንኛ ችግር መሆኑን የሚናገሩት የፈጠራ ባለሙያ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ክትትልና ድጋፍ ሊያደርላቸው ይገባል ይላሉ፡፡ የማህበረሰቡ ችግር ለመቅረፍና ሀገራዊ የሳይንስ ግኝትና ፈጠራን ለማበረታታት የሚደረገው ጥረት ልዩ ትኩረት እንደሚያሻውም ይናገራሉ፡፡
የተመራማሪው የወደፊት ዕቅድ
የፈጠራ ባለሙያው ወደ ፊት ብዙ የፈጠራ ሥራ የመሥራት ዕቅድ ሰንቀዋል፡፡ ለዚህም የሚረዳቸው ምርምሮችን በማድረግ ላይ ሲሆኑ በተለይ ከከተማ ይልቅ የገጠሩን ህብረተሰብ ህይወት ሊለውጡ የሚችሉ የፈጠራ ሥራዎችን የመሥራት ዕቅድና ለዚህም ጥረት ማድረግ መጀመራቸው ይገልፃሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የማህበረሰቡ ችግር በመመርመር የተሻሉ የፈጠራ ውጤቶች በማበርከት ወደፊት በመስኩ የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከት ህልማቸው ነው፡፡
ሀገራዊ ችግርንና ማህበረሰባዊ መሰናክሎችን የሚቀርፉ የፈጠራ ሥራዎች በሀገር ደረጃ ትኩረት ተሰቶዋቸው እየተሰራባቸው አለመሆኑንና አሁን ያለውም የፈጠራና የምርምር በስፋት ሊሰራበት እንደሚገባ ይህም ከሆነ የፈጠራ ባለሙያዎች ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠርላቸው ይጠቁማሉ::
የፈጠራ ባለሙያውና መምህሩ መልዕክት
የፈጠራና የምርምር ሥራ ተደጋጋሚ ጥረት ትዕግስትና ትጋት የሚያስፈልገው ነው፡፡ ወደ ፈጠራና ምርምር ሥራ የሚገቡ አዳዲስ የፈጠራ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች ተስፋ ሳይቆርጡ መትጋትና መልካም ውጤት በመመኘት ተደጋጋሚ ጥረት ማድረግ ይገባል::
በተለይ ለጀማሪ የፈጠራ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች ታላቅዋን ሀገራቸውን እንዲያስቡና በምርምር ሥራቸው ማህበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸውን ምክረ ሀሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡ የፈጠራ ሥራዎቻቸው ከውጤት ለማድረስና ማህበራዊ ጠቀሜታውን ለማረጋገጥ በሚያደርጉት ሂደት የገጠማቸውን ችግር በማሳያነት በማንሳት ተመራማሪዎች በሞራልና በተሻለ መንፈስ ሥራቸውን መሥራት የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታ ወሳኝ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ በትዕግስት የተፈለገ ደረጃ ላይ መድረስ የሚያስችል ወኔና ውስጣዊ ፍላት መጎናፀፍ በፈጠራ ሥራ የሚጠይቅ ዋሳኙ ሃላፊነት መሆኑን ያስገነዝባሉ፡፡
የፈጠራና ምርምር ሥራዎች በተፈለገው መልክ ተግባር ላይ ውለው ጥቅም እንዲሰጡ ለምርምር ሥራዎቹ እውቅ በመስጠት ማበረታት እንዲሁም ድጋፍና ክትትል ከማድረግ በተጨማሪ የምርምር ሥራ ምቹ የሚያደርጉ ሁኔታዎች በመንግሥት ሊመቻቹ እንደሚገባና አሁን በሳይንስ ዘርፍ እየታዩ ያሉ ለውጦች ተግባራዊ የሚሆኑበትና ከዚያም ላይ እንደ ሀገር የሚገኘውን ጥቅም ለማስቀጠል የሚሠሩ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡
እኛም የፈጠራና ምርምር ሥራ ሀገራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የፈጠራ ባለሙያዎችን በመደገፍ ለምርምርና ፈጠራ ሥራቸው ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ጥቅም ላይ የሚውልበት መንገድ ሊመቻች ይገባል እንላለን፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ 12/2011
ተገኝ ብሩ