የዳበረ የዲፕሎማሲ ባሕል ያላት ኢትዮጵያ በለውጡ ዘመንም ይህንኑ በማስቀጠል ዘርፈ ብዙ ስኬት እያስመዘገበች እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ:: ኢትዮጵያ ቀደምት ከሚባሉና የረጅም ዘመን ዲፕሎማሲያዊ ታሪክ ካላቸው አገራት መካከል አንዷ ነች:: በየዘመኑ የነበሯት መሪዎችም የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ የየበኩላቸውን ጥረት ማድረጋቸውንም የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ:: በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ አካሔድን በመከተል ሕዝቧን ከዲፕሎማሲ ፍሬ ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ትገኛለች::
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ የተጓዘችበት የዲፕሎማሲ ሒደት ምን ይመስላል? ያስገኘውስ ውጤት እንዴት ይገለጻል? ስንል የዘርፉን ምሁራን ጠይቀናል፤ ምሁራኑ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ሲካሔድ የነበረው የዲፕሎማሲው ጥረት የዳበረውን የዲፕሎማሲ ባሕል ያስቀጠለ ሲሆን፣ በዚህም ዘርፈ ብዙ ውጤቶች የተመዘገቡበት እንደሆነ ያስረዳሉ::
ካነጋገርናቸው ምሁራን መካከል አንዱ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በማኅበረሰብ ሳይንስ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑ ዓለምሰገድ ደበሌ (ዶ/ር) ናቸው:: የኢትዮጵን የመንግስት ግንኙነት ከአገራት ጋር ያለውን የዲፕሎማሲ ሒደቱን ስናይ አጠቃላይ ኢትዮጵያ የዳበረ የዲፕሎማሲ ባሕል ወይም ልምድ አላት ማለት እንችላለን ይላሉ:: ያም ሆኖ ግን የኢትዮጵያ ዘመናዊ ዲፕሎማሲ የተጠናከረው በ20ኛ ክፍለ ዘመን አካባቢ ነው:: በ20ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ ኢትዮጵያ የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል መሆን የዲፕሎማሲ ውጤት እንደሆነም ያመለክታሉ::
እርሳቸው አንደሚሉት፤ በወቅቱ የጣሊያንን ወረራ አቤቱታን ለማቅረብም የተሞከረበት ነበር፤ እንደዚያ እያለ የቀድሞው አጠራሩ የአፍሪካ አንድነት/የአሁኑ አፍሪካ ኅብረት የተመሰረተው ኢትዮጵያ በተጫወተችው ዲፕሎማሲ ጥረት ነው:: በኢትዮጵያ እንደየዘመኑ በነበሩት መሪዎች አተያይ የዲፕሎማሲውም አካሔድ ይለያያል::
በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን የነበረው ዲፕሎማሲያዊ አካሔድ ከደርግ ዘመን፣ የደርግ ዘመኑ ደግሞ ከኢሕአዴግ ይለያያል:: የመለየቱም ምስጢር ከርዕዮት ዓለም መቀየር ጋር ተያይዞ የሚተገበር በመሆኑ ነው:: ስለዚህም ዲፕሎማሲው እየተከተለ የሚሔደው ያንን ነው::
ለምሳሌ በደርግ ዘመን መንግሥት ሲያጋድል የነበረው ወደራሽያ ነው፤ እንዲሁም የራሽያ አይነት ስልት ካላቸው አገሮች ጋር ዲፕሎማሲው ሲደረግ እንደነበር የሚታወስ ነው:: በኢሕአዴግ ጊዜም እንደዚያው ግንኙነቱ ቀጥሎ ከእነ አሜሪካ ጋር እና ከሌሎች የአውሮፓ አገራት ጋር ግንኙነቱን ሲያደርግ ነበር ይላሉ::
የቀድሞው ዲፕሎማት ተሻለ ሰብሮ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል የነበረው የዲፕሎማሲ ሥራ ካስገኘው ስኬት ውስጥ አንዱ የቀድሞው አፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ አፍሪካ ኅብረት መቀመጫውን አዲስ አበባ ሊያደርግ የቻለው በኢትዮጵያ ተጽዕኖ ፈጣሪነትና በተገኘው ዲፕሎማሲያዊ አካሔድ ነው ሲሉ ተሻለ (ዶ/ር)፣ የዓለምሰገድ (ዶ/ር)ን ሐሳብ ያጎለብታሉ::
እርሳቸው እንደሚሉት፤ እውነት ለመናገር በአንድ ወቅት በዲፕሎማሲው ረገድ ከፍታም፤ ዝቅታም ታይቷል:: እንዲህም ሲባል ፈተናው ከበድ ያለበት ወቅት እንደነበር ለመጥቀስ ነው:: ይህ አይነቱ ፈተና ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም አገሮች የሚያጋጥም ክስተት ነው:: እንዲያም ሆኖ ትልቁ ስኬት ከዚያ ውስጥ በመውጣት ዛሬ ላይ መድረስ መቻል ሲሆን፣ ይህም የአሸናፊነት ምልክት ነው:: በወቅቱ በኢትዮጵያ ላይ ተጠራርተውና ተደራርበው የመጡትን የጠላትን በትርና ምት በመቋቋም የተገኙት ውጤቶች ሊጠቀስ የሚችል ስኬት ነው::
ኢትዮጵያ እንደ አገር፣ እንደመንግሥትና ሕዝብ እንቅልፍ የላትም፤ ተግዳሮት ይበዛባታል:: አንደኛ በዓባይ ግድብ ሲያጋጥመን የነበነረው ግብግብ ሲሆን፣ ይህ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም:: እሱ ሌላኛው የውጫሌ ውል ሆኖብን የሰነበተ ጉዳይ ነበር ይላሉ:: የአውሮፓን ተጽዕኖ ተቋቁመው አገራችንን ከቅኝ ግዛት ነጻ ያደረገ ያ ትውልድ የሰራውን ያህል ተጋድልዎ በመስራት ግሩም በሆነ ዲፕሎማሲያዊ አካሔድ ከዓባይ ግድብ ጋር የነበረውን ፈተና አልፈነዋል ማለት ይቻላል:: ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ በመሰራቱም ዛሬ የዓባይ ግድብ መጠናቀቅን ተከትሎ ሪቫን ሊቆረጥ ተቃርበልና፤ ይህ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስኬት ነው ሲሉ ያስረዳሉ::
ተሻለ (ዶ/ር)፣ አንዳንዶች ኢትዮጵያን ሁሌም አጣብቂኝ ውስጥ ለመክተት በብዙ ጥረት ይደረጋል፤ አንዱም በአገራችን የተካሔደው የሰሜኑ ጦርነት ነው ይላሉ:: መንግስት ወደዚህ ጦርነት የገባው አስገዳጅ በሆነ ሁኔታ ነው:: ያለፈው የሁለት ዓመቱ ጦርነት በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ግልጽ ነው:: ጥቂት የማይባሉ መንግስታትም በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር ጥረት ማድረጋቸው አይዘነጋም:: ተግዳሮት ገጥሞን የነበረው በዲፕሎማሲያችን ድክመት ሳይሆን ተቀናቃኝ የሆነው አካል ዓለም አቀፍ ይዘት ባለው አካሔድ በመረባረቡ እንደሆኑ ዲፕሎማቱ ያመለክታሉ::
አክለውም ይህ የሰሜኑ ጦርነት ፈተና ግን በፈተናነቱ እንዳይዘልቅ በፕሪቶሪያ ስምምነት ጉዳዩ ተጠናቆ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ፊቷን ወደልማት መመለስ መቻሏ ሌላኛው ስኬት ነው:: በሌላ በኩል ከግብጽ ጋር ያለው ግብግብ ምንም እንኳ እልህ አስጨራሽ የሆነ ቢሆንም ከመጋረጃ ጀርባ በተደረገው ዲፕሎማሲ ጥረትና ጥንቃቄ ኢትዮጵያ ውጤታማ መሆን እንደቻለችም ነው የሚናገሩት:: ውጤቱን ሊያመጣ የቻለው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ አመራርና የዲፕሎማሲ ብቃት ነውና መንግስታችንና ሕዝባችን የሚፈልገውን ነገር ማድረግ ችሏል:: ይህ ቀላል ሥራ አይደለም ብለዋል::
ከለውጡ በኋላ እና በለውጡ ጊዜ ዲፕሎማሲው ቀጥሏል የሚሉት ዓለምሰገድ (ዶ/ር)፣ አንዳንድ አዳዲስና ለየት ያሉ እሳቤዎችም እየተጨመሩበት ያሉ መሆኑን ተናግረዋል:: እንደ እርሳቸው አባባል፤ ለውጡ ከመጣ በኋላ ለየት የሚለው ዲፕሎማሲ የሚባለው ለምሳሌ ከአፍሪካ ቢጀመር ከአፍሪካ ቀንድ አገራት ጋር እርቅ ማውረድና ሰላም መፍጠር የሚል ነው:: ለአብነት ያህል ለብዙ ዘመን ተቀያይመው የነበሩ የኢትዮጵያና_ኤርትራ ግንኙነት ከዓመታት በፊት ወደእርቅ መምጣትን ማስታወስ ይቻላል::
ሌላው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ላይ ትኩረት ተደርጎበታል ያሉት መምህሩ፣ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ላይ ከአፍሪካ አገራት በተለይ ከምስራቅ አፍሪካ አገር እንዲሁም ከአፍሪካ ቀንድ አገራት በትብብር እንስራ የሚል አንድምታ ያለው ነው ብለዋል፤ ከአውሮፓ አገራት ጋርም እንዲሁ ግንኙነት እንደነበር ጠቅሰው፤ በእርግጥ ከአውሮፓ አገራት ጋር ያለን ግንኙነት አንዳንዴ ወጣ ገባ የሚል እንደሆነ አመልክተዋል:: እንዲህ ለማለታቸው አንዱ ምክንያት በተለይ በሰሜኑ ጦርነት ጊዜ የነበረው የዲፕሎማሲያዊ አካሔድ በተለይ ብቅ ጥልቅ ማለቱን ተከትለው ነው:: ነገር ግን ካለፈው ዓመት ጀምሮ ዲፕሎማሲው የተሻሻለበት ሁኔታ የታየበት ነው ብለዋል::
እንደ ዓለምሰገድ ገለጻ፤ በለውጡ ጊዜ እየታየ ያለው የዲፕሎማሲው ጥረት የዳበረውን የዲፕሎማሲ ባሕል የሚያሳይ ነው:: ይህ ዲፕሎማሲ የሚጠቅመን ከአገራት ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር፣ የኢትዮጵያን ገጽታ ለማጎልበት፣ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ፣ የንግድ ግንኙነቶችን ለማካሔድ፣ አገራዊ ፍላጎታችንን አስጠብቀን ለመጓዝ ነው:: በአሁኑ ወቅትም እየተከናወነ ያለውም በዚሁ መልኩ ነው::
ልክ የሰሜኑ ጦርነት ኢትዮጵያ ባደረገችው ዲፕሎማሲያዊ አካሔድ በፕሪቶሪያው ስምምነት ውጤታማ ማድረግ እንደተቻለ ሁሉ፤ ብዙዎች የሚመኙት ግን ደግሞ ያልተሳካላቸውን የብሪክስ አባልነት ጉዳይ ኢትዮጵያ ልታሳካው መቻሏ በዲፕሎማሲው ረገድ ሌላኛው ትልቁ ስኬት እንደሆነ ገልጸዋል::
እርሳቸው እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት የብሪክስ አባል መሆን ብቻ አይደለም፤ ከተለያዩ አገራት ጋር፣ ከአረብ ኢምሬቶች ጋር እንዲሁም ከቱርክም ጋር ጥሩ የሆነ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ፈጥራለች:: ወደ ሩቅ ምስራቅ ቻይና ስንሔድ ደግሞ እንዲሁ በፊት የተጀመረ የዲፕሎማሲ መሰረት እንደተጠበቀ ሆኖ እሱ ወደ ቋሚ ትብብር ያደገ መሆኑ የማይዘነጋ ነው:: ቻይናውያን በኢትዮጵያ በብዙ ፕሮጀክቶች የሚሳተፉ ሲሆኑ፣ ሥራዎቻቸውንም በሰዓቱ በማጠናቀቅ የሚታወቁ መሆናቸው ያለውን መልካም ግንኙነት የሚያመላክት ነው:: ኢንቨስትመንቶችን ወደ አገራችን በመሳብ በኩል ውጤት እንዳለም ጠቅሰው፤ ለአብነት ያህል የተባበሩት አረብ ኢምሬቶችም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ትብብራቸውን እያጠናከሩ እንደሆነ ተናግረዋል::
ከሳምንታት በፊት በአንካራ የተደረገው የኢትዮጵያና የሶማሊያ ሁለትዮሽ ስምምነት በኢትዮጵያ ላይ ሊደረግ የታሰበውን ከበባ ያጨናገፈ ነው የሚሉት ደግሞ ተሻለ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ ይህ የዲፕሎማሲ ውጤት ነው ማለት ይቻላል ብለዋል:: ከዚህም በላይ ሰላማዊ አየር መተንፈስ የሚያስችልም ነው ብዬ አስባለሁ በማለት አስረድተዋል:: በእርግጥ እንዲህ ሲባል ብዙ ጥንቃቄዎች እንደሚያስፈልጉ ከግንዛቤ በማስገባት ነው፤ የማያስተኛ ፈተናም እንዳለ ሊታወቅ ይገባል:: ምክንያቱም ሁኔታዎች ሲስተዋሉ ተኝተው የሚያሳድሩ አይነት አእንዳይደሉ ገልጸዋል::
እርሳቸው እንደሚሉት ከሆነ፤ እንዲያም ሆኖ ግን የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ጥርስ ያለው አንበሳ ነው ማለት ይቻላል:: ኢትዮጵያ በአንበሳነቷ ትታወቃለች:: እንዲህ ሲባል በባዶ መፎከርና ማቅራራት ሳይሆን በተግባር ተፈትኖ የተረጋገጠ በመሆኑ ነው:: ለዚህ አንበሳነት ሌት ተቀን ለተጉ አካላትም ክብር ይገባቸዋል:: ከዚህም በላይ መስራት ደግሞ ይቻላል:: አገራዊ እድገታችንንና ለውጣችንን ብቻ ሳይሆን አሕጉራዊ ተሳትፏችንም ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችል አምናለሁ:: የትኛውንም ጉዳይ በአገር አቀፍ ደረጃ፣ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ መደረኮች ላይ በመግለጽም ሆነ በማሳመን ኢትዮጵያ ዛሬም ፊተኛው መስመር ላይ እንዳላች ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል:: ስለዚህ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከአገር አልፎ ለቀጣናውም ሆነ ለአህጉራችን የሚተርፍ መሆኑ እውን ነው::
ተሻለ (ዶ/ር) በጥቅሉ እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ረገድ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ስኬታማ ከሆነችባቸው አንዱ የዓባይ ግድብ ነው፤ ግድቡ ዛሬ ላይ መድረሱ ታላቅ የዲፕሎማሲ ውጤት ነው:: የዲፕሎማሲ ውጤት ነው ሲባል በእርግጥ የአመራሩ፣ የሕዝቡም ጭምር መሆኑ ግልጽ ነው:: ነገር ግን ግብጾች የዓባይ ግድብን በተመለከተ በጣም ብዙ ጊዜ በጽጥታው ምክር ቤት አጀንዳ ያስያዙበት ጉዳይ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በኩል በድል ሊጠናቀቅ በመብቃቱ እጅግ የሚያስደንቅ ነው ማለት ይቻላል:: ሁለተኛው የዲፕሎማሲ ድል ነው ብለው የሚገልጹት የሰሜኑ ጦርነት በሰላም መፍታት የተቻለበትን ሒደት ነው:: ሶስተኛው የዲፕሎማሲ ድል ብዙዎች የሚፈልጉት ነገር ግን ያልተሳካላቸው የብሪክስ አባልነታችን ጉዳይ ነው:: አራተኛው ደግሞ የግብጽንና መሰሎቿን ከበባ ለማፍረስ የተደረገው ሙከራ ሲሆን፣ ይኸውም የአንካራው ስምምነት ነው:: አምስተኛው ደግሞ ከቀይ ባሕር ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ በኩል የቀረበው ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ እውቅና እያገኘ የመምጣቱ ምስጢር የዲፕሎማሲ ሥራ ውጤት ነው:: ለአብነት ያህል በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ብቅ ብለው የነበሩ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት በዚህ ጉዳይ ለኢትዮጵያ የሰጡት ምላሽ መልካም የሚባል ነው::
ይህን የቀይ ባሕር ጉዳይ ኢትዮጵያ ባነሳችብት ወቅት ጎረቤት አገራትን ጨምሮ ሌሎች በምን ያህል ርቀት ጉዳዩን በአሉታዊ ጎኑ ሲያራግቡት እንደነበር የሚታወስ ነው:: የጠቅላይ ሚኒስትራችን ርዕይ የሆነው የባሕር በር ጥያቄ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙዎችን አሸብሮ እንደነበርም የሚታወቅ ነው:: ነገር ግን ይህ ጉዳይ በተሰራው ዲፕሎማሲ እያደር ጋብ ብሎ ሲሞግቱን የነበሩ አካላት ሐሳባቸው እየተሸረሸረ የመጣበቱን ሁኔታ ማስተዋል ችለናል:: በጥቅሉ ያለፉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲዊ አካሔድ ጠንካራና ውጤታማ ነው::
ልክ እንደ ተሻለ (ዶ/ር) ሁሉ ዓለምሰገድ (ዶ/ር)፣ ከሰሞኑ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ሁለቴ ብቅ የማለታቸው ነገር የዲፕሎማሲ ጥረት ውጤት ነው ይላሉ:: ፈረንሳውያንም እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት እያደረጉ የሚገኙ ናቸው:: ከኢኮኖሚ ትብብር በተጨማሪ የባሕል ትስስሩን የማጠናከር ነገር ይታያል:: ይህ ከበፊቱም ጀምሮ ያለ ሲሆን፣ ለምሳሌ ትምህርት ቤቶችን በማቋቋም፣ የጥናት ማዕከልንም በማቋቋም ረገድ ግንኙነታቸው የጎለበተ ነው ማለት ይቻላል:: ዛሬም የሚታየው ነገር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ ሳይቋረጥ ቀጥሎ መሄዱን ነው ብለዋል::
ሌላው የአፍሪካ ኅብረት ኢትዮጵያ ውስጥ መቆየቱ በራሱ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ አካሔድ መሆኑን የሚያሳይ ነው:: ምክንያቱም የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይሆን ከዚህ ቀደምም ቢሆን ብዙ ማንገራገር እንደነበር የሚታወቅ ነው:: ዛሬ ያንን አስቀጥሎ መቆየቱ በራሱ አንድ ትልቅ ስኬት ነው ሊባል እንደሚችል ተናግረዋል::
የሰሜኑ ጦርነት ወደተኩስ አቁም መጥቶ ስምምነት ላይ እንዲደርስ እና መግባባት እንዲፈጠር መደረጉ ትልቅ ነገር ነው ሲሉ እንደ ተሻለ (ዶ/ር) ሁሉ ይናገራሉ:: የፕሪቶሪያው ስምምነት የዲፕሎማሲ ውጤት እንደሆነም በመግለጽ የእርሳቸውን ሐሳብ ይጋራሉ:: ብሪክስን መቀላቀልም እንደ አንድ አዲስ ነገር ማየት የሚቻል ሲሆን፣ ይህ ኢትዮጵያ ብሪክስን የመቀላቀል ጉዳይ የምዕራባውያንንና የአውሮፓውያንን ተጽዕኖ መቀነስ የሚያስችልም ጭምር ነው ይላሉ::
እንደ ዓለምሰገድ (ዶ/ር) ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በቀጣናዊ ትስስር ረገድ ስትታይ በኢጋድ ያላት ሚና የሚጠቀስ ነው:: በአብሮነት የመስራት መርሁም እንደ አንድ መልካም ነገር ሊታይ የሚችል ነው::
ምሁራኑ እንዳሉት ከሆነ፤ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ውጤታማ ናት፤ በቀጣይ ብሔራዊ ጥቅማችንን አስጠብቀን ከጎረቤቶቻችን ጋርም ሆነ ከሌሎች ጋር የጀመርናቸውን ዲፕሎማሲያዊ አካሔዶች አጠናክሮ መሔድ ያስፈልጋል:: ዲፕሎማሲያችንን ሊጎዱ የሚችሉ እንደ ሰላም መደፍረስ አይነት ችግሮቻችንን እየፈታን መሔድ ይጠበቅብናል:: የውስጥ ችግሮችን ለመፍታት መጣሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ከውጭም በኩል ያለውንም መልካም ነገር አጠናክሮ ማስቀጠሉ ተገቢ ነው::
ለምሳሌ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልንደመጥ በምንችልባቸው መድረኮች ሁሉ መስራትና በተለይ ከግብጽ ጋር ያለንን ሁኔታ እውነታውን ለማሳወቅ መጣር ያስፈልጋል:: የተጀመሩ እንደተጠበቁ ሆነው ከአውሮፓ ኅብረት አገራት መሃል በእነሱም በመጠቀም የተሻለ የዲፕሎማሲ ውጤት እንዲገኝበት ማድረግ፤ በተለይ ኢንቨስትመንትን፣ ትብብርን፣ ኢኮኖሚ ፍሰትን እንዲሁም ንግድን የምናቀላጥፍበት ሁኔታ ቢመቻች መልካም ይሆናል::
በዚህ ዙሪያ ዲፕሎማቶቿ ንቁ ሆነው በአገሪቷ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ መሳተፍና ዲፕሎማሲውን ማቀላጠፍ ይጠበቅባቸዋል:: ድሮ እንደሚደረገው ወደ አንድ አገር ከሔዱ በኋላ ጎን ለጎን የግል ሥራ መሥራትና ሌላ ሌላ ነገር ማድረግ ሳይሆን ዘመኑን የዋጀ ዲፕሎማሲያዊ አካሔድን በመከተል ለአገር የሚተርፍ የዲፕሎማሲ ሥራ መስራት ይኖርባቸዋል::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 22 ቀን 2017 ዓ.ም